ምርጫና ምርጫን ታሳቢ ተደርገው የሚከናወኑ ተግባራት በመርህ ደረጃ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ታሳቢና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሀገርን እንደ ሀገር፤ ሕዝብንም /ዜጎችን / እንደ ሕዝብ ተጠቃሚና አሸናፊ ለማድረግ የሚከናወን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው።
ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ መሪዎችን ወደ ሥልጣን የማምጣት ሥርዓት ነው ። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ዋነኛው ተዋናይ ሕዝብ ነው ። ሕዝብ ዛሬዎቹን ጨምሮ ነገዎቹ የተሻሉ እንዲሆኑ ካለው መሻት /ሰብዓዊ ፍላጎት /አንጻር ይህንን ፍላጎቱን በተበጀ ሥርዓት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሄድበት አግባብም ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ የተነሳም የአንድ ሀገር ሕዝብ ወደ ምርጫ ሲሄድ እነዚህን እውነታዎች በአግባቡ መረዳት ፤ ከዚሁ መረዳት በሚመነጭ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ምርጫና የምርጫ ጉዳዩ ሲታሰብ እውነታው ከግለሰቦችና ከቡድኖች ፍላጎት ከፍ ያለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።
በተለይም ከአምባገነናዊ አገዛዞች ውስጥ የኖረ ሕዝብ ከአምባገነኖች ያተረፈው ነገር ምን እንደሆነ በተጨባጭ በሕይወት ልምምዶቹ የሚያውቀው ስለሆነ በምርጫ ጉዳይ ላይ በመረዳት/በእውቀት/ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል ። ምርጫን አስመልክቶ የሚጓዙት እያንዳንዷ እርምጃ ከትናንት ሕይወቱ የምትዋጀው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
ከዛም በላይ የእያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ እንደሕዝብና እንደሀገር ፤ ሀገርና ሕዝብን የሚያሻግር አቅምና ባህል መፍጠር የሚችል ስለመሆኑ እርግጠኝ መሆን ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ማህበራዊና ትውልዳዊ ኃላፊነት ነው። ነገ ስለምትኖረው ሀገር እና ነገን ስለሚረከበው ትውልድ ባላደራ የመሆን እውነታን ማሳያም ጭምር ነው።
በምርጫ ሀገር አሸነፈች የሚባለውም ይህንን አስተሳሰብ መሰረት ባደረገ መንገድ ምርጫ ማካሄድ ሲቻል ነው። ከዚህ ውጪ ምርጫን እንደ ተራ የሕዝብ ፍላጎት መግለጫ አድርጎና አቅሎ ማየት በሀገር ነገዎችና በመጪው ትውልድ ላይ የጭካኔ ውሳኔ የመወሰን ያህል ነው። የተፈጠሩ ዕድሎችን በተሳሳተ የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ሆኖ ማምከንም ከፍ ያለ የታሪክ ተጠያቂነት ሊያመጣ የሚችል ነው ።
በምርጫ ሀገር አሸነፈች የሚባለው ምርጫው ሀገር ከመጣችበት አስከፊ መንገድ ሲዋጃት ብቻ ነው። ቀጣይ ሀገራዊ የችግር ትብታቦችን ፤ ትብታቦች የፈጠሩትን ጠባሳና ግርዶሽ ገፎ መሄድ የሚያስችል ዘላቂ መንገድ መፍጠር ሲያስችል ነው ።ይህን ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥት ይልቅ የሕዝብ ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው። ስለሆነም ምርጫ በሰከነ መንፈስ ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል።
በሀገራችን ከምርጫ ጋር የነበረው እውነታ ከዚህ ጋር የሚጣጣም አይደለም ። ቀደም ባሉት ጊዜያት በሥልጣን ላይ የነበሩ ቡድኖች ከተላበሱት የአምባገነንነት ባህሪ አንጻር እውነታውን ማሰብም በብዙ መልኩ የሚከብድ እንደነበር ለመናገር አስቸጋሪ አይደለም ። ሁሉም በሚባል ደረጃ የይስሙላ ናቸው።
በሀገራችን ምርጫዎች የተካሄዱት የቡድኖችን ሕዝብ የመግዛት ፍላጎት ሕጋዊ መሰረት ለማስያዝ ነበር። ከዚህ ያለፈ ዓላማ ስላልነበራቸው ሕዝባችንን ከመጣበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መዋጀት ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዛ ይልቅ ለሕዝባችን ተጨማሪ ችግሮች መፍጠሪያና የስቃይ ምንጭ ሆነውም ነበር። ከዚህ የተነሳም ሕዝባችን ምርጫን ሲያስብ ችግርን በዋነኛነት እንዲያስብ ተደርጓል።
ትናንት ትናንት ነው ፤ ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ነው ፤ ነገ ደግሞ በራሱ የራሱ ቀን ነው። ማህበረሰብም በነዚህ በሚንሰላሰሉ ቀናቶች ህያው በሆነ መስተጋብር ውስጥ ይኖራል። መማር ከፈለገና ለዚህ የሚሆን ስክነት ካለው ከትናንቶች ይማራል፤ በዚህም የዛሬ ስህተቶችን ይቀንሳል ፣ ቢያንስ የትናንት ጥፋቶቹን አይደግምም። እንደ ማህበረሰብ ስለ ነገዎቹ ሲያስብም ከትናንት ተምሮ ከዛሬ ማንነቱ ላይ ስለሚነሳ ነገዎቹ የትናንት ጥፋቶች ሰለባ አይሆኑም።
እኛም እንደ ሀገርና ሕዝብ በአንድ አሻጋሪ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ። የታሪክ ምዕራፉ በእጃችን ነው፣ መሻገር ሆነ አለመሻገር ግን በፊታችን ያለ ምርጫ ነው ። ከመጣንባቸው ብዙ ትናንቶች ተምረን ሰክነን ይህንን ምእራፍ በርግጥም የመሻገሪያ ምእራፍ ልናደርገው እንችላለን።
ይህንን ታሪካዊ ምዕራፍ የመሻገሪያ ምዕራፍ ለማድረግ ስለ ምርጫ ያለንን የተሳሳተና የተዛባ አመለካከት በአግባቡ ልናስተካክለው ይገባል። የምርጫ ጉዳይ በዲስኩር ውበት ግለሰብን ሆነ ቡድንን ከመምረጥ ያለፈ ትልቅ ትርጉምና ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው ልንረዳም ይገባል።
ስሜት ቀስቃሽ ችግር ተንታኝ ዲስኩሮች የቱንም ያህል ተሰካክተውና አምረው ልብ አማላይ ቢሆኑ፣ በራሳቸው ሕዝባችንን ከመጣበትና ካለበት ችግር የሚዋጁት አይሆኑም። በዚህ ስሌት የሚመዘኑ ምርጫዎችም የቱን ያህል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ናቸው ሊባልላቸው ቢችልም ሕዝባችንን ሊያሻግሩት ቀርቶ አንድ እርምጃ አንኳ ሊያራምዱት አይችሉም ።
መጪው ምርጫ ትርጉም ያለው ፤ ከመጣንበትና ካለንበት ችግር የሚዋጀን ሊሆን ይገባል። በትውልዶች መካከል ብዙ ዋጋ የከፈልንበት፤ ከሀገርና ሕዝብ ከፍታና ልዕልና ጋር የተሳሰረ፤ የምርጫ ካርድ አውጥቶ ከመምረጥ ያለፈ ስክነትና ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013