ዕድሜ ይስጥህ ተብሎ ሲመረቅ ተሽቀዳድሞ አሜን የሚል ሁሉ በየፌርማታው የተሰጠውን ዕድሜ ሲቀንስ ታገኙታላችሁ፡፡ ቀንሶ የተናገረው ዕድሜ ተቀባይነት እንዲያገኝ አካላዊ ገጽታውን ከዓመታት በፊት ከነበረበት ዕድሜ ጋር ለማቀራረብ መከራውን የሚበላ ዕድሜ ቀሻቢ ጥቂት አይደለም፡፡ ዕድሜ ትንሽ ሲገፋ ወጣት መስሎ ለመታየት ጺምንና ጸጉርን ሙልጭ አድርጎ መላጨት፤ ቀለም በመቀባት ሽበትን መደበቅ፤ እልፍ ሲልም ሜካፕ መለቅለቅ ፋሽን ሆኗል፡፡
በጠራራ ጸሐይ ጃንጥላ ይዘው ሲሽከረከሩ የሚውሉ «ወጣቶች» አይታችሁ ከጸሐዩ ለመከለል ነው ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል፡፡ «ሙቅ ለጉፋን እግረመንገድ ለሆድ» እንዲሉ፤ ጥላ የሚይዙት «ደራሽ ዝናብ መጥቶ የተቀባነው ቀለም በግንባራችን ተንቆርቁሮ ጉድ እንሆናለን» ብለው ስለሚሰጉ ነው፡፡ በዘመኑ ወጣት የሚዘወተሩ አልባሳት ላይ ሙጭጭ በማለት ወጣቱ ላይ ዋጋ የሚሰቅሉ አናረጅም ባዮች እየጨመሩ ነው፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአብሮ አደግ ጓደኛዬ ጋባዥነት በአንድ የወጣቶች የውይይት ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ መድረኩ ላይ ጠና ጠና ያሉ አራት ጎልማሶች ተደርድረዋል፡፡
አስቸጋሪውን የወጣትነት የዕድሜ ክልል እንዴት እንዳለፉት በቅርብ እርቀት ሆነው ልምድ እያካፈሉ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ቁጭ ከማለቴ አንደኛው ተናጋሪ «እኛ ወጣቶች» እያለ ዲስኩሩን ሲያጧጡፈው ሰማሁ፡፡ በሆዴ «ድንቄም ወጣት» እያልኩ ስዘባበት ጓደኛዬ ከላይ የመጡ የወጣት ማህበር አመራሮች መሆናቸውን ነገረኝ፡፡ ጉድ አልኩ፡፡ የእነዚህ የወጣት ማህበር አመራር ተብዬዎች ወጣትነት አልዋጥ ብሎ ተናነቀኝ፡፡ በወጣትነት ዘመናቸው የያዙትን ወንበር እስከ እርጅና ዘመናቸው ለማስጠበቅ እየጣሩ ይሆን? በማለት ራሴን ጠየኩ ( አፍሪካዊም አይደሉ)፡፡ እኔ የምለው … ወጣትነት ላይ ፖዝ ማድረግ ይቻላል እንዴ? ተደምረናል እያሉ ዕድሜያቸውን በ10 ዓመት ቀንሰው የወጣት ማህበር አመራር ሆነው ፊጥ ሲሉ ትንሽ አያፍሩም? ሼም ኦን ዩ ብዬ ስብሰባውን አቋርጬ መውጣት ፈልጌ ነበር፡ ፡ ነገር ግን ጓደኛዬ ወፈር ያለ አበል መኖሩን ቀደም ብሎ ስለነገረኝ ትዕግስተኛ ሆንኩ፡፡ ለነገሩ ዕድሜን በመቀሸብ የአገራችንን እግር ኳስ ተጫዋቾችን የሚወዳደር ያለ አይመስለኝም፡፡ የኛ ሀገር እግር ኳስ ተጫዋቾች ዕድሜ ይቀንሳል እንጂ አይጨምርም፡፡
በብሄራዊ ቡድን የአንድ ወጣት ዕድሜን አሳልፈው ለወጣት ቡድን ሊመረጡ ይችላሉ፡፡ ልክ ናቸው እኮ ገቢ እንጂ ዕድሜ ሲጨምር ደስ አይልም፡፡ ለዓመታት በዕድሜ ማጭበርበር ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑን የሚተኩ ተጫዋቾች ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ግን ችግሩን ለመቅረፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች በሚገኙ 2010 የእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የዕድሜ ምርመራ ተደረገ። በዚህ ምርመራ ትክክለኛ ዕድሜ ላይ ተገኝተው ምርመራውን ማለፍ የቻሉት 702 ተጫዋቾች ብቻ ሆኑ፤ 1308ቱ ምርመራውን ማለፍ አልቻሉም። ከእነዚህ ውስጥ 982ቱ የመጀመሪያውን የተክለ ሰውነት ምርመራ እንኳን ማለፍ ሲሳናቸው 326ቱ ደግሞ ቀዳሚውን ምርመራ አልፈው በኤም አር አይ ወንፊት ተንገዋለሉ፡፡
በወቅቱ ኤም አር አይ ለዋለው ውለታ የአክሮባቲስቱ ኮሜዲያን ተወዳጅ ሙዚቃ «እያንጓለለ» ተዘፍኖለታል፡፡ «ዕድሜ ዳኛው» ብሎ የዘፈነውስ ማን ነበር? ድሮ ቀረ ልለው እኮ ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ዕድሜ ራሱ ሊዳኝ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡ እስኪ ሆላንድ ሀገር የሆነውን ላጫውታችሁ፡፡ ኢሚሌ ራቴባንድ የተባለ ሆላንዳዊ የ69 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ዕድሜውን በ20 ዓመት ዝቅ ለማድረግ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል።
የ69 ዓመቱ ኢሚሌ ራቴባንድ «በፍርድ ቤት ስምን እና ጾታን መቀየር ይቻላል። ታዲያ ዕድሜን መቀየር ለምን አይቻልም?» ሲል ይጠይቃል፡፡ በዕድሜዬ ምክንያት ከሥራ ቅጥርና ከፍቅር አጋር መፈለጊያ ድረ ገጾች ሳልፈልግ ተገልያለሁ ባይ ነው፡፡ «ዕድሜዬ 69 በመሆኑ ብዙ ነገር አጥቻለሁ፤ 49 ቢሆን ግን ብዙ በሮች ይከፈቱልኛል፡፡ አዲስ ቤት መግዛት፤ የተለያዩ ዓይነት መኪናዎችን ማሽከርከር፤ ብዙ ሥራዎችን መሥራት እና ባለኝ መልክ መንደላቀቅ እችላለሁ። የግል ሐኪሜ የሰውነት ክፍሎቼ የ45 ዓመት ሰው እንጂ የ69 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ አይነት አለመሆናቸውን አረጋግጦልኛል።
ስለዚህም ራሴን ‘ወጣት’ ብዬ ነው የምገልጸው» ይላል። ጡረተኛው ኢሚሌ ራቴባንድ በጥያቄው መሰረት ዕድሜው በ20 ዓመት ዝቅ ከተደረገለት ለውለታው ከጡረታ የሚያገኘውን ጥቅማ ጥቅም እርግፍ አድርጎ ለመተው ቃል ገብቷል። እኛ የሽሮና በርበሬ ዋጋ ይቀነስልን እያልን ጠዋት ማታ ስንጮህ በሌላው ዓለም ያሉ ሰዎች ይቀነስልን የሚሉት ነገር ድንቅ አይልም? ከዚህ ቀደም በዓመት ከ 275 ሺህ እስከ 460 ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው የካናዳ ዶክተሮች ፊርማ አሰባስበው «ደመወዛችን ይቀነስ» ብለው መጠየቃቸውን ስሰማ «የሶስተኛው ዓለም» ሰው መሆኔ ወለል ብሎ ታይቶኝ ነበር፡፡
የራስን ዕድሜ ቀንሶ መናገር «መብት» ሊሆን ይቻላል የሀገርን ዕድሜ መቀነስን ምን ይሉታል? የኢትዮጵያ ዕድሜ ሶስት ሺህ ዘመን ሳይሆን 100 ዓመት ነው ( የመቶ ዓመት ታሪክ ያላት ሀገር ነች) ብሎ በአደባባይ የተናገረ ሰውም ድርጅትም ተመልክተናል፡፡ እንዴት ሰው (በተለይ ደግሞ ድርጅት) 2 ሺህ 900 ዓመት አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ይሸመጥጣል? እነዚህንስ ዕድሜ ይንሳችሁ ብሎ መርገም ነበር … ግን እናንተን ብመርቅ ይሻለኛልና ዕድሜ ይስጣችሁ !!
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
የትናየት ፈሩ