-ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ወንድወሰን መኮንን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የዘመቻና መረጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ
አዲስ ዘመን:- በሀገሪቱ ከተደረጉት ሪፎርሞች (ማሻሻያዎች) ውስጥ ትልቁ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በተደጋጋሚ የተገለጸው የመከላከያ ሪፎርም ነው፡፡ ለመሆኑ ምን አይነት ማሻሻያ ዎች (ሪፎርሞች) ተካሂደው ነው ያንን ቢያብ ራሩልን?
ጀነራል ብርሀኑ:- የሪፎርም ስራ ሂደት ነው፡፡ በአንዴ ተጀምሮ የሚቋጭ አይደለም፡፡ ሪፎርማችን 12 ፕሮግራሞች አሉት፡፡ አደረጃጀት ቀይረናል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሕዝብ እንዲመስል የማመጣጠን ስራ ተሰርቷል፡፡ ሠራዊቱ በኑሮው፣ በልማቱ፣ በቴክኖሎጂ፣ በአዳዲስ አደረጃጀቶች የታጀበ እንዲሆን ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ሪፎርሙ በጥቂት ወራት የሚገባደድ አይደለም፡፡ የሚቀጥልና ዓመታትን የሚፈጅ ነው፡፡ በአጭር ግዜ ውስጥ መሰራት ያለባቸው ተሰርተዋል፡፡ በመካከለኛው ጊዜ መሰራት ያለባቸው ደግሞ ዝግጅት እየተደረገባቸው ነው፡፡ ከረዥም ጊዜ አንጻር የሚሰሩ ስራዎች ደግሞ ስትራቴጂክ ፕላን ወጥቶ በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን:-የሪፎርሙ ስኬቶች ምንድን ናቸው ? ጀነራል ብርሀኑ ጁላ:- አንደኛ ሠራዊቱ በውስጡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ተችሏል፡፡ “ሠራዊቱ ወያኔ ነው፤ ከመጠን በላይ ኃይል ይጠቀማል፤ ተዋጽኦው ትክክል አይደለም” እየተባለ ሲተች መኖሩ ይታወቃል፡፡ ሕዝቡም ይሄን አምኗል፡፡ መቀየር አለበት የሚል ኃሳብም ነበረውበአሁኑ ሰ ዓት የሕዝባችንን ጥያቄ መልሰናል። የመከላከያ ሠራዊታችን ገለልተኛ እንዲሆን አስተሳሰቡ እንዲቀየር ተዋጽኦው እንዲስተካካል፤ በግዳጅ ስምሪት ወቅት የኃይል አጠቃቀሙ “በሩል ኦፍ ኢንጌጅመንት” መሰረት ያደረገ እንዲሆን ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ይሄንንም ለማስተካከል የአደረጃጀት ለውጥ ተደርጓል፡፡ የአደረጃጀት ለውጥ የመከላከያና የሀገራዊ ደህንነት ጥብቅ ምስጢር ነው፡፡ ይሄንን በጋዜጣ ልገልጽ አልችልም፡፡ ከፍተኛ ለውጥ ነው የተደረገው። ምስጢር ያልሆኑ ነገሮችን ለመናገር ያህል ባሕር ኃይል እንዲሁም የሳይበር ቴክኖሎጂ እንዲኖረን እየሰራን ነው፡፡ አዲስ ዘመን፡- አሁን የጠቀሱልኝ አገሪቷ የባሕር ኃይል እና የሳይበር ቴክኖሎጂ ባለቤት እንድትሆን የተጀመረው ስራ ምን ላይ ይገኛል፤ እስካሁን መሬት ላይ የወረደ ነገር የለም? ጀነራል ብርሀኑ- በጥናት ደረጃ ነው ያለው፡፡ ከባድ ስራ ነው፡፡ ምን አይነት ባሕር ኃይል ይኖረናል? እንዴት ይደራጃል? እንዴት ይሰለጥናል? የሚለው ነገር በዝርዝር መሰራት አለበት፡፡ በሀገራችን የነበረው የራሳችን ተሞክሮ መቀመር አለበት፡፡ የሌሎች ሀገራትን አደረጃጀት ተሞክሮና ልምድ መውሰድ አለብን፡፡ ይሄንን የሚሰሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች (ኤክስፐርቶች) መኖር አለባቸው፡፡ ኤክስፐርቶች ተደራጅተዋል፡፡ የጥናትና ምርምር ስራ እየተሰራ ነው፡፡ እንዴት ይደራጅ ?ምን ያህል የሰው ኃይል፤ ምን ያህል ትጥቅ ይኑረን? የሚለው ስራም እየተሰራ ነው፡፡ ከሀገሮች ጋር ኃይል እንዲያሰለጥኑልን እየተነጋገርን እየተግባባን ነው፡፡ ድጋፍ ለመስጠት የተዘጋጁ ሀገሮች አሉ፡፡ ለጊዜው ባሕር ኃይሉን ለማቋቋም አዛዥ ተመድቧል፡፡ አዛዡ የራሱን ስታፎች ይዞ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በየግዜው የተሰራው ስራ ይገመገማል፡፡ የደረሰበት ደረጃ ታይቶ አዲስ አቅጣጫ ይሰጥበታል፡፡ የእኛን የነበሩትን የባሕር ኃይል ኤክስፐርቶች ለመጠቀም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህን ስራ እንዲሰሩ የተመደቡ ሰዎች እውቀቱና ልምዱ ያላቸውን ሌሎች ባለሙያዎች እየጋበዙ አብረው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው ባሕር ኃይል አባላት የነበሩ ልምዱ እውቀቱ ችሎታው ያላቸው ባሕረኞች ሀገራዊ ጉዳይ ስለሆነ በብዙ መስክ ማገዝ መርዳት መቀላቀል ይፈልጋሉ፡፡ እንዴት ያዩታል?
ጀነራል ብርሀኑ፡-መቀላቀል ችግር የለውም፡፡ ማነው ባሕር ኃይል የሚሆነው ተብሎ የተቀመጠ መመዘኛ (ሪኳየርመንት) አለ፡፡ በአካል ብቃት፣ በጤና እና በዕድሜ ማሟላት ያለበትን የሚያሟላ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ብዙዎቹ በዕድሜ ቢገፉም እውቀታችንን፣ ልምዳችንን፣ ተሞክሯችንን ለተተኪው ትውልድ አዲሱ ባሕር ኃይል ሲቋቋም በማገዝ ለሀገራችን አስተዋጽኦ ማድረግ እንፈልጋለን ይላሉ፡፡
ጀነራል ብርሀኑ፡- አሁን ገና ጥናት፣ ምርምርና ድርድር ላይ ነን፡፡ ፍላጎቱ ያላቸውን የቀድሞ ባሕር ኃይሎች በተመለከተ በመከላከያ ሚኒስቴር ስር ለሚቋቋመው ባሕር ኃይል የተመደበለት አዛዥና ስታፍ ስላለ እነሱ ናቸው ይሄን ስራ የሚሰሩት፡፡ አዲስ ዘመን ፡-ሠራዊቱን ከቦታ ቦታ የማንቀሳቀስ ፍጹም መብት የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በአንዳንድ ቦታዎች የታዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁን ምን ላይ ነው ያለው? ጀነራል ብርሀኑ፡- አንድ ጊዜ የሆኑ ንትርኮች አጋጥመው ነበር፡፡ ተፈተዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱን በተፈለገው አቅጣጫ እንዳይንቀሳቀስ ሊያግድ የሚችል ምንም ኃይል በዚህ ሀገር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡-እስቲ ወደ ጎንደር እንሂድ፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ሰሞኑንም እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አሉ፡፡ ሰው ሞቷል፡፡ ንብረት ወድሟል፡ ፡“መከላከያ ሊረዳን አልቻለም፤ ስንጠይቅ እያየ ነው የሚያልፈው” የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ፡፡ “በምዕራብ ወለጋ የተከሰተውን ችግር በሳምንት ውስጥ ማስተካከል የቻለው መከላከያ ጎንደር ቢኖርም ግጭት ሲነሳ እርምጃ አልወሰደም” ይላሉ፡፡ ግጭቱን የሚያስነሱት ኃይሎች ሞርታር፣ ድሽቃ እና ስናይፐር አላቸው ነው የተባለው፡፡ የክልሉ መንግሥት በራሱ ሚሊሺያ እና ፖሊስ ችግሩን መፍታት አልቻልኩም ብሎ ለእናንተ ጥያቄ አላቀረበም ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- በጎንደር በነበረው ሁኔታ መከላከያ ካለስሙ ስም ሲሰጠው የነበረው መከላከያ የሚጠየቅበትን ሁኔታ ካለማወቅ የተነሳ ነው፡፡ መከላከያ በግልጽ በተቀመጠ ሕግ ነው የሚሰራው፤ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ነው የሚመራው፡ ፡ የትኛው ግዳጅ ላይ እንደሚሳተፍ ያውቃል፡፡ ጎንደርን በተመለከተ ክልሉ እኔ አልችልም፤ የእኔ የጸጥታ ኃይሎች እዚህ ያለውን ግጭት ማቆም አልቻሉም ስለዚህ መከላከያ ገብቶ ያረጋጋ የሚል ጥያቄ አልጠየቀም፡፡ ሲጠይቅ ሕጉን ተከትለን እንሰራለን፡፡ አሁንም ቢሆን ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ሲከሰቱ ከክልሉ ኃይሎች ጎን በመሆን እየተከላከለ ያለው መከላከያ ነው፡፡ ሙሉ ስምሪት ውስጥ ለመግባት ግን ግልጽ የመንግሥትን ትዕዛዝ ይጠይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡-እነሱ ባይጠይቁስ ፌዴራል መንግሥቱ ዝም ይላል ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- ዋናው ሕገ-መንግሥቱን ማወቅ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ የሀገሪቱ ገዢ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ሕግ ነው፡፡ አንድ ክልል የጸጥታ ጉዳዩን ራሱ መያዝ (ማስተዳደር) አለበት፡፡ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፣ አድማ ብተና፣ ሚሊሺያ ስላለውም በክልሉ ውስጥ የሚፈጠርን ግጭት ራሱ መፍታት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምዕራብ ወለጋ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የኦሮሚያ ክልል ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ገብታችሁ አረጋጉ ብሎ ለመከላከያ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው ገብታችሁ ችግሩን የፈታችሁት ማለት ነው?
ጀነራል ብርሀኑ፡- አዎ፡፡ የአማራ ክልል ችግሩን ለመፍታት በሕግ የተቀመጠ ስልጣን አለው፡፡ ክልሉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጎንደር ያለውን ግጭት ማስቆም ስላልቻልኩ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ይሄንን ግጭት ያስቁም የሚል ጥያቄ መጠየቅ አለበት፡፡ ኦሮሚያ እንደዚህ ነው ያደረገው፡፡ ሠራዊታችን በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ክልሎች ሁሉ ታክቲካልና ስትራቴጂካል እዞች አሉት። በሚገባ በተደራጀና በታጠቀ መልኩ ዝግጁ ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ የእኛ ዋነኛው ተልእኮ የሀገራችንን ዳር ድንበር፤ ሉአላዊነት፤ የአየር ክልል መጠበቅ፤ ከማንኛውም የጠላት ወረራና ጥቃት ነቅቶ መከላከል ነው፡፡ ይህም ሆኖ በሀገር ውስጥ በሚፈጠሩ የሰላም መደፍረሶች ሁኔታው በአካባቢው ከሚገኘው ኃይል በላይ ሲሆን ክልሎቹ ለፌዴራል መንግሥቱ መከላከያ እንዲገባና እንዲያረጋጋ ሲጠይቁ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ትእዛዝ ሲሰጠን ብቻ ነው የምንገባው፡፡ ይሄንን ግልጽ የሆነ እውነት ሰው በአብዛኛው አይረዳውም፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ከተቀመጠልን ኃላፊነት ውጭ መንቀሳቀስ አንችልም፡፡ እውነቱ ይሄ ነው፡፡ሁሉም ሊረዳው ይገባል፡፡ አዲስ ዘመን፡-ከኦነግ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታራቂ ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ገብተው እንዳስማሙ በመገናኛ ብዙሀን ተገልጿል፡፡ የኦነግ ሠራዊት ተጠቃሎ ወደ መንግሥት ካምፕ ገብቶአል? ጀነራል ብርሀኑ ጁላ፡- አሁን ያልከውንና እርቅ እየተደረገ ነው የሚለውን መረጃ በሚዲያ ሰምቼያለሁ፡፡ እርቅ ስለተደረገ ወደካምፕ ይግቡ የሚል መመሪያ ከመንግሥት አልመጣም፡፡ ለምን ቢባል እርቁ የተከናወነ አይመስለኝም፡፡ እርቅ እናደርጋለን፤ በአጭር ግዜ እናስገባለን፤ እኛ ኃላፊነት እንወስዳለን የሚሉ ሰዎች በሚዲያ እየወጡ ሲናገሩ ሰምቼአለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ለመንግሥት የደረሰው ነገር የለም ?
ጀነራል ብርሀኑ፡-ሸኔ የሚባለው የኦነግ ቡድን ከመንግሥት ጋር ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ሠራዊቱ ግዳጁን ያቁም፤ በትጥቅ እየተዋጋ ያለው ኃይል ደግሞ እዚህ ካምፕ ይግባ የሚል ስምምነት እኔ አላየሁም፡፡ በወሬ ደረጃ እኔም ሰምቻለሁ፡፡ በእርግጥ የማያከራክረው ነገር ቢኖር መንግሥት ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ይፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ጀነራል ችግሩ እንደቀጠለ ነው ማለት ነው?
ጀነራል ብርሀኑ፡- ምን ይቀጥላል? አሁን እኮ አብቅቷል፡፡ ሞቷል፡፡ ምንም አይቀጥልም፡፡ ወደየት ይቀጥላል? በፊት የነበረው እኮ መንግሥት ከዛሬ ነገ ይገባሉ ብሎ ስለለቀቃቸው ነው፡፡ ሲለቃቸው ሙሉ ወለጋ ነጻ መሬት መሰላቸውና ፈነጩበት፡፡ ነጻ የመሰላቸውን መሬት እየተጠቀሙ ሀገሪቱን በሙሉ የማዳረስ ዕቅድ ነበራቸው፡፡ መንግሥት አራት ወር ዝም አላቸው፡፡ ታገሰ፡፡ ምክንያቱም በውሉ መሰረት ይገባሉ የሚል እምነት ነበርና፡፡ ቢታይ እየሰለጠኑ፣ እየተጠናከሩ፣ አቅም እያጎለበቱ የመንግሥትን መዋቅር አፈራርሰው ቀጣናውን ተቆጣጠሩት፡፡ ይህ ቀረው የማይባል ከፍተኛ ግፍና ወንጀል በሕዝቡ ላይ ፈጸሙ፡፡ ይህንን ሲያይ ሕዝቡ ጮኸ፡፡ መንግሥት የለም ወይ? የሚል ነገር ከሕዝቡ ሲመጣ ሕግ እንድናስከበር ለመከላከያ ትእዛዝ ተሰጠ፡፡ ተቆጣጥረነዋል በሚሉት አካባቢ በሙሉ ገባን፡፡ አሁን አስተካክለነዋል፡፡ ያፈራረሱት የመንግሥት መዋቅር በነበረበት ተመልሶ ተደራጅቷል፡፡ የተዘጉ መንገዶች በሙሉ ተከፍተዋል፡፡ ንግድና እርሻ እየተካሄደ ነው፡፡ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ተከፍተዋል፡፡ የፖለቲካ ተቋማት ስራ ጀምረዋል፡፡ ወደ ጫካ የሸሹ ወደ በረሀ የወረዱ ጥቂቶች አሉ፡፡ በሰላም ከገቡ መንግሥትም መከላከያም ደስተኛ ነው፡፡ የሀገራችንን የሕዝባችንን ሰላም ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡ ተሸንፈዋል በሚል እስከመጨረሻው እነሱን ማሳደድ አንፈልግም፡፡ የትጥቅ ትግሉን ትተው፤ ለሰላም በመቆም ወደ ሕዝቡ ቢቀላቀሉ የመንግሥትም የመከላከያም ፍላጎት ነው፡፡ መንግሥት ከመጀመሪያው ጀምሮ ክፍት ያደረገው ዕድል ይሄንን ነው፡፡ ጦርነት ይቁም፤ አያስፈልግም ነው ያለው፡፡ እነሱ ናቸው ያፈነገጡት፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደገና ወደ ኋላ እንመለስ፡፡ ባለፈው በሰጡት መግለጫ ላይ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች የሚለው አገላለጽዎት የተመነዘረበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ አስተያየት ቢሰጡበት?
ጀነራል ብርሀኑ፡- ይሄንን ጉዳይ በተለያየ መገናኛ ብዙሀን በጋዜጣ በመጽሄት በማሕበራዊ ሚዲያ የተጠቀሙበት ሰዎች ምክንያታቸው ንግድ (ቢዝነስ) ነው፡፡ የተባለውን በአግባቡና በቅንነት ከመረዳት ይልቅ ወሬ ሰንጥቀው ቀይረው የሕዝብ ትኩረት ለማግኘትና ገበያ ለመሳብ ተጠቅመውበታል፡፡ እኔ የተናገርኩት ግልጽ ነው፡፡ በቅማንትና በአማራ ብሔረሰብ መካከል ግጭት አለ፡፡ ሕዝቡ አብሮ ለዘመናት የኖረ ነው፡፡ ምን እንደተፈጠረ ይታወቃል፡፡ የማንንት ጥያቄን የአማራ ክልል መልሷል፡፡ ጥያቄው ከተመለሰ በኋላ ግጭቱ ለምን እንደቀጠለ ግልጽ አይደለም፡ በዚህ ግጭት መሀል ሰላማዊ ሰዎች ተጎድተዋል፡ ክልሉ ችግሩን እፈታለሁ ብሎ ሞክሯል፡፡ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ በሽምግልና በፖለቲካዊ ውይይት፤ በምክር ቤት ውሳኔም ጸጥታውን ለማረጋጋት ያለውን የጸጥታ ኃይል ተጠቅሞ ሞክሯል፡፡ ሊፈታው ግን አልቻለም፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ከክልሉ አቅም በላይ ስለሆነ መከላከያ ይግባና ይሄን ኃላፊነት ይውሰድ የሚል መመሪያ አልመጣም፡፡ በዚህ ምክንያት ግጭቱ ቀጥሏል፡፡ እዚህ ግጭት ውስጥ ብዙ ኃይሎች እጃቸውን አስገብተዋል፡፡ በዚህ ግጭት እጃቸውን ካስገቡት ውስጥ ሽፍቶች አሉበት፡፡ በተለያየ ምክንያት ዱር ቤቴ ያለው ሽፍታም ሆነ ሌላ የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ኃይል፣ ቅማንት እራሱ አለኝ የሚለው ጥያቄ፣ የአማራ ክልል ይሄንን ችግር ለመፍታት የሄደበት አካሄድና ሌሎችም ምክንያቶች ተዳምረው ጉዳዩን ውስብስብ አድርገውታል፡፡ እዚህ ውስብስብ የጸጥታ ችግር ውስጥ ብዙ ኃይሎች እጅ አስገብተዋል ነው ያልኩት፡፡ ከእነዚህ አንዱ ሽፍታ ነው ያልኩት፡፡ ሽፍታ ደግሞ እዛ ሞልቷል፡፡ ግንደ በረትም ሰላሌም ሽፍታ አለ፡፡ ጎንደር ውስጥ ሽፍታ የለም ከሽፍታ ነጻ ነው የሚል ሰው ካለ ሊከራከር ይችላል፡፡ እኔ ግን ጎንደርን በደምብ ስለማውቀው ምናልባትም ሀገሪቱ ውስጥ ካለው ሽፍታ በቁጥር ቢታይ በአካባቢውም እንደ ባህል የሚቆጠር ስለሆነ አለ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉ በጣም ትላልቅ ተብለው የሚታሰቡ አንዳንድ ሰዎች የጎንደር ሕዝብ ሽፍታ ተባለ ብለው ተናግረዋል፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሕዝብ ሽፍታ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡በዚህ መልኩ ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ ሀገር ለመምራት መዘጋጀት በጣም ከባድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ሶማሊያ ውስጥ አልሻባብ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ በእኛም በኩል የአጸፋ እርምጃ ተወስዶአል፡፡ ምንድነው የተፈጠረው?
ጀነራል ብርሀኑ፡- በኢትዮጵያ የሚመራ ሴክተር 3 የሚባል እዝ አለ፡፡ ሰላም አስከባሪውም እዙም የእኛ ነው፡፡ ከባይደዋ የሚወጣ የኮንቮይ እንቅስቃሴ ነበረ፡፡ አልሻባብ ደፈጣ (አምቡሽ) አድርጎ ጉዳት አድርሷል፡፡
አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያ የመረጃ ክፍል ምን ይሰራል ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- የመረጃ ችግር አይደለም፡፡ የኮንቮይ አመራሮች ከልክ ያለፈ ጀብደኝነት ነው፡፡ ገምግመነዋል፡፡ ከግዳጅ ስምሪት በፊት መሪዎች ሁልጊዜም ገለጻ ይደረግላቸዋል፡፡ የተቀመጠ አሰራር አለ፡፡ አንድ ኮንቮይ እንዴት ይሄዳል፤ እንዴት ይታጀባል፤ ከአንዱ መኪና ሌላው መኪና ድረስ ምን ያህል እርቀት ሊኖረው ይገባል፤ ተጠርጣሪ አደገኛ ወረዳዎችን እንዴት ያልፋል ወ.ዘ.ተ የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያካትቱ ወታደራዊ አሰራሮች አሉ፡፡ ደምቡና አሰራሩን በጥብቅ ያለመከተል ጀብደኝነት ያስከተለው አደጋ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ተጠያቂ መሆን በሚገባቸው አመራሮች ላይ ምን እርምጃ ወሰዳችሁ ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- ኃላፊው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ጉዳት ደርሷል፡፡ አልሻባብ አስቀድሞ የታቀደ ደፈጣ አዘጋጅቶ ማጥቃት ቢሰነዝርም ሠራዊቱ እጅግ በሚያኮራ ጀግንነት ተዋግቷል፡፡ አንድም የተማረከ የለም፡፡ የእኛ ሠራዊት ባልጠበቀው የጠላት የበላይነት ውስጥም ቢሆን በፍጹም ቁርጠኝነት ተዋግቷል፡፡ ተሰውቷል፡፡ ቆስሏል፡፡ እጅ በእጅ ውጊያ ድረስ ገብቷል፡፡ እነሱንም እንዳልነበሩ አድርጎ መቷቸዋል፡፡ እጅና እግሩ ቆስሎ እስከመጨረሻው ድረስ የተዋጋ የታችኛው አመራር አለ፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በዚህ ድንገተኛ ውጊያ ውስጥ የጠላትን እቅድ አፍርሰው በከፍተኛ ጀግንነት ተዋግተዋል፡፡ ጀግንነትም ፈጽመዋል፡፡ ቦታው እዛው ባይደዋ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ተዋጊው ሠራዊት ጥይት እየዘነበበት ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ ጀግንነት ፈጽሟል፡፡ አልሻባብ ይሄን በማድረጉ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ኪስማዮ አካባቢ ከ60 በላይ ተዋጊ ሞቶበታል፡፡ የእኛ አየር ኃይል በወሰደው የማጥቃት እርምጃ ከ60 በላይ የአልሻባብ ተዋጊ ተደምስሷል። አልሻባብ ተዋጊ ሠራዊቱን ብቻ አይደለም ያጣው፡፡ ከባድ መሳሪያዎቹ በሙሉ ወድመዋል። የኢትዮጵያን ሠራዊት ተንኩሶ ዋጋ ሳይከፍሉ መውጣት የሚባል ነገር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡-በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር አካባቢ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም የአልሻባብ ተዋጊዎች በግልና በቡድን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ሰርገው በመግባት እየተሰባሰቡ ነው፤ እንዲያውም የፖለቲካ ድርጅቶችን ሽፋን በማድረግ ጭምር ነው የሚገቡ የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው? ጀነራል ብርሀኑ፡-እንደዚህ የሚባል መረጃ የለም፡፡ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ፍላጎቱ ሊብላላ ይችላል፡፡ በተግባር ግን እንደዛ አይነት ነገር የለም፡፡ ለመግባት የሞከሩ አልሻባቦች ነበሩ ተይዘዋል፡፡ አልሻባብ ኢትዮጵያ ለመግባት አይሞክርም ብሎ የሚያስብ ካለ ሞኝነት ነው የሚሆነው፡፡ እስከዛሬም ያልገባው ስላልቻለ ነው፡፡ ወደፊትም አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡-የመከላከያ ወታደራዊ አልባሳትን ሊለውጥ ነው የሚባል ነገር በስፋት ይሰማል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀደም ሲል ካኪ፤ ቅጠልያ ልብሶች ነበሩት፡፡ ሬንጀር ልብስ ከአየር ወለድ በስተቀር ሌላው የጦር ክፍል እንዲለብስ አይፈቀድለትም ነበር፡፡ አሁን የታሰበው የአለባበስ ለውጥ እንዴት ነው ቢያስረዱን?
ጀነራል ብርሀኑ ጁላ፡- ሀሳብ ነው ያለው እንጂ የተወሰነ ነገር የለም፡፡ ገና እየሰራንበት ነው። መለወጥ አለብን የሚል ሀሳብ አለ፡፡ ዩኒፎርም የምንቀይርበት ዋነኛው ምክንያት የሠራዊቱ ዩኒፎርም ተዘርፏል፡፡ አንዳንዱ በተቋሙ ነባር አመራር እጅ የነበረ በውሳኔ ብዙ ኃይሎች እጅ ገብቷል፡፡ አሁን ለምሳሌ ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ ሸኔ ኦነግ ለብሶ ሲዋጋ የነበረው ሬንጀር ነው። ሞያሌ ላይ በተደረገ ግጭት የተሳተፉ ሰዎች ሬንጀር ለብሰው ነበር፡፡ ሕዝቡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መከላከያውንና ሌላውን መለየት አልቻለም፡፡ በእርዳታና በድጋፍ ስም ከእኛ ውጭ ወደጎረቤት ሀገሮች የወጣ ሬንጀር ልብስ አለ፡፡ ይሄንን ሁኔታ ለመቀየር የግዴታ ዩኒፎርሙን መቀየር አስፈላጊ ነው ብለን አምነንበት እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የዘንድሮ የመከላከያ ቀንን እንዴት ለማክበር አስባችሁዋል፤ ጀነራል ብርሀኑ፡- ሰባተኛው የሠራዊት ቀን ዛሬ የካቲት ሰባት ይከበራል፡፡ የካቲት ሰባት ቀኑ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ ሠራዊቱ የተቋቋመበት ቀን ስለሆነ ነው እለቱ የሚከበረው። የዘንድሮው የሠራዊት ቀን አከባበር መሪ መፈክር “ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን እንጠብቃለን፤ ሕዝባዊ ባሕሪያችን የተጠበቀ ይሆናል፤ የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን” የሚል ነው፡፡ በዚህ ላይ ተመስርቶ ነው የሚከበረው፡፡ የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው ለውጥ በተጀመረበት ጊዜ የሚከበር የሠራዊት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሠራዊቱ በጣም መሰረታዊ የሆነ ሪፎርም የጀመረበት፣ አደረጃጀቱ የተቀየረበት፣ ተስፋው የለመለመበት ጊዜ መሆኑም ጭምር ነው፡፡ ቀደም ሲል በሠራዊቱና በሕዝቡ መካከል የነበረው ጥርጣሬም በከፍተኛ ደረጃ ተወግዷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለሠራ ዊቱ የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድነው ?
ጀነራል ብርሀኑ፡- አሁን የመጣውን ለውጥ ያመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወይንም አክቲቪስት ያመጣው ለውጥ አይደለም፡፡ በእርግጥ የየራሳቸው ሚና ነበራቸው፡፡ በወሳኝነት ለውጡን ያመጣው ሕዝቡ ነው፡፡ ስርዓት የሚቀይር ሕዝብ ነው፡፡ የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ማዕበል የለውጥ አመራር ፈጥሯል፡፡ የለውጥ አመራሩ ደግሞ ሕዝቡ ልክ ነው ብሎ ከሕዝቡ ጋር ወግኗል፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው ነው መደረግ ያለበት ብሎ ከሕዝቡ ጋር ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ልክ አይደለም የሚሉ አመራሮችም በብዛት ነበሩ፡፡ እንዲያውም ሕዝቡ ልክ ነው ይሉ የነበሩት ከሕዝቡ ጋር የወገኑት በጣም ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለኝ መልእክት ይሄንን ለውጥ አንተ ያመጣኸው ለውጥ ስለሆነ በአይነ ቁራኛ ቀን ከሌሊት ነቅተህ ጠብቀው ነው የምለው፡፡ አደናቃፊዎች ሲያጋጥሙህ ሞተህ ለውጡን እንዳመጣህው ሁሉ እድል አትስጠው ጠብቅ የሚል ነው መልእክቴ፡፡ የለውጥ አመራሩም በጥሩ ሁኔታ እየተራመደ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሕዝብ እያዳመጠ፤ መጥፎ አሰራሮችን ብልሹ አዋጆችን እየቀየረ፤ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እየሰራ፤ ሰብአዊ መብት እንዲከበር እያደረገ፤ አፈና እንዳይኖርም እያደረገ ነው፡፡ ሕዝቡንም እያቀራረበ አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት እየሰራ ነው፡፡ ይሄንን የለውጥ አመራር ማገዝ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ሠራዊታችን ደግሞ ራሱ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ሠራዊቱ የሕዝቡ ልጅ፤ ከሕዝቡ ውስጥ የወጣ ኃይል ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ጎጆ የወጣ ነው፡፡ ሠራዊቱ ራሱ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ በነበረው ሁኔታ በሙሉ ረክቶ የሚኖር አልነበረም፡፡ በሠራዊቱ ውስጥም ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌም ያህል በመከላከያ ውስጥ የብሔራዊ ተዋጽኦ ጉዳይ ጠንካራ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ‹‹የሚደረጉ ስምሪቶችን ትክክል አይደለም፤ ከሠራዊቱ ውስጥ የሕዝቡ ጥያቄ በዲሞክራሲያዊ መንገድ መስተናገድ አለበት፡፡ ሙስና ሀገር እያጠፋ እያወደመ ነው›› የሚሉ ነበሩ፡፡ ሠራዊቱ ውስጥም የከረረ ትግል ነበር፡፡ ሕዝቡ ዝም ስላለ ሠራዊቱ ራሱ ሕዝቡን ወክሎ ስርዓት ሊቀይር አይችልም፡፡ ስርዓት የሚቀይረው ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ የሁሉ የበላይ ነውና፡፡
አዲስ ዘመን፡-ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ጀነራል ብርሀኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡