ልጆች ብዙ ጊዜ የተወሰኑ ልማዶችን ለምሳሌ የእርሳስ ጫፎችን ወይም ጣቶቻቸውን መምጠጥ፣ የጆሮ ጌጦቻቸውን መሳብ ወይም መነካካት፣ ፀጉራቸውን ማሰር ወዘተ የሙጥኝ ብለው ይይዛሉ። ለዚህም ምክንያት እስካሁን ድረስ ይህ ነው ተብሎ አይታወቅም። ነገር ግን አንዳንድ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ በሚያስተውሉት የተደጋገመ ባህሪ ሲጨነቁ አብዛኞቹ ወላጆች ደግሞ የልጆች የተለመደ ባህሪ እንደሆነና ቀለል አድርገው በመመልከት ያልፉታል።
በልጆች ላይ የተለመዱ ልማዶች የትኞቹ ናቸው?
በመካከለኛ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች የሚፈፅሟቸው በጣም የተለመዱ ባህሪዎች የሚባሉት፡ ነገር ግን ወላጆችን የሚያሳስቡ ልማዶች የሚባሉት እንደ አውራ ጣት መምጠጥ፣ ሰውነት ማንቀጥቀጥ፣ የጭንቅላት ድብደባ፣ የጣት ጥፍር መንከስ፣ ፀጉር ማዞር፣ ማስተርቤሽን ወዘተ ናቸው።
እነዚህን ልማዶች የተለመዱ ናቸው በማለት ወላጆች እራሳቸውን ያፅናናሉ። ለምሳሌ እንደ አውራ ጣት መጥባት እና የሰውነት ማንቀጥቀጥ ያሉ ልማዶች በጨቅላነታቸው የሚጀምሩ እና በመካከለኛ ልጅነት ቀስ በቀስ እየጠፋ የሚሄዱ ናቸው።
አብዛኛዎቹ በመካከለኛ ዓመታት የሚገኙ ልጆች አውራ ጣት የሚጠቡት ልጆች በቤታቸው ለብቻቸው በሆኑ ግዜ፣ በሚተኙበት ጊዜ፣ ቴሌቪዥን በሚመለከቱበት ጊዜ ወይም በሚበሳጩበት ጊዜ ያዘወትራሉ። ብዙውን ጊዜ ይህ ባህሪ እንደ ብርድ ልብስ ማቀፍ ያሉ ቀደም ባሉት ዓመታት ከሌሎች ባህሪዎች ጋር አብሮ ይመጣል።
እነዚህን ልማዶች መቼ ያቆሙታል?
ብዙውን ጊዜ ከ6 እስከ 8 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ እና የበለጠ ራስን መግዛትን እና ራስን መረዳት ሲያዳብሩ፣ አውራ ጣቶቻቸውን መምጠጥ ያቆማሉ። በተለይ የእኩዮች ጫና እየጨመረ ሲሄድ ባህሪያቸውን የመተው ዝንባሌ እያሳዩ ይሄዱና እየተውት ይሄዳሉ።
በተመሳሳይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የመካከለኛ ዓመት ልጆች አልጋ ላይ ለመተኛት ራሳቸውን የማንቀጥቀጥ ባህሪ በመደበኛነት ያሳያሉ። ለምሳሌ እስከ ጉልበታቸው እና እስከ ደረታቸው ድረስ ሊያሽከረከሩ እና አልጋው እስከሚንቀሳቀስ ድረስ አልፎም ተርፎም ግድግዳዎቹ ላይ እስከማውጣት ድረስ በንቃት ይተገብራሉ።
ሰዎችን “የሚያበሳጩ” ልማዶች የትኞቹ ናቸው?
የጣት ጥፍር መንከስ ወይም መብላት፣ አፍንጫ መነካካት ወይም መጎተት፣ ፀጉር መጠቅለል በጣም የተለመዱ እና የሚያበሳጩ የልጅነት ልማዶች ናቸው። የልጅነት ልማዶች የምንላቸው ልጆች እድሜያቸው ከ3 እስከ 6 ዓመት ሲሆናቸው የሚጎለብቱ ናቸው። እነዚህ ልማዶች ረዘም ላሉ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ። እንደ ሌሎቹ ራስን ማጽናኛ ልምዶች እነሱ ውጥረትን የሚቀንሱ፣ “ጊዜ የሚያባክኑ” እና ከንቃተ ህሊና ወይም ከንቃተ ህሊና ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ናቸው።
የልጅነት ልማዶች መደጋገም የሚያስከትለው ውጤት
የእነዚህ ልማዶች ድግግሞሽ ብዙውን ጊዜ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ወይም የወላጅ ጣልቃ ገብነት ሳይኖርባቸው ወደ ማብቂያ ወይም ወደ መቀጠል ሊሄዱ ይችላሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት ጥፍሮቹን የሚነክስ ልጅ ሌላውንም የሰውነት ቆዳ በመንከስ ብዙውን ጊዜ የደም መፍሰስ ወይም ህመም እራሱ ላይ ሊያስከትል ይችላል። ምናልባትም ይህ ተፈጥሮአዊ ውጤት በመጨረሻ ለልማዱ መጥፋት ወይም መተው ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል። ያም ሆነ ይህ እነዚህ ልምዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዙ እየጠፉ የሚሄዱ ናቸው።
የልጅነት ልማዶችን እንዴት ማስቆም ይቻላል?
እንደ መጀመሪያ ማስቆሚያ እርዳታ የልጅዎን ልምዶች ችላ ይበሏቸው! ብዙውን ጊዜ እነዚህ ልማዶች ከጊዜ በኋላ ይጠፋሉ። እነዚህን ልማዶች ለማስቆም ከፍተኛ ትኩረት በሰጡ ቁጥር አልያም በከባድ ቃላቶች ሲናገራቸው፣ ሲያፌዙባቸው ወይም ሲቀጧቸው ልማዱን ከማስቆም ይልቅ ሊያባብሰው እና ልማዱ እየጨመረ እንዲመጣ ያደርገዋል። ስለሆነም ቤተሰብ ከዚህ ድርጊት ሊቆጠብ ይገባል።
ቅጣት ልማዶችን ለማጥፋት ውጤታማ መንገድ አይደለም። እነዚህን ልማዶች እያዩ ችላ ማለት ግን ለአብዛኞቹ ወላጆች ከባድ ሂደት ሊሆን ይችላል። ቢሆንም እናት ወይም አባት በልማዱ ሳይበሳጩ ችላ ማለት ከቻሉ ስሜቶቹ እንዲጠፉ ያግዛል፤ ቢሆንም አሉታዊ አስተያየቶችዎን ለማቆየት ይሞክሩ እና ልማዱ እስኪያልፍ ይጠብቁ የሚለው ጠቃሚ ምክር ነው።
ልጆችን እንዴት እንርዳቸው?
ልጅዎ ልማዱን ሳያደርግ በቆየ ጊዜ ያድንቁት፣ የፈለገውን ማበረታቻ ይፈፅሙለት። ለምሳሌ የሚወደውን ነገር መግዛት ወይም ከሚፈልገው ቦታ መውሰድ ወዘተ ተገቢ ነው። ልጅዎ ጣትዎን መንከስ ወይም መምጠጥ ሲጀምር ለማስታወስ በጣቶች ወይም በቆዳዎች ላይ ሊቀመጡ የሚችሉ እንደ መራራ ጣዕም ያሉ ውህዶችን ይጠቀሙ። እነዚህ ግን የተጠኑ ጉዳት የማያደርሱ ሊሆኑ ይገባል። ይህ አካሄድ በአንፃራዊነት ዝቅተኛ የስኬት መጠን አለው፣ ነገር ግን ቀላል እና ውጤታማ ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል። ስለነዚህ ምርቶች ፋርማሲ ይጠይቁ።
የባህሪ ለውጥ ለማምጣት አዎንታዊ ማጠናከሪያ በጣም ስኬታማው መንገድ ነው። ልጆችዎ እነዚህን አዎንታዊ የባህሪ መቀየሪያ መንገዶች ሲተገብሯቸው ማየትና በአጽንዖት መከታተል ይኖርበዎታል። ተግብረው ሲገኙ ይሸልሟቸው። ዕለታዊ ሽልማቶች በጣም ጠቃሚ ናቸው።
ምንጭ:- ዋናው ጤናዎ ድረገጽ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013