ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ ኑሯቸውን በአሜሪካን ሀገር ያደረጉ የህክምና ባለሙያና ልጆችን በማሳደግ የተሳካላቸው እናት ናቸው። እኚህ ሴት ሀገሬ ላሉ ወላጆች ይጠቅም እንደሆነ ብለው ሀሳባቸውን ማካፈል ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ለዛሬም ልጆቻችን እርስ በእርስ እንዲተሳሰሩ የወላጆች ሚና ምን መምሰል አለበት? በሚል ምክራቸውን በዚህ መልኩ አቅርበውልናል።
አንድ ወላጅ በልጆቹ መካከል ንፁህ የሆነ ፍቅርና ከዚያም በተጨማሪ ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር ምን ማድረግ ይችላል? ወላጅ ሆኖ በልጆቹ መካከል እንደዚህ አይነት ግንኙነት እንዲኖር የማይመኝ ወይም የማይፈልግ የለም።ነገር ግን እንደዚህ አይነት ግንኙነት ዝም ብሎ በተፈጥሮ ብቻ አይመጣም።እንዲዚህ አይነት ግንኙነት እንዲፈጠር ወላጅ ትልቅ ሚና ይጫወታል።የወላጅ አስተዋጽኦም በጣም ወሳኝ ነው፡፡
የወላጅ ሚና የሚጀምረው አዲሱ ልጅ ገና በእናት ሆድ ውስጥ እያለ ገና ከመወለዱ በፊት ነው።ይኸውም እናት እርጉዝ እያለች እቤት ውስጥ ላለው ልጅ ስለ አዲሱ ልጅ በማውራት፤ አዲስ ልጅ ሊመጣ ነው ብሎ በመንገር ሆድዋን እያስነካች እስቲ ስም እናውጣለት፣ ማን እንበለው? በማለት ልጁን ማስተዋወቅ ያስፈልጋል።ይህም የአዲሱ ልጅ መምጣት ለነባሩ ልጅ አዲስና ድንገተኛ ክስተት እንዳይሆንበት ለማለት ነው፡፡
አዲሱ ልጅ እንደተወለደ ደግሞ በሕፃኑ እንክብካቤ ላይ ታላቁን ልጅ ማሳተፍ በጣም ይጠቅማል።ለምሳሌ ሕፃኑን መጥቶ እንዲስመው ማድረግ፣ በጥንቃቄ እንዲቀርበው እግሩን ማስነካት፣ ጡጦ እንዲያቀብል ማድረግና በመሳሰሉት መንገዶች ታላቁን ወደ ታናሹ እንዲቀርብ ማድረግ ይረዳል።እርግጥ እዚህ ላይ የወላጅ ጥበቃና ጥንቃቄ አስፈላጊ ነው።ምክንያቱም ታላቁ ሳያውቀው ሕፃኑን እንዳይጎዳው በማሰብ ነው፡፡
በዚህ ላይ ወላጅ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት አብዛኛውን ሐሳቡን በአዲሱ ልጅ ላይ አድርጎ ትልቁን ልጅ ችላ የማለት ሁኔታ እንዳይፈጠርና ትልቁም ልጅ ይህ ስሜት እንዳይሰማው ለማድረግ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልጆቹ ከፍ ካሉ በኋላ የወላጅ ትልቁ ሚና ልጆቹ አብረው እንዲጫወቱ ማድረግ ነው።በተለይ ደግሞ አብረው እየተጫወቱ ሳለ በጨዋታ ላይ በሚጣሉበት ሰዓት ብዙውን ጊዜ በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ነው።
በጨዋታ ላይ ልጆች መጋጨትና መጣላት ያለ ነው።በዚህን ጊዜ ልጆች ሮጠው ወደ ወላጆቻቸው መጥተው እንዲዳኙዋቸው ይፈልጋሉ።በዚህን ጊዜ ወላጆች በመሐል ገብተው መዳኘት ለልጆቹ የእርስ በርስ መተሳሰር አይጠቅምም።የተሻለው መንገድ ልጆቹን ሂዱ የራሳችሁን ችግር ራሳችሁ ፍቱ ብሎ ልኮ በመከታተል ራሳቸው ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረግ ይጠቅማቸዋል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ላይ ወላጅ ማድረግ ያለበት ትልቁ ጥንቃቄ ለአንዱ የማዳላት ወይም አንዱን እንደ አጥቂ ሌላኛውን እንደተጠቂ እንዳይመለከት ነው።ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ስሜት ከተፈጠረ በወንድምና በእህት መካከል የቅናት ወይም የጥላቻ ስሜት ስለሚፈጥር እዚህ ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በልጆቹ መካከል የመተሳሰር ግንኙነት እዲፈጠር ሆነ ብለን አንዳንድ የሚያስተሳስሩ ነገሮች ማድረግ አለብን።ለምሳሌ ከልጅነታቸው ጀምሮ አንዱ የሌላውን የተወለደበትን ቀን እንዲያከብር ማድረግ፣ በዚያን ቀን አንዱ ለሌላው አስቦ ማስታወሻ ለመልካም ምኞት መግለጫ እንዲለዋወጡ ማድረግ እና የመሳሰሉትን ባህሪያት ቢያዳብሩ በልጆቹ መካከል ትልቅ የመፈቃቀርና የመተሳስር ስሜት ይፈጥራል።ይህንን ከዓመት ዓመት እንደ ቤተሰብ ባህል አድርጎ በመያዝ ትልቅ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።በዚህና ይህንን በመሳሰሉ መንገዶች ልጆቹ በሕይወታቸው ሁሉ የተሳሰሩ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡
የልጆቻችን የእርስ በርስ መቀራረብና መፋቀር ከሁሉ በላይ የሚጠቅማቸው ለራሳቸው ለግልና ለማህበራዊ ሕይወታቸው ነው።ይህም በትንሽነታቸው የውጭ የእኩያ ጫና እንዳያጠቃቸው ይረዳቸዋል።ምክንያቱም እቤት መጥተው አንዱ ለአንዱ ስለሚያወራ አድገውም ከሄዱ በኋላ በየጊዜው ስለሚገናኙ ለአዕምሮ ጤና ጭምር በጣም ይጠቅማቸዋል። ከዚያም ባለፈ በቤት ውስጥ በፍቅር ያደገ ለማህበረሰቡም እንዲሁ አሳቢ ይሆናል። ይህ መተሳሰር በልጆቻችን መካከል እንዲኖር የእኛ የወላጆች ሚና በጣም ትልቅ ነው ይሉናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013