አበኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ልማት ታሪክ ባህር ዛፍ የሀገሪቱን የማገዶ ፍላጎት በማሟላትና ለቤት ግንባታ በመዋል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ እንደሆነ ይታወቃል። ባህርዛፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ አፄ ዳግማዊ ምኒልክ ባለውለታ እንደሆኑም አብሮ ይነሳል። የባህርዛፍ ችግኝ የተተከለበትን መሬት ግብር ምህረት በማድረግ ህዝቡን ለማበረታታት የተጠቀሙበት ዘዴም አይዘነጋም። ከእርሳቸው በኃላ የነበሩት የሀገር መሪዎችም የባህርዛፍ ተክልን በማስፋፋት ሚና ነበራቸው። በወቅቱ ሀገሪቱ ከነበረባት የማገዶ ችግር በመነሳት የባህርዛፍ ተክል መላ ሀገሪቱን እንዲሸፍን ቢደረግም ከመሬት ለምነት ጋር ተያይዞ ጉዳትም እንዳለው ይነገራል። ባህርዛፍ በተተከለበት ቦታ ሌሎች ተክሎች ወይንም ዕፅዋቶች የማደግ ዕድላቸው ዝቅተኛ እንደሆነ፣ በአካባቢው ያሉትን ምንጮች በማድረቅ፣ በአጠቃላይ በአካባቢ ሥነምህዳር ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የባህርዛፍ ችግኞች ከተተከለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አዲስ አበባ ከተማ ቀዳሚ ስትሆን፣ በእንጦጦ ላይ ተክሉ በስፋት መኖሩ ይጠቀሳል። የአካባቢ ሥነምህዳር እንዳይጠበቅ በማድረግ ተጽዕኖ ማድረሱም ሲነገር ቆይቷል። በተክሉ ምክንያት ተጎድቶ የተራቆተውን የእንጦጦ አካባቢ በመታደግ የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ተፈጥሯዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ማልማትና መንከባከብ ተግባሩ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ከመንግሥት ለአረንጓዴ ልማት በተረከበው ቦታ በባህር ዛፍ ተክል ተሞልቶ እንጦጦ አካባቢ በሀገር በቀል ችግኞች በመተካት ባከናወነው መልሶ የማልማት ሥራ ይዞታው እንዲቀየር በማድረግ የአካባቢው ሥነምህዳር እንዲቀየርና ለቦታው ተስማሚ የሆነ ንጹህ የአየር ፀባይ እንዲፈጠር ማድረግ ችሏል። ቀደም ሲል በአካባቢው ከባህርዛፍ ተክል ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሥጋት የነበረው የጎርፍና የአፈር መሸርሸር ስጋት ለመቅረፍ መቻሉን፣ በአካባቢው ደርቀው የነበሩ ምንጮች መጎልበታቸውን፣ ከአካባቢው ተሰደው የነበሩ እንደ ምኒልክ ዱክላ፣ አነርና የመሳሰሉ የዱር እንስሳት እንዲሁም ብርቅዬ አዕዋፋት ተመልሰው መኖር መጀመራቸውን ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ማህበሩ ባደረገው ጥረት አካባቢው ሥነምህዳሩ ተጠብቆ ፓርክ ሆኖ ለቱሪስት መስህብነት ስለበቃው የእንጦጦ ጥብቅ ደን የገለጹልን የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ሥራአስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ፤ማህበሩ በ1984 ዓ.ም ሀገር ወዳድ በሆኑና የትውልድን አደራ ለመቀበል ተነሳሽነቱ ባላቸው የተቋቋመ ሲሆን፣ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮም ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ፣ ቀጥታ ኃላፊነት ካላቸው ተቋማት ጋር በመሆን ቅርሶች እንዲያዙና እንዲመዘገቡ፣ለችግር የተጋለጡትንም ለመንግሥት በማመላከት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ኃላፊነቶቹ አንዱ ከመንግሥት በተረከበው አንድ ሺ ሶስት መቶ ሄክታር መሬት ላይ የአረንጓዴ ልማት፣ የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ ስራን መስራት ይመለከታል። የተረከበው ቦታ በባህርዛፍ ተክሎች ብቻ የተሸፈነ ነበር። ሆኖም ቦታውን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦችን በማስተባበር የነበረውን ባህር ዛፍ በማምከን ወይም በማስወገድ በምትኩ በሀገርበቀል የችግኝ ተክል እንዲሸፈን በማድረግ ነው ዛሬ የዕንጦጦ ፓርክ ለመባል የበቃው። ማህበሩ ለልማት ከተረከበው መሬት ወደ አምስት መቶ ሄክታር የሚሆነው በሀገር በቀል ተክል ሸፍኖ ደን ደረጃ ላይ ደርሷል። በ2012ዓ.ም በጀት አመትም ወደ 160 ሄክታር ሀገር በቀል ተክሎች የተተከሉ ሲሆን፣ በመጪው ክረምት ደግሞ ተጨማሪ በ50 ሄክታር መሬት ላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅቷል።
ማህበሩ የነሐስ፣የብርና የወርቅ ደረጃ በመስጠት ነው አጋሮቹን በማሳተፍ ችግኝ የመትከል፣ እንክብካቤና ጥበቃ ሥራውን በማከናወን ላይ የሚገኘው። ከልማት አጋሮቹም ሞሐ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣አዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ፣ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ጥቂቶቹ ናቸው። አጋሮቹ የሚያለሙበትን ቦታ በመውሰድ ችግኞችን ተክለው በመንከባከብ ነው ሚናቸውን የሚወጡት። በተጨማሪም ማህበሩ በአካባቢው ለሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግም ትብብርና ዕገዛ ያደርጋሉ። የአካባቢው ነዋሪና የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በልማቱ ይሳተፋሉ። ከልማቱም እንዲጠቀሙ ማህበሩ አስፈላጊውን ሁኔታ ያመቻቻል። የአካባቢው ማህበረሰብ እስካሁን ካገኛቸው ጥቅሞች አንዱ ከጎለበተው ምንጭ እና በአካባቢው በተፈጠረው ንፁህ የአየር ፀባይ ተጠቃሚ ከመሆኑ በተጨማሪ የጎርፍ ስጋቱም ቀንሶለታል።
የተለያዩ አካላት ዕገዛ የዕንጦጦ ፓርክ ለዚህ የበቃ ቢሆንም ማህበሩ በማስተባበር፣ዕቅድ በማውጣትና ለሥራው በጀት በመመደብ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በተለይ ደግሞ በቦርድ ጭምር የሚመራው በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው የማህበሩ አባላት በገንዘብ፣በቁሳቁስና በሀሳብ በመደገፍ ያላቸው ሚና የላቀ ነው። ማህበሩ ሲመሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ በብሪቲሽ ካውንስል ተቋም ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ማይክል ሰርጀንት የሚባሉ እንግሊዛዊ በእንግሊዝ ሀገር አባላትን በማሰባሰብና ቦርድም እንዲመሰረት በማድረግ ከማህበሩ ምሥረታ ጀምሮ እስካሁን ሳይለዩ በመሥራት ለማህበሩ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ባለውለታ ለመሆን የቻሉ ሰው መሆናቸውም የልማቱን ሥራ አጠናክሮታል።
ማህበሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ጥበቃ ከማድረግ ባለፈ ጥቅም እንዲሰጥ ማህበሩ ጥረት ያደርጋል። አካባቢው ላይ የባህርዛፍ ተክል በነበረበት ወቅት የሥነምህዳር ወይንም የብዝሃህይወት ስብጥር አልነበረም። ባህርዛፍ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባለፈ አካባቢያዊ ሥነምህዳር አገልግሎት አልነበረውም። በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ አልሆነም። ሥነምህዳሩ ከተመለሰ ወዲህ ግን በአካባቢው 13 ምንጮች ጎልብተዋል። ወደ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የእርከን ሥራም ተሰርቷል። በጎ ፈቃደኛ የአረንጓዴ ልማት ተሳታፊዎች በሚፈጽሙት ክፍያ የአካባቢው ማህበረሰብ ችግኝ ይተክላል። ይንከባከባል። ማህበሩም በጥበቃ ሥራ ለ40 ያህል ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በነዚህ ሁሉ ክንውኖች የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ነው። በአሁኑ ጊዜ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻነቱ እየጨመረ በመምጣቱ የአካባቢው ማህበረሰብ አረንጓዴ ልማቱን እየጠበቁ የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ ነገሮችን የማመቻቸት ሥራ መሰራት እንዳለበት በማህበሩ ግንዛቤ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል። ወደፊት በአካባቢው ለሩጫ ዝግጅት ልምምድ የሚያደርጉ አትሌቶች (ሯጮች) በአረንጓዴ ልማቱ እንዲሳተፉና እያንዳንዱም ሯጭ በራሱ እንዲሰይም በማድረግ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማህበሩ በሥፋት ለመንቀሳቀስ አቅዷል። ማህበሩ ከከተማ አስተዳደሩ ጋርም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ የበለጠ ለመንቀሳቀስ ይፈልጋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ባይከናወንም በየጊዜው በክረምት ችግኝ የመትከል ሥራ ይሰራል። ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ የማህበሩ ሚና እንዴት ይገለጻል? ለሚለው ጥያቄያችን አቶ መቆያ በሰጡት ምላሽ፤ ማህበሩ ልማቱን በተወሰነ አካባቢ እያከናወነ ቢሆንም የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ቀድሞ ነው የጀመረው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ ለማህበሩ እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። በአሁኑ ጊዜ ቀጥተኛ ድጋፍ በማድረግ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አባል ሳይሆኑ ከማህበሩ ጋር መሥራት የጀመሩት በዚህ አጋጣሚ ነው። ማህበሩ ለአረንጓዴ አሻራ በመጠኑም ቢሆን ችግኝ በመስጠት ቀደም ባሉት ጊዜያቶች ተሳትፏል።
ማህበሩ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል አቶ መቆያ ያነሱት ማህበሩ ከምሥረታው ጀምሮ ሲጠቀምበት የነበረው የችግኝ ጣቢያ በኦሮሚያ ክልል እንደተወሰደበትና ማህበሩም ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ጉዳዩ መፍትሄ እስኪያገኝም ሌላ ችግኝ ጣቢያ ለማቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ ነው ።
ጥብቅ ደኑ ለኢንደስትሪ ግብአት የሚሆን አቅርቦት እንዲኖረው እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ከፍ እንዲል በማድረግ ረገድም ማህበሩ ስላለው ዕቅድ አቶ መቆያ እንዳስረዱት፤ የማህበሩ ዋና ተግባር ወይንም ቅድሚያ የሰጠው ሥነምህዳሩን ሊጠብቅ የሚችል ችግኝ በመትከል አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ ነው። ዛፍ የሚቆረጥበት ዕድሜ ላይ ሲደርስ በባለሙያ በማስጠናት ወደ ኢኮኖሚ ጥቅም የሚቀየርበትና ተተኪ ችግኞች የሚተክሉበት ሁኔታ ወደፊት ይመቻቻል።
ማህበሩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ የደን ልማት ለመስራት ስላለው ዕቅድም አቶ መቆያ እንደገለጹት፤ በ2014ዓ.ም ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ድጋፍ በማድረግ ከክልሎች ጋር አብሮ ለመሥራት አቅዷል። ከዚህ ቀደም ለደሴ አካባቢ ችግኝ በመስጠት ትብብር አድርጓል። ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከቅርስ ጋር በተያያዘ አብሮ ይሰራል። ማህበሩ በአሁኑ ጊዜ በድርጅት 19፣ በግለሰብና በተለያየ መንገድ ደግሞ ወደ አራት መቶ አባላት አሉት።
ማህበሩ ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው በአካባቢ ጥበቃና በቅርስ ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ በመቀጠል በትውልድ ቅብብሎሽ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ከአዲስ አበባ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር እያከናወናቸው ሥላሉት ተግባራትና የሰራቸውን ሥራዎች የዓለም ቅርስ ቀንን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ በአረንጓዴ ልማት፣ በቅርስ ጥበቃና በቱሪዝም ኢንደስትሪው ውስጥ ለሚገኙ አካላት፣እንዲሁም ከተለያዩ ማህበራትና የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፃ አድርጓል። በዕንጦጦ ፓርክ ላይ ያከናወናቸውን የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችንም አስጎብኝቷል። ፓርኩን ከጎበኙት መካከልም ሥለፓርኩ መሥህብና በሀገር ደረጃ እየተከናወነ ሥላለው አረንጓዴ አሻራ ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
ሀሳባቸውን ካካፈሉን መካከልም የአንበሳ መድኃኒት ቤት ሥራ አስኪያጅና ፋርማሲስት ወይዘሮ ፋሲካ ከበደ አንዷ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት ማህበሩ አረንጓዴ ልማትን በማከናወንና ቅርስን በመጠበቅ በድርብ ኃላፊነት ሥራ አደራውን እየተወጣ መሆኑን በተግባር በሥፍራው ተገኝተው አረጋግጠዋል።
ማህበሩ ቦታውን ከማልማቱ በፊት የነበረውን ይዞታ ያውቁ ሥለነበር ባማረ ሁኔታ በባለሙያ የተደገፈ ሥራና ለውጥ ማየት በመቻላቸው ተደስተዋል። በትብብር ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ተገንዝበዋል። ትልቁ ተግባር ማስተባበር በመሆኑ በዚህ በኩል ማህበሩ ሚናውን በመወጣቱ ምሥጋና አቅርበዋል። ማህበሩ የተሰጠውን ኃላፊነት በዚህ መንገድ እንዲወጣም ተቋማቸው በአረንጓዴ ልማቱ አጋር በመሆን አሻራውን አሳርፏል። እርሳቸውም የዚሁ አሻራ አካል በመሆናቸው ደስተኛ ናቸው። አረንጓዴ ልማት ላይ አሻራን ማሳረፍ የሁሉም ድርሻ መሆን እንዳለበት በተግባር በማየታቸው ከዚህ በኃላ ወደ ኃላ እንደማይሉ ነው የገለጹት።
አረንጓዴ አሻራን ማኖር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ደን እንዲሆን የማድረግ ሃላፊነትን መወጣት መሆኑን ወይዘሮ ፋሲካ ያምናሉ። እርሳቸው በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የተከሉትን ችግኝ አንዴ ብቻ ሄደው እንዳዩና አሁን ሲጎበኙ ካልሆነ በስተቀር ተመላልሰው አለማየታቸውን ያስታውሳሉ። ምንም እንኳን በሥራ እና በተለያየ ምክንያት በጊዜ እጥረት ገንዘብ በመክፈል ሌሎች እንዲከባከቡ ቢያደርጉም ብቻውን በቂ ነው ብለው አያምኑም። ከዚህ በኃላ የተከሉት ችግኝ የት እንደደረሰ እንደሚከታተሉ ቃል ገብተዋል።
ወይዘሮ ፋሲካ በአረንጓዴ ሥፍራ መዝናናት ያስደስታቸዋል። እንጦጦና አካባቢው ደግሞ እንዲህ እንደእርሳቸው አረንጓዴ ቦታ ለሚያስደስተው ሰው ምቹ ነው ብለው ያምናሉ። ማህበሩ የሚያከናውንበት የአረንጓዴ ልማት ሥራና ባማረ ሁኔታ የተሰራው የእንጦጦ ፓርክ በአንድ አካባቢ መገኘታቸውና መስህብ መሆናቸው ለከተማው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን፣ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶችም ጥሩ የቱሪስት መዳረሻ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላው በእንጦጦ ፓርክ ተገኝተው የማህበሩን እንቅስቃሴ የጎበኙት አቶ አብይ አበበ፤ እንደ ወይዘሮ አዜብ ሁሉ ማህበሩ በሰራው ሥራ ተደስተዋል። ‹‹አዲስ አበባ ከተማ ስትቆረቆር ባህርዛፍን መሠረት ያደረገ ልማት ስለነበር ያንን በማስቀረት እንደ ኮሶ፣ዝግባ፣ ቀጋ ያሉ ሀገር በቀል ዛፎች ዝርያቸው እንዳይጠፋና ትውልድም ይህን ሀገራዊ ሀብት እንዲያስቀጥል መንገድ ስለሚፈጥር በማህበሩ የተሰራውን ሥራ አስደናቂ ነው›› በማለት ሀሳብ ሰጥተዋል። በየክረምቱ እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የማህበሩን እንቅስቃሴ ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለው ያምናሉ። በግላቸውም ተሳታፊ በመሆን ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ይናገራሉ ።
በማህበርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዱ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ሚናውን መወጣት ከቻለ የካርቦን ልቀትን መከላከል ይቻላል። እንደ ኢትዮጵያ ግብርናዋ በተፈጥሮ ዝናብ ላይ ለተመሠረተ ሀገር ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አረንጓዴ ልማትን ማጠናከር ግድ ይላል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013