መቼም የሚመች ፣የሚደላን መቀመጫ የሚጠላው የለም። እንዲህ አይነቱ ማረፊያ በተገኘ ጊዜ ሰፋ ደልቀቅ ቢሉበት አይከፋም ። ደግሞስ ከሚቆረቁር፣ ከሚጎረብጥ ነገር ምን ይገኛል ምንም ። ለዚህም ነው አንዳንዶች ከእንዲህ አይነቱ ምቾት በቀላሉ መነሳትን የማይሹት።
ወዳጆቼ ስለምቾት ከተነሳማ የአንዳንድ ባለስልጣናትን ጉዳይን ሳያወጉት ማለፍ አይቻልም፤ እንዲያው ለወጉ ይነሳ እንጂ እነሱ የፈለገውን ቢባሉና ቢወቀሱ ደንታቸው አይደለም። ለምን ከተባለም መስሚያ ጆሯቸው ማገናዘቢያ አዕምሯቸው በምቾት ተደፍኗል። አይ! ምቾት ስንት ያሳያል፣ያሰማል መሰላችሁ።
እንግዲህ የአንዳንዶችን የስልጣን ምቾትን ካነሳን ጥቂት እጅግ በጣም ጥቂቱን ጉዳይ እንንቀሰው። ደግሞስ ተወቀሰ አልተወቀሰ ምን ይመጣ ብላችሁ። አዎ! አይሰሙንም እንጂ ቢሰሙን ደግሞ ለታዛቢዎች የሚሆን ምላሽ አይቸግራቸውም። ደግሞ ለምላሽ። ይህማ የተለመደ ድንቅ መገለጫቸው አይደል።
መቼም በዕድልም ይሁን በአጋጣሚ፣ በዕውቀትም ይሁን በብቃት፣ ስልጣን ይሉት መቀመጫ ላይ አረፍ ማለቱ ይኖራል ። የሥልጣን አይነቱ ደግሞ እንደቦታውና እንደየደረጃው መለየቱ አይቀርም ። ይህ መሆኑም አይከፋም። የተሰጠን ኃላፊነት ለተገቢው ስፍራና ዓላማ ካዋሉት እሰዬው ያስብላል። የሕዝብ ምስጋናም አይለያቸውም።
የእኔ ጽሑፍ አጀንዳ ያተኮረው በስልጣናቸውን ያላግባብ በሚጠቀሙትና በስልጣናቸው ልክ የማይሰሩትን ነው። በስልጣን ቆይታቸው ሕዝብ ከማገልገል ይልቅ መጠቀሚያ ስለሚያደርጉ ባለስልጣናት ግርም ይሉኛል፤ አስቀድሜ እንደጠቆምኩት የሥልጣን አይነቱ እንደየቦታው ይለያል፤ስልጣን ሲባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሌሎች አቻዎች ጋር ከሚመደቡት ሚኒስትሮች ጀምሮ በተዋረድ እስካሉት የቢሮ ኃላፊዎች፣ ይዘልቃል። ሰንሰለቱ ከፍና ዝቅ ሲልም መስመሩ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ብሎም እስከ ቀበሌ አመራሮች ሊዘልቅ ይችላል።
ለዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገርን ስለሚወክሉ ታላላቅ ሚኒስትሮችና በእነሱ ደረጃ ስለሚገኙ አካላት ጉዳይ ማንሳቱ ይቆየኝ ። አንዳንዶች እያልኩ ስለማነሳቸው ጥቂት ባለስልጣናትና ኃላፊዎች ሕዝቡ ስለነሱ ከሚለው ጥቂቱን ጀባ ልበል።
እንዲህ አይነቶቹ ባለወንበሮች መነሻቸው ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ይሉትን አባባል ይመስላል። ስልጣን ከያዙ ማግስት ጀምሮ እጃቸው በእጅጉ ይረዝማል። ዓይናቸውም የሚሹትን ለማግኘት ቦዝኖ አያውቅም። ተከታዮቻቸው የበረከቱ ባለጉዳዮቻቸው የተወሰኑ ናቸው።
አንዳንዴ የስልጣን እርካብ አያድርገው የለም። ከወገን ይልቅ የራስ ጥቅምን ያስቀድማል። የገቡትን ቃል አስክዶ የህልም እንጀራ ያስጋግራል። ህልሙ ደግሞ ቅዠት አልያም ምኞት ብቻ ሆኖ አይቀርም። አስቀድመው ያቀዱትን፣ሲያስቡ የኖሩትን ውጥን ሁሉ ከግብ የሚያደርስ ነው ።
ብዙ ጊዜ ስልጣንን የአንዳች ጉዳይ መነሻና መጠቀሚያ የሚያደርጉ ባለስልጣን ተብዬዎች ህልማቸውን (የመስረቅ አባዜያቸውን) ዕውን ሳያደርጉ ዕንቅልፍ የላቸውም። እንዲህ አይነቶቹ ህልመኞች ወትሮም ግባቸው የበዛ ጥቅም ነውና በየጓዳው አይጥ ለመሆን የሚያግዳቸው የለም።
አዎ! አይጦች ናቸው፡፤ትላልቅ ባለጥርስ አይጦች ። ውስጣ ውስጡን በአፍንጫቸው አነፍንፈው፣የሚሹትን ያገኙታል። ያገኙትን ፈጥነው ለመቀርጠፍና ለመቦጨቅ አይዘገዩም ። አይጦቹ የከፉ ናቸውና የያዙትን ሲቦተርፉ ቦታ አይመርጡም። እዚህም እዚያም እየቀደዱ፣ እየቀረደዱ የያዙትን መዋጥ ል ምዳቸው ነው።
አይጦቹ ከእህል ጎታው ዘልቀው ያሻቸውን ሲፈጽሙ ምህረት የላቸውም። በእነሱ ዘንድ የሚጣልና የሚመረጥ አይኖርም። ፍሬና ገለባ፣ስንዴና እንክርዳድ፣ምርትና ግርድ ሳይሉ ሆድ እስኪሞላ፣ ቁንጣን እስኪያስጨንቅ ይሰለቅጣሉ ።
እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በሥልጣን ሰበብ በሚመጣ የበዛ ጥቅም የሚታየው አንዳንድ ድርጊት በክፉዎቹ የጓዳ አይጦች ይመሰላል፡፤አይጦቹም እኮ እልፍኙን በገሀድ ስላገኙት ነው መጫወቻ ያደረጉት። ሰው ባልበዛ ኮሽታ ባልኖረ ጊዜ የሌሊቱን ጭርታ ተጠቅመው ጉድ ማድረግ ልምዳቸው ነው።
እነ እንቶኔም ለቡጥቦጣቸው የሚያመች የራሳቸው መላ አያጡም። የተጠጋቸውን ሁሉ በታማኝነት አይቀርቡም። ሚስጥረኞቻቸው ከሌሎች የተለዩ ናቸው። ለእነሱ ከሆነ ሁሌም ቢሯቸው ክፍት ነው። ቢሯቸው በመጡ ጊዜ በባለጉዳይ ቀንና ቀጠሮ አይስተናገዱም ።
ርምጃቸው የተለካ፣እይታቸው የታለመ ነው። ያሻቸውን ሰዓት ቆይተው የፈለጉትን አውርተው ቢወጡ ለምን የሚላቸው የለም። እነሱ ካሉ ሌላ ባለጉዳይ ቦታ የለውም።
ሚስጥረኞቹ እንግዶች የመሬቱን፣የገንዘቡን፣ የካርታና ውሉን ጉዳይ አውርተው ተፈጣጥመው እስኪያበቁ ተራ ጠባቂ ባለጉዳዮች ቦታ የላቸውም። በአሰራር ሂደቱ መጠየቅና መወቀስ እንዳይኖር ደግሞ ጥንቃቄና ትህትናው የተለየ ነው።
የሰለጠኑ የሚመስሉ ጸሐፊዎቻቸው በየአፍታው ፈገግታ እየቸሩ፣ የገባው ሚስጥረኛ እስኪወጣ ተረኞችን ያባብላሉ፡፤እንዲህ የሚሆነው ግን ሁሉም ስፍራ ላይሆን ይችላል፤ አንዳንዶቹ ደጅ ለሚጠኑ ሰዎች ደንታ የላቸውም። በአለቆቻቸው ቢሮ ዘብ ቆመው ብዙኃንን ያንገላታሉ። ለልዩ እንግዶቹ እንጂ ለዘወትር ባለጉዳዮች ፈጽሞ አይጨነቁም።
ባለወንበሮቹ በእነሱ የሥልጣን ሙያ ፈቃድ ትዕዛዝን መፈጸም፣የግል ፍላጎትን መሙላት ልምዳቸው ሆኖ ይቀጥላል ። በዚህ የመስመር ጉዞም የሚገኝ የትኛውም ጥቅም እንዲያመልጣቸው አይሹም ። ከመሻራቸው በፊት የሚቀመጡበትን ሰፊ ወንበር እንዳሞቁ፣እንዳሰፉ ይዘልቃሉ።
አንዳንዴ በደል የበዛባቸው፣ችግር የተደራረበባቸው ነዋሪዎች ጉዳያቸውን አቤት ሊሉ ይመጣሉ፡፤ምናልባትም የእነሱ ቅሬታ ባለሥልጣኑ ከልዩ እንግዶቹ ጋር የፈጸመው የግል ጥቅም ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፤እንዲህ በሆነ ጊዜ ደግሞ ተበደልን ባዮቹ አስቸኳይ መፍትሄ ቀርቶ ሰሚ ጆሮ አያገኙም ።
አንዳንዴ ጉዳዩ ሲብስ፣ ነገሮች ሲደራረቡና አቤት ባዮች ሲበራከቱ ሀሳቡ ከፍ ብሎ ለሚዲያ ይበቃል። እውነታውን እንመርምር መፍትሔ እናመላክት የሚሉ ጋዜጠኞችም ቅሬታ ወደተሰማበት ክፍል ያመራሉ፤ በቀናት አልያም በወራት የቀጠሮ ምልልስ ዕድል አግኝተው ጥያቄዎች ያቀርባሉ፡፤ጥያቄዎቹ ተቋሙ ላይ ስለሚነሳው ቅሬታ፣ ተመዘበረ ስለተባለው ሀብትና ገንዘብ ፣ስለሕገወጥ የመሬት ይዞታና ስለባለጉዳዮች እንግልት ጭምር ይሆናል።
ወዳጆቼ ! መቼም ይህን ሰዓት በቦታው ያለውን ባለሥልጣን ተብዬ አለማየት ነው። ልብሱን አሳምሮ አንገቱን በከረባት አስሮ፣ አይኑን በጨው አጥቦ ምላሽ መስጠት ይጀምራል፡፤
ጥያቄው እየበረታ ፣እውነታው እየተገለጠ ሲሄድም የተለመደውን አይነት ምላሽ ይደጋግማል ። እንዲህም ይላል‹‹እኔ ወደዚህ ኃላፊነት የመጣሁት በቅርብ ጊዜ ነው፡፤ አሁን እየተባለ ያለውን ጉዳይ በሚመለከት ያለፈው ካቢኔ ብቻ ነው መልስ ሊሰጥ የሚችለው ›› እያለ እርግጠኝነቱን ያሳያል፡፤
እዚህ ላይ ጠያቂ ጋዜጠኞች ብርቱ ካልሆኑ ራሱን እያወደሰ ያለፈውን እየወቀሰ ለመናገር የሚመልሰው የለም። አያይዞም በቦታው ያሉ ባለሥልጣናት የሕዝብ አገልጋይ ሊሆኑ እንደሚገባ ሊያስተምር ይሞክራል። ሙስና ይሉትን የዘመኑን አይቀሬ ቃል እየደጋገመም መግለጫውን ሊያዳብር ንግግሩን ሊያሳምር ይሞክራል። ጉድ እኮ ነው! እንዲህም አድርጎ መግለጫ የለ።
ከመግለጫው መስጠት ማግስት የተናገሩትን በቴሌቪዥን መስኮት እያዩ አንገታቸውን ይወዘውዛሉ። ለሚያያቸው እንዲህ ያድርጉ እንጂ ውስጣቸውን አሳምረው ያውቁታል፤ የፊታቸውን ገጽታ እንዲህ ቢያስነብቡም በሆዳቸው ግን ‹‹ይህን ምስኪን ሕዝብ ሰራንለት፣ ተጫወትንበት›› እያሉ ማላገጣቸው አይቀርም፤
የእነሱ ቡድኖች የሚባሉ ልዩ እንግዶቻቸውም የመግለጫውን ሙሉ ቃል እየሰሙ በፈገግታ ይጠቃቀሳሉ። በውስጥ አዋቂነት የሾሙት የቢዝነስ አጋራቸው ባለው ሥልጣንና ኃይል ተጠቅሞ ከዘመኑ ጥቅም ስላካፈላቸው አድናቆትን ከምስጋና ይቸሩታል። ለእራሳቸውም ቢሆን ለእሱ ከለገሱት ታላቅ አድናቆት ያህል የድርሻቸውን ይወስዳሉ።
አሁንም ከባለስልጣን ተብዬዎች ድርጊት ጋር እየተጓዝኩ ነው፤ መቼም እናንተዬ የሥልጣን ትንሽና ትልቅ የለውም ብለን የለ ። አንዳንዱ ባለበት፣በተቀመጠበት ወንበር ሆኖ አጋጣሚውን ለመጠቀም የማያደርገው አይኖርም።
አስቀድሜ እንዳልኩት የሥልጣን ተዋረድ ከትልቅ ጀምሮ ትንሽ እስከሚባለው ኃላፊነት ይዘልቃል፡፤ዳሩ ትንሽ ይሉት ኃላፊነት የለም ለካ ። ሁሉም እንዳለበትና እንደተሰጠው ተልዕኮ የድርሻውን ይወጣል ። ጉዳዩ ኃላፊነቱ ላይ አይደለም፡፤ዋናው ነገር የሚፈጸመው ድርጊትና ያለበት ደረጃ ላይ ይወሰናል፡፤
የደረጃውን ጉዳይ ካነሳን ደግሞ ከፍና ዝቅ እያለ በሚሄደው የሥልጣን ተዋረድ የሚፈጸመውን አንዳንድ እውነታን ማየት ግድ ይላል፤ አዎ! ከፍ ያሉት አንዳንድ ባለሥልጣናት በስራቸው በሚያስተዳድሩት የሕዝብ ሀብትና ንብረት ያሻቸውን ይፈጽማሉ። አንጡራ ሀብት ታቅፋ በድህነት በተፈረጀችው ታላቅ ሀገር ጉያ ውስጥ ተወሽቀው ሀብታም ለመሆን ይሮጣሉ።
የእነዚህ ጐምቱ ባለስልጣናት ስግብግብነት እንዳለ ሆኖ እንደአቅማቸው የሕዝብ ኃላፊነትን ተረከብን ባዮቹ የሚፈጽሙት ድርጊት ደግሞ ሌላውን ገጽታ ያሳያል፡፤ እነዚህኞቹ እግራቸው ከተመደቡበት ተቋም እንደረገጠ የስልጣን ማሳያ የሆነው ጥቅማጥቅም ተከብሮ ይቆያቸዋል። ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ፣ደረጃውን የጠበቀ ተሽከርካሪ ፣ከሌሎች የተሻለ የውሎ አበል ክፍያና ሌሎችም ጥቅማጥቅሞች አይቀርባቸውም ።
እነዚህን ጥቅሞች ሲረከቡ ግን አስቀድሞ በእጃቸው ያለውን የመንግሥት ንብረት ለሌሎች መስጠትን አይፈልጉም ። ቀድሞ የተረከቡት የቀበሌ ቤት ቢኖር አዲሱን ቪላ ይዘው የበፊቱን ሁለተኛው ቤታቸው ያደርጉታል ። ቢችሉ አከራይተው ካልሆነም ለሌሎች አሳልፈው ይጠቀሙበታል።
ውብ በሚባል ምንጣፍ በተሽቆጠቆጠው ቢሯቸው ሲገቡ ምቾት ያለው ተሽከርካሪ ወንበር ይቀበላቸዋል። ከእሱ አረፍ ብለው የቢሮ ስልካቸውን ይጠቀማሉ። ስልኩ ለግል ጉዳያቸውም ሆነ ለአንዳንድ የመንግሥት ስራ ጉዳይ የሚጠቀሙበት ነው። ባሻቸው ጊዜ አንስተው ወደፈለጉት ስፍራ የፈለጉትን ያህል ቢያወጉበት ለምን የሚላቸው አይኖርም። አሁንም ለምን ከተባለ ደግሞ ሰዎቹ የበቁ፣ የነቁ የመንግሥት ባለሥልጣናት መሆናቸውን ፈጥኖ የሚናገር አይጠፋም።
እኛም ብንሆን እኮ ባለሥልጣን መሆናቸውን ሳናውቅ ቀርተን አይደለም። አዎ ! ባለሥልጣን ናቸው ብሎ ለመናገር ቃላትና አቅም አላጣንም፤አሁንም ቢሆን ስለማንነታቸው አሳምረን እንመሰክራለን ። ለእኛ ችግርና ስጋት የሆነው ያልተገባ ድርጊታቸውን እንዴት እናጋልጠው ብለን ማሰባችን ነው ። ‹‹ወቸ ጉድ!›› አለ አያ ጉለሌ። አያ ጉለሌ በእኛ ሰፈር ከሚገኝ ሽንጠ ረጅም አስፓልት ከወዲያ ወዲህ ሲሮጥ የሚውል የአዕምሮ ህመምተኛ ነው፤ጉለሌን ‹‹አወቅነው›› የሚሉ አንዳንዶች ካበደና ራሱን ከጣለ ዓመታትን አስቆጥሯል ይሉታል። እሱ ግን የሚናገረውን ጠንቅቆ ያውቃል።
አንዳንዴ ከሩጫው መሀል ቆም ይልና አሰብ አሰብ ያደርገል። ወዲያውም ያየ የተመለከተውን ሁሉ በትዝብት እየቃኘ የልቡን ይዘከዝካል። ውይ ታድሎ! እንዲያው አንዳንዴ እሱን ባደረገኝ ያስብላል፡፤አሁን ጉለሌ ያሻውን ቢናገር የፈለገውን ቢለፈልፍ ማን ነገሬ ይለዋል ። ማንም።
እኛ ግን ሁሌም እያየን ከመታዘብ የዘለለ ለምንና እንዴት ማለት አንችልም፡፤ምንአልባት ‹‹ማወቁንማ እናውቃለን ፣ብንናገር እናልቃለን›› ይሉትን ተረት እንተርተው ይሆናል፤እሱንም ቢሆን በልባችን ነው፤ የደጋገምነው እንዲሁ ለምን ባዩ ይበዛና ትርጉሙ ይዛባል። ወይ ጉድ ደግሞ ባለሥልጣናቱ ጆሮ ደርሶ እንዲህ ለማለት ተፈልጎ ነው ተብሎ ጣጣ ያምጣብን እንዴ? ‹‹ጎመን በጤና አሉ›› እማማ ሻሼ።
አዎ! ባለስልጣናት እኮ ሁሌም ቢሆን ሊከበሩና ሊፈሩም ይገባል ። ይህን የምለው እኔ ብቻ አይደለሁም። ሁሉም ሲናገረው የሚውለው ሀቅ ነው። በተለይ አንዳንዶቹ ለወሬ የሚተርፍ ጊዜና ቦታ የላቸውም። ጉዳያቸው የበዛ፣ባለጉዳዮቻቸው የበረከቱ ናቸው።
አንዳንዶቹ የሚጓዙበት መኪና ከዘመናዊነትም በላይ በእጅጉ ውድ የሚባል ነው ። በእነዚህ አስደማሚ መኪኖቻቸው ሲጓዙ እነሱ ያዩናል እንጂ እኛ አናያቸውም። የመኪናው መስታወት ይህ እንዲሆን አይፈቅድምና አይተናቸው ባናውቅ አይደንቀንም። ደግሞ ባናያቸው ባያዩን ምን እንዳይመጣ ምንም።
አሁንም ከእነሱ ጋር እየዘለቅሁ ነው፤የመኪናውን ጉዳይ ካነሳን አይቀር ዝቅ ባሉት ባለስልጣናት ሳይቀር የሚሆነውን ልማድ እናንሳው ። መቼም እነዚህ መኪኖች ሰዎች ቢሆኑ ብዙ ይናገሩ ነበር። በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ያሉ ሹመኞች በግላቸው ከሚሰጣቸው ሾፌርና ዘመናዊ መኪና ባለፈ ለሚስትና ልጆቻቸው ጭምር የሚመደቡ ተሽከርካሪዎች ሁሌም አገልጋዮች ናቸው ። የእነዚህ መኪኖች ሾፌሮችም የመሥሪያ ቤቱን ሰራተኞች መደበኛ የሥራ ጊዜ የሚጋሩ በመሆናቸው ከብዙኃን መጋጨታቸው አይቀርም።
በመሥሪያ ቤቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መኪኖቹ ለአስቸኳይ ሥራ ጉዳይ መፈለጋቸው አይቀሬ ነው። ምናአልባት ግን የባለሥልጣኑ ሚስት ገበያ ለመሄድ ብትሻ በአንዲት የስልክ ጥሪ ብቻ የድርጅቱን የሥራ ዕቅድ ማስለወጥና መንገዱን ማስቀየስ ትችላለች። ለዛውም በአስቸኳይ።
እንዲህ ይሆን ዘንድ ጥብቅ ትዕዛዝ የተቀበለው የአለቃ ሾፌር ለትዕዛዙ መከበር አስተዋጽኦው የጎላ ነው ። ይህን ባያደርግ የሚጠብቀውን ያውቃል። የአለቃ ሚስት የገበያ ሽንኩርት ከሚቀር እንጀራ የሚበላበት የመሥሪያ ቤቱ መደበኛ ስራ ጥንቅር ቢል ይወዳል።
ይህ ብቻም አይደለም። በአለቃ ሚስት ትዕዛዝ ከገበያ የሸመተውን ሁሉ ከቤት አራግፎ ልጆችን ሊያመጣ ወደ ትምህርት ቤት ይከንፋል ። ልጆቹ ካሉበት ደርሶ የሚወስዳቸውን መኪና ዘመናዊነት ማድነቅና ከሌሎች ማወዳደር ይወዳሉ ። በዚህ በኩል ደግሞ ጣጣ የለም። በሚገባ አምሮና ተወልውሎ በቂ ነዳጅ የጠገበው ባለ ሁለት ቁጥር መኪና የልብ ሀሳብን ይሞላል። ከሌሎች እኩል ያደርጋል። ምን ችግር አለ ከሞኝ ደጃፍ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ደጅም ሞፈር ይቆረጣል።
‹‹ እንክት! ››
ከትዝብት
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013