ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቁ የፋሲካ በአል ዛሬ ይከበራል። በእምነት፤ ክርስቲያንና ልዩ የሚባሉ ሶስት ልጆች በዓሉን እንዴት ለማሳለፍ እንደሚያሳልፉ ስጠይቃቸው ከቤተሰቦቻችን ጋር እየተደሰትን፣ የተቸገሩትን እየረዳን እናከብረዋለን ብለውኛል። እናንተስ በዓልን በምን መልኩ እያከበራችሁ ነው?
እነ ልዩ አያቶቻቸው ጋር ሄደው አብሮ መብላት፤ አያቶቻቸውን በመታዘዝና፤ የአያቶቻቸውን ጉርሻ በመጉረስ እንደሚያሳልፉት ነግረውኛል። የአያቶቻቸውን ጉርሻ እጅግ በጣም የሚወዱት መሆኑን የነገሩኝ ሲሆን፤ ይህ አይነት የበዓል አከባበር አብሮነታቸሁን ስለሚያጠናክር ለወላጆቻችሁ እየታዘዛችሁ በጎ ነገሮችን እያደረጋችሁ እንድታከብሩ እመክራችኋለሁ።
በአል ሲከበር መረዳዳት፣ መተጋገዝ ኢትዮዽያዊ ባህላችን እንደሆነ ታውቃላችሁ። ይህንን ሁልጊዜ የህይወታችሁ መርህ በማድረግ ያላችሁን ነገር ከሌላቸው ጋር በመካፈል በዓላትን የደስታ ቀኖቻችሁ በማድረግ ማሳለፍ ይኖርባችኋል። ልጆች ደስታ በመተጋገዝ ብሎም ሌላው ሰው ሲደሰት በማየት የሚገኝ ነገር ነው። ስለዚህ ልጆች መስጠታችሁ ከልባችሁ መሆን አለበት።
ልጆች ለመስጠት ስታስቡ የማትፈልጉትን ነገር ብቻ ሳይሆን የምትወዱትንም የሚያስፈልጋችሁን ነገር ማካፈል ሁልጊዜም ትክክል ነው። ይህን ስላችሁ አንድ ያነበብኩት ታሪክ ትዝ አለኝ።
ታሪኩ እንዲህ ነው። አባት እና ልጅ እየተራመዱ ሳለ አባት ለልጁ ሁለት ፓም ወይም አፕል ይገዛላታል፤ ልጅቷም ሁለቱን ፖም በሁለት እጆቿ አንድ አንድ ያዘች። አባትም አንድ ፖም ልታካፍለው ትችል እንደሆነ ጠየቃት። ሴት ልጁ ይህን ስትሰማ በፍጥነት አንደኛውን ፖም በትንሹ ግምጥ አደረገቸው እናም አባቷ ተናግሮ ከመጨረሱ በፊት ከሁለተኛው ፖምም በትንሹ ግምጥ አደረገች።
አባት በሁኔታው ተገረመ፣ አዘነም።‘ምን ዓይነት ስግብግብ እና ራስ ወዳድ ልጅ ነው ያሳደኩት? እንደ ወላጅ የቱ ጋር ነው ያጠፋሁት?’ እያለ ማሰብ ጀመረ። እንዴት ብሎ ሴት ልጁን ስለማጋራት እና ስለመስጠት ማስተማር እንዳለበት እያሰበ ፈገግታው ከፊቱ ላይ ጠፋ።
እናም በድንገት ሴት ልጁ በአንድ እጇ ላይ አንድ ፖም ይዛ “አባዬ ይህን ውሰድ፣ ይኸኛው በጣም ለስላሳና እና ጣፋጭ ነው” ብላ እጇን ዘረጋችለት።አባቷም በሆነው ነገር ተገርሞ ቃላት ስላጣ ዝም አለ።
ልጆች ለመስጠት ስታስቡ ቅድሚያ ስስትንና ሰግብግብነትን ከውስጣችሁ ማጥፋት አለባችሁ። ከዚያ በኋላ ምንም ያህል የምትወዱትና የምትሰስቱለት ነገር ቢሆንም ከማካፈል ወደኋላ አትበሉ።
በዚህ በዓልም የተቸገሩትን በመርዳት ያላችሁን በማካፈል በፍቅር፣ በመተሳሰብና በትህትና ታሳልፉ ዘንድ ምኞቴ ነው። መልካም የፋሲካ በዓል ይሁንላችሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013