ከአርሶ አደር እስከ ከተሜ ፣ ከዝነኛ ባለሃብት እስከ እለት ጉርሥ ፈላጊ ምስኪን ድረስ ያለው ማህበረሰብ ልጆቹን ትምህርት ቤት ይልካል፤ ያስተምራል፡፡ ገቢው ከዕለት ፍጆታ ያልዘለለ ማህበረሰብ ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ልጆቹን በማስተማር በኩል አይታማም፡፡ የሚከፍለውን ማንኛውንም አይነት መሰዋዕትነት ከፍሎ ልጆቹን ያስተምራል፡፡ የወላጆች ፈተና አሁን አሁን እስከ ዩኒቨርስቲዎች ድረስ ዘልቆ መግባቱ ይነገራል፡፡ ዩኒቨርስቲ ልጅን መላክ ለእናቶች ተጨማሪ ምጥን ፈጥሯል፡፡ ልጃቸው በዩኒቨርስቲ ሥም ወጥቶ በመቅረቱ የእግር እሣት ሆኖ የማይሽር ጠባሳ የተፈጠረባቸው እናቶች በሀገሪቱ በርካታ ናቸው፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዩኒቨርስቲ ወጣት ተማሪዎች አልፎ አልፎ የሚያሳዩትን ያልተገባ ባህሪ በማስመልከት ከፓርላማ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ ጦር ቤዝ (መሰረት) ሊጠቀም የሚፈልግ ኃይል ሊኖር እንደሚችል መግለጻቸው ተጠቃሽ ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ “ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከመግባታቸው በፊት በዝግጅት ወቅት አንድ ወር ቀደም ብሎ የክልልና የዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ አመራሮች ባሉበት ውይይት ተደርጓል፡፡ ተማሪዎች በሚገቡበት ጊዜም ግንዛቤው ኖሯቸው ራሣቸውን ከአላስፈላጊ ድርጊት መጠበቅ እንዲችሉ ኦሬንቴሽን ተሰጥቷቸዋል፡፡ የፖለቲካ አጀንዳውን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አስገብቶ የሚያገዳድል ፖለቲከኛ ያለው እኛ ሀገር ብቻ ነው፡፡ ወጣት ተማሪዎችን እሳት አስጨብጦ ለፖለቲካ ትርፍ የሚማግድ ጨካኝ ፖለቲካ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚስተዋለው ኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ በአለም ላይ የለም፡፡ ተማሪዎች የፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ ሊሆኑ አይገባም፡፡ መንግሥት የሚሰራው እንደተጠበቀ ቢሆንም በመጀመሪያ ማስተዋልና መጠንቀቅ የእነሱ ሥራ ነው፡፡ የእነሱ ኃላፊነት ነው፡፡ በሚደርስባቸው ችግር ተጎጂዎቹ እነሱና ለፍተው ያስተማሯቸው አርሶ አደር
ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡ የመጡበትን አላማ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ተማሪዎች የሐሳብ ልዩነት ሲያጋጥማቸው ለውይይት ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ የሰሙትን መረጃ ሳያጣሩ የራሳቸውን እና የጓደኞቻቸውን ሕይወት መገበር እና አደጋ ላይ መጣል አስፈላጊ አይደለም፡፡ እናቶቻቸው በምን መንገድ አስተምረው እዚህ እንደሚያደርሷቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች በማይረባ ነገር ጊዜያቸውን ማባከን የለባቸውም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምንጠብቀው ሃሳብና ሃሳብን አጋጭቶ ጠቃሚ ሃሳብ የሚያፈልቅ እንጂ እንደ ድሮው ድንጋይና ድንጋይ አጋጭቶ እሣት የሚፈጥር ትውልድ አይደለም፡፡ እሱ ትምህርት ቤት(ዩኒቨርሲቲ) መግባት አያስፈልገውም፡፡ ሥራ ቀጣሪ ኩባንያዎችና መስሪያ ቤቶችም የሚቀጥሩትን ሰራተኛ ፕሮፋይል ማጣራት አለባቸው፡፡
አንድ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ መቼ ገብቶ መቼ ወጣ የሚለውን ማጣራትና መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ እስከ ስምንት ዓመታት ድረስ ዩኒቨርሲቲ የቆየን ተማሪ ማጣራት፣ ምን ስትሰራ ቆየህ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ውይይት ተደርጎም፣ መልዕክት ተላልፎም ሃሳቡን የሚያስተናግድ ኃይል አልጠፋም ብለዋል፡፡ ወጣት ሣሙኤል ቢሻኖ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በልዩ ፍላጎት ትምህርት መስክ 3ኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ በቅርቡ በተካሄደውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ተያይዞ የተነሱ ሃሳቦችንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት የሰጡትን ምላሽ እንዴት ታየዋለህ በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ከመመረቂያ ጊዜያቸው በላይ በዩኒቨርስቲዎች የሚቆዩ ተማሪዎች መኖራቸውን የንግግሩ መንደርደሪያ አድርጓል፡ ፡ ይህ መሆኑ በተማሪዎችም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ ወጣቶች ጊዜያቸውን ከማቃጠላቸው በተጨማሪ ወላጆቻቸውንና መመረቃቸውን የሚጠብቁ ቤተሰቦቻቸውን ያስከፋሉ፤ ሀገርንም ለጉዳት ይዳርጋሉ ሲል አብራርቷል፡፡ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በራሳቸው በኩልም ይሁን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ያልታሰበ ክስተት አንድ ወይም ሁለት ዓመት ከመመረቂያ ጊዜያቸው ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ ለሶስትና አራት ዓመታት እና ከዚያ በላይ መዘግየት ግን በራሱ ችግር ነው፡፡
እነዚህ ተማሪዎች ጊዜው በረዘመ ቁጥር የሚያሻሽሉት ነገር በትምህርታቸው ላይ እንደማይኖር ገልጿል፡ ፡ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለከፋ የሥነ-ምግባር ችግር ሲጋለጡ የሚስተዋሉትም በግቢው ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ለረዥም ዓመታት ሲኖሩ በሚታዩ ወጣቶች መሆኑን ገልጾ፤ ምክንያታቸው በውል መታወቅ ይኖርበታል፤ ለብጥብጥና ለችግር መፈጠር ዋና ምክንያቶች ይሆናሉ፤ አላማውን ለማሳካት በሰላም በሚማረው ተማሪ ላይ ጭምር ችግር ይፈጥራሉ በማለት ወጣት ሣሙኤል ቢሻኖ ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታዎቻቸው በየእለቱ አላማቸውን ማሰብ፣ ቤተሰቦቻቸውን ማሰብ፣ ተምረው ለመድረስ ከፊታቸው ያስቀመጡትን ተስፋ ማሰብ ከቻሉ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት ማለፍ ይችላሉ፡፡ በጣም ታጋሽ፣ትሁት እና አስተዋይ ያደርጋቸዋል፤ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያነሱትን ሃሳብና ምክር እኔም እጋራዋለሁ ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመት የሶሻል ሳይንስ ተማሪ የሆነው ወጣት ተመስገን ታደገ እንደገለጸው፤ የዶክተር አብይ መምጣትን ተከትሎ ለውጦች አሉ፡፡ ወጣቶችም ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው እድሎች በየዘርፉ እየሰፉ ነው፡፡ በዚያው ልክ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ዶክተር አብይ ምርጥ መሪ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችም አካባቢም ሆነ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሰላም እንዲመጣ መልፋት ከጀመረ አስር ወር አልፎታል፡፡ እረፍት የሚያውቅ አይመስለኝም፡ ፡ በእኔ እምነት ‹‹አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ሥቦ…›› እንደሚባለው አይነት ሆኖብኛል፡ ፡ ሌላው አካል በሚፈልገው ደረጃ እያገዘው አይመስለኝም፡፡ ይሄን በትክክል የምትረዳው በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች እና በሀገሪቱ ጫፍ አካባቢዎች ህግና ሥርዓት በተገቢው የማይከበርባቸው እንዳሉ ወጣት ተመስገን ታደገ ተናግሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩኒቨርሲቲ ወጣት ተማሪዎችን በሚመለከት የተናገሩት ትክክኛ ሃሳብ ነው፡፡ በርካታ ተማሪዎች ምክንያታዊ ባለሆኑ ሃሳቦች ተጃምሎ የመመራትና የመከተል አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ የእከሌ ብሔር፣ የእከሌ ብሔር በሚል አስተሳሰቦችን በጠበበ መልክ ማራመድ አለ፡፡ ተማሪዎችን በብሔር ማደራጀት ውስጥ ውስጡን ይሰራል፡፡ ሲሰራ ቆይቷል፤አሁንም የተፈጠረው አደረጃጀት ሥራውን እየሰራ ነው ብሏል፡፡ የእከሌ ብሔር ስብሰባ እዚህ ሆቴል ተጠርቷል እየተባለ በየጊዜው ተማሪዎች በየብሔራቸው ይሰበሰባሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሚሰበከው የፖለቲካ ወሬ ከራሳቸው ብሔር በስተቀር የሌላውን ብሔር ማክበር በሚያስችል መንገድ የሰፋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከዚያ ሲመለሱ በጥላቻ መተያየት ይጀምራል፣ እየጠነከረ ይሄድና ለግጭት መፈጠር ሰበብ ይሆናል ብሏል፡፡ በትምህርታቸው ውጤት ማነስ የተባረሩ ተማሪዎች ያለ ሥራ በግቢ ውስጥ የሚኖሩ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ ይሄ የታወቀ ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የብሔር ወሬዎችን በማቀጣጠል ቀዳሚዎች ናቸው፡፡
ተስፋም ስለቆረጡ ይሆናል የሚለው ወጣቱ በተመሳሳይ ከዩኒቨርሲቲዎች ውጪ በሚገኙ ወጣቶች እና በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ ስለብሔሩ ብቻ መሰበኩ አሁን ላይ ለግጭት መዳረጉን ገልጿል፡፡ ወጣቱ ብሔር ተኮር እንቅስቃሴውን ትቶ ሁላችንም‹‹ የአዳምና ሄዋን ዘር አንድ ነን፤ ሁላችንም ሰው ነን›› ብሎ እኩል ወደ ማክበሩ እና ወደ ፈጣሪ ቃል ካልተመለሰ አስቸጋሪ እንደሚሆን ወጣት ተመስገን ታደገ ስጋቱን አንስቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን ወጣት ብዙ አታገኝም፡፡
በየአካባቢው የእከሌ ዘር የእከሌ ዘር በሚል ተጠምዷል፡፡ በአንጻራዊነት በእምነት ተቋማት አካባቢ የተሻለ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ይነሳል፡፡ ምክንያቱም በአንድ እምነት ውስጥ ብዙ ብሔሮች በመኖራቸው የእከሌ ብሔር ብሎ ለማንሳት ባለመመቸቱ ይመስለኛል ብሏል፡፡ ወጣት ሰናይት ቢተው የሥራ ማስታወቂያ በማንበብ ላይ አግኝተን ካነጋገርናቸው ወጣቶች አንዷ ናት፡፡ በዚህ ዓመት ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ሳይንስ መመረቋን በመግለጽ ንግግሯን ጀመረች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዩኒቨርስቲዎች አዳዲስ እውቀት የሚያመነጩ ወጣቶች ማፍራት አለባቸው፡፡ ከተማሪዎቹም የምንጠብቀው ይሄን ማድረግ እንዲችሉ ነው ብለዋል፡፡ ግን በእኔ እምነት አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከምታገኘው አካዳሚክ እውቀት በበለጠ ስለማንነት ትማራለህ፡፡ ሁሉም የራሱን ብሔር በማግዘፍ ተቆርቋሪ መስሎ ሲያወራ ትሰማለህ፡፡ በዚያው ልክ ሌላውን ብሔር ሲከራከር ትታዘባለህ፡፡ ወደ ግጭት ሁሉ የሚሄዱ እንዳሉ ወጣቷ ተናግራለች፡፡ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ተማሪዎ ቻቸውን፣ የአሰራር ሥርዓታቸውን፣ የአስተዳደር ሰራተኞቻቸውን እና መምህራኖቻቸውን ጭምር የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲኖራቸው እንደ አዲስ ማስተማር ያለባቸው ይመስለኛል፡ ፡ በዩኒቨር ሲቲዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንዲቀነቀን የሚያስገድድ ህግ ካልወጣ በስተቀር ማስተካከል ሊያስቸግር ይችላል ብላለች፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ሙሀመድ ሁሴን