ሀገር በሕዝቦች፣ ሕዝቦችም በሀገር ይገለጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ስትታወስ ኢትዮጵያውያን መጠራታቸው፤ ኢትዮጵያውያን ሲታወሱም ኢትዮጵያ መወሳቷ የዚህ እውነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይሄ የሀገር እና ሕዝብ የአብሮነት መጠሪያ፤ የስም መወራረስ የሚገልጠው የአይነጣጠሌነት ማኖሪያ ደግሞ አንድ ኃያል ምልክትና መወከያ ጉዳይ አለ፡፡
ይሄ መወከያ ዓርማ ደግሞ እንደየሀገራቱ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ የጥበብና የልዕልና ደረጃ ገናንናነትን ይጎናጸፋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ባለ ታሪክ፣ ባለ ጥበብ፣ ባለ ገድል እና የነጻነት ቀንዲል የሆኑ ሀገራት ደግሞ ይሄ ዓርማቸው የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የብዙሃን ምልክት ሆኖ ይወረሳል፡፡ ዛሬ ላይ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መታወቂያ ዓርማና ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማዋ በብዙ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ውስጥ ቀለሙ ተቀይጦ የሚገኘው፡፡
ምክንያቱም ይሄ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባለቀለም ጨርቅ ብቻ አይቀለም፡፡ ይልቁንም የነጻነት፣ የባለታሪክነት፣ የአልሸነፍ ባይነት፣ የድል አድራጊነት፣ ወራሪን የማሳፈር ጀብድና ባለገድልነት፣ የመተባበርና በሕብር የጸና አንድነት፣… ወካይ ማሕተም ነው፡፡ ቀለማቱም ቢሆኑ ቱባ ትርጓሜን የያዙ፤ በተስፋና ሕብር የደመቀ ተደማሪ ዓርማን ያዘሉ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚታዩት ሦስት ቀለማት (አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩ)ን ብንመለከት፤ አረንጓዴው የሥራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በተፈጥሮ የታደለች፣ የአስራ ሦስት ወር ባለጸጋ፣ ቢያንስ ዘጠኝ ወራትን ዝናብ የምታገኝ፣ ዓመቱን ሙሉ በሚፈስሱ ወንዞቿ ዓመቱን ሙሉ ማምረትና ሕዝቦቿን መመገብ የሚያስችል ሀብት የታደለች ሀገር መሆኗን እንዲገልጽ ሆኖ በውክልና የተቀመጠ ነው፡፡
ቢጫውም ቢሆን፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ተጠቅማ የመልማት እና የመበልጸግን፣ የትናንት ገናና ታሪክና ገድሏን መልሶ የመጎናጸፍንና ሌሎችም ከፍ የማለት ተስፋዎቿን፤ ለሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት ምድርነቷን ብቻ ሳይሆን፣ ከትናንት እስከ ዛሬ ለሰው ልጆች ፍትሕ መስፈን የሠራች መሆኗን የተግባር ማንነቷን በወካይ ዓርማዋ ላይ ያኖረችበት ነው፡፡
ሦስተኛውና ቀዩ የቀለም ውክልናዋ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የነጻነት ምድርነቷን፤ ይሄ ነጻነት ደግሞ በኢትዮጵያውያን የደምና የሕይወት መስዋዕትነት የጸና ስለመሆኑ፤ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ ለዚህ ነጻነት እና ለሕዝቦች እኩልነት ሰፍኖ መዝለቅ የሚደረግን የመስዋዕትነትና የጀግንነት ገድል የሚያመለክት ነው፡፡
በእነዚህ ሦስት ቀለማት ላይ አርፎ በመሃል ላይ የሚገኘውና ቢጫ ፍንጣቂ ብርሃንን የያዘው ባለ ሰማያዊ መደብ ክብ ዓርማ ደግሞ፤ ኢትዮጵያውያን ከትናንት እስከ ዛሬ ለአብሮነትና ነጻነታቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ሰላማቸው ከፍ ያለ ዋጋ መክፈላቸውን፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ በየትኛውም እንቅስቃሴያቸውና ተግባራቸው ሰላምን አስቀድመው የሚሠሩ የሚተጉ ስለመሆናቸው የሚናገሩበት ምልክታቸው ነው፡፡
ዛሬ ይሄን ዓይነት ከፍ ያለ የማንነት መግለጫ እና ወካይ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማችንን ቀን ሰጥተን ስናከብረውና ስናስበው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፤ አብሮነትና ኅብረታችን፤ ወንድማማችነትና ፍቅራችን ከምንም በላይ ጸንቶ እንዲዘልቅ ዳግም ቃል የምናድስበት እንዲሆን በማድረግ ነው፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ፣ ኢትዮጵያ የትናንት ገናን ማንነቷን የሚመልሱ፤ ሙሉ ነጻነትና ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን ለመከወን፤ የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ዕድገትና ስኬት ለማስቀጠል፤ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም እንዲሆን የሚጠበቀውን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ሁላችንም ከእኛ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለንን ቁርጠኝነት ለመላበስ ሰንደቅ ዓላማችንን ጨብጠን ቃል የምንገባበት በመሆኑ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለአብሮነታቸው፣ ለብልጽግናቸው፣ ለመልካም ጉርብትናና ትብብራቸው አቅም የሚሆነውን ሰላም ለማጽናት ሰንደቅ ዓላማቸውን አስቀድመው የሚናገሩበት መድረክ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በውስጥ የጥፋት ኃይሎች፤ በውጪ ደግሞ የኢትዮጵያን ከፍ ማለት የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ዙሪያችንን እያንዣበቡ ባሉበት ወቅት፤ የሰንደቅ ዓላማውን ስሜት መላበስ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
በመሆኑም ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ስናከብር፤ አንድም የውስጥ አብሮነትና አንድነታችንን የማጽናት ቃላችንን በማደስ፤ ሁለተኛም፣ ኢትዮጵያ የልማትና የሕልውና ጥያቄዋን ለመመለስ ለምታደርገው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች መንገዶቿ ሁሉ ሰላማዊና ትብብር መሆኑን በማሳየት፤ ሦስተኛም፣ የሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ፍቅር ያልገባቸው ማናቸውም ኃይሎች ቢኖሩና የሰላም መንገድ እንቢኝ ቢሉ፤ የትናንቱ የኢትዮጵያውያን ገድል በዛሬው ትውልድ ደም ውስጥም ስለመኖሩ በማስገንዘብ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሰንደቅ ዓላማችን የአብሮነታችን ማሰሪያ፣ የአሸናፊነታችንም ማብሰሪያ የሚሆነው ይሄን በማድረግ ውስጥ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም