መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ ሰሞነኛውን ስቅለትና ትንሳኤን ታሳቢ በማድረግ “ ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። “ የሚል ዘመን ተሻጋሪና ወርቅ ይትበሀል ትተውልን አልፈዋል ። ጨለማ ፣ የምድር መናወጥ፣ ክረምት ፣ ሰደድ እሳት ፣ በረዶ ፣ ጎርፍ ፣ መገፋት ፣ መዋረድ ፣ መገረፍ ፣ መቸንከር ፣ መሰቀል ፣ መከዳት ፣ መሸጥ ፣ ወዘተረፈ አርብ ቢሆንም ፤ መንጋቱ ፣ ብርሀን በጨለማ ላይ መንገሱ ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ ፣ መከበሩ ፣ መፈወሱ ፣ ትንሳኤ፣ ቀን መውጣቱ ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።
ክርስቶስ ሞትን ድልነስቶ እንደተነሳበት እሁድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ማንነትን ኢላማ ካደረጉ ጥቃቶች፣ ሞቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ የሀብት ንብረት ውድመቶች ፣ ከችግር ፣ ከድህነት ፣ ከተመፅዋችነት፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ከፈተና ፣ ከወረርሽኝ ፣ ከጭቆና ፣ ከአፈና፣ ከጥላቻ ፣ ከሴራ ፣ ከደባ ፣ ከሀሰተኛ መረጃ፣ ከከበባ ፣ ከውጥረት፣ ከአክራሪ ብሔርተኝነት ፣ ከትህነግ ርዝራዥ ፣ ከሸኔ_ኦነግና ከጉምዝ ሽፍታ ጥቃት ፣ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ወከባ ፣ ከሱዳን ወረራ፣ ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ጫና ፣ ከአለማቀፍ ሚዲያውና የመብት ተሟጋቾች የክስ ድሪቶ ፣ ነጻና ተአማኒ ካልሆነ ምርጫ ፣ በገዛ የተፈጥሮ ሀብታችን የበይ ተመልካች የነበርንባቸው ዘመናት ፣ ወዘተረፈ ነጻ የምንወጣበት አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት፤ ትንሳኤ’ችንን ፣ ህዳሴ’ችንን የምናይበት ቀን ይመጣል።አርብ አልፎ እሁድ ይመጣል ። “ ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። “ እያልን በእምነት በተስፋ እንጠባበቃለን ። ደግሞም ይሆናል ።
ከአምስት አመት በፊት ባጋጠመኝ አደጋና የጤና እክል ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኜ ቤት ለመዋል፣ ተሽከርካሪ ወንበረ/ ዊልቼር / ፣ አጓጓዥ / ወከር /ና ከዘራ ለመጠቀም ተገድጄ ነበር ። ለመልበስ፣ ለማውለቅ፣ ውሃ ለመጠጣት ለመመገብ፣ ለመታጠብ፣ ለመተኛት፣ ለመነሳት የሰው እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር። ስልክ ለማነጋገር ፣ የቴሌቪዥን ቻናል ለመቀየር እርዳታ ያስፈልገኝ ቆይቷል ። ሁሉ ነገሬ በሰው እርዳት ላይ የተመሰረተ ነበር ። መላ ህይወቴ ተመሰቃቅሎ ነበር ። ስራዬን አጣሁ ። በጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ከአአዩ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ ጥቂት ሲቀረኝ ተቋረጠ ። ህልሜ ተስፋዬ ተጨናገፈ። በመጨረሻም ለጭንቀትና ለድብርት ተዳርጌ ነበር ። በቅርብ ደግሞ በኮቪድ 19 ተጠቅቼ በሞትና በሕይወት መካከል ነበርሁ ።አርብ ነበርና !
እንዲህ አይነት ብዙ የሕማማት “ አርቦችን “ በህይወቴ እንዳሳለፍሁት ሁሉ እናንተም ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በህይወታችሁ መውደቅ መነሳቶችን ፣ ህማማትን ፣ አርቦችን ማሳለፋችሁ አይቀርም ። በግል ህይወታችሁ ፣ በትምህርታችሁ ፣ በፍቅራችሁ ፣ በትዳራችሁ ፣ በንግዳችሁ ፣ በሕልማችሁ፣ በራእያችሁ ፣ በድርጅታችሁ ፣ በሀይማኖታችሁ፣ በጤናችሁ ፣ በቤተሰባችሁ ፣ በማህበረሰባችሁ፣ በሕዝባችሁ ፣ በሀገራችሁ ፣ ወዘተረፈ ላይ አርብ ሆኖባችሁ / ቀን ጨልሞባችሁ/ እንደ እየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ተዛብቶባችሁ፣ ተገምድሎባችሁ፣ ታስራችሁ፣ ተገርፋችሁ ፣ ተሰቅላችሁ፣ ተቸንክራችሁ፣ ተዋርዳችሁ፣ ተፈትናችሁ፣ ባመናችሁት ተክዳችሁ፣ በባልንጀራችሁ በ ‘ 30 ‘ ዲናር ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ፣ ሰማይ ተደፍቶባችሁ ወዘተረፈ ይሆናል። ዛሬም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፋችሁም ሊሆን ይችላል።አርብ ነውና !
ካለፉት ሁለት መቶ አመታት ወዲህ ያሉትን ጊዜያት እንኳን ብንወስድ እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ሺህ አርቦችን ፣ በድርቅ ፣ በርሀብ ፣ በቸነፈር ፣ እናት ልጇን እስከ መብላት የተገደደችበት እንደ ክፉ ቀን ያለ እንደ 67ቱ በርሀብ የሞተች እናቱን ጡት የሚጠባበት፣ እንደ …77 … 87 … ወዘተረፈ ያሉ ጠኔዎችን ፣ ችጋሮችን አሳልፈናል። ዛሬም ከዚህ አዙሪት በቅጡ ሰብረን መውጣት አልቻልንም ። እንደ ህዳር በሽታ ፣ ፈንጣጣ፣ ከ76 ወዲህ ደግሞ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ፣ ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ደግሞ ኮቪድ – 19 የእልቂት ጥላውን አጥልቶብናል ።
በግብፅ ፣ በደርቡሽ ፣ በቱርክ ፣ በእንግሊዝ፣ በጣሊያን፣ በሱማሊያ ፣ በኤርትራ ተወረናል ። ዛሬም የክተት ነጋሪት የሚያስጎሹምብን አልጠፉም ። በመቶዎች ሊቆጠሩ በሚችሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች አልፈናል። ከዘመነ መሳፍንት እንኳን ብንጀምር በመሳፍንቱ ፣ በመኳንንቱ ፣ በነገስታቱ መካከል ለስልጣን ፣ ለዘውድ ሲባል በተካሄደ የእርስ በእርስ ግጭት ጦርነት ወገናችን ተጨራርሷል ። አጼ ቴዎድሮስ ፣ አጼ ዩሐንስ ፣ አጼ ምኒልክ ፣ ልጅ እያሱ ፣ ንግስት ዘውዲቱ ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና መንግስቱ ጉዳቱ ፣ ጥፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም በእርስ በእርስ ግጭት ፣ ጦርነት ተፈትነዋል ።የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !
ባለፉት 50 አመታት ወዲህ በተቀነቀነ የማንነት ፓለቲካ የተነሳ በሀገራችን ጥላቻ ፣ ቂም ፣ በቀል፣ ልዩነት ተጎንቁሏል። ጎሳን ፣ ሀይማኖትን፣ርዮተ ዓለም (አይዶሎጂን) መሰረት አድርገን ተጋጭተናል። ተጋለናል። አብያተ ክርስቲያናትን ፣ መስጊዶችን አቃጥለናል ። ቀይ ፣ ነጭ ሽብር ተባብለን ተጨራርሰናል። እናት አባት በቀይ ሽብር የተገደሉ ልጆቻቸውን እሬሳ ሲለምኑ የጥይት ዋጋ ተጠይቀዋል። የዚችን ሀገር ታሪክ እስከወዲያኛው ሊቀይር የሚችል ፍም እሳት የሆነ አንድ ትውልድ ተጨርሷል ። በእርስ በርስ ጦርነት በብዙ አስር ሺህዎች የሚቆጠር ዜጋ አጥተናል። የሀገር ሀብት ወድሟል ። ሀገር አጥተናል። ዛሬ ድረስ ከዚህ ሀንጎቨር አልወጣንም ። በተለይ ባለፉት ሶስት አመታት ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ለማየት የሚዘገንኑ፣ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል።የሀገር የሕዝብ አርብ ነበርና !
በተለይ በቀዳማዊ ትህነግ/ ኢህአዴግ 27 አመታት በፓለቲካ አመለካከታችን፣ በጎሳችን በጅምላ ተገርፈናል። ተገልብጠናል። ተሰቃይተናል። ተግዘናል። ተሰደናል። ሰው በመሆን ብቻ ከፈጣሪ የተቸርናቸውን የማሰብ፣ የመናገር ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ ፣ የመሰብሰብ መብቶች ተረግጠዋል። በደምሳሳው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል። በገዛ ወንድሞቻችን እንደ ባሪያ ተገዝተናል። ተረግጠናል። ተገፍተናል ። ሀብታችንንና ሀገራችን በቀን በአደባባይ ተዘርፈናል። ሀገር በቁሟ በአውሬዎች ተግጣለች ። የድሀ ጉሮሮ ታንቆና በእኛ ድህነት ጥቂቶች በተድላ ፣ በቅንጦት፣ በደስታ ፣ በፍሰሐ ተንደላቀዋል። እየተንደላቀቁም ነው።አርብ ነበርና !
ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ዴሞክራሲን ነጻነትን መሸከም ተስኖን ፤ የፓለቲካ ምህዳሩ መስፋትን እንደ እኩይ አጋጣሚ ተጠቅመን ዜጎችን በማንነታቸው አፈናቅለናል ፣ ገለናል ፣ ሮማውያን እንኳን ያላደረጉትን ዘቅዝቀን ሰቅለናል ። ከእነ ህይወታቸው በእሳት አቃጥለናል። ወደ ገደል ጥለናል። ሩጦ ተጫውቶ ያልጠገበን ህጻን ብላቴና ብልት ሰልበናል ። እህቶቻችንን ደፍረናል ። ዛሬ ድረስ አግተናል። በሕዝብ ፣ በክልልና በዩኒቨርስቲዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማንነት ግጭት እንዲቀጣጠልና ሀገር ወደ ለየለት ቀውስ እንድትገባ በአደባባይ ቀስቅሰናል ። ለፍፈናል ።አርብ ነበርና !
ለእሁድ መዳረሻ ፣ ለትንሳኤ ፣ ለንስህ ፣ ለጥሞና፣ ለአንድነት ፣ ለፍቅር ፣ ለሰላም ለይቅርታና ለሕዳሴ መጀመሪያ በግብፅ አንድ አደረገን ። እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቆም አስቻለን ። ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ደግሞ ወደ ሰውነታችን ፣ ወደ ቀደመው ማንነታችን እንድንሸበለል ያለ ልዩነት የሰው ልጅንና ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃ ቫይረስ ሰደደብን።የእሁድ አጥቢያ ነውና !
ዛሬ በኮሮናቫይረስ በተነሳ የሰው ልጅና የአለም ህልውና ላይ አደጋ ተደቅኗል ። ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል ። ተገለባብጧል ። ፍርሀት ፣ ጭንቀት፣ ሞት በሰማዩ ረቧል ። ሞት እንደ ጥላችን ይከተለን ጀምሯል ። ከምንወዳቸው ተለይተናል ። በየቤታችን ከተናል። በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ’ችን ተቀይሯል ። ከአብያተ ክርስቲያናት ፣ ከመስጊድ ደጆች ተባረናል። ከስራ ታቅበናል ። ተገድበናል ። የእለት ጉርሳቸውን በእየለቱ እየሰሩ የሚያገኙ ወገኖች ለችግር ተዳርገዋል። ትምህርት ቤቶች ዩኒቨርስቲዎች በወረርሽኙ የተነሳ በራቸውን በመዝጋታቸው ተማሪዎች ቤት ለመዋል ተገደዋል ። የሀገርና የሕዝብ ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተጎዳ ነው ። ከሕዳር በሽታ ፣ ከኤች አይ ቪ /ኤድስ ፣ ከኩፍኝናከፈንጣጣ ፣ ከፓሊዎ ፣ 1ኛውና 2ኛው የአለም ጦርነቶች በአንድ ላይ ተደምረው ፣ ከ9/11 የሽብር ጥቃት በላይ የሰው ልጅ ህልውናን የሚፈትን ወረርሽኝ ዙሪያችንን ከቦናል ። አስደንብሮናል ።አርብ ነውና !
“ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ። “ እያልሁ እጽናና ተስፋ አደርግ ነበር ። ዛሬ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆን ፣ የማይነጋ ፣ ዙሪያዊ ገደል ፣ ተራራ ፣ ተስፋ ቢስ ቢመስልም ፤ ነገ ቀን ይወጣል ፣ ይነጋል ፣ ደልዳላ ይሆናል እሁድ ይመጣል እያልሁ እጽናና ነበር። እምነቴም አምላኬም አላሳፈረኝም ። ዛሬ ጤናዬ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል ። በቅርብ ሙሉ በሙሉ ይሻለኛል ብዬ አምናለሁ ።የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬን በደጋግ ሰዎች እገዛና ማበረታት በነጻነት ጀምሬ’ለሁ። ተስፋዬ ለምልሟል ። በዋሻው መውጫ ብርሀን እየታየኝ ነው ። ያቋረጥሁትን ትምህርቴን አጠናቅቄ ሶስተኛ ዲግሪዬን እሰራለሁ ። በዚች ሀገር የሚዲያ ኢንዱስትሪ የዜግነት ድርሻዬን እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። ዛሬ ላይ እንዲህ ህልመኛ የሆንኩት አርብ አልፎ እሁድ እንደሚመጣ በማመኔና ተስፋን በመሰነቄ ነው ። ከስቅላቱ በኋላ ትንሳኤው እንደሚከተል በማመኔ ነው ።እሁድ ይመጣል !
እየሱስ ክርስቶስ ከተዋረደባት ፣ ከተተፋባት፣ ከተገረፈባት ፣ ከተቸነከረባት ፣ እንደ ወንበዴ ፣ ወንጀለኛ አንዳች መተላለፍ ፣ ነቀፋ ሳይገኝበት ፣ ሞት የተፈረደበት፣ በመስቀል ተቸንክሮ ከተሰቀለባት ፣ ጎኑ ከተወጋባት በኋላ” አርብ “ እንደ ተቀሩት የሳምንቱ ቀናት የጊዜ መለያ ብቻ አልሆነም ። የጨለማ ፣ የስቃይ፣ የመከራ ፣ የፈተና ፣ የውርደት ፣ የግፍ ፣ የበደል ፣ የመገፈፍ ፣ የራቁትነት የመሰቀል ወዘተረፈ ተምሳሌት ጭምር እንጂ ። ኤልደር” ዛሬ አርብ ነው “ ያሉት ይሄን መሰሉን ቀን ፣ አመት ፣ ዘመን ነው ።ዛሬ አርብ ነውና ፤
ሆኖም መግነዙን ፈቶ ፣ የመቃብሩን ቋጥኝ አንከባሎ፣ ሞትን ድል አድርጎ ፣ በብኩርና በሶስተኛው ቀን በድል ተነስቷል ። አርጓል ። በደሙ ዘላለማዊ ድህነትን ፣ በግርፋቱ ህያው የፈውሱን አክሊል አቀዳጅቶናል። ሀጢያትን ደምስሶ ከልዑል እግዚአብሔር አስታርቆናል። ከኦሪታዊ ሕግ ፣ ከባርነት፣ ከሀጢያት ነጻ አውጥቶናል። እሁድ መጥቷልና !
ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ ፣ ሕዝብና ሀገርም እንዲህ ባለ ተመሳሳይ ጨለማ ፣ ፈተና ፣ መከራ ፣ ቸነፈር፣ ውርደት፣ ግርፋት ፣ መቸንከር ፣ ደም መፍሰስ ፣ ስጋ መቆረስ ፣ ጀርባ መተልተል ፣ ግማደ መስቀሉን ተሸክሞ ተራራ መውጣት ፣ ጎን መወጋት ፣ የሾህ አክሊል መድፋት ፣ ወዘተረፈ አልፈዋል ። እልፍ አእላፍ አርቦችን አሳልፈዋል ። ዳሩ ግን የትንሳኤው እሁድ ይመጣል።እሁድ ይመጣልና !
ከእዚህ ክፉ ወረርሽኝ ፣ ከፓለቲካ ስብራት ፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነት ፣ ከደባ ፓለቲካ ፣ ከድህነት፣ ከእርዛት፣ ከርሀብ ፣ ከኋላ ቀርነት ፣ ከልዩነት ፣ ወዘተረፈ ወይም ከአርብ ወጥተን ፤ የሀኪሞችን ምክር፣ የመንግስትን ማሳሰቢያ በመተግበር አርብን አልፈን እሁድን እናያለን። የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረን ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገንብተን አርብን አልፈን ለእሁድ እንበቃለን ። የብልፅግና ትልማችንን ለማሳካት ሌት ተቀን በመትጋት ፣ ሙስናን፣ ብልሹ አሰራርን ፣ ስንፍናን ፣ ዳተኝነትነት በማስወገድ አርብን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገራለን ። እሁድን በተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን ። ልዩነትን ፣ ጥላቻን፣ ጎሰኝነትን ፣ የታሪክ እስረኝነትን ፣ የሴራፓለቲካን ወይም ብዙ አርቦችን በጽናት በብርታት አልፈን ለትንሳኤና ለህዳሴ / ለእሁድ እንበቃለን ። ደግሞም እናምናለን ይሆናል።” ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል ! “
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013