
አዲስ አበባ፡- የሉባን ስልጠና ማዕከል መገንባት ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት የሰለጠነ የሰው ኃይል ክህሎትና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች መካከል ያለውን የክህሎት ክፍተት እንደሚሞላ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ገለጹ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተገነባው የሉባን ስልጠና ማዕከል ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ እ.ኤ.አ በ2018 በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ጉባኤ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሺ ጂ ፒንግ የሙያና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በአፍሪካ ውስጥ አስር የሉባን ስልጠና ማዕከላትን እንደሚከፈቱ ገልጸው ነበር፡፡የእነዚህ ማዕከላት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት መከፈት በኢንዱስትሪዎች የሰው ኃይል ክህሎት ፍላጎትና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመሙላት እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
ቻይና የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ የንግድ አጋር መሆኗን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፤ በመሰረተ ልማት፤ በቴሌኮሙዩኒኬሽን፤ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችንም በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈች ነው ብለዋል፡፡«የብልጽግና ጉዟችን ያለ ብዙ ድካም ሊሳካ እንደማይችል እንረዳለን፣ ለዚህም ቻይና ረሃብንና ኋላቀርነትን ድል ለማድረግ የሄደችበት መንገድ ትልቅ ትምህርት የምንወስድበት ነው» ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተከፈተው የሉባን ስልጠና ማዕከል ለነዚህ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎችም አቅማቸውን ለመገንባትና የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚረዳ የጥናትና ምርምር ማዕከል እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገራት በተለያዩ መስኮች ከፍ ያለ አጋርነት ቢኖራቸውም በትምህርትና ስልጠና መስክ ያላቸው ትብብር አመርቂ ነው፡፡ዛሬ ላይ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ ያሉ የሥራ መስኮች የቴክኖሎጂ እገዛ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው፤ የሉባን ስልጠና ማዕከል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መገንባት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሮቦቲክስና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ጥሩ አቅም እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ምሩቃኖቻችንም 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተገነባው ሉባን የስልጠና ማዕከል በ830 ስኩየር ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ 96 ሰዎችን ለማስተማር፣ ለማሰልጠንና የአቅም መለኪያ ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013