ጊንጦችና ሸረሪቶች የሩቅ ዝምድና አላቸው ይባላል። ሸረሪት፣ እርሷን ለመገናኘት የመጣውን ድንጉላ “ሸረሮ” (የእኔ ውልድ ቃል ነው፤ ለወንዱ ሸረሪት) ከተገናኛት በኋላ ቅርጥፍ አድርጋ ትበላውና የቀብር ሥርዓቱን በሆዷ ውስጥ ታከናውንለታለች። አዝና ይሆን…? እንጃ፤ ሸረሪትኛ የምታውቁ ልትነግሩን ትችላላችሁ።
ይህ ተፈጥሯዊ የመበላላት ህግ በሴቴዋና በወንዴው ጾታ፤ ጦርነት አንድ ለአንድ ይደመደማል። ከዚያም እርሱን በማባዛት ይሁን በተጋቦው መንገድ እጮቹ ተፈልፍለው ብዙ ሸረሪቶች የእለት ከርሳቸውን ለመሙላት በየሥፍራው ሽርር ማለት ይጀምራሉ። ይህም በዘመነ መሳፍንት ደጃዝማቹና ደጃዝማቹ፣ ከነሰራዊታቸው ከሚያልቁበት ውጊያ ወደ ቤተ-መንግስት ሽኩቻ ብቻ የሄደበትን፣ ዘውግ ያስታውሰናል።
ወደጊንጥ ስንመጣ፣ ደግሞ ጊንጥ በአንድ ጊዜ በርካታ ልጆችን ትፈለፍላለች። እንደሌሎቹ ፍጥረታት ፍልፍል ጊንጦቹ፣ የእናታቸውን ጡትና ሙቀት አግኝተው ለማደግ አይደለም፤ ከእናታቸው የሚጠጉት። ወዲያውኑ የእናታቸውን ቆዳ፣ ቀጥለውም ሥጋዋን መብላት ይጀምሩና በመጨረሻም አጥንቷን እምሽክ አድርገው ነው፤ የሚበሉት።
እናት በገዛ ልጆቿ ተበልታ በምታልቅበት ወቅትም፣ የእነርሱ ራስን የመቻል እድገት መነሻ ይሆንና የራሳቸውን ህይወት ይጀምራሉ። በእናት ግድያና ሞት የተሰራ፣ ህይወት መሆኑ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷ ጊንጥም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ በልጆቿ ትበላለች። ይህ የመበላላት ህግ በጊንጥ ትውልዶች ነፍስ ውስጥ የሚቀጥል ነባር ደመ-ነፍሳዊ ሁነት ነው።
ጊንጦች፣ በህብረት ሊገድሉ ይዘምታሉ፤ በኋላም ይዘመትባቸዋል እንጂ፣ ከዚህ ሁነት በኋላ አንድ ላይ ላይቆሙ ነው፤ የሚለያዩትም።
የዛሬውን ዋና ነገሬን፣ ጊንጥ እና ጊንጠኛነት ያልኩትም ለዚህ ነው። ሐገሬ ያለችበት አጣብቂኝ፤ ሐገሬ ያለችበት ሞገድ፣ እንዲህ እየተተረጎመ ነው። ከትናንት በስቲያ አጣዬ፣ ቀጥሎ ሸዋ ሮቢት፣ ቀጥሎ ካራ ቆሬ፣ ቀጥሎ ኮቻ፣ ቀጥሎ እና ቀጥሎ፣ በምእራባዊውም ሆነ ሰሜን ምእራብ አቅጣጫ እንዲህ እንዲህ እየተባለ፣ በደቡብም እስከ ስም አይጠሬ ድረስ፣ እንሂድና ነገራችንን እና መጯጯሁ ይቀጥል፤ ይሆን? ወይስ ቆም ብለን፣ አካሄዳችንን እንገምግም።
ከመጀመሪያው ጀምሮ እየሆነ ያለውን ነገር አላጣሁትም፤ የሚለው መንግስት፣ ያላጣውን ነገር ማስታገስ እንዴት እንዳቃተው ለማወቅ ግራ አጋቢም አደናጋሪም ቢሆንም አንድ እንቆቅልሽ መኖሩ ግን አጠያያቂ አይደለም። እናም ይኸው መንግስት ሊወስድ የሚገባውን ፈጣንና ወሳኝ ርምጃ በመውሰድ የሚነሱ አገር አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን አጢኖ መግታት እንደሚገባው ሁሉ እየሆነ ያለውን ቱማታም በሰከነ መንገድ ሁሉም ወገን ሊያየው ይገባል ብዬ አምናለሁ።
የደሃው ህዝብ ትምክህት እኮ፣ ከአምላኩ በታች በመንግስት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ጊንጦቻችን ግን ይህንን አመኔታ መሸርሸር ግባቸው እንደሆነ ህዝቤ የተገነዘበ አልመሰለኝም። ይህንን ደግ ተመካሂነት፣ የመንግስት ያለህ ባይነት፣ ለጊዜውና በጊዜ ሂደት አልፎ ለሚቀር ርዕዮተ-ዓለም ሲባል ይህን ምስኪን ህዝብ መንግስት አጋልጦ ትቶታል መባሉን ግን ውስጤ ሊቀበለው አልቻለም፤ እና አሁን የሚያስቆጣንን ነገር ለዘብ አድርገን በጽኑ እንድናስብ አሳስባለሁ።
ሁልጊዜ ጦርነት፣ ጦር በያዙ ወንዶች ይጀመርና፤ በሰላማዊ ሰዎች ማለትም አረጋውያን፣ ህጻናትና ሴቶች ላይ ጥቃቱን አበርክቶ ያወርደዋል። እነዚህ ሲቪላውያን ደግሞ መንግስት ለዚህ ጉዳይ ተነሱ፣ ሲላቸው የሚነሱ፣ አዋጡ፣ ሲላቸው የሚያዋጡ ሆነው ሳለ፣ በራሱ በመንግስት ቸል ተብለው ለጥቃት ሲጋለጡ የታዩ እንዲመስል ሁለተኛው የጠላቶቻችን ውጊያ ስልት እየሰራ ይመስላል።
ጊንጦቹ፣ ደግሞ ለተለያዩ ጉዳዮች ብሩን ሳይኖረው ሰጥቶ፣ ንብረቱን አካፍሎ፣ በአንድ ቀን አዳር የልጅ ልጅ ልጅ ካየበት ቀዬ፣ “የእንቶኔ ዘር ነህና” ለቅቀህ ውጣ፣ አስብለው እንዳይመለስ ቤትና ንብረቱን እያቃጠሉበት ነው።
ምን የሚሉት ፈሊጥ እንደሆነ እየገባኝ የመጣው ግን ዘግይቶ ነው። የግራ ማጋባቱ ስሌትም ይሆን ይሆንን? መጠራጠሬም አልቀረም። የተመረጡትን ቦታዎች እስቲ ልብ ብላችሁ አጢኑ። አማራና ኦሮሞ ድንበርተኛ የሆኑባቸው ወይም አማራ በስፋት በሚኖርባቸው የኦሮሚያ ግዛቶች ላይ ነው።
ከዚያም አፋርና ኢሳዎችን እንዲሁ እየጠቀጠቁ ነው። ይህ የግንደ ቆርቁር ወፍነት ሴራና አሽክላ ሁሉ፣ በሐገር ውስጥ ጎጆ ቀልሶ ለመኖር ሳይሆን ዛፊቱ ሐገራችን የጀመረቻቸውን የልማት ውጥኖች በአጭር ለማስቀረትና እዚህም አዚያም የተነሱትን እሣቶች በማጥፋት እንድትወጠር አለፍም ሲል እንደ ሐገር እንድትከሽፍ ነው።
( Ethiopia, One of the failed state in east Africa ለማለት ተቁለጭልጨው እየጠበቁን ነው፤ ) እና ባሰቡልን ጉድጓድ እንውደቅ ወይስ በትዕግስትና ጥበብ ሴራቸውን እንበታትን? በዚህ ወሳኝ ምእራፍ ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቀው እውነት ይኼ ነው። ምርጫው በእጃችን ነው።
ይህ ዘዴ ግልጽ ነው፤ የልጅነት ትዝታውን በዚያ ስፍራ ያጣ፣ ያለፈ ህይወቱን በተወለደ እና ባደገበት ሥፍራ (እትብቱ በተቀበረበት) በውድመት የተነጠቀ ሰው ለመመለስ አለመሻት ብቻ ሳይሆን ሁሉን ተነጥቋልና፤ ሁሉንም ይጠላል። ስለዚህ ስለስፍራው ሲያስብ፣ ስለ ደጋጎቹ ቀናት ሳይሆን ውርሱንና ቅርሱን ስላስጣለው ድንገታዊ የወራሪ ጥቃት ስለሚያስብ አገር ጥሎ፣ አንድ ወደፈረንጅ አሽከርነት፣ ወደባዕድ አምላኪነት ቢያስብ አለዚም ሌላ ስፍራና ሁኔታ በመጠበቅ እርሱም የጊንጦቹን መንገድ ሊከተልና ሊተባበረን ይችላል፤ ብለው ክፉ ፈጻሚና አስፈጻሚዎቹ ጊንጦች ስላቀዱ ነው። ወገኔ ሆይ! በዙሪያችን ያሉትን፣ ሶሪያውያንን እና የመናውያንን ልብ ብለህ ተመልከት።
ሶሪያውያኑ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ለብዙ ሺህ ዓመታት በካበተ ታሪክ፣ በህንጻ ግንባታ፣ በእምነት ስርጭት፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊና ቁርዓን፣ ምስክርነቶች ጭምር የቆዩ ጠቢባን ተዋጊዎችና የዘመናዊው አረባዊ ኣለምም ድንቅ ክስተት የነበሩ ህዝቦች ናቸው።
ይሁንናም ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ከገቡ በኋላ ወደስፍራው ላይመለስ የቻለ ስልጣኔ፣ ወደስፍራው በቀላሉ የማይመለስ መሰረተ ልማት፤ በቀላሉ የማይመለስ ክፉ የታሪክ ጠባሳ ትቶ፣ በጦርነቱ ከሶሰት መቶ ሺህ በላይ ህዝቧን ገብራ፣ በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ወደ አውሮጳና አሜሪካ ያስሰደደች የጊንጥ ሐገር ሆናለች።
የአዲስ አበባ ጎዳናዎችም የተመጽዋች ሶሪያውያንን ገጽታ ከመላመድ አልፋ አካሏ አድርጋቸዋለች። “አባ፣ ኡማ …ብር ስጥ እና ስጠይ…” የሚሉ ህጻናት ፈስሰው ከመታየት አልፈው፣ ኑሯችን ከሆኑ ዓመታት አስቆጥረዋል።
ጊንጥነት ለስደት፣ ለልመናና ለባይተዋርነት፣ አለፍም ሲል ለግዳጅ ወሲብ ባርነት የሚያጋልጥ ርግማን ነው። ይኼንን እያስደረጉብን ያሉት እጆች ረቂቅ ናቸው። አዎ፣ ጊንጦቻችን ድርጊቱን እንዲፈጽሙ፣ የፈረጠመ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት አሉ።
ወዲህ እርዳታ ለመስጠት ተከለከልን፣ በወዲያ ሰብዓዊ መብት ጣሳችሁ፣ በወዲህ ድርድሩን ከእኛ ጋር አድርጉት፤ በሚል የእሺ – ነገ ፈሊጥ፣ በማጓተት ስልት እያወዛገቡን ያሉ ኃይሎች ሴራ ተውሳስቦ እያስጨነቀን ነው። ለዚህም የድንበር ወረራ ታክሎበት፣ ሐገሪቱን በአስጨናቂ ምጥ ውስጥ ከትተዋታል። በዚህ አጋጣሚ፣ (American Made) የሚለውን ፊልም እንድታዩ እጋብዛችኋለሁ።
አንደኛውን ሰፊ ቁጥር ያለውን ህዝብ በሌላኛው የታጠቀ ኃይል አማካይነት በማስጠቃት ተጠቂውን “ልታልቅ ነው፤ ልትፈጅ ነው፤” በማስባል አደጋው ወደከፋ የእርስ በእርስ ፣ ጥላቻና የህዝብ ለህዝብ ግጭት እንዲያድግ መግፋት አንዱ ስልት ነው። ይህም እየተሰራ ነው።
ቀጥዬ የማነሳውን ሀሳብ ለማስተንተን እና ሥራው ታቅዶበት እየተከናወነ ያለ የብዙ ሃያላን እጆች ሐገራችን ላይ እንዳለ ማጤን አስፈላጊ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ሳይንቲስት መሆን አይጠበቅብንም፤ በየትኛው ሐገር ነው፤ በምርጫ ተወዳድሬ አሸንፋለሁ ብሎ የተዘጋጀ ፓርቲ፣ ይመርጠኛል የሚለውን ህዝብ በስናይፐርና በመትረየስ የሚያስጨርሰው? በየት ሐገር ነው፤ ለምርጫው አራት ሳምንት የቀረው ፓርቲ፣ አንድ ከተማ ሙሉ እንዲጋይበት ታጣቂ በጎን ይልካል፤ ብሎ ማሰብ የሚቻለው። እና ጊንጦቹ ጉዳያቸው ከሐገር ሳይሆን ለተላኩበት ዓላማ በመሆኑ ነው፤ ይህንን የግፍ ጽዋ ህዝብን የሚያስጎነጩት። አሁን እየተቀጣጠለ ያለውን ሰልፍ ስታዩት ፊልማቸው በከፊል እየሰራ መሆኑን ማየት አይቸግርም። ኦ፣ ሐገሬ ሆይ!!
ከዕለታት በአንደኛው ቀንም፣ አንድ አማርኛ እንደ ነገሩ የሚናገር ሶሪያዊ ትልቅ ሰው፣ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመገረም ቀርቦ፣ “እኛን ከሐገር ያስወጣንን ጉድ እናንተ እየጀማመራችሁት እየሰማን ነውና፤ ሐበሾች ይህንን የደም ቀልድ ብትተውትና ነገራችሁን በውይይት ብትፈቱት ጥሩ ነው፤ አለና በመቀጠልም ጦርነት አሸናፊንም ተሸናፊንም አያኮራም፤ ጦርነት እሳት ነው፤ ሲበላ ነው እንጂ፣ የእሳቱን መነሻ አታውቁትም፤ ከየት እንደተወረወረ አይታወቅምና።
ኢትዮጵያውያን፣ እሳቱን እያራገባችሁት ነው፤ እኛ ሲጀማምረን ልክ እንደ እናንተ ነበረ፤ ያደረገን። ጦርነት ስደት ነው፤ መሰደድ ምን እንደሆነ ካልገባችሁ የእኔንና የልጆቼን አኗኗር ተመልከቱ፤ ስደተኛ እኮ ዛሬ እንጂ ነገ የለውም፤ ማደሪያ እንጂ ቤት የለውም፤ ሰማይ ጣራው፣ ምድር መኝታው ናት” በማለት ሲያሳስብ፣ አዳምጫለሁ። (ለዚህ ተቃንቶ የቀረበ ነው)
በእውነት እንዲህ ያለ አስተዋይ ዓይን ከሌለን፣ ታውረናል፤ እንዲህ ዓይነት አርቆ የሚያስብ ልብ ከሌለን ታምመናልና፤ ሕክምና ያስፈልገናል። በዚህ መንገድ መራመድ ካልቻልን እንዴት አድርገን ትልቋን ሐገር እንደ ሐገር እንደምናስቀጥል አይገባኝም። የተሰራችውንና ዘመናት ያስቆጠረችውን ሐገር ማጠናከር ይሻለናል ወይስ በጽናት የተመሰረተችን ሐገር አፍርሶ እንዳዲስ መስራት ይመርጧል? በዘመናዊው ኣለም ውስጥ መፍረስ የጀመሩ የትኞቹ ሐገራት ናቸውስ፤ ተመልሰው የቆሙት። ጦርነት ያላቆማቸውን ያህል ትናንሹ ቁርቋሶ ሁሉ፣ አንኮታኮታቸው እንጂ አላፀናቸውም፣ ጥፋታችን ከአያያዛችን በመሆኑ አያያዙን ማቃናት ያቀናናል እንጂ፣ በደም ማፍሰስ መገፋፋት አያኗኑረንም።
ጦርነት ባለበት በዚያ፣ ንብረትና ሐብት መወረስ፣ ለወራሪው ሃይልና ፈቃድ መገዛትና አለፍ ሲልም፣ አስገድዶ መደፈር በስፋት ይፈጸማል። ስለዚህ ነው፤ ጦርነት ወንድ ነው፤ ከራሱ ጋር ጀምሮ በሴቶች ጥቃት የሚፈጽምና አባታቸውን የማያውቁ አእላፍ “ልጆች” መፈልፈያ አውዳሚ “ማሽን” ነው፤ የምለው። እንዲያውም የመጀመሪያውን ምሳሌ ለማጠናከር በዘንድሮ ሁኔታ ተዋጊዎቹ፣ በእናታቸው ማህፀን አድገው ሲወለዱ፣ እናታቸውን የሚበሉና እናታቸውን የማያከብሩ ጊንጦች ነው፤ የሆኑት።
ይህች ሐገር ባላት ጥሪትና ሐብት ያስተማረቻቸው፣ የኳለች – የዳረቻቸው፣ የካበቻቸው፣ ትላልቁን ሹመትና ሐብት የሰጠቻቸው ሆና ሳለ፣ እንደገና ይህችኑ ሐገር “በመፀየፍ” የሚጎዷትና ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል ሥራ የሚሰሩት እነርሱው ሆነዋል።
ጊንጥ ሆይ! የሶሪያን ምድር፣ ተዋጊ ሶሪያውያን ራሳቸው፣ ምን እንዳደረጓት ካላስተዋልክ፣ ስደት የሚያደርሰውን ሃይል ለመታዘብ፣ ካቃተህ በዙሪያህ ያሉትን ፀጉረ-ለውጥ ሶሪያውያንና የመናውያንን ተመልከት። የመኖች፣ ከእኛ የአኗኗር ባህል ጋር የሚያቀራርብ የታሪክና የትውፊት ዳራ በስፋት ስላላቸው፣ ሰሜንና ደቡብ የመን ተባብለው ለሁለትና ሶስት አሰርት አመታት ተለያይተው ኖረው በመጨረሻም፣ “ተቀላቀሉ” በተባሉ በአጭር ዓመታት ውስጥ፣ “ሱኒ እና ሺዓ” ተባብለው በመጠዛጠዝ፣ ሰሜኑም ደቡብ፣ ደቡቡም ሰሜን ሆነና ድብልቅልቅ ባለ ግጭት ውስጥ ከተዘፈቁ ሁለት አሰርት ዓመታት አልፈዋል። ይህ ጊንጣዊ አካሄድ፣ የመንን የመን አድርጎ የሚያዘልቅ አልመስል ብሎ፣ ባለፉት አሰርት ዓመታት የጊንጥ ልጆቿ ጥርስ ፣ የየመንን ስጋዋን አልፎ አጥንቷን እየቀረጠፈ ነው።
ይህንና ይህን፣ መሰል ታሪኮች ወደ አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ሳንርቅ፤ እዚሁ ቅርብ ሶማሊያ አለችልንና ማረጋገጥ ይቻላል። ሁሉም ጊንጦች ግን፣ ወደ አሰቡት አልደረሱም። ዛሬም በማያባራ ግጭት፣ በማያባራ ስደትና ፍልሰት ውስጥ ናቸው፣ ሐገራቱ። የሚያሳዝነው ነገር ልክ እነዚያ ጊንጦች በልጆቻቸው (በፍልፍሎቻቸው) ተበልተው እንደሚሞቱ ሁሉ፣ እነዚሁ ተዋጊዎችም በመሰል ተዋጊዎች ተበልተው ማለቃቸው የገዛ ታሪካችን ምስክር ነው።
በሰው ልጆች ጦርነት አሸናፊም ተሸናፊም ወገን የለም፤ ሟችና ገዳይ እንጂ። ዓለምን ያናወጠው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጠናቀቅ ሞተ፤ ተብሎ የቀረበውን የሰው ልጅ አኃዝ ስታዩት ዘግናኝ ነው፤ ሃምሳ ሚሊዮን ህዝብ ከግራውም ከቀኙም፤ ከተዋጊውም ካልተዋጋውም ክፍል ከጀርመን እስከ ሩሲያ ምስራቅ ጠረፍ በተዘረጋው ሐገር ሁሉ እና በኋላም ጦርነቱን ከተቀላቀለችው አሜሪካ ጭምር ሚሊዮናት መሞታቸው አልቀረም። ጦርነቱን የቀሰቀሰችው ሀገር ጀርመን ግን፣ ለዚህ ሁሉ ውድመት ምክንያት ናት/ ነበረች፤ ተብሎ ከምድር ላይ ካርታዋ አልጠፋም፤ ህልውናዋ አልከሰመም።
በእርሷ ምክንያት ያ፣ ሁሉ ነፍስ ይጥፋ እንጂ፣ ጀርመናውያን እንዳለ አልተሸነፉም፤ በወረራ ሃያልና ገናና “አባት” ሐገር (ፋዘር ላንድ ይሉ ነበር ናዚዎች) ትሆናለች፤ ከፍ እናደርጋታለን ያሏትን ጀርመን ግን፣ በጦርነቱ አቅቷቸው፣ በኋላ ላይ ግን፣ በሚያስደንቅ መንገድ በሰላምና በሳይንስ ግስገሳ፣ በላጭ ሐገር አድርገው ልህቀት የሚታይባት ምድር ሆናለች። በጦርነቱ ወቅት ግን ጀርመን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እስከ አጥንቷ የዘለቀ ድብደባ በራሷ ጦስ ገጥሟታል። ጦሶቿም የገዛ ልጆቿ ናዚዎች ጊንጥ ሆነውባት ነው። በተራቸው እነርሱም በለኮሱት እሳት ተለበለቡ እንጂ።
ማንም ሐገርም ሆነ ሃይል አስፈሪነቱ ጊዜያዊና አላፊ ነው። ማንም ብርቱ ቢመስል ለጊዜው ነው፤ ደርግ በሰዓቱ በአፍሪካ ሃያል የተባለ ጦር-ኃይል፣ የነበረው ቢሆንም ወድቋል፤ በዚያን ወቅት ሽምቅ ተዋጊ የነበሩት ሃይሎች አስራ አምስት ዓመት በጫካ ይቆዩ እንጂ አልረቱትም፤ ከዚያ ይልቅ ደርግ ራሱን እንደ ጊንጥ በመብላት ነው፤ እርስ በእርሱ ተገዛግዞ የወደቀው። ደርግ የልማት ስትራቴጂ፣ የውጊያ ጥበብ ድህነት፣ የመርህ እጦት አልነበረም፤ የጣለው፤ መርሆውን ለመተግበር በተከተለው የግድያ ስትራቴጂ ተጠልፎ እንጂ። በ1981 ዓ.ም በተቃጣበት መፈንቅለ-መንግስት ተሳተፉ፤ ያላቸውንና፣ ሐገሪቱ በሁሉም የጦር ኃይል ሰልፍ ውስጥ ምርጥ የተባለ እውቀትና ልምድ የነበራቸውን ልጆቿን ሁሉ ያለምህረት ቅርጥፍ አድርጎ በመብላት ነው፤ ራሱን በጥፊ መትቶ የወደቀው።
የቆመ ሲመስለው ከእርሱ በምንም ደረጃ ወደረኛ ባልነበሩት ቁምጣ ለባሽ፣ ደቃቃ ልጆች ፍልሚያ ፊት መቆም ሳይችል ቀረ። የትህነግ ሰራዊት ከመቀሌ የጀመረውን ውጊያ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ነው፤ አዲስ አበባ የገባው። እናም ቀፎ ሆኖ ቆሞ የነበረውን መንግስት ነው፤ ገፋ አድርገው አራት ኪሎ ዘው ያሉት። ያኔም ገናናነቱ ምናምንቴ ሆነና አረፈው። እናም የምለው፣ ደርግ ጊንጥ ሆኖ የበላው ራሱን ነው።
የትህነግም ጉዞ እንደዚያው ነው። በአየርም ቢመጣ፣ በምድርም ሊፎካከርን የሚሞክር ኃይል ከፊታችን መቆም አይችልም፤ የሚቋቋመን ማንም የለም፤ እያሉ ነው፤ 44 ዓመት በስንት ፕሮፓጋንዳ ያደራጁት ድርጅታቸውና ማንነት በሶስት ሳምንት ውስጥ ምናምንቴ ሆነው የቀሩት። ከተተኮሰባቸው አረርም ይልቅ፣ የውስጠ ድርጅታቸው ራስን አግዝፎ የማየት ብካይነት እና ውስጠ ነጻነት እጦት ነው፤ ጊንጥ ሆኖ በልቶና አንክቶ የረመረማቸው።
ታላላቆቹን የዓለም መንግስታት ብናይም እንዲሁ ነው፤ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ በፈረንሳይ፣ ኣዶልፍ ሒትለር በጀርመን፣ ወዘተ…የውድቀታቸው ምክንያት ጊንጥነታቸው ነው። ጊንጠኝነት፤ እንደ አስተሳሰብ ባለቤቱን እየበላ ህልውናውን የሚያከስም፣ ደግሞም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተከታተለ የሚሄድ የማያቋርጥ መርገም ነው። ኢትዮጵያን፣ በዚህ ጊንጥኛ መንገድ ለማስኬድ ደፋ ቀና የሚሉት ወገኖች መጪው ጥፋት ያልታያቸው፣ ወይም ሲያውቁ የሚያጠፉ የድውይ አስተሳሰብ አዝማቾች ናቸው። እነዚህም ጊንጦች ናቸውና ይፍጠንም ይዘግይ ውድቀታቸው አይቀሬ ነው።
ሰው ከፍቅርና መተሳሰብ ከመቻቻልና ራስን ከመግዛት ሐሳብ ሲያፈነግጥ የስሜቱ እስረኛ በመሆን አጥፊ ወደሆነ ርምጃ ይገባል፤ ያኔም ሌላውን የጎዳ እየመሰለው በራሱ ላይ እርግማን ያመጣል። ይህ ክፋት ደም ወደማፍሰስ ሲመጣ ደግሞ አፍራሽነቱ ማቆሚያ የለውም። እናም ጦር መዛዡ ኃይል፣ ይህንን ቢገነዘብና እያደረገ ካለው ሐገር አጥፊ፣ እናትን የማንከት ክፉ ጥፋት በመቆጠብ ራሱን ያስተካክል። ዘማች ጊንጥ ሆይ፣ ከጊንጥኛ ዘመቻህ ራስህን ከልክል፤ አለበለዚያ ፍጻሜህ አያምርም።
ኢትዮጵያ ሐገራችን ሁልጊዜ የጨለመባት ሲመስል ንጋቷ እየመጣ፣ ያበቃላት ሲመስል እያንሰራራች በርካታ የታሪክ ገፆችን አገላብጣለች። ከእንግዲህ አይሆንላትም የተባለባት ጊዜ ብዙ ነው። እንደተሟረተው አላበቃችም፤ አታበቃምም፤ ይልቅ የተገላቢጦሽ በኢኮኖሚም፣ በፖለቲካም፣ በሐገራዊ ሥነ-ልቡናና በመንፈሣዊ ልህቀት ከፍ የምትልበት ጊዜ ተቃርቧል፤ ግድባችን ሌሎችን ሳያደኸይ ይሞላል፤ ሌሎችን ሣናጫጭም እናድጋለን፤ ጊንጠኛነት መቼም በሐገራችን ምድር አብቦ አያፈራም። የጊንጦች ህልምም አይሳካም፤ አበቃሁ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2013