አዲስ አበባ ከተማ ስትመሰረት የነበሩት ቤቶች ምሶሶና ማገራቸው እንጨት፣ግድግዳቸው ወይንም ልስናቸው ደግሞ በአፈርና ጭድ የተቦካ ጭቃ፣ጣሪያቸውም የሳር ክዳን የለበሰ እንደሆነ ከታሪክ መረዳት ይቻላል።ግብአቱ ዛሬም ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም ዘመኑ በሚጠይቀው የብረት፣ሲሚንቶና ሌሎች የግብአት አይነቶች እየተተካ ይገኛል።ስልጣኔ ከተጀመረ በኋላ የቤት ግንባታ ግብአት ዘመኑ በሚጠይቀው እየተተካ ቢሆንም ከጥንቶቹም ዘመናዊ ግንባታ የጎበኛቸው፣የሥነህንፃ ጥበባቸውም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ቤቶች መኖራቸውንና በቅርስነት ቢያዙ ታሪክም ውበትም ይሆናሉ ብለው ለቅርስ ተቆርቃሪ የሆኑ ወገኖች ይሞግታሉ።በዚህ ረገድም ብዙ ውዝግቦች ተፈጥረዋል።በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከከተማ መልሶ ማልማትና ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት ጋር በተያያዘ ብዙ ቤቶች በምትካቸው ህንፃዎች ተገንብተዋል።የተረፉና ይፈርሳል፣አይፈርስም በሚሉ ወገኖች መካከል ጉዳዩ በህግ ተይዞ በክርክር ላይ ያሉም ይገኛሉ።
በዚህ ሙግት መካከል አሮጌውን በአዲስ የመተካቱ የመልሶ ማልማት ሥራ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠናክሯል።በስፋት እየተነሳ ያለው በዚሁ ከተማ በመሆኑ ትኩረታችንም በዚሁ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበርና የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ዓለምአቀፍ የቅርስ ቀንን አስመልክተው በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይም ጉዳዩ በስፋት ተነስቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ መልሶ የማልማት የግንባታ ሥራ ለጥንታዊዎቹ ግንባታዎች ወይንም ቅርሶች ሥጋት እየሆነ ነው?እንዴትስ ማጣጣም ይቻላል?በመድረክ የተነሱትንና የባለሙያ ማብራሪያ አካተን እንደሚከተው አቅርበናል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማና የአርክቴክቸር ቅርስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለውን መልሶ ማልማት ይደግፋሉ።ለቅርስ ስጋት ተደርጎም መወሰድ የለበትም ይላሉ።ነገር ግን ሥጋት የሚሆነው ልማቱና ቅርስ ጥበቃን አጣጥሞ ማስኬዱ ላይ እንደሆነ ይገልጻሉ።ማንኛውም አዳዲስ የከተማ ልማት ሥራ ሲሰራ ቅርስ ቤትን ያገናዘበ ጥናት አብሮ መካተት እንዳለበት ይናገራሉ።ክፍተቱን ወደ ሌላ መግፋት ብቻ ሳይሆን እንደእርሳቸው በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችና መምህራን ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውና እርሳቸውም ይህንኑ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።ለአብነትም ፒያሳ አካባቢ ሰራተኛ ሰፈር ወይም ባሻወልዴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቅርስን ያገናዘበ የቤት ልማት ግንባታ እንዲከናወን ጥናት ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ትልቁ ክፍተት ብለው ያነሱት የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ሲለዋወጡ የጥናት ሥራዎችንና ምክክሮችን ወደኋላ መለስ ብሎ አለማየትና ለቅርሶችም ያለው ግንዛቤ አንዱ ከሌላው መለያየቱን ነው።በሥርዓተትምህርት ውስጥ ተካትቶ ትምህርት ተሰጥቶ ቢሆን የግንዛቤ ክፍተቱ ይቀረፍ ነበር ብለው ያምናሉ።
አዲስ አበባ ከተማ ከተመሰረተች ወደ 140 ዓመት አካባቢ እየሆናት ቢሆንም ወጣት ከተማ ናት የሚሏት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ስለአመሰራረቷ እንዲህ አስታውሰዋል።ከተማዋ ከመመስረቷ በፊት ከነበረው እንጦጦ ጀምሮ አሁን ጉለሌ በሚባለው አካባቢ መንደሮች ነበሩ።በአረንጓዴም የተሸፈነች ነበረች።ብዙ ወንዞችም ነበሯት።አዲስ አበባ ከተማ ከእንጦጦ ረባዳማና ከእንጦጦም የተሻለ የአየር ፀባይ ነበራት።ለከተማነት ስትመረጥም በተስማሚ አየር ፀባዩዋ፣ለቤት መሥሪያና ለማገዶ የሚሆን የእንጨት ግብአት አቅርቦት አላት በሚሉ መነሻዎች ነው።ንጉሱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በወቅቱ የዘመቻ ግዴታ ላይ ስለነበሩ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ አዲስ አበባ ከተማን በመቆርቆር ወይንም በመመስረት የጎላ ሚና ነበራቸው።
ከተማዋ ለመኖሪያነት ስትመረጥ የከተማ አሰራር ባህል ያን ያህል አልነበረም።መንደሮች ናቸው የነበሩት።ህዝቡም ባህላዊ የሚባለውን አይነት ነበር የሚኖረው።ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሹመት ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንዲመጡ በማድረግ ቤት ሰርተው እንዲኖሩ ይደረግ ነበር።መንደሮቹም ሥያሜ ይሰጣቸው ነበር።አሁን የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃቤት የሚገኝበት የገበያ ቦታ ነበር።ቤተመንግሥቱ የተመሰረተበት ቦታ ደግሞ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚከናወኑበትና የንጉሱም መኖሪያ ሆኖ ያገለግላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አመሰራረት ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ሲነጻጸር የተለየ ነው።አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ሥርዓት ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ግንባታቸውም የቅኝ ገዥዎቹን ሀገራት የሚያንጸባርቁ ናቸው።አዲስ አበባ ከተማ የተመሰረተችው ግን በሀገሯ ሰዎች መሆኑ ለየት ያደርጋታል።ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖረው ማህበረሰብ የተሻለ ገቢ ካለው ማህበረሰብ ጋር በአንድ አካባቢ ይኖራል።አገልግሎቶች በቅርበት ላይ ይገኛሉ።ሀገሪቱን ቀስ በቀስ ስልጣኔ ሲጎበኛትና ከሌሎች ሀገሮች ጋርም ግንኙነት ሲፈጠር እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጀመሩ።የነዋሪዎች ቁጥርም እየጨመረ፣መተላለፊያ መንገድ ማውጣት፣ቀድሞ ነዋሪው በተለያየ ዘዴ ይሻገራቸው የነበሩ ወንዞች ድልድይ እንደሚያስፈልጋቸው፣በአጠቃላይ የከተማ መሠረተ ልማት ለማሟላት፣የከተማዋን ነዋሪ ለማስተዳደር ሥርዓትና ደንብ ማውጣት እንደሚያስፈልግ እየታመነበት መጣ።በመሆኑም ፒያሳ አካባቢ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ ማዘጋጃ ቤት ተቋቋመ።በወቅቱም ሶስቱ የከተማዋ አካል ተብለው የሚጠሩት ቤተ መንግሥት ፣ ፒያሳ አራዳ ፣ ባቡር ጣቢያ አካባቢዎች ነበሩ። መንግሥት ከህንድ ፣ ከግሪክ እና ከሌሎችም ሀገሮች የህንፃ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችና አዳዲስ የህንፃ ሥራዎች መታየት ጀመሩ።
በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ወቅት የጦር አመራሮቹ አዲስ አበባ ከተማ የምዕራባውያኑ አይነት የከተማ አሰፋፈር መልክ ስላልነበራት በፍጹም ከተማ አይደለችም።ወደሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀይረን መኖር አለብን የሚል ሀሳብ አንስተው ነበር።ነገር ግን የንጉሱ መቀመጫ አዲስ አበባ ከተማ በመሆኑ ከተማዋን ወደ ማሻሻል ሥራ ገቡ።በወቅቱ የፋሽስቱ መንግሥት ትልቁ ፖሊሲ የነበረው ጣሊያን በጣም እየተጣበበች ስለሆነ ብዙ ሰው ከሀገሩ ወጥቶ መሥራት አለበት የሚል ነበር።በከተማዋ ብዙ ቤቶችና መንገዶች ለመሥራት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ መሥራት ጀመሩ።ግንባታዎቹ አንዱ የቅኝ ግዛት መገለጫዎች ነበሩ።መርካቶም አሁን ካለው ይዞታ በፊት በነበረው የጣሊያን አሻራ ነበረበት።አመሰራረቱ ግን የተለመደውን ባህላዊ አሰራር የተከተለ ነበር።ምንም እንኳን ፋሽት ጣሊያን እንደወዳጅ የሚታይ ባይሆንም በግንባታው ዘርፍ በኢትዮጵያ ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል።
ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ሀገሪቱ በአዲስ አስተዳደር መመራት ስትጀምር ማስተርፕላን ይሰራ የሚል ሀሳብ መጣ። ከእንግሊዝ ባለሙያ መጥቶ የከተማዋን ማስተርፕላን አዘጋጀ ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ በፈረንሳዮች ሌላ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ።እነዚህ ባለሙያዎች በትላልቅ መንገዶችና አደባባዮች ግንባታ ላይ ያተኩራሉ ። እነዚህ ደግሞ ብዙ ቤቶች እንዲፈርሱ ምክንያት ይሆናል ። ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንዲህ ያሉ ሥራዎች መኖራቸው ቅርስ ቤቶች እንዳይተርፉ ምክንያት ሆኗል።ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያለው የከተማ ፕላን በምዕራባውያን አስተሳሰብ የተቃኘ እንደሆነና ሀገር በቀል የሆነ ዕውቀትን ማድነቅ ላይ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።በከተማዋ የማንነት አሻራን የሚያጠፋ ቅርስን ለማጥፋት የሚያደርስ ለግንባታ የሚውል የቦታ ችግር አለ ብለው አያምኑም። ህንፃዎች ስለበዙ የከተማ መገለጫ ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው ይላሉ።ገቢን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ግንባታም ምንነትን እንደማያሳይም ተናግረዋል።በዚህ መንገድ ከቀጠለ የሥልጣኔ ተወራራሽነት እንዳይጠፋም ይሰጋሉ።ከ1960ዎቹ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ቁመታቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ህንፃዎች ግንባታ መኖሩንና በአዲስ አበባ ከተማ የማስተር ፕላን ክለሳም ወደ አስር መድረሱንም አመልክተዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ብዙዎችን በክፍተት ቢያነሱም በቅርቡ ስለተካነውና በጥሩ መልኩ ካነሱት ግንባታ መካከል የመስቀል አደባባይ ይጠቀሳል።እርሳቸው እንዳሉት ግንባታውን የያዙት ሰዎች እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች ሀሳብ እንዲያካፍሉ ተጋብዘው ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል።ቅርስነቱ እንደተጠበቀ አገልግሎቱን ማስፋት ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንዲሰራ በመደረጉ ቅርስም ልማትም አሸናፊ የሆኑበት ሥራ ለመስራት ተችሏል።የምህንድስና ጥበብ በደንብ ተግባር ላይ ከዋለ ከተማ ይለማል።ቅርስም ይድናል።በዚህ መልኩ ከቀጠለ ወደፊት ተስፋ ይኖራል።ቅርሶችን አለማፍረስ ብቻ ሳይሆን ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግም ጎን ለጎን መታየት ያለበት ሥራ መሆኑን ያነሱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ብዙ ሀገሮች ቅርስ እንዳይነካ ጥንቃቄ የሚያደርጉት ቱሪስቶችን በመሳብም ሆነ ለከተማዋ ነዋሪ በመዝናኛነት ውሎ ገቢ እንዲያስገኝ በመፈለግ መሆኑን አስረድተዋል።ታሪካቸውን እያስተዋወቁ ቅርሶቹ ለከተማም ውበት እንዲሆኑ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ውስጥ በምትገኝ ሻርዣ ከተማ ውስጥ የነበረን ቅርስ በባለ 15 እና ከዛ በላይ በሆነ ህንፃ ተተክቶ ነገር ግን ቱሪስት ወደ ሥፍራው ባለመሄዱ እንደገና ከተማዋን ወደ ቀድሞ የመመለስ ሥራ ለመሥራት መገደዳቸውን አስታውሰዋል።እንዲሁም አርቆ በማሰብ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት የመድረኩ ተሳታፊዎች መካከልም አቶ አህመድ ዘካሪያ የቅርስ ጉዳይ በጥቂት ተቆርቋሪዎች ብቻ ሳይሆን እንደሀገር መታሰብ አለበት ብለዋል።እንደ አቶ አህመድ የአካባቢ ስያሜዎች እንኳን ቅርስ ናቸው።መርካቶ በህንፃ ይዘቱን ከመቀየሩ በፊት ቅቤ ተራ፣ምናለሽ ተራ፣ሽንኩርት ተራ ተብለው ይጠሩ የነበሩ አካባቢዎች አሁንም መቀጠል ነበረባቸው።ያኔ በነዚህ አካባቢዎች ሲነግዱ የነበሩ ዛሬ ላይ አብዛኞቹ በልጆቻቸውና በቤተሰብ አባል ተተክቷል።ተተኪዎቹ ትዝታ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ መሰራት ነበረበት።በአጠቃላይ መርካቶን የሚያስታውስ መረጃ እንኳን የለም።አካባቢ በሌላ የግንባታ ይዞታ ሲቀየር መሰረቱን መልቀቅ የለበትም።ታሪክም ሀብትም ስለሆነ።በዚህ በኩል እርሳቸውም የሚመለከተው አካል ጋር በመሄድ ጭምር ሀሳብ በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት አድርገዋል።ተቆርቋሪ ኖሮ በተግባር አለማየታቸው አሳዝኗቸዋል።
‹‹ዛሬ በሌላው ዓለም ዳውን ታውን የሚባል አላቸው።ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ባለ 50 እና ባለ መቶ ወለል ፎቅ ለመሥራት ነው ሩጫው›› የሚሉት አቶ አህመድ ቅርስ ይጠበቅ ብሎ መናገሩ እንዳደከማቸውም በቁጭት ጭምር ተናግረዋል።
ልጅ ኤርሚያስ ተሰማ የተባሉ አስተያየት ሰጭም ዛሬ በቁጥር ተተክተው የሚጠሩ አካባቢዎች መጠሪያ ስማቸው ሲቀየር ምክንያታዊ ነገር እንኳን እንዳልተቀመጠላቸውና ስሜት የሚሰጡ እንዳልሆኑም ተናግረዋል።እርሳቸው ቻይና ሀገር ሄደው ቤጂንግ በሚባለው ከተማ ውስጥ ያዩትንም ለተዳሚው እንዳካፈሉት እንኳን ቅርስ ሲፈርስ ስያሜ እንኳን እንዳይጠፋ በሀገሩ መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ታዝበዋል።ቅርስ ባለበት አካባቢ መንገድም ሆነ ሌላ ግንባታ ለማከናወን ቅርሱን በማይነካና እይታውንም በማይጋርድ መልኩ እንደተከናወነ በጉብኝታቸው ወቅት ማየታቸውን ገልጸዋል።ሌሎችም የመድረኩ ተሳታፊዎች መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር ሀገራዊ የሆኑ ሀብቶችም አብረው እንዲቀየሩ ከተደረገ የማንነት መገለጫ መጥፋት ብቻ ሳይሆን ሀብትም ይባክናል የሚል ስጋት እንዳላቸው አስተያየት ሰጥተዋል።ዘላቂ የሆነ ሥርዓት ሊበጅ እንደሚገባና የትምህርት ሥርዓቱም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መፈተሸ እንዳለበት ሀሳብ ሰጥተዋል።በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃንም ግንዛቤ በመፍጠርና መረጃ በመስጠት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከመፍረስ ከተረፉት ቅርስ ቤቶችና ተጠግነው ጥቅም ላይ ከዋሉት በአፄ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ለንጉሱ ባለውለታ የነበሩ የአርመን ዜግነት የነበራቸው የሙሴ ካቺክ ቦጎሲያን ቅርስ ቤት ይጠቀሳል።በልደታ ክፍለከተማ ጎላ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው ይህ ቅርስ ቤት ለቀበሌ ጽህፈት ቤትና ለወታደሮች መኖሪያ አገልግሎት ውሎ ነበር።ከዚህ ሁሉ በኋላም ለረጅም ዓመት ተዘግቶ ቆይቷል።ተጎድቶ የቆየውን ቅርስ ቤት በጎፈቃደኛዋ ወይዘሮ ሰላማዊት አለነህ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተውበት ለስዕል ማሳያ እንዲውል አድርገውታል።ወይዘሮ ሰላማዊት የቅርስቤት መፍረስ ቁጭት ውስጥ ስለከተታቸውና የዜግነት ኃላፊነታቸውንም ለመወጣት ሲሉ ያደረጉት ተግባር እንደሆነ አጫውተውኛል።የመንግሥት ተቋማት ተናብበው ባለመሥራታቸው የድንበር፣የባለቤትነት ጥያቄዎችና የተለያዩ መሰናክሎችን በትዕግሥት አልፈው ለውጤት እንዳበቁት አስታውሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ፋኢዛ መሐመድ ስለቅርሶች ሰፊ ግንዛቤ የኖራቸው ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ እንደሆነና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ብዙ ቅርሶች መኖራቸውን ተናግረዋል።በቅርሶች ጥበቃ ላይ ቢሮአቸው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013