የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት እያስመዘገበ መምጣቱ እንዲሁም የህዝብ ዕድገቱ በእጅጉ በመጨመሩ ምክንያት የኃይል ፍላጐት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል ። በአሁኑ ወቅትም በኢንዱስትሪ፣ በግብር፣በአገልግሎት ዘርፉ እንዲሁም የእያንዳንዱ ግለሰብ የቤት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እና ፍጆታ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
ይሁንና በአገሪቱ አስተማማኝ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ እንዲሁም የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማትን በበቂ ሁኔታ የሚደግፍ የኃይል አቅርት እና አገልግሎት ተደራሽነት አይስተዋልም።የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ከ45 ከመቶ ያልዘለለ ከመሆኑም በላይ ኢ- ፍትሃዊነት ያለበት ስለመሆኑም ይገለፃል።
አገሪቱ የኃይል ማመንጨት በአብዛኛው በውሃ ላይ ጥገኛ በመሆኑ ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል።የማስተላለፊያ፤ማከፋፈያና ማሰ ራጫ ዘርፉ በበቂ ሁኔታ ያልተዳረሰ፤ የኃይል ፍላጎቱን በበቂ ሁኔታ መሸከም የማይችልና በየወቅቱ አስፈላጊ ጥገና የማይደረግለት ከመሆኑ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና የአቅርቦት ውስንነት የሚታይበት ነው።
ይሁንና የኃይል ዘርፉ ከሌሎች የልማት ሥራዎች ቀድሞ በመገኘት ሌሎች የልማት ሥራዎችን በማነቃቃት ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንዲሁም ፈጣን የማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለበት የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ሲገልፁ ይሰማል።
‹‹የዘመናዊ የኃይል ምንጭ ስብጥሩን በማስፋት፤ የማስተላለፊያና ማሰራጫ መሰረተ ልማትን በማጠናከርና የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን የዘርፉን የአገልግሎት ጥራትና አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፉ ተሳትፎ እጅጉን ወሳኝ ነው›› ሲሉም ይደመጣል።
የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄም፣ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ለማጎልበት አገሪቱን ለኢንቨስትመነት ከሚመቹ አገራት ተርታ ለማሰለፍ ሙስናን ጨምሮ ሌሎችም መሰናክሎችን ከማስወገድ ባሻገር ለኃይል መሰረተ ልማቱ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አፅንኦት ይሠጡታል። የግሉ ዘርፍ በዚህ ረገድ የሚኖረው ሚናም አይተኬ ስለመሆኑ ያወሳሉ።
በኢትዮጵያን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት የኤሌክትሪክ ዘርፉን በማልማት ተግባር መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ መቆየቱን መታዘብ እንችላለን።ይሁንና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት የሚፈልገውን ኃይል ጥማት ለማርካታ እና ለማሟላትም የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ወሳኝ መሆኑ ለክርክር የሚበቃ አይደለም።፡
ይህ በመታመኑም በ2010 ዓ.ም የመንግሥትና የግል አጋርነት የሕግ ማዕቀፍ ይፋ ሆኗል። ውሳኔውም የግል ባለሀብቶች በኃይል ማመንጨትና ማከፋፈል ዘርፍ እንዲሳተፉ ሰፊ እድል ከፍቷል። የመንግሥትና የግል አጋርነት ስምምነት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማገዝ የሚችሉና በግል ባለሀብቶች ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያስችል አመቺ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ፤ ግልጽነትን፣ፍትሀዊነትን፣ ለገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ ማስገኘትን፣ ቅልጥፍናን እና ዘላቂነትን ማበረታታት ታሳቢ ያደረገ ነው።
አጋርነቱም የአዳዲስ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ዲዛይን፣ግንባታ፣ ፋይናንስ፣ ጥገና እና ሥራ ማስኬጃ፤ የነባር የመሠረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ግንባታ፣ ማዘመን፣ ፋይናንስ፣ ማስፋፋት፣ጥገና እና ሥራ ማስኬጃ፤ የአዲስ ወይም ነባር የመሠረተ-ልማት አውታሮችን አስተዳደር፣ ሥራ አመራር፣ሥራ ማስኬድ ወይም ጥገናም ይመለከታል።የአገሪቱ የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲው ዋነኛ አላማ፣የግል ባለሃብቶች ተሳትፎን ማበረታታትና በዘርፉ በሚደረገው ኢንቨስትመንት የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሆነ ያመላክታል።
የአገሪቱ የኢነርጂ ምርት ከካርቦን ልቀት ነጻ በሆኑ በታዳሽ ኢነርጂ ምንጮች ላይ እንዲመሠረትና በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ውስጥ ዋነኛ ስትራቴጂ ሆኖ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን ከዚህ ሀብቷ የራሷን የኢነርጂ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ቀጠናዊ የኃይል ትስስሩን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ለማሳደግ እንዲሁም ዘርፉ በአካባቢው ጂኦፖለቲካዊ መረጋጋት የሚኖረውን ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ሃብት ያላት አገር ናት። የተለያዩ ጥናቶችም የአገሪቱ የሃይድሮ ፓወር አቅም 45 ሺ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል መሆኑን ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅትም መንግሥት የኃይል አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ልማቱ የሚጠይቀውን ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ የሃይድሮፓወር ልማት ፕሮጀክቶችን በአገሪቱ ዋና ዋና ወንዞች እና ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ከእነዚህ መካከልም 6 ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጨው እና ሲጠናቀቅም ከአፍሪካ ቀዳሚ የሃይድሮ ኤሌክትሪከ ኃይል ማመንጫ የሚሆን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እና 1ሺ 870 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው የጊቤ ሶስት ፕሮጀክትም ሌላው ማሳያ ነው።
ይሁንና ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት እድገቷ የሚጠይቀውን ፍላጎት ለማሟላት የኃይል አማራጫን ማስፋት ብሎም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የጀመረችውን እርምጃ ወደ ሩጫ መቀየር የግድ ይኖርባታል።በተለይም የአየር ንብረት ላይ ተፅእኖ የማያሳድሩና ከብክለት ነፃ የሆኑ አማራጮችን ማስፋት የግድ ይላታል።
በአሥር ዓመቱ የልማት እቅድም ማለትም በ2030 ዓ.ም የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እስከ 17 ሺ ሜጋ ዋት እንደሚደርስ ይጠበቃል። በዚህ ሂደትም በመንግሥት ተሳትፎ እና ህዝብን ማእከል ባደረገ መልኩ በራስ አቅም በሚሰበሰብ ገንዘብ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን መገንባት በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም።
በመሆኑም በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት እና አቅርቦት ጋር ከሚሰሩ የሶስተኛ ወገን ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ መተግበር የግድ ይላል።ይህም ዘላቂ ፣አስተማማኝ እና ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ለመዘርጋትም ሆነ ያሉትን ለማጎልበት እጅጉን ወሳኝ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም።የአገሪቱ መንግሥት ይህን አካሄድ ጠንቅቆ የተረዳ ይመስላል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ግቦችን ለማሳካት የኃይል አማራጫን የማስፋት እና ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም እየተጋች ትገኛለች።የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ በያዝነው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ የበለስ ጃዊ የኃይል ማስተላለፊያና መስመርና ማከፋፈያ ፕሮጀክት የምረቃ ፕሮግራም ላይ እንዳሉት በአገሪቱ ከተለያዩ የኃይል አማራጮች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት በበርካታ መዋለ ንዋይ የኃይል አማራጮችን ከውሃ፣ ንፋስ፣ እንፋሎት፣ ፀሐይ በማምረት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራች መሆኑን ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቱ የሚፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለማሟላት የመንግሥት እና ግሉ ዘርፍ የትብብር የኢንቨስመንቱ ተሳትፎ እየጎለበተ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው።
በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል በሚደረግ ትብብር የፕሮጀክቶችን ጥራት ለማሻሻል ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም ውጤታማ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል። ከሁሉም በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማጎልበት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተሰምሮበታል።
እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት 23 በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ትብብር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አሉ። የአንዳንዶቹም ቦታ መረጣ፣ የአዋጭነት ጥናት ተጠናቀዋል። ሥራ የጀመሩ ብሎም ለመጀመር በሚያስችል ተክለ ቁመና ላይ የሚገኙም አሉ።
ከእነዚህ ውስጥም ስምንቱ የፀሐይ ኃይል፣አምስቱ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች፣ አምስቱ የነፋስ ፣ ሶስቱ የመንገድ እንዲሁም አንድ በቤት አንድ በፔትሮሊየም ፕሮጀክቶች እንዲሰማሩ ይሁንታን አግኝተዋል። የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የትብብር ቦርድ ለተዋናዮቹ ፈቃዱን ሰጥቷል። ቦርዱ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን ሰባት ያህል ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ሁለቱ ደግሞ ከግል ዘርፉ የተውጣጡ ናቸው።.
ኢትዮጵያ በመልክአምድራዊ አቀማመጧ ምክን ያት ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ማምረት የሚያስችል አቅም አላት። ስምንቱ የመንግሽት እና የግሉ ዘርፍ የትብብር የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችም 798 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።
እኤአ በ2019 ታህሳስ ወር የመጀመሪያው የመን ግሥት እና ግሉ ዘርፍ ትብብር የኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል። ፕሮጀክቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ከሚባሉ በኃይል አስተዳደር እና አቅራቢ ተቋማት አንዱ ለሆነው ACWA ተሰጥቷል።
በተመሳሳይ ጊዜም ACWA ሁለት ረጅም ጊዜን መሰረት ያደረጉ የኃይል ጊዜ ስምምነቶችን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተፈራርሟል። 125 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክት ሲሆን ሁለተኛው ዙር ስምምነትም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ታዳሽ የኃይል አማራጮች ሃብታም ናት።ለነፋስ እና ለእንፋሎት ወይንም ጂኦተርማል ኃይል ያላት እምቅ አቅም እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለመሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ይመሰክራሉ። በብሄራዊ ባንክ እኤአ በ2018/19 ይፋ እንዳደረገው መረጃ ከሆነም ኢትዮጵያ ከጂኦተርማል ኃይል 10ሺ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላት።እንዲሁም ከነፋስ ኃይል አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላት።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጮች ለማስፋት ያላትን ቁርጠኝነት በሚያሳይ መልኩ ለነፋስ እና ለጂኦተርማል ወይንም ለእንፋሎት ኃይል አቅርቦት ትኩረት መስጠት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። የአዳማ የነፋስ ኃይል ማመንጫም ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ሆኖ ይቀርባል።
የአዳማ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 34 ተርባይኖች አሉት።በአገሪቱ የመጀመሪያው የነፋስ ኃይል ማመንጫ ነው።51 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅምም አለው።በተመሳሳይ አዳማ ሁለት የነፋስ ኃይል ማመንጫ ከአፍሪካ ግዙፍ የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች መካከል ከኬንያው ቱርካና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ነው። 153 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው።
ኢትዮጵያ ከከርስ ምድር እንፋሎት እስከ 6 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ቢኖራትም እስካሁን ከመስኩ የተጠቀመችውን ለመግለፅ በሚያስደፍር መጠን አይደለም።በመሆኑም በጂኦተርማል ምርት የሚሳተፉ አጋሮችን ለመጋበዝ በርካታ ሥራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
ከኮርቤቴ ከርሰምድር እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የትግበራ ስምምነትን መጋቢት ወር 2020. መፈረሙ የሚታወስ ነው። ስምምነቱም በሁለት ምእራፍ 50 እና 100 ሜጋ ዋት ማቅረብን ይመለከታል።
በልማት እቅዱ የጂኦተርማል ምርትና ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በማመን መንግሥት በዘርፉ ለሚሰማሩ በርካታ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ይህን ማበረታቻዎች ከተቋደሱ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
የቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክትን የልማት ሂደት 50 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ነው። ይህ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ነው እየተከናወነ ያለው። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ትልቁ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል።ኩባንያው የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሸጥ የሚያስችለውን ስምምነት በጥቅምት 2010 ዓ.ም. መፈራረሙ ይታወሳል።
የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄም፣የግሉ ዘርፍ ፊት አውራሪ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት ኢንቨስትመንቱን በማጎልበት የአገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማጎልበት እጅጉን ዋሳኝ ነው።
በተለይ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ማድረስ እና በዲፕሎማሲው መስክ አሸናፊ ሆኖ መውጣት በቅርብ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚፈልገው ኃይል ጥማት ለማርካት እጅግ ወሳኝ ነው።
አቶ ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፣‹‹ኢንቨስትመንት በማስፋት ፣የኢኮኖሚ መዋዠቆችን ለመከላከል እንዲሁም የኑሮ ውድነት ፈር ለማስያዝ የኃይል አማራቾች ማስፋት፣ የተጀመሩትን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ፊት አውራሪ እያደረጉ መዝለቅ ፍቱን መፍትሄ የመሆን አቅሙ ግዙፍ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል‹‹ ነው ያሉት።
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ማጠቃለያም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቱ የሚፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለማሟላት መንግሥትም በየደረጃው ለሚሳተፉ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ለማጎልበት አነቃቂ አዳዲስ ማበረታቻዎችን ማድረጉን መቀጠል ይኖርበታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013