ስፖርት ጤንነትን ከመጠበቅና ከመዝናኛነት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ክንዋኔ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ አሁን አሁን እያደገና እየሰፋ የመጣው ስፖርትን ለማህበራዊ ኃላፊነትና በጎ ተግባራት ማዋል ዋናውና ተጠቃሽ ዘርፍ ሲሆን፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በቀላሉ የህዝብ ንቅናቄን ለመፍጠር እንዲሁም ዓላማን ለማሳካት መቻሉም ውጤታማነቱ በተለያዩ መድረኮች እየታየ ነው።
የኮትዲቯራውያን ኩራትና መለያ የሆነው ተወዳጁ የእግር ኳስ ተጫዋች ዲድየር ድሮግባ «የእርዳታው ንጉስ» የሚል ተጨማሪ መጠሪያ ተሰጥቶታል። ይህ ስም የተበረከተለት ደግሞ የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም በሚያደርገው መጠነ ሰፊ እርዳታ ነው። ድሮግባን የመሳሰሉ ሌሎች ስፖርተኞችም ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በመክፈት እንዲሁም ተጽዕኖ አሳዳሪነታቸውን በመጠቀም በዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይሳተፋሉ። በዚህም በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ፣ በበሽታ ለሚሰቃዩ፣ መሰረተ ልማት ለሚያስፈልጋቸው እንዲሁም ወላጅ አልባ ህጻናትን በመደገፍ ምስጉን ለመባል ያስቻላቸውን ተግባራት ያከናውናሉ።
ስፖርት የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ የውድድር አዘጋጆች፣ ክለቦችና ተጫዋቾች ከሚያገኙት ረብጣ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ማካፈልን ባህል እያደረጉት ይገኛሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማት የበጎ አድራጎት ሥራን ለማከናወን የወጠኑ ውድድር አዘጋጆች የተለያዩ ውድድሮችን ማዘጋጀታቸው እየተለመደ መጥቷል። የውድድር አዘጋጆቹ የተለያዩ ታዋቂ አትሌቶችን በመጋበዝና በማሳተፍ ህዝቡን የማነቃቃትና ገንዘብ የማሰባሰብ እንዲሁም መልዕክት የማስተላለፍ ሥራ ያከናውናሉ።
በቅርቡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሃዋሳ ከተማ ያከናወነውም ይኸው በጎ አስተሳሰብ ነው። የኢትዮጵያ አንድ መገለጫ እየሆነ ያለው ተቋም ዓመታዊ ውድድሮችን በማዘጋጀት ይታወቃል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮቹ መካከል አንዱ በሃዋሳ ከተማ የሚካሄደው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ሲሆን፤ በዘንድሮው የሩጫ ውድድር ላይም 200 አትሌቶች፣ 200 ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚሮጡና የውጭ ሀገር ዜጎች፣ 700 ህጻናት በጥቅሉ 4ሺ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳታፊዎች ነበሩ። ከውድድሩ በተጓዳኝም የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉበት እንዲሁም በጎ ተግባራት የተከናወኑበት መርሃ ግብሮች ተካትተዋል። በተለይ በዚህ ወቅት በሀገሪቱ ባሉ ውሃማ ስፍራዎች ላይ የተጋረጠው አደጋ የህልውናም ጭምር መሆኑ ይታወቃል። በደለል መሞላትና በቆሻሻዎች መበከል የሃዋሳ ሐይቅ እየተጋፈጠው ያለው አንዱ ችግር በመሆኑ «የሃዋሳ ሐይቅን እንጠብቅ» የሚል መልዕክት ተላልፎበታል፤ የሩጫው ተሳታፊዎችም ከውድድሩ መካሄድ አስቀድሞ የጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል።
የውጭ ሀገራት ዜጎች እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎች በተሳተፉበት እንቅስቃሴ በርካታ ኪሎ ግራሞችን የሚመዝን ቆሻሻ ተወግዷል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የከተማዋን የቱሪስት መስህብ የመጨመር ሥራ ሌላኛው የውድድሩ ዓላማ ነበር። በዚህም በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችን በሩጫ ውድድሩ ላይ ለማሳተፍ ተችሏል። የቀድሞው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አንጋፋው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በርካታ መልዕክቶችን ይዞ በደመቀ ሁኔታ የተካሄደ ውድድር መሆኑን ይገልጻል። ከሃዋሳ ሐይቅና ከግብር መክፈል ጋር በተያያዘ መልዕክቶች የተላለፉበት ነበር።
ሃዋሳ ያለ ሐይቁ አሁን ባለችበት ሁኔታ ልትገኝ እንደማትችል የሚጠቁመው ኃይሌ፤ ለማንም ሰው የማይተውና ሁሉም ተባብሮ ሊጠብቀው የሚገባ መሆኑንም ይጠቁማል። ከከተማው ወደ ሐይቁ የሚገቡትን ቆሻሻዎች ህዝቡ እየተከታተለ ሊያስወግድ እንደሚገባ፤ ካልሆነ ግን ሌሎች ሐይቆች ላይ የተከሰተው ሁኔታ እጣ ፋንታው እንደሚሆንም አሳስቧል። ከዚህ በተጨማሪ በውድድሩ ላይ በርካታ የውጭ ዜጎች መሳተፋቸው በቱሪዝም በኩል የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሲሆን፤ ከተማዋን ምቹ በማድረግ የቱሪስቶች ቁጥር እንዲበራከትና ከዚህም ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚቻል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ይጠቁማል።
የበርካታ ብርቅዬ አትሌቶች ማፍሪያ ከሆነችው በቆጂ በርካታ ስመጥር አትሌቶችን በመመልመል አሁን ላሉበት ያደረሱትና የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ በውድድሩ ላይ በተጋባዥ እንግድነት ተገኝተው ዕውቅና ከተሰጣቸው በኋላ በውድድሩ ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ሲገልፁ« ከሀገር ውስጥ አልፎ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ያሳተፈው ውድድር፤ ስፖርቱ የሚያድግበት እንዲሁም የውጭ ሀገራት ዜጎች ስለ ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁበትና በትክክል የሚገነዘቡበት ነው። በመሆኑም ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው» ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ብርሃን ፈይሳ