ነቀዝም ሆነ ማንኛውም ተባይ በእህል ላይ ከፍተኛ ብክለትና ብክነት ያደርሳል። በተለይ እህሉን ከጥቅም ውጪ ባያደርገውም እንኳን ጠዓሙን በማበላሸት ይታወቃል። በምስራቁ የሀገራችን ክፍሎች በተለይ ነቀዝ አርሶ አደሩ ለዘርና ለክፉ ቀን ብሎ ያስቀመጠውን እህል ከጥቅም ውጭ የሚያደርግበት አጋጣሚ ቀላል እንዳልሆነ የተለያዩ አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
ሌላው ቀርቶ ለቀለብ ብለው በጎተራ ያኖሩትን እህል በሁለትና ሦስት ወራቶች ውስጥ ብቻ ነቀዝ እምሽክ አድርጎ በመብላት የሚያበላሽበትና የአርሶ አደሩን ቤተሰብ ቀለብ በማሳጣት ለተለያየ ችግር የሚያጋልጥበት ሁኔታም እንዳለ ነው የሚገልፁት። በአጠቃላይ በሀገራችን በነቀዝ ተባይ አያሌ አርሶ አደሮች ሲቸገሩ ቆይተዋል። ችግራቸውን ለመቅረፍ የተለያዩ የነቀዝና የተባይ መከላከያ ኬሚካሎችን ሲጠቀሙም ኖረዋል። ሆኖም የነቀዝ መከላከያ ኬሚካሉ ብዙም ችግራቸውን መፍታት አልቻለም።ይልቁኑም ለተጓዳኝ የጤና እክል ያጋልጠን ይሆናል የሚል ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።
በነቀዝና በተባይ ችግር ለገጠማቸው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እነሆ መፍትሔ ያላቸው የዛሬ 16 ዓመት የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ማቅረብ ሥራ የገባው የሃይቲ ትሬዲንግ ሀውስ የተባለው የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅራቢ ነው።
ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት አርሶ አደሩን ለጤና ችግር የሚያጋልጠውን የነቀዝ መከላከያ ኬሚካል ምክንያቱ ምን ይሆን ሲል ማጥናት ያዘ። ጥናቱ ይሄን ኬሚካል ተጠቅመው ነቀዝን እየተከላከሉ ላሉም ሆነ ባለመጠቀማቸው ነቀዝ ምርታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰባቸው ላሉ አርሶ አደሮች መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ነበር።
የሃይቲ ትሬዲንግ ሀውስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅራቢ ገበያና ሽያጭ ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ እንዳጫወቱን ሃይቲ በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ከማረሻ፣መውቂያና ማጨጃ ትራክተር ጀምሮ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ እንዲሁም አሰራርን የሚያቀሉ ቴክኖሎጂዎችን ያቀርባል።
ሆኖም በዚህ ድጋፍ ጭምር እያደገ ያለውን የአርሶ አደሩን ምርታማነት ነቀዝ በእጅጉ ሲፈታተነው 16 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ እንደ ሀገር በተከሰተው የአየር ንብረት መለዋወጥ ተፅዕኖ ጭምር ነቀዝ አርሶ አደሩን መፈታተኑ እየተባባሰ መምጣቱን በማስተዋል በዝምታ ማለፍ አልፈለገም።
አርሶ አደሩን ለማገልገል እንደተመሰረተ አንድ ተቋም የሆነ መላ መዘየድ እንዳለበት አሰበ። አስቦም አልቀረም በተጨባጭ የአርሶ አደሩን ችግር በጥናት ወደ መለየት ገባ። ‹‹ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ነቀዝን ለመከላከል ይጠቀም የነበረው ኬሚካል ነበር›› ያሉት ኃላፊው ተቋሙ ባጠናው ጥናት ኬሚካሉ በአርሶ አደሩ ላይ የካንሰር፣ የቆዳ፣ በተለይ በሴት አርሶ አደሮች ላይ ከወሊድ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች እንደሚያመጣ የለየበት ሁኔታ ነበር።
ከጥናቱ ይሄን ከተገነዘበ በኋላም አርሶ አደሩ ነቀዝን በዘላቂነት መከላከል የሚችልበትን መፍትሄ ማመቻቸቱንም ተያያዘው። ፈጥኖም ‹‹ዋበህል›› የተሰኘና ከኬሚካል ነፃ የሆኑ ከረጢቶች በማምረት መላውን ወደ ተግባር ቀየረው። ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ጀምሮ ለሰፊው የሀገራችን አርሶ አደር እህሉን ከትቶ ከነቀዝ የሚከላከልበትን ‹‹ዋህበል›› የተሰኘና የተለያየ መጠን ያለው የነቀዝ መከላከያ ከረጢት አምርቶ በስፋት በማሰራጨት ማቅረብ ጀመረ። በዚህም አርሶ አደሩ እንደ በቆሎ፣ሽንብራና ሌሎች የጥራጥሬና የእህል ምርቶችን ከነቀዝ መታደግ ቻለ።
አቶ መሐመድ እንዳሉን የነቀዝ መከላከያ ቴክኖሎጂው ከረጢት ወደ ስርጭት የገባው በግብርና ምርምር ተቋም ተፈትሾ ትክክለኛነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው። ስርጭት በዩኤስ አይዲ ወይም በዩኤስ ኤድ ፊድ ዘፊውቸር በሚባል ዓለም አቀፍ ተቋም የተደገፈ ነው። እንደ ሀገር ካለው ሕዝብ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራው አርሶ አደር ቁጥሩ 87 በመቶ እንደመሆኑ ተደራሽነቱ ይህን ሁሉ አርሶ አደር ታሳቢ ያደረገ ነው። ሆኖም አሁን ላይ የቴክኖሎጂው ስርጭት ተደራሽ እየሆነ ያለው በነቀዝ ተባይ ተጋላጭ ከመሆናቸው አንፃር ቅድሚያ በተሰጣቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ነው። በዚሁ መሰረት አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የተለያየ አካባቢ ያሉ ቦታዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ይጠቀሳሉ። በአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞን ከኬሚካል ነፃ የሆነው የነቀዝ መከላከያ ከረጢት ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ በስፋት እየተከፋፈለ ይገኛል። በርካታ ለነቀዝ ተጋላጭ የሆኑ የእህል ዓይነቶች ቢኖሩም በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ባሉ ወረዳዎች በተለይም የሽንብራና በቆሎ ምርት በሚያመርቱ አካባቢዎች በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን አቶ አህመድ ነግረውናል። ‹‹ጥቅሙ የሀገርም የግልም የጋራ ዕድገት ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።
ቴክኖሎጂው የቀረበበት ዋና ዓላማ አርሶ አደሩ ከነቀዝ ነፃ የሆነ ጤናማ እህል እንዲኖረው ማስቻል እንደሆነም ኃላፊው ገልፀውልናል። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅትም ማዳበሪያ ጨምሮ ከኬሚካል ነፃ የሆኑ የነቀዝ መከላከያ የላስቲክ ከረጢቶችን በማስተዋወቅና በማቅረብ ላይ ይገኛል። ከረጢቱ እህልና ዘርን ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ ያከማቻል። በቀላሉ የሚንቀሳቀስና በቤት ውስጥም ሆነ በውጪ የሚቀመጥም ነው። እንዳይቀደድና እንዳይበሳ በመጠበቅ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና በተደጋጋሚ አገልግሎት ላይ ማዋል የሚያስችል ነው። ከዚህ አኳያም የነቀዝ መከላከያ ቴክኖሎጂውን በሂደት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ለማድረስም ሆነ ሌሎቹን በማምረት ለአርሶ አደሩ እያቀረባቸው ያሉ ቴክኖሎጂዎች በማሰራጨት መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለአርሶ አደሩ ብድር ከማመቻቸት ጀምሮ ድጋፍ በማድረግ አብረውት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለያየ ቦታ ያገኘናቸውና ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችም ይሄን የኃላፊውን ሀሳብ ይጋሩታል።
‹‹በነቀዝ ተጎጂ ከሆነው አርሶ አደር ብዛት የተነሳ ስርጭቱ ተደራሽ እንዲሆን የሌሎች ድጋፍ ያስፈልገዋል›› ያሉን በአዳማ ከተማ አባ ገዳ ገልማ አዳራሽ ይሄንኑ ቴክኖሎጂ ጨምሮ ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች በቀረቡበት አውደ ርዕይ ላይ ያገኘናቸው አርሶ አደር ቡልቱ በልሁ ናቸው።
አርሶ አደሩ ነቀዝ የበቆሎና ሽንብራ ምርታቸውን በተደጋጋሚ ስለሚያጠቃባቸው ሲቸገሩ መኖራቸውንም ይናገራሉ።ችግራቸው በነቀዝ ምክንያት ለዘር የሚሆን እህል ሁሉ እስከ ማጣት የዘለቀ እንደሆነም ገልፀውልናል። የዛሬ ዓመት ከኬሚካል ነፃ የሆነ የነቀዝ ከረጢት በመግዛት ተጠቃሚ ከሆኑ ጀምሮም ችግሩ የተቃለለላቸው መሆኑን ይገልጻሉ።
ሌላዋ በነቀዝ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ከነገሩን አርሶ አደሮች መካከል በኦሮሚያ ክልል አደአ ወረዳ ደንካካ ቀበሌ በአንድ ሰርቶ ማሳያ ተሞክሮ ላይ ያገኘናቸው አርሶ አደር ሌሊሴ ገለሶ ናቸው። አርሶ አደሯ ቀደም ባሉት ዓመታት የሚያስቀምጡት እህል እጅግ ለነቀዝ ተጋላጭ በመሆን የሚበላሽበት ጊዜ ብዙ ነበር። ለቀለብ ብለው የሚያስቀምጡት በቆሎ ሦስት ወር እንኳን ቢቀመጥ ጠዓሙ የታማ የታማ በማለት ይለወጣል። ዓመትና ሁለት ዓመት ማስቀመጥ ፈፅሞ አይችሉም ነበር። የነቀዝ መከላከያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከሆኑ በኋላ ግን በገዙት ከኬሚካል ነፃ የሆነ 100 ኪሎ የሚይዝ ከረጢት 100 ኩንታል በቆሎ ለሁለት ዓመታት ማስቀመጥ ችለዋል። ይሄን በቆሎ ለቀጣይ ሁለት ዓመታትም ከከረጢቱ ባለማውጣት ለማስቀመጥና በእርግጥም አምራቾቹ እንዳሉት ከረጢቱ እህልን ለአራት ዓመታት የመከላከል አቅም እንዳለው ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።
ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ሴት አርሶ አደር ዘቢደሩ ደምሌም ቴክኖሎጂው ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ነግረውናል። ከረጢቱን ተጠቃሚ በመሆናቸው አምና ለዘር ወቅት በከረጢቱ ቋጥረው ያስቀመጡትን የሽንብራ ዘር በመጠቀማቸው የዘር ችግር እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ። አቅም ፈጥረው አስር ኩንታል የሚይዘውን ከረጢት የመግዛትም ዕቅድ አላቸው።
አርሶ አደር ግዛው ስመኘው በበኩላቸው በሰጡን አስተያየት ከኬሚካል ነፃ የሆነው የነቀዝ መከላከያ ከረጢት በፊት ይጠቀሙት ከነበረው ኬሚካል በእጅጉ ተመራጭ ነው። ዋጋው ቀላል መሆኑም ብዙ አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙበት ያስችላል።በተለይ አርሶ አደሩ በኬሚካል ይከላከል በነበረበት ጊዜ በሴት አርሶ አደሮች ላይ የተለያየ የጤና እክሎችን ስለሚያስቀር እሳቸውን ጨምሮ በሁሉም አርሶ አደሩ ዘንድ ተፈላጊ ነው።
አርሶ አደሩ ኬሚካሉ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል ከሚል ስጋት መጠቀሙን ትቶ የነበረ መሆኑንም አልሸሸጉንም። በዚህ የተነሳ እህሉ በነቀዝ እየተበላ ይበላሽ ነበረ። ለቀለብ እንኳን የተቀመጠው ተበላሽቶ ለሌላ እህል ግዢ ይዳርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። የፕላስቲክ ከረጢቱ ቴክኖሎጂ ጠቀሜታን አስመልክተውም ‹‹ አርሶ አደሩ ለዘር የሚሆን እህል እንዲኖረው ያደርጋል። ያስቀመጠው በነቀዝ በመበላሸቱ ለዘር ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪም ያስቀራል›› ብለዋል።
‹‹አብዛኛው የአካባቢያችን አርሶ አደር መሬቱ በበሬ የሚታረስና የተበጣጠሰ በመሆኑ ባለ አንድ ኩንታል ከረጢት ነው የሚጠቀመው›› ይላሉ። ሆኖም በትራክተር የሚታረስ ሰፊ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች የጎተራ መጠን ያለውና ብዙ ኩንታል እህል መያዝ የሚችል ከረጢት ቢመረት ተጠቃሚውም አቅራቢውም ድርጅት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በመጠቆም አስተያየታቸውን ቋጭተውልናል።
በሁሉም ቦታ ያገኘናቸውና ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች እንደነገሩን ከረጢቱን ደጋግሞ መጠቀም ይቻላል።ይሁንና እስከ አሁን ባለው ሂደት ባይገጥማቸውም ላስቲክ በመሆኑ ሊቀደድ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አላቸው። በመቆሸሽና በመንገላታት ነቀዝን የመከላከል አቅሙ ይቀንሳል የሚል ጥርጣሬም ገብቷቸው ነበር ። ድርጅቱ ጥያቄያቸውን መሰረት አድርጎ ከኬሚካል ነፃ ከሆነ ላስቲክ ጋር ማዳበሪያም ያመረተበት ሁኔታ አለ።
እኛም ዋበህል የተሰኘውና ከፕላስቲክ የተሰራው የነቀዝ መከላከያ ቴክኖሎጂ አየር በማሳጣት ዘዴ ሻጋታና እርጥበት እንዳይኖረው በማድረግ ነቀዝን ሙሉ ለሙሉ የሚከላከል መሆኑን በማስገንዘብ ጽሑፋችንን አሳረግን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013