የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 87 የመከላከያ መርሆዎች በሚል ርዕስ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦን ያካተተ፣ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የሆነና ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገንተኝነት ነጻ በሆነ አኳኋን ሥራውን ያከናውናል በሚል ደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሠራዊቱ ታማኝነቱ ለሕዝብና ለሕገ መንግሥቱ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለሆነም በየደረጃው ያለ የሠራዊት አባል ሕዝባዊነትን በመላበስ ሥራውን ያከናውን ዘንድ ይጠበቃል፤ ይገባልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ ሕዝባዊና ሕገ መንግሥታዊ ተልእኮ ተሰጥቶት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እንደ አዲስ የተቋቋመበት ቀን ‹‹የመከላከያ ሠራዊት ቀን›› ተብሎ ዛሬ ይከበራል፡፡
የዘንድሮው የሠራዊት ቀን አከባበር መሪ መፈክር «ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንጠብቃለን፤ ሕዝባዊ ባሕሪያችን የተጠበቀ ይሆናል፤ የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን» የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሠራዊቱን ሕዝባዊነት ይበልጥ በማጠናከር በሕዝብ የመጣውን ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የሠራዊቱ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ትልቅ ኃላፊነትን የሚያሸክም ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የሠራዊቱ ሕዝባዊ ባህርይና ሕዝባዊነት ዛሬም በቦታው መኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡
የዘንድሮው የሠራዊት ቀን ለውጥ በተጀመረበት፣ መከላከያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጭምር የተመሰከረለትን ስኬታማ መሰረታዊ ለውጥ (ሪፎርም) በሚያካሂድበትና አደረጃጀቱ በተቀየረበት እንዲሁም ተስፋው በለመለመበት ጊዜ የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ሠራዊቱ ከምድርና አየር ኃይል በተጨማሪ የባህርና የሳይበር ቴክኖሎጂ ባለቤት በሚሆንበት መንገድም ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሠራዊቱ አቅም በማጠናከር ሕዝቡንና ሕገ መንግሥቱን በሚገባ ለመጠበቅ፣ የውጭ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለመተናኮስ እንዳያስብ /ዲተር/ የማድረግ አቅምን የሚያሳድግ ነው፡፡ በአጠቃላይ የለውጡ ትሩፋት ነው፡፡
ቀኑ ቀደም ሲል በሠራዊቱና በሕዝቡ መካከል የነበረው ጥርጣሬ በከፍተኛ ደረጃ በተወገደበት ወቅት መከበሩም ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬም ቢሆን ሠራዊቱ የሕገመንግሥቱ እና የሕዝቡ አለኝታ መሆኑን በሚገባ በተግባር በመግለፅ ሕዝባዊነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ማሳየት አለበት፡፡ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የዘመቻና መረጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ «በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ዋናው ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡ ፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም አክቲቪስቶች እና ሌሎችም በለውጡ ላይ የየራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም በወሳኝነት ለውጡን ያመጣው ግን ሕዝቡ ነው፡፡ የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ማዕበል የለውጥ አመራር ፈጥሯል፡፡ የለውጥ አመራሩ ደግሞ ሕዝቡ ልክ ነው ብሎ ከሕዝቡ ጋር ወግኗል፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው ነው መደረግ ያለበት ብሎ ከሕዝቡ ጋር ቆሟል» ብለዋል።
ጄኔራሉ እንደገለጹት የለውጡ ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ ሠራዊቱ ሕዝባዊ ባህሪው በሆነው የህዝብን ፍላጎት ተከትሎ የመሄድ ጉዞው በጽናት መቀጠል አለበት፡ ፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማክበርና በማስከበርም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ መቼም የማይሸረሸር መሆኑንም ደጋግሞ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ የለውጥ አመራሩም ሕዝብ እያዳመጠ፤ መጥፎ አሰራሮችንና ብልሹ አዋጆችን እየቀየረ፤ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እየጣረና ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና አፈና እንዳይኖር በጽናት እየሠራ ነው፡፡ ሕዝቡን እያቀራረበም በልዩነት ያጌጠች አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግም ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም ይሄንን የለውጥ አመራር ማገዝ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነውና የዘንድሮው የሠራዊት ቀን መሪ መፈክር ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክር ሆኖ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡ ፡ ሠራዊቱ የሕዝቡ ልጅ፤ ከሕዝቡ ውስጥ የወጣ ኃይልና የአገር አለኝታ ነውና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅና ለውጡን በማስቀጠል ተግባሩ ሊተጋ በዚህች ታሪካዊ ዕለት ቃሉን ሊያድስ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011