“The Prodigal Daughter “ ፤ በተሰኘው የጄፍሪ አርከር ማለፊያ ልቦለድ ፦ የታሪኩ ባለቤት የሆኑት ዋና ገፀ ባህሪያት ፍሎሬንቲ እና ሪቻርድ ባልና ሚስት ቢሆኑም የተለያየ ፓለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ናቸው ። ፍሎሪ የዲሞክራት ሪቻርድ የሪፐብሊካን ፤ ታሪኩ በተዋቀረበት መቼት(መቼና የት)አልያም ዘመን የዴሞክራት እጩ የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ 35ኛ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በመሆን በጠባብ ልዩነት ሪቻርድ ኒክሰንን ይረታሉ ።
የፕሬዝዳንት ኬኔዲ በዓለ ሲመት ድንቅ አነቃቂ ንግግር የፊሎሪን የሀገሯ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝዳንት የመሆን የልጅነት ሕልሟን ከተኛበት ይቀሰቀስባትና በጨዋታ መሀል ወግ አጥባቂ የሪፐብሊካን ደጋፊ የሆነው ባለቤቷን” …ውዴ ! የዴሞክራት እጩ ሆኘ ብቀርብ ትደግፈኛለህ ? “ ስትል ድንገት ትጠይቀዋለች ፤ እሱም ያለአንዳች ማመንታት ፤” ይዘሽው የምትቀርቢው የፓሊሲ ሀሳብ ይወስነዋል። … “ ሲል ተደራሲውም እሷም ያልጠበቁትን መልስ ሰጠ ። ፍቅሬ ፣ የልጆቼ እናት ስለሆንሽ ብሎ “ እንዴታ…! አንቺ ለመወዳደር ያብቃሽ እንጅ ከቶ ማንን ልደግፍ… !? “ አላላትም ።
ይህ የሪቻርድ መልስ አብዛኛዎቹን የሀገራችንን የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ሙሁራን፣ ፓለቲከኞች ፣ ጋዜጠኞች ፣ ፀሐፍት ፣ ጦማርያን ፣ ደራሲያን ፣ ወዘተ .. . ከፓሊሲ ሀሳብ ይልቅ ለዘውጋዊ ማንነትና ውግንና መታመናቸው ሀገሪቱንም ሆነ ሕዝቡን ውድ ዋጋ አስከፍሏል እያስከፈለም ይገኛል ። የዞረ ድምሩ ሀንጎቨሩም ገና ለአመታት አብሮን ይኖራል ። ቁስሉም በቀላሉ አይጠግግም ። በምርጫ ዋዜማ ሆነን ስናሰላስለው ደግሞ አንድምታውና ዳፋው ያስጨንቃል ።
ያለፉት 30 አመታትም ሆኑ ከዚህ ቀደም ያሉት አመታት ያለፉት በዘውግ፣ በብሔር፣ በማንነት ፓለቲካ መሆኑ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ብኩርናችንን፣ ቀደምትነታችንን አስቀምቶናል። አሰውቶናል። አስማርኮናል ። እንደ ሪቻርድ በምክንያታዊነት ሳይሆን ሁሉን ነገር በዘውግ መነፅር እንድንመለከት አድርጎናል ።
ሰሞነኛው የታሪካችን ፣ የኢትዮጵያዊነታችን ጠባሳ መንስኤም ይኸው ነው። እፉኝቱና ከሀዲው ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋና የጦር መሳሪያ ዘረፋ ፤ በሰሜን ሸዋ አጣየ ፣ ሸዋ ሮቢትና አካባቢው ፤ በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ፤ ሳምሪ በተሰኘ በትህነግ ገዳይ የወጣት ክንፍ ከ1000 በላይ አማራዎች በግፍ ሲጨፈጨፉ ፤ በጉራ ፈርዳ የደረሱት ጥቃቶችና ግጭቶች መጥቀስ ይቻላል።
እንዲሁም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች ፤ ጃዋር ተከብቢያለሁ በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎ ማንነትንና ሀይማኖትን ኢላማ ያደረጉ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ፣ ውድመቶችና ዘረፋዎች ፤ ኦነግ ሸኔ በተመሳሳይ ሁኔታ በጉጂና በምዕራብ ኦሮሚያ በኦሮሞዎች ላይ የፈጸመው ጥቃትና ዘረፋ ፤ በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ በከፍተኛ ባለስልጣናትና የጦር አመራሮች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች ሀገራችንን ወደለየለት የማያበራ ዕልቂት የመዝፈቅ እምቅ አቅም የነበራቸው ሁነቶች የፅንፈኛ ዘውጌ’ዊነት ቅርሻዎች ናቸው ።
የሚያሳዝነው እንደ ጭፍጨፋው ሁሉ አወጋገዙም ማንነትን የተከተለ ነው። አማራ ሲጠቃ ሆ ብሎ የሚያወግዘው በአብዛኛው አማራ ሲሆን ኦሮሞ ሲጠቃም አውጋዡ ኦሮሞ ነው ። በንጹሐን ላይ ጥቃት ሲፈጸም ያለ ልዩነት ማውገዝ እየቀረ ነው ። ይሄ እኩይ መንፈስ ወደ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎችና ተቃዋሚዎች መጋባቱ ደግሞ ክፉኛ ያሳስባል ። ውስጠ ፓርቲ መሳሳቡም ሌላው አደጋ ሆኖ ብቅ ብሏል ።
ከጭፍን ጥላቻ፣ ከጎሰኝነት ይልቅ በተጠየቅ፣ በአመክንዮ በተመሰረተ ንግግር ፣ ውይይት ፣ ሙግት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ቢቻል ለዚህ ዘግናኝ ግፍ ባልተዳረግን ነበር። የሚያሳዝነው የደባ ፣ የሴራ ኀልዮት ተጨምሮበት የተፈጠረው ውዥንብር ከሰማዕታቱ ይልቅ ነፍሰ ገዳዮችን በጀግንነት ሊያከብር መሞከሩ ዘውጌ’ዊነት ህሊናችንን እንዴት እንደጋረደው ያሳያል ። በሆነው ነገር ሙሾ ከማውረድ ይልቅ መውጫችን ላይ መነጋገር ይበጃል ብዬ ስለማምን፤ የመውጫችን በር የሀሳብ ልዕልናና ሰውነት ነው እላለሁ ።
አዎ …! ዘውጋዊ ማንነት ሀገርን ፣ ወገንን ፣ ፍቅርን ፣ አንድነትን ፣ መተሳሰብን፣ ምክንያታዊነትን፣ ተጠየቃዊነትን፣ እውቀትን፣ ሰብዓዊነትን ፣ ታሪክን … ፤ አስገብሮን በምትኩ ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን ፣ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞን ፣ ዘረኝነትን ፣ ግብታዊነትን ፣ ኢአመክንዮኣዊነትን ፣ ኢተጠያቂያዊነትን፣ ድንቁርናን ፤ አስታቅፎናል ። የጥላቻን ፣ የመጠራጠርን የጦር እቃ አስታጥቆናል ፣ የቂምን የሾህ አክሊል ፣ የበቀልን ጡሩር አስለብሶናል ።
የሶስት ሺህም ሆነ ከዛ በላይ የሆነውን የታሪካችንን ቀለም አደብዝዞታል። በአራቱ ማዕዘናት ቀውስ መቀፍቀፉ ሳያንስ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን እጃችንን ይዞ ሊያስረክበን እየዳዳው ነው። ከዚህ ከፍ ሲልም ምሽግ አስይዞናል። ጉድብ አስጎድቦናል። በዚህ ይዞታችን፣ አኳሃናችን ለሀገራችን የምንመኘውን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም።
ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ፍትሕንና እኩልነትን ለማስፈን ፤ ሌብነትን ዘረፋን ከዚች ሀገር ለመንቀል የሕግ የበላይነትን ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን እውን ለማድረግ በእውነት ላይ የተመሰረተ ይቅርባይነትን ለመሻት ወዘተ. ባለፉት 27/50 ዓመታት በብሔር፣ በዘውግ ፓለቲካ የተዘረፍናቸውን የተነጠቅናቸውን ከላይ የተዘረዘሩትን ምርኮዎቻችንን ማስመለስ አለብን።
ምርኮዎቻችንን የምናስመልሰው በዘውግ፣ በብሔር ግርዶሽ ተሸብበን ውረድ እንውረድ እየተባባልን የጥላቻ ጦራችንን በመስበቅ ፤ የቂም በቀል ቀስታችንን ፍላፃዎቻችንን ለማንበልበል ለማስፈንጠር ደጋን በመወጠር አይደለም ። በእውቀት ፣ በሳይንስ፣ በተጠየቅ፣ በምክንያት ላይ በተመሰረተ የሰከነ የሀሳብ ፍጭት ሙግት በማድረግ ገዥ ሆኖ ልዕልና ያገኘውን ሀሳብ ፍኖተ ካርታ በመከተል ሊሆን ሲገባ ነው።
በአንጻሩ በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ያለው ግን በብሔር በዘውግ የተቆፈረ ምሽግ ይዞ መጠዛጠዝ ነው የውይይቱ፣ የንግግሩ ፣ የሙግቱ መሰረት የሚገነባው በሳይንሳዊ እውቀት ፣ በምክንያታዊነት ፣ በተጠየቃዊነት ፣ በእውነት፣ በሀቅ አለት …ሳይሆን ፤ በዘር ፣ በጎሳ ፣ በማንነት፣ በዘውግ፣ በሀይማኖት ፣ …፤ ድቡሽት ላይ በተቀለሰ ጎጆ ነው ።
ወገንተኝነት ታማኝነት ለሀቅ ፣ ለአመክኖአዊነት፣ ለህሊና ሳይሆን ለተገኘበት ጎሳ ወይም ዘውግ ነው ። በዚህ አሰላለፍ ሀገራችንን ከገባችበት ቀውስ ማውጣት አይደለም እርስበርሳችን መቀባበል፣ መነጋገር፣ መደማመጥ አልቻልንም ። ለፅንፈኝነት ፣ ለአክራሪነት ተዳርገናል ። እውቀት ፣ ተጠየቅነት ፣ ምክንያት ፣ ሳይንስ በዘውጌአዊነት ፣ በብሔርተኝነት ተደፍቀዋል ።
በተለይ በዚህ ሶስት አመታት ከምክንያታዊነት፣ ከተጠያቂነት፣ ከአብርሆት ይልቅ በማንነት፣ በዘውግ ተከፋፍለን ምሽግ ይዘን፣ የተከላከልናቸውን፣ የተጠዛጠዝንባቸውን፣ አቋም የወሰድንባቸውን፣ የተሟገትንባቸውን፣ ጥያቄዎች፣ ስጋቶች፣ ፍላጎቶች ህልቆ መሳፍርት የላቸውም። ታዲያ በማንነት ተቧድነን የተቆራቆርሳቸውን ልዩነቶች ይዘን ነው ወደ ምርጫ የምንሔደው በተጨባጭና በተተግባሪ ፓሊሲ ነው ድምጻችንን የምንሰጠው!? ወይስ አማራ ስለሆንን አማራ፣ ኦሮሞ ስለሆንን ኦሮሞ ፣ ሶማሌ ስለሆንን ሶማሌ፣ ወዘተረፈ ነው የምንመርጠው !?
በማንነት ላይ የተመሠረተ ፓለቲካ ብሶትን እየጋለበ ፤ ቁጭትን እያቀነቀነ ፣ እኛና እነሱ እያለ እየከፋፈለ ፤ ፍርሀትን እየለፈፈ ፤ ልዩነትን እያሰፋ ፤ ጥላቻን እየሰበከ ፤ ጠላት እየፈጠረ ፤ ቂምንና በቀልን እየጎነቆለ ፤ ቁስልን እየነካካ ፤ ለውድቀቱና ለክስረቱ ሁሉ ሌላውን ብሔር ሀጢያት ተሸካሚ እያደረገ ለአገዛዝ የሚያበቃ አቋራጭ መንገድ ነው ። ዜጎች አማራጭ የፓሊሲ ሀሳቦችን እንዳያዩ ህሊናንም ሆነ አይንን የሚጋርድ ጥቁር መጋረጃ ነው። ከፍ ብዬ ለማሳየት እንደ ሞከርኩት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረን ሰው ከሰው ተራ የሚያወጣ ነው ።
ተጠየቃዊነትን፣ አመክንዮአዊነትንና ሰብዓዊነትን አስጥሎ ወደ እንስሳነትና አውሬነት የሚያወርድ ክፉ ወረርሽኝ ነው። ሰው በመሆን የተላበሳቸውን ጸጋዎች ገፎ ራቁት የሚያስቀር መሆኑን ሰሞነኛ ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ አረመኔያዊ ግፎች አፍ አውጥተው ይናገራሉ። ሞታችን ሀዘናችን በማንነት መቃብርና ድንኳን የተለያየ ስለሆነ ቀብራችንም ሆነ ሀዘናችን ለየቅልና በየተራ ነው ።
አማራው ሲሞት የሚያዝነውና የሚያለቅሰው አማራ ብቻ ነው ። ኦሮሞው ፣ ትግሬው፣ ወላይታው፣ ኮንሶው ፣ ወዘተረፈ የሚያለቅሰውና ሀዘን የሚቀመጠው እንዲሁ በማንነቱ በደኮነው ድንኳን ነው። የሰሞኑን ሰልፍ ለመቀላቀል ሰው መሆን ኢትዮጵያዊ መሆን በቂው ነበር ። ማንነትን መጠየቅ አልነበረበትም።
ማንነትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት በአንድ ብሔርና ሀይማኖት ተወስኖ የሚቀር አይደለምና ። የማንነት ፓለቲካ አስኳል ማንነት እንጂ የሀሳብ ልዕልና ስላልሆነ ዜጎች የሀሳብና የፓሊሲ አማራጭ እንዳይኖራቸው ኮርኩዶ የሚይዝ ጠፍር ነው። ተዋኽሶውም ሆነ ልፋፌ ሀቲቱ መነሻና መድረሻው በትንታኔ የተቀመረ ፓሊሲ ሳይሆን ፍርሀትና ቁጭት ስለሆነ ዘላቂና ፍቱን መፍትሔ የለውም።
ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጋር ደግሞ አይንና አፍንጫ ነው ። ለማንነቱ የወገነ ስለሆነ ነጻ ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ አይደለም ። በሀብት ብሔርተኝነት( Resource nationalism) ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ ተጠቃሚው በማንነቱ የተሰለፈ ልሒቅና ጭፍራው ስለሆነ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚታሰብ አይደለም።
ፓለቲካዊ ተሳትፎውም ለማንነቱ ቅድሚያ የሚሰጥና የሚያደላ ስለሆነ ፓለቲካዊ ምህዳሩ አሳታፊ ሊሆን አይችልም። ዘውጌያዊ የፓለቲካ ልሒቃኑን በጥፋቱ ልክ ተጠያቂ የሚያደርጉ ሕጎችና ስርዓቶች በማንነት ፓለቲካ ሽባ ስለሚሆኑ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ይንሰራፋሉ ።
ማንነት ወደ ሌቦችና ግፈኞች ዋሻነት ይቀየራል ። ባለፉት ሶስት አመታት ተጠያቂነትን ለማስፈን የተደረገው ጥረት እውን ሳይሆን ጨንግፎ ሲቀር ታዝበናል ። ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ብሔራቸውን መደበቂያ ጫካ ሲያደርጉ ተመልክተናል ። መንግስትም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንደሆነበት በተደጋጋሚ ሲያማርር አድምጠናል።
እንደ መውጫ
የማንነት ፓለቲካ መንበር ላይ ለመቆናጠጥ እርካብ ፤ አገዛዝ ላይ ለመቆየት ማዘናጊያ ጊዜያዊ ስልት እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ባለፉት 30 አመታት ቀምሰንና ዳሰን አረጋግጠናል። ከፋፍሎ ለመግዛት የቆመ የጥል ግድግዳ መሆኑን ከእኛ በላይ አስረጂ ፣ ምስክርና እማኝ ሆኖ የሚቀርብ የለም።
ለዘመናት ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረን ፤ አንተ ትብስ ፣ አንቺ ትብሽ ተባብሎ የኖረን ፤ ሀገሩ ስትወረር በአንድነት ደሙን ያፈሰሰ አጥንቱን የከሰከሰ በወል መስዋዕትነት ቃል ኪዳን የገባን እና የተጋመደን ሕዝብ ለመለያየት የተያዘውን ትንቅንቅ በአይናችን በብረቱ እየተመለከትን ነው ።
በፈጠራና በሀሰተኛ ትርክት መርዝ የተለወሰ የልዩነትና የጥላቻ ፓለቲካ ሀገራችንንም ሆነ እኛን እንዴት እንደ ጎን ውጋት ቀስፎ እንደያዘንና ትንፋሽ እንዳሳጣን እየተመለከትህ በማንነትህ/ሽ ምረጡኝ ብትል መስሚያ የለንም ።
ምንም እንኳ የፌደራል ስርዓቱ በዋነኛነት በቋንቋ ማንነት የተዋቀረ ቢሆንም ፤ አማራ፣ ኦሮሞ ፣ አፋር ፣ ሱማሌ ፣ ጋምቤላ ፣ ወዘተረፈ ወይም አብሮ አደግ አልያም ጓደኛ ስለሆንህ ብቻ አልመርጥህም። ሀገራችንን ከተዘፈቀችበት አረንቋ ለማውጣት ይዘኸው የመጣህ ፓሊሲ ይወስነዋል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ ይጠብቅ !አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013