የቴሌኮም ዘርፉ የአክሲዮን ሽያጭና ጠቀሜታ

ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ሰፊ ሚና እንዲኖረው የሚረዱ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቷል። የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ ተከትሎ በቴሌኮምና የፋይናንስ ዘርፎች ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ስትራቴጂያዊ ርምጃዎች መውሰዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።

የካፒታል ገበያን በማቋቋም ኢኮኖሚውን ለማቀላጠፍና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የካፒታል ገበያው የአክሲዮን ሽያጭ ሥርዓቱን ማዘመን በርካቶችን ለኢንቨስትመንት የሚስብ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

ሰሞኑን የ130 ዓመት አንጋፋውን ተቋም የኢትዮ ቴሌኮምን 10 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያውያን ለመሸጥ መወሰኑን ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል። በቀጣይ ሰፊ የካፒታል ገበያ እንዳለ አመላክተው፤ ለአሁኑ ግን የኢትዮ ቴሌኮምን አክሲዮን በመግዛት ኢትዮጵያውያን ሊረባረቡ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለመግዛትም ከዝቅተኛው ብር 9 ሺህ 900 ወይም 33 አክሲዮኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ብር 999 ሺህ 900 ወይም 3 ሺህ 333 አክሲዮኖች ድረስ መግዛት እንደሚቻልም ይፋ ተደርጓል። በኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተጀመረው ለሻጩም ሆነ ለገዥው የሚያበረክተው ፋይዳ ምንድነው በሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ አካላት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የኢትዮ ቴሌኮምን አክሲዮን ለመሸጥ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በጥንቃቄ ተከናውነዋል፤ ሒደቱንም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላና በእንግሊዝና ኬንያ የሚገኙ ተመሳሳይ ሥራ የሚያከናውኑ ተቋማት ጭምር አይተው ያደነቁት ነው።

የቅርብ ጊዜ የተቋሙ የ2016 የኦዲት ሪፖርት ተሠርቶ ትርፋማነቱና አዋጭነቱ ተረጋግጦ ለሽያጭ የቀረበ አክሲዮን መሆኑን ጠቁመው፤ አክሲዮኑን የሚገዙ ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ልክ እንደጡረታ ገንዘብ ትርፋቸውን እየተቀበሉ እራሳቸውን የሚጠቅሙበት ዕድል መቅረቡን ይገልጻሉ።

ዶክተር ብሩክ እንደሚያመላክቱት፤ የአክሲዮን ሽያጩ የካፒታል ገበያን አሠራርና የሕግ ማዕቀፎችን ያሟላ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ተደራሽነቱን የማስፋት አቅም ያለው፣ የወደፊት የተሻለ ተስፋና ራዕይ ያለው ተቋም በመሆኑ ማህበረሰቡ ድርሻውን በመግዛት ሊጠቀም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ኃላፊ ሃና ተኸልኩን በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም ያቀረባቸውን የካፒታል ገበያ ምዝገባ ሰነዶች በዝርዝር መታየታቸውን ያስረዳሉ።

ኢትዮ ቴሌኮም በመጀመሪያ ዙር 10 በመቶ የባለቤትነት ድርሻን ለኢትዮጵያውያን በመሸጥ ሥራ እንደሚጀምር በገለጸው መሠረት የመደበኛ አክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን ኩባንያው ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማህበርነት መቀየሩን ነው ያስታወቁት። ሰኔ ወር ውስጥ 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት በአክሲዮን ማህበርነት መመዝገቡንም አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በጸደቀው የደንበኛ ሳቢ መግለጫ (prospecctus) የወጡ መስፈርቶችን የሚያሟላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ግለሰብ መደበኛ አክሲዮኖችን ገዝቶ እንዲጠቀም አስፈላጊው የሕግ ድጋፍ መመቻቸቱን ይጠቁማሉ።

በመሆኑም የካፒታል ገበያ የሕድ ድጋፍ ስጋት እንደማይኖር ተናግረው፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ስነደ መዋዕለ ንዋይ የመካተቱ ሂደት ሲጠናቀቅ የተገዙ መደበኛ አክሲዮኖች የመሸጥ፤ የመተላለፍና ከማንኛውም መደበኛ አክሲዮን ወደ ሌላ ባለቤትነትን ማስተላለፍ እንደሚቻል ያስረዳሉ።

የአክሲዮን ገዥዎችን የኩባንያው ባለቤትነት ፍትሐዊነት ለማረጋገጥና የህብረተሰቡን ተሳትፎውን ከፍ ለማድረግን የቀረቡትን የአክሲዮን ግዢ ጥያቄዎች የመደልደል ኃላፊነት የኩባንያው መሆኑን ነው ያስታወቁት።

ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ 79 ሚሊዮን የቴሌኮም ደንበኞችን ከማፍራት ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ያለ ትርፋማ ድርጅት በመሆኑ አክሲዮኑን መግዛት አዋጭ ነው የሚሉት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው።

ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር ዲጂታል ክፍያና ሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን በማሳለጥ 50 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራቱን ጠቅሰው፤ በዘርፉ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማፋጠን ላይ ያለውን ተቋም አክሲዮን መግዛት አትራፊ ኢንቨስትመንት መሆኑን ያስረዳሉ።

አንድ ግለሰብ ከአክሲዮኑ ዋጋ በተጨማሪ የአንድ ነጥብ አምስት በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ በመክፈል አክሲዮኖቹን መግዛት እንደሚችል ነው ያስታወቁት።

የባለቤትነት ድርሻው በዋናነት ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ሚና የበለጠ ለማስፋት፣ የኩባንያውን ውጤታማነት ለማሻሻል፣ ካፒታል የሚያገኝበትን ዕድል ለማስፋትና ተቋም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ጥራትና ተደራሽነት ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ይላሉ።

ኃላፊዎቹ እንደሚናገሩት፤ እያንዳንዳቸው 300 ብር የሆኑ 100 ሚሊዮን አክሲዮኖችን በመሸጥ የሚገኘው ገቢ ለተጨማሪ ልማት የሚውል በመሆኑ አትራፊ የሆነውን ኩባንያ መቀላቀል ውጤታማ ኢንቨስትመንትን እንደማከናወን ይቆጠራል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You