ወደ ቦሌ መንገድ በሚወስደው አቅጣጫ መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው አዲስ አበባ ሙዚየም ውስጥ ነኝ። ከግቢው የመግቢያ በር ጀምሮ ሙዚየሙ በውስጡ የያዘውን እምቅ የታሪክ ሀብት እየጎበኘሁ ነው። እናንተም ውድ አንባቢዎች ተከተሉኝ አብረን እንጎብኝ። ወደ ሙዚየሙ ለመግባት ሁለት አማራጮች አሉ።
አንደኛው በመስቀል አደባባይ በኩል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በተለምዶ ፍላሚንጎ ተብሎ በሚጠራው በጀርባው ዞሮ በሚገኘው መግቢያ መጠቀም ይቻላል። በጀርባው በኩል የተለያዩ ግንባታዎች በመኖራቸው ለጎብኝው ምቾት ላይሰማ ይችላል። ግን ጊዜያዊ በመሆኑ እንደ ችግር አይታይም።
የሙዚየሙ ውበት ከውጫዊ ገጽታው ይጀምራል። በመግቢያ በሩ ላይ ቀድመው የሚያገኙት በሳር ክምክም ክዳን የተሰራው ጎጆ ቤት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የመኖሪያ ቤት የግንባታ ታሪክ ያስታውሰናል። ዛሬም በሳርቤት ክዳን የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ቢኖሩም በከተማ ደግሞ እንዲህ በትውስታ የማንነት መገለጫና የቱሪስት መስህብ ሆኖ ትኩረት እየሳበ ይገኛል።
ዋናው የሙዚየም ቤት አሰራርም እንዲሁ ጥንታዊ ነው። የቤቱ ክዳን ቆርቆሮ፣ ጣሪያው፣ ምሶሶው፣ የውስጥ በሮቹና መስኮቶቹ ከነተሰሩበት የግንባታ ግብአት ዕድሜ ጠገብ አይመስልም። ኪነህንፃው ባለበት መጠነኛ የሆነ እድሳት ከመደረጉ በስተቀር ቤቱ እንደተጠበቀ እንደሆነ ከሙዚየሙ አስጎብኝ ዓለሙ አበበ ለመረዳት ችያለሁ። ከአስጎብኝዬ ዓለሙ አበበ ጋር ቆይታችን ቀጥሏል። ወደ ሙዚየሙ ውስጥ ዘለኩ። በጥቁር ቀለም የተነሱ የሰውና የተለያዩ ብዛት ያላቸው ምስሎች በግድግዳ ላይ ተሰቅለዋል። የነገሥታት የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎችና አልባሳት በመልክ በመልኩ ተደርድረዋል።
የጽሁፍ መግለጫዎችም ከፎቶግራፎቹ መካከል ተሰቅለዋል።ሙዚየሙ የተለያዩ ክፍሎች አሉት።የአዲስ አበባ ሙዚየም በውስጡ ከያዟቸው በፎቶግራፍ የተደገፈና ሌሎችም ቅርስ በበለጠ የቤቱ ታሪካዊነት ይጎላል።አስጎብኝው እንዳስረዳው ቤቱ እኤአ በ1880 ነው የተገነባው። ቤቱን የሰሩት የህንድ ዜግነት ያላቸው ሀጂ ቀዋስ የተባሉ መሐንዲስ ናቸው።ቤቱ ያረፈበት ቦታ ከፍታ ተመርጦና ለቤተመንግሥቱም ትይዩ እንዲሆን ታስቦ ነው።በወቅቱ የነበሩ ነገሥታት ከፍታ ቦታ ላይ ግንባታ ማከናወን ይመርጡ እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል።
ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ቤቱን ያሰሩት ለጥይት መጋዘን ወይንም ለመሳሪያ ማከማቻ እንዲውል ነበር።ይሁን እንጂ በኋላ ላይ የራስ ብሩ ወልደገብርኤልና ባለቤታቸው ወይዘሮ አማከለች መኖሪያም ሆኖ አገልግሏል። ባልና ሚስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላም ልጆቻቸው ዘነበወርቅና ፍቅርተ ብሩ ኖረውበታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለሆቴል፣ የመድኃኒት መሸጫ(ፋርማሲ)፣ትምህርት ቤት ሆኖ አገልግሎት ሰጥቷል።ከዚህ ሁሉ አገልግሎት በኋላ ነው ሙዚየም ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገው።
ሙዚየም የመሆን አጋጣሚው የተፈጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አንድ መቶኛ አመት የምስረታ በዓል ላይ ነው። በወቅቱም የአዲስ አበባ ከተማን ታሪክ የሚያሳይ ሙዚየም እንደሚያስፈልጋት ሀሳብ ይነሳል።ሀሳቡም በተግባር የዋለው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩት ከንቲባ ዘውዴ ተክሉ ሲሆን፣ከህዳር ወር 1979ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ሙዚየም ተመሰረተ። ሙዚየሙ ስድስት አዳራሾችና ተጨማሪ የጊዜያዊ ኤግዚቢሽን ክፍሎች አሉት።ስድስቱም አዳራሾች ስያሜ ወይም መጠሪያ ስም ተሰጥቷቸዋል። የመጀመሪያው አዳራሽ የከተማ ምስረታ ይባላል።
ለአዳራሹ ይህ ስያሜ የተሰጠው አዲስ አበባ ከተማን የመሰረቱት እቴጌ ጣይቱና ዳግማዊ አፄ ሚኒልክን ታሪክ የያዘ ነው።እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው የአፄ ዳግማዊ ሚኒልክ አያት ንጉሥ ሳህለስላሴ አዲስ አበባ ከተማ አሁን በተመሰረተችበት ቦታ እንድትቋቋም ተንብየው እንደነበር ታሪክ እንደሚያስረዳ በአስጎብኝው ዓለሙ ገለጻ ተደርጎልኛል።ምስላቸውም በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛል።አዲስ አበባ ከተማ እንዴት ተመሰረተች ከሚለው ጀምሮ ያለውን ሂደት የሚያሳይ በምስል የተደገፈ መግለጫዎች የሚገኝበት ክፍል ነው። ሁለተኛው አደራሽ ደግሞ ዕድገት አዳራሽ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ይህ ክፍል ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ከተመሰረተች በኋላ የእድገት እንቅስቃሴዋን የሚያስቃኝ ነው።በተጨማሪም አፄ ዳግማዊ ሚኒልክ ከተለያዩ የአውሮጳ ሀገሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አውሮጳውያኑ የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ዘመናዊ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ ያደረጉትን ሂደት ያገኛሉ። የአፄ ሚኒልክ ኢንጂነር፣ ፎቶግራፍ አንሽ፣እንዲሁም አማካሪያቸው ሆነው ሲያገለግሏቸው የነበሩት አልፍሬድ ኢልክ የተባሉ የስዊዘርላንድ ዜጋ ዘመናዊ ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ አፄ ሚኒልክን በማገዝ ትልቅ ባለውለታ መሆናቸው በዚሁ ክፍል ውስጥ ታውሰዋል።
ሶስተኛው አዳራሽ ደግሞ የኢትዮጵያውያኖች ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር አፍሪካ ተምሳሌት በሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ አድዋ አዳራሽ ተብሎ ተሰይሟል።በዚህ ክፍል ውስጥ ጥንታዊያን ጀግኖች አባቶችና እናቶች በግፍ ኢትዮጵያን ሊወርር የመጣውን ወራሪውን ፋሽስት ጣሊያን በመጣበት እግሩ እንደሚለስ የመከቱበትን ባህላዊና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ እነ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ባልቻ አባነፍሶን የመሳሰሉ የዓድዋ ጀግኖች እንዲሁም ከሰዓሊ መርገበ ሚካኤል የተበረከተ ዓድዋ የሚል ስያሜ ያለው ስዕል እና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ወራሪውን ጣሊያን ለመመከት የክተት ዘመቻ ሲያውጁ ‹‹ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ጉልበት የሌለህ በፀሎትህ››ብለው ለህዝቡ ጥሪ ሲያቀርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለይም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ታቦት ይዞ ጦርሜዳ በመዝመት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ጭምር በአዳራሹ ይጎበኛሉ።
አራተኛው አዳራሽ ደግሞ ፋሽስት አንድ ዲፕሎማሲ ይባላል። ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ከወራሪው ጣሊያን ጋር ይያያዛል።ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ መውረሩ ይታወሳል።ፋስሽት ጣሊያን እኤአ በ1888 በኃይል ኢትዮጵያን ወርሮ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ተዋርዶና አፍሮ ከተመለሰ በኋላ 40 አመት ቆይቶ ዳግም ተመልሷል።ከተመለሰ በኋላም እኤአ ከ1928 እስከ 1933 የቆየባቸው አመታት ፋሽስት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ምክንያቱም ፋሽስት ጣሊያን ብዙ ጥፋቶች የፈጸመበት ጊዜ ነው። ለአብነትም በጠራራ ፀሐይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ንጹሐን ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፏል። እነዚህን ሁሉ ኩነቶች ተሰንደው በምስል ተደግፈው የኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ የሚጎበኝበትን ክፍል አስጎብኝው ገለጻ እያደረገ ሲጎበኙ ታሪኩን በአይነህሊና ወደ ኋላ መለስ ብለው እንዲቃኙ ያስችሎዎታል።
አምስትና ስድስት ተብለው የተሰየሙት አዳራሾች ተያያዥ የሆኑ ታሪኮችን የያዙ መሆናቸውን አስጎብኝው ዓለሙ ይገልጻል።ክፍሎቹ ልደት አዳራሽ የሚል ስያሜ ነው ያላቸው ሲሆን፣የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚመለከቱበት አዳራሽ ነው።የአዲስ አበባ ከተማ አንድ መቶኛ የምስረታ በዓል ሲከበር በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግለሰቦችና እንግዶች ስጦታ በማበርከት መልካም ምኞታቸውን የገለጹበት ኩነት የሚገኝበት ነው።
በዚህ ረገድ የማይዘነጉትና ዛሬ በህይወት የሌሎት በስዕል ሥራቸው ስመጥር የሆኑት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ እና ሰዓሊ ለማ ጉያ በጊዜው ያበረከቱት የጥበብ ሥራ ይገኝበታል። ስድስተኛው አዳራሽ ላይ ለየት ባለ ሁኔታ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማን በተለያየ ጊዜ የመሯት ከመጀመሪያው ከንቲባ ቢትወደድ ወልደጻዲቅ ጎሹ ጀምሮ 30 የሚሆኑ ከንቲባዎች ፎቶግራፎች ይገኛል።
ጊዜያዊ ተብሎ በተለየው አዳራሽ ደግሞ የስዕል ኤግዚቢሽን ነው። ለሁሉም ሰዓሊ ክፍት ሲሆን፤ የሥዕል ሥራዎቹን በዚህ አዳራሽ ውስጥ በማስቀመጥ መጠቀም ይችላል።ለጎብኝዎችም ክፍት ነው።በዚህ መልኩ ተዋቅሮ የተደራጀው ክፍል ጎብኝው በቀላሉ አዲስ አበባ ከተማ ከየት ተነስታ የት ደረሰች የሚለውን ለመረዳት ያስችለዋል።
በነበረኝ የጉብኝት ቆይታ ምስረታ አዳራሽ ውስጥ ሆኜ ካየኋቸው አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ከተማዋ ከመመስረቷ በፊት ቀድመዋት የተመሰረቱትን አክሱም፣ ላልይበላ ጎንደር የመሳሰሉትን ታሪክ የሚያስታውስ በፎቶ ግራፍ የተደገፈ፣እንዲሁም የነገሥታት አልባሳትና የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያዎቻቸው ድሮ ደንበጃን ተብሎ የሚጠራ የባህላዊ መጠጥ የሚቀመጥበት ዕቃ ትኩረቴን ሳበው።
ደበጃኑ መልኩ ጥቁር ስለሆነ እይታን ይስባል። አስጎብኝዬን ዓለሙን ስለደንበጃኑ ጠየኩት። እርሱም አንድ መቶ አመት ዕድሜ ያስቆጠር ጠጅ በውስጡ መያዙን ነገረኝ።ደንበጃኑ ከነጠጁ ከራስ ብሩ ወልደገብርኤልና ወይዘሮ አማከለች ቤተሰቦች የተበረከተ መሆኑም ነግሮኛል። ጠጅ በባህሪው ዕቃ ሰብሮ ይወጣል።ወይም ይፈነዳል። እሽጉ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆኑን ነው የሚያሳየው።
አፄ ሚኒልክ ቤተመንግሥታቸውን ከአንኮበር ወደ እንጦጦ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ያለውን ሂደት፣ ፍልውሃና ፒያሳ አካባቢ፣በዚያን ወቅት ሰዎች ጥፋት ሲያጠፉ በአደባባይ በግርፊያ ሲቀጡ፣ መንግሥት ነጋሪት በመጎሰም ለህዝብ መልዕክት ሲያስተላልፍ፣ ገበያ እንዲሁም በወቅቱ ግራዝማች፣ ቀኝ አዝማችና ደጅ አዝማቾችን ጨምሮ የእቴጌ ጣይቱና የአፄ ምኒልክ አልባሳት በአደራሹ ውስጥ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የተለያዩ ሀገራት እንግዶች እንዲህ በሙዚየሙ ቆይታ ካደረጉ በኋላ አለያም ከመጎብኘታቸው በፊት እንደ ምርጫቸው አረፍ ብለው ውጫዊውን የሙዚየም አካል እያዩ ዘና የሚሉበት ሥፍራ በሙዚየሙ ግቢ ውስጥ ይገኛል። በመዝናኛው የምግብና መጠጥ መስተንግዶ ይሰጣል። ወደ መዝናኛው የሚሄዱ እንግዶች እግረመንገዳቸውን ሙዚየሙን ለመጎብኘት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል።
ግን ስንቶች አጋጣሚውን ይጠቀሙ ይሆን? እግረመንገዴን የሙዚየሙን አስጎብኝ ጠይቄው የሚታሰበውን ያህል እንዳልሆነ ነገረኝ። በመዝናኛው ግቢ ውስጥ ሙዚየም መኖሩንም የማያውቁ እንደሚኖሩ ይገመታል። ሙዚየሙ በመኖሩ የሚደነቁትን ያህል ግን ለመጎብኘት ፍላጎታቸው አናሳ ነው።በጎብኝው በኩል ችግሮች ቢኖሩም በሙዚየሙ በኩልም ክፍተት መኖሩን ነው ተረድቻለሁ።
አስጎብኝ ዓለሙ ተግዳሮት የሚላቸውና በጥሩ ጎን ካነሳቸው ሀሳቦች ሙዚየሙ በሚገባው ልክ እንዲታወቅ በማድረግ ረገድ ሥራዎች ይቀራሉ። በዙሪያው ተሰባስበው ጫት የሚቅሙ በመኖራቸው ለደህንነት ሥጋት ነው። ለጉብኝት ወደ ሙዚየሙ ሲሄዱ ዝርፊያ ያጋጠማቸውም እንደነበሩ አስታውሷል።እንደ አስጎብኝው ማብራሪያ አዲስ አበባ ሙዚየም ከሌሎች በከተማዋ ከሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር በንጽጽር ሲታይ ያን ያህል ጎብኝ አለው ለማለትም አያስደፍርም።
ቢኖሩ እንኳን አብዛኞቹ ጎብኝዎች ወይም የሙዚየሙ ደንበኞች ተማሪዎች ናቸው። ከክፍለ ሀገር ጭምር ተማሪች የሚመጡ ሲሆን፣ ቅዳሜና ዕሁድ ሙዚየሙ ሥራ ይበዛበታል።ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ብዛት ተጠቃሚ የነበሩት ተማሪዎችም ቀንሰዋል።ለተወሰነ ጊዜም የማስጎብኘት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር።አሁን ደግሞ መልሶ በማንሰራራት ላይ ይገኛል።
አዲስ አበባ ሙዚየም ለኢትዮጵያ አየርመንገድ በቅርብ ርቅት ላይ ሆኖ፣ ቱሪስቶችም ሆኑ ለተለያየ የሥራ ጉዳይ የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚያርፉባቸው ሆቴል ቤቶች በአቅራቢያው ይገኛል።ይህን ዕድል መጠቀም አለመቻሉ ሙዚየሙን የሚያስተዳድረውን አካል ተጠያቂ ያደርገዋል። የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራትና በአካባቢው ያሉ ክፍተቶችን ቀርፎ ምቹ በማድረግ መሥራ ነበረበት። ሙዚየሙን የሚገኝበትን አቅጣጫ ጠቋሚ የማስታወቂያ ሰለዴ በተለያየ ግልጽ ቦታ እኔም አላየሁም።
እነዚህ ሁሉ ክፍተቶች ባለቡት ሙዚየሙን ከተማሪዎች ውጭ በአማካይ 50 ሰዎች ይጎበኛሉ። ይህ ከቅድመ ከኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽን በሽታ በፊት ያለው መረጃ ሲሆን፤ አሁን ገና በአዲስ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሙዚየሙ ለጎብኝዎች የሚያስከፍለው።ለተማሪዎች ሁለት ብር፣ ለአዋቂ ኢትዮጵያውያን 10 ብር ለውጭ ሀገር ዜጎች ደግሞ 50 ብር ነው።በጉብኙቱ አብራችሁኝ የነበራችሁ አንባቢዎች የቀረውን ለእናንተ ትቻለሁ።ቸር ሰንብቱ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013