ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል እንዲሉ የከሀዲውንና እፉኝቱን ትህነግ መደምሰስ ተከትሎ አፈር ልሶ እንዲነሳ ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ የውሃ ሙሊት እንዲጨናገፍ እና በሀገሪቱ ታሪክ በአንጻራዊነት ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ ፣ ተአማኒ ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ተብሎ እና “የቋጠሮዎች ሁሉ መፍቻ ፤” ተደርጎ የሚጠበቀው ምርጫ እንዲደናቀፍ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ጭፍራዎ ቻቸው አገር ለማተራምስ እየሰሩ ይገኛሉ።
በተለይ ለፍርፋሪ ሀገራቸውን የከዱ ባንዳዎች ፣ በውስጥም በውጭም ያሉ የትህነግ ርዝራዦችና የዓለምአቀፍ ተቋማቱ የተሰገሰጉ የጥቅም ተጋሪዎቹ ፤ በአፍቃሪ መለሷ ሱዛን ራይስ የተጠመዘዘው የባይደን አስተዳደር ፤ በሀሰተኛ መረጃ የተደናገረው ዓለምአቀፍ ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ መንጋ ፤ የመንግስታቱ ድርጅት ፤ ግብጽ ፣ ሱዳን ፣ ወዘተረፈ ከየጎሬያቸው ወጥተውና ግንባር ፈጥረውና ተማምለው ሀገራችንን ለማተራመስ የመጨረሻውን የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ነው ።
የማይታረቅ ልዩነት አላቸው ተብሎ የሚታመኑ ኃይላት ሳይቀሩ ሳይነጋገሩ በጥቅሻ ተግባብተው በአንድነት ለጥፋት ታጥቀው ተነስተዋል። የትህነግ ርዝራዥ ፣ የኦሮሞና የአማራ አክራሪ ብሔርተኞች እንዲሁም ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስና ጓዶቹ ፓለቲካዊ ከፈን ቀደው ተነስተዋል ። መቼም ዘንድሮ በዚች ሀገር ያልተነሳ የለም ። ኮቪድ 19 ፣ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትንም በአናቱ ይደርቧል ።
ይሁንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ላይ በለውጥ ኃይሉ መለሳለስ ፣ ዳተኝነት ፣ ተቋማዊ እንዝህ ላልነት ፣ ፓለቲካዊ ማባበል ፣ በሕዝብ ግንኙነትና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተስተዋለው መዘናጋት ለውጡ ግለቱንና ተቀባይነቱን ጠብቆ እንዳይቀጥልና የገዛ ትርክቱን እንዲነጠቅ ማድረጉ ሳይዘነጋ ። በከባድ መስዋዕትነት የተገኘው የሰሜኑ አንጸባራቂ ድል በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ ጠልሽቷል። ያለፉት ሶስት አመታት ዘርፈ ብዙ ግጭቶችና ቀውሶች ተካረውና ጉነው ጡዘት (climax) ጫፍ ላይ ደርሰዋል ።
በመጪዎቹ ተከታታይ ሁለት ወራቶች ውስጥ የሚካሄደው ነጻና ተአማኒ ምርጫና ሁለተኛው ዙሩ የሕዳሴው ውሃ ሙሊት የጡዘቱ ወካይ ናቸው ። በተጻራሪ ኃይላት ማለትም በኢትዮጵያና በጸረ ኢትዮጵያን መካከል የተፈጠረው ትንቅንቅና ግጭት ተካሮ ጫፍ ይደርሳል ። ግጭቱ እንደተካረረ ስለማይቀጥል ምርጫው ሲካሄድ ውሃው ሲሞላ መርገቡና መፈታቱ አይቀርም ።
በስነ ጹሑፉ አለም ይህ ሒደት ልቀት (resolution) ይባላል ። መካረሩም ሆነ ጡዘቱ መርገቡና መፈታቱ አይቀርም ። ተፈጥሮአዊ ነውና ። ይህን ተከትሎ ተጻራሪ በሆኑ ገጸ ባህሪያት ሕይወት ላይ በአዎንታም ወይም በአሉታዊ ለውጥ ይመጣል ። ሀገራችን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ። የጠለቀችው ጀምበር መውጣቱ ፤ ጨለማው መንጋቱ አይቀርምና ። ከፈጣሪ ጋር ኢትዮጵያን ያሉ ያሸንፋሉ ። ዳሩ ግን እስከዚያው ድረስ ትልሙ ወይም ሴራው(plot) አዳዲስ ተዋንያንን ወይም ገጸ ባህሪያትን እለት በዕለት እያስተዋወቀን ነው ። የግጭቱ ደራሲዎች ከቀረጹልን አጃቢ ገጸ ባህሪያት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስ ቀዳሚው ነው ። አንቱታ የነፈግሁት ሁለት ጸጉር ካበቀለ ሶስቱን አገዛዦችን ሸኝቶ አራተኛውንም ተያይዞት እያለ ስለቀለለብኝ ፤ ሽበቱም የእንጨት ሽበት ሆኖ ቢቸግረኝ ነው ።
ሻለቃ ለውጡ እንደባተ ለደጅ ጥናት ይሁን ለስልጣን ቅልውጥ አዲስ አበባ መጦ ይቺ ሀገር በሌለ ጎኗ ከወር በላይ ሒልተን ሆቴል አሳርፋ አስተናግዳዋለች ። ለነገሩ በዚያ ሰሞን ከፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ውጭ ማን ያልተጦረና ስፓንሰር ያልተደረገ ዲያስፓራ ፓለቲከኛ አለ ። ደጅ ጥናቱ አልተሳካም መሰል ሻለቃ ከ35 አመታት በላይ በስደት ወደኖረበት አሜሪካ እንደተመለሰ ብዙ ሳይቆይ” የዐቢይ መንግስት ከሽፏል፤” በማለት ጥርሱን የነቀለበትን የከሽፏል ካርድ አወጣ ። አሟረተ ። ሰሞኑን ደግሞ በቀድሞው የጎንደር ፋሲለደስ ኪነት ተወዛዋዥ ፣ ከሕብረ ትርኢት አቅራቢ አበበ ገላው ማህበራዊ ሚዲያ ቀርቦ 180 ዲግሪ ተሸብልሎ ከወግ አጥባቂነት ወደ አክራሪ ብሔርተኝነት በመቀየር የአማራ ርዕስት ሳይመለስ ፤ አዲስ አበባ አራት ኪሎ ገብቶ ከምንልክ በኋላ የተነጠቀውን ዙፋን ሳይነጥቅ ቤቱ እንዳይገባ ለአማራ ወጣት ጥሪ አደረገ ።
የሽግግር መንግስት ምክር ቤት መቋቋሙንም በነካ አፉ አወጀ ። በአንድም በሌላ መልኩ ለአንድ ትውልድ እልቂት ተጠያቂ መሆኑን ዘንግቶ በአሜሪካ ሆኖ ሌላ ዙር እልቂትን ለፈፈ ። አብዮቷ ልጆቿን እንደ ድምት ስትበላ በህይወት ተርፎ ለስደት የበቃው በመተወን ብቃቱ መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል ። የሚተውነው ደግሞ በተለያየ ገጸ ባህሪ ነው ።
ሰውየው የሁለት አለም ሰው ነው ። የገሀዱና የፈጠራ አለም ። የፈጠራው አለም የገሀዱ አለም ነጸብራቅ መሆኑን ያጤኑአል ። በገሀዱ አለም ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስ ይባላል። በ1940 ዓ.ም ይችን አለም ተቀላቀለ ። የፊታችን ሀምሌ መጨረሻ የ73 አመት አዛውንትና ሽማግሌ ነው ። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮነን ተከታትሏል ። በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛንጊዜው ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በ1964 ዓ.ም በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ሰርቷል ። በሀገረ አሜሪካ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በዓለምአቀፍ ሕግ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል ።
ከ2006 ዓ.ም አንስቶ እስከዛሬ በአሌክሳንድሪያ ቨርጅኒያ ግዛት የአፍሪካ የስትራቴጂካዊና የደህንነት ተቋም መስራችና ዋና ዴይሬክተር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል ። ወደ ሀገረ አሜሪካ ደርግን ከድቶ እስከኮበለለበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገለ ሲሆን በኤርትራ የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ አስተባባሪ እና የእርዳታና መልሶ ማቋቋም ኮሚሽነር እስከ መሆን ደርሶ ነበር ። ጮሌና ብልጣብልጥ ነው ። በእጁ የገባች እያንዳንዷን አጋጣሚ ሳያባክን ጨልጦ ይጠቀማል ። እርዳታ ማስተባበሪያ እያለ ከዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ከምዕራባውያን ጋር ጥሩ ወዳጅነትን መስርቷል ።
በ1977 ዓ.ም በወቅቱ ዜጎች በርሀብ እንደ ቅጠል እየረገፉ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ወደ አውሮፓ እንደወጣ የውሃ ሽታ ሆኗል ። ሳይማር ያስተማረውን ወገኑን በዚህ ክፉ ቀን ከዳው ። በወገኑ ሞት ኑሮውን አደላደለ ። በወቅቱ ኒውዮርክ ታይምስንና አሶሴትድ ፕሬስን ጨምሮ ታዋቂ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች የመክዳቱን መርዶ ተቀባብለውታል ። ለእነ ሞሳድ ፣ ሲአይኤና ኤም አይ 5ና6 ለሁሉም ወይም በአንዱ ለሶስቱ ይሰልል ስለነበር ነው ትልቅ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው የሚሉ ወገኖችም አሉ ። የሚያሳዝነው ክህደቱ ሳያንስ በእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የውጭ አካውንት የሚገኝን 300ሺህ የአሜሪካ ዶላር አውጥቶ መሠወሩ ነው ።
በዚህም ለርሀብ የተዳረጉ ጨቅላዎችንና አራሶችን ህይወት ለአደጋ መዳረጉን ፤ ከእነሱ ጉሮሮ ቀምቶ በለንደንና በካሊፎርኒያ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን መግዛቱን በወቅቱ የወጣ የደርግ መግለጫ ያስረዳል ። ይሄን ክስ ሰውየው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያስተባብላል ። በደማሙ ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” በተሰኘው ልብ ሰቃይ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተዋቀረ ረጅም ልቦለድ የተቀረጸው ሰለሞን በትረጊዎርጊስ ግን የዛን ጊዜው የቀይ ኮከብ ዘመቻ አስተባባሪ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስ መሆኑን ራሱ በገደምዳሜ ያምናል ። ሰውየውን ከገሀዱ አለም ማንነቱ ይልቅ የፈጠራው አለም ሰለሞን ይገልጸዋል ።
ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ በ1974 ዓ.ም በአስመራ በጓድ መንግስቱ ሀይለማሪያም የታወጀው የቀይ ኮከብ ሁለ ገብ ዘመቻ የማስታወቂያና የፕሮፓጋንዳ አስተባባሪ ነበር ። በዚህ አጋጣሚ የታዘበውን እውነት ነው እንግዲህ በ1975 ዓ.ም በልቦለድ መልክ ለንባብ ያበቃው ። ሆኖም መጽሐፉ 500 ቅጂዎች ብቻ እንደተሸጠ በ24 ሰዓት ከገበያ እንዲሰበሰብ ተደርጓል ። መጀመሪያ በዓሉን ከስራው አሳገደው፤ ከወራት በኋላ ደግሞ ደብዛውን አስጠፋው ። እንደወጣ አስቀረው ።
በዓሉ ለባለቤቱ ፣ ለልጁ ፣ ለቅርብ ዘመዶቹ ፣ ለጓደኞቹና ለአድናቂዎቹ ድንገት ከተሰወረ ይኸው 40 አመት ሊሞላው ነው ። አሟሟቱ እንቆቅልሽ እንደሆነ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል ። የዘመቻውን መክሸፍና አቅጣጫ መሳት በገለጸበት በዚህ መጻሀፍ ዋናም ሆኑ አጃቢ ገጸ ባህሪያቱ የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ መሪዎችና ጭፍራዎች ነበሩ ። ሰለሞን በትረጊዎርጊስ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስ ፤ የፕሮቶኮል ሹሙ ፍስሐ ገዳ ተድላ ረጋሳ ፤ ፋሲካ ሲደልል መጽሐፈ ዳንኤል ፤ ዋና ገጸ ባህሪው ጸጋዬ ራሱ በዓሉ ግርማ እንደነበረ ይነገራል ። ሻለቃ ዳዊት በዓሉን ከሀገር እንዲወጣና ራሱን እንዲያድን መክሬው ነበር ይበለን እንጂ ከበዓሉ መሰወር ጀርባ የእሱ እጅ ስላለመኖሩ እርግጠኛ አይደለንም ።
“ኦሮማይ” ዘንድሮ ወደ እንግሊዘኛ ተመልሷል ቢባልም ገበያ ላይ አላጋጠመኝም። ሰለሞን በትረጊዎርጊስ መሰሪና ብልጣብልጥ ነው። እንደ ጥበበኛው ሰለሞን “ጥበቡ” አላዋጣ ሲለው በስውር በበትሩ ሸንቆጥ ያደርጋል ። ሰውዬው/ሰለሞን/ሻለቃው ደም ደም የሚሉ ሁለት መጽሐፍትም አሉት ። በአንድም በሌላ መልኩ በእጁ ደም ስላለበት ሁለቱም መጽሐፎቹ አፍቃሪዬ ደም ናቸው ። የመጀመሪያው “Red Tears” ሁለተኛው ደግሞ “ክህደት በደም መሬት” የሚሉ ናቸው ። ሰውየው በአገኘው አጋጣሚ ጓዶቹን እንደ አስቆርቱ ይሁዳ አሳልፎ እየሰጠ ራሱን ግን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ይልሀል ። የደርግን ግፍ ከውጭ ሆኖ ይተርክልሀል ።
የመልሶ ማቋቋምና እርዳታ ማስተባባሪ ኮሚሽነር እያለ በተፈጠረለት እድልና ትውውቅ ከኩብለላው በኋላ በሀገረ አሜሪካ ቨርጂኒያ ባቋቋመው የስትራቴጂካዊና የደህንነት ተቋም አማካኝነት በአፍሪካ ሀገራት ቀውስና የእርስ በርስ ግጭት ረብጣ ዶላሮችን አፍሷል። ሰውየው ልክ የዛሬ አመት በዚህ ወር “የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ከሽፏል፤” ማለቱን ተከትሎ ፤ “መክሸፍስ እንደ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊሱ ‘መክሸፍ ‘…!?” በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ ባስነበብሁት መጣጥፍ፤
“…አበው እመው ቅቤ መዛኝ ፣ ድርቅ ያወራል ፤ የሚል ወርቅ ይትበሀል አላቸው። ዘንድሮ ድርቅ ስለሆነ ቅቤ አልገባም በማለት ዋጋ ለመጨመር፣ ለማስወደድ ፤ የፖለቲካ ነጋዴም ለማትረፍ መንግስት ከሽፏል ፣ ወድቋል እያለ ያሟርታል ። ፍርሀት ፣ ሽብር ይነዛል ። በዚህ ነው የሚያተርፈው ፣ የሚሸቅጠው ። መክሊቱ በሀገር መክሸፍ ላይ የሚቦካ ፣ የሚጋገር ነውና ። የሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስ ‘ የአብይ መንግስት ከሽፏል ፤ ‘ ሟርት መግፍኤው ይሄው ነው ። እሱን ጨምሮ መሰል የንግድ ሸሪኮቹ ከቀድምዋ ዛየር ፣ ከሶማሊያ ፣ ሴራሊዮን ፣ ሶማሊያ ፣ ናይጄሪያ ፣…፤ መንግስታት መክሸፍ ማግስት ከክሽፈት እንዲያገግሙ በማማከር ስም ረብጣ ዶላሮችን ሰለመዛቃቸው ለመናገር የግድ ነብይ መሆን አይጠይቅም ።
ለእነዚህ የፓለቲካ ነጋዴዎች እና የእነሱን ዳና ተከትለው ለሚገቡ ዓለምአቀፍ” እረጂ “ ድርጅቶች የአንድ መንግስት መድከም ፣ መክሸፍ ፤ ግዳይ እንደመጣል ነው ። ግራም ሃንኮክ “የድህነት ጌቶች “(Lords of poverty) እግረመንገድ ያስታውሷል ። ሻለቃው አሁንም ሟርትን ከነውጥ ለንጥቆ በአዲስ ማንነት የመጣው በቅዠቱ ሀገር ስትፈርስ ታይቶት ቆርቆሮዋን ፣ ግድግዳና ማገሯን ፣ በርና መስኮቷን “ምናለሽ ተራ” ለመሸጥ ነው ። እሱና ጭፍራዎቹ ይፈርሱ ይሆናል እንጂ ሀገሬ አትፈርስ ። ይልቁን ገና በእነሱ ፍርስራሽ ታንሰራራለች ።
እንደ መውጫ
እንደ ድፍረት፣እንደ ብልግና አይቆጠርብኝና ፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ ይመክራሉ፣ይዘክራሉ ፣ ይገስፃሉ ፣ …፤ ብለን የምንጠብቃቸው አንጋፋ ፣ ጉምቱ አባት ልሒቃን በስተእርጅና በስሜት እየተንተከተኩ ሀገሪቱን ወደማይፈለግ አቅጣጫ እየመሯት ነው ። ዕድሜ ፣ መማር መመራመር ምራቅ ካላስዋጠ ፣ መስከን ፣ ማመዛዘን ካላስቻለ ፤ ስሜት ካላስገዛ ፤ ለሽበት ለሽበትማ እንጨትም ፣ ድንጋይም ሽበት አለው። በተለይ የሶስት መንግስታትን እድሜ ስልቅጥ ያረጉ አንቱ የተባሉ አባት ሙሁራን ይሸመግሉናል ፣ ያስታርቁናል ፣ ያቀራርቡናል ፣ … ፤ ስንል በማህበራዊ ሚዲያው በየጋዜጣውና በየመፅሔቱ ወፈፍ ሲያደርጋቸው እያነበብን ፤ ከእነሱ በአራት እጥፍ የሚያንሱ ዘለው ያልጠገቡ ፤ እሳትና ውሃ ያለዩ ብላቴናዎች ፤ የእነሱን ፁሑፍ እያነበቡ ለጥፋት ቢነሳሱ ለምን ይገርመናል !?
ከአያቶቻቸው ያልተማሩትን መስከን ፣ ማመዛዘን ከማን ሊማሩት ይችላሉ !? የሻለቃ ሰሞነኛ አስደንጋጭ የሁከትና የነውጥ ጥሪም ከፓለቲካ ነጋዴነት በተጨማሪ የእነዚህ አንጋፋ ፣ አባት ልሒቃን ቅርሻ አካል ነው ። አባት ሙሁራን በምታምኑት ፈጣሪ እንማፀናችሁ እንደ ፈሪሳውያን ፣ ፀሐፍት ፣ ወትዋችነቱን activism ተውትና መካሪ ፣ ዘካሪ ፣ አስታራቂ ፣ አቀራራቢ ፣ ገሳጭ ፣ … ፤ ሁኑ !!! ካልቻላችሁ ደግሞ በቃ ዝምም…በሉ ፤ የእድሜ ፀጋ እኮ ለአርምሞም ፣ ለጥሞናም ነው ።
“እኛ እንፈርሳለን ፣ እንደክማለን ፣ እንወድቃለን እንጅ ኢትዮጵያ አትፈርስም !!! “
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013