ከኢትዮጵያ ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪዎች መካከል አንዱ የሆነውንና ከእነዚህ መሣሪዎች መካከልም ‹‹ከባዱና ጥንቃቄን የሚጠይቀው ነው›› የተባለለትን ዋሽንት በመጫወት ወደር ያልተገኘላቸው አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ነበሩ:: ዋሽንት መጫወት የለመዱት የአራት ዓመት ሕፃን ሳሉ እንደነበር ራሳቸው ተናግረዋል::
የ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ልብ ወለድን ትረካ ተወዳጅ እንዲሆን ያስቻለውና ትረካው የታጀበበት የዋሽንት ድምፅም የእርሳቸው የትንፋሽ ውጤት ነው:: መቼም የልብ ወለዱን ትረካ የሰማ ሁሉ ያን ልብ አስኮብላይ ዋሽንት ሊረሳ አይችልም:: ለብዙዎች፣ መጽሐፉን ከማንበብ ይልቅ ትረካውን መስማት የሚያስደስታቸውም ለዚህ ነው::
በ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› እና በሌሎች የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያስተዋወቁ ድንቅ የጥበብ ፈርጥ ነበሩ:: የበርካታ አንጋፋ ድምፃውያንን የሙዚቃ ሥራዎች በዋሽንት ያጀቡና ሥራዎቹም በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆኑ ያደረጉ አንጋፋ ከያኒም ነበሩ::
ዋሽንት ታዋቂና ተወዳጅ እንዲሆን በብርቱ የጣሩ፤ ከዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ ጋር እንዲዋሃድ ያደረጉ፤ ለባሕላዊ ሙዚቃ ታላቅ ውለታ የዋሉ የድንቅ ትንፋሽ ባለቤት … እኝህ አንጋፋ የጥበብ ሰው የዋሽንቱ ንጉሥ አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ ናቸው::
ዮሐንስ የተወለደው በ1939 ዓ.ም በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት አገው ምድር አውራጃ፣ ባንጃ በተባለ ስፍራ ነው:: አባቱ መምሬ አፈወርቅ ጀምበሬ ቄስ ስለነበሩ ልጃቸውም የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆን ይፈልጉ ነበር:: ስለሆነም ልጃቸው ዮሐንስ በመንፈሳዊ ትምህርቱ እንዲበረታ እንጂ ዋሽንት እንዲጫወት ስለማይፈልጉ ዋሽንቱን ሰባብረው እሳት ውስጥ ይከቱበት ነበር::
የታዳጊው ዮሐንስ ልብ ግን አስደማሚ ድምጽ ከምታወጣው ሸምበቆ እንጂ ከአባቱ ምኞት ጋር አልነበረም:: እንዲያውም በተወለደበት አካባቢ ተወስኖ አባቱ የተመኙትን የቄስ ትምህርት ከመማር ይልቅ ወደ አካባቢው ከተሞች እየሄደ መዋል ጀመረ:: ወደ ፋግታ እና አዲስ ቅዳም ከተሞች ድረስ ብቅ እያለ የከተሜን ሕይወት ተመለከተ:: የአካባቢው ሕዝብም ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ይመክረው ነበር:: በ17 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ መጣ:: አዲስ አበባ እንደደረሰም ወደ አዲስ አበባ የሄደበት አውቶቡስ ባለቤት የነበሩት አቶ ንዋይ ወልደማርያም ከእርሳቸው ጋር እንዲኖር ወደቤታቸው ይዘውት ሄዱ::
‹‹ባላገሩ›› የሚለው የአዲስ አበባ ልጆች ሽሙጥና ጉንተላ ግን ዮሐንስን ምቾት አልሰጠውም:: የሰፈሩ ልጆች ስድብና ሹፈት ከትዕግሥቱ በላይ የሆነበት ዮሐንስ፣ አገር ቤት ሳለ በሚያውቀው ትግል አዲስ አበቤ ጓደኞቹን እያነሳ ያፈርጣቸው ጀመር:: የጎረቤቱ ሁሉ አቤቱታ የጠነከረባቸው አቶ ንዋይም ዮሐንስን አዲስ ልብስ አልብሰው ወደ አዲስ አበባ በመጣበት አውቶቡስ ወደ አዲስ ቅዳም መለሱት::
ዮሐንስ በአዲስ ልብሱ ሆኖ አዲስ አበባ ደርሶ መመለሱን ለአካባቢ ሰዎች እየተናገረ ከሰነበተ በኋላ በድጋሜ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ:: ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው በመንገዱ ላይ በነበሩ ከተሞች ወደሚገኙ ጠላና ጠጅ ቤቶች ጎራ እያለ፣ እየዘፈነና ሰውን እያዝናና ነበር::
አሁን አዲስ አበባ ዮሐንስን የተቀበለችው እንደመጀመሪያው አይደለም፤ ዮሐንስም ቢሆን በዚህ በሁለተኛው ጉዞው አዲስ አበባ የደረሰው ባዶ እጁን ሳይሆን አገር ቤት ሳለ ሲጫወትባት ያደገውን ዋሽንቱን ይዞ ነበር:: ቀደም ሲል ይጣሉት የነበሩት ጓደኞቹ ጭምር ዮሐንስ ዋሽንት ሲጫወት ዙሪያውን ከብበውት መመልከት ጀመሩ:: ፀባቸው የልጆች ፀብ ነበርና ልጆቹ በዮሐንስ የዋሽንት ጨዋታ ስለተማረኩ ዮሐንስን መውደድና ማክበር እንዲሁም ሻይና ሳምቡሳ ይጋብዙት ጀመር:: ከጓደኞቹ ጋር አብሮ መጫወት የዘወትር ተግባሩ ሆነ:: ከዕለታት አንድ ቀን ዮሐንስ እንደለመደው ከጓደኞቹ ጋር ሊጫወት በወጣበት አንድ ሰው አግኝተውት ወደ ትልቅ ጠጅ ቤት ይዘውት ሄዱ:: እዚያም ጠጅ ለሚጠጣው ሰው ዋሽንት ተጫውቶ ብዙ ገንዘብ አገኘ::
አንድ ቀን አንድ ወዳጁ መርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ይዞት ሄደ:: እዚያም ከበሮ እየመታ አልፎ ሂያጁን የሚያዝናናና ሰው ሁሉ ቆም ብሎ እየተመለከተ ሳንቲም የሚሰጠው አንድ ሰው ተመለከተ:: ዮሐንስም ከባለ ከበሮው ጂግሶ በዳሶ ጎን ቁጭ ብሎ ዋሽንት መጫወት ጀመረ:: ጂግሶ ከበሮውን፣ ዮሐንስም ዋሽንቱን ይዘው እየተጫወቱ፣ ሙያቸውን እያሳደጉና ሳንቲም እያገኙ ሕይወታቸውን ቀጠሉ:: ዮሐንስ ጠጅ ቤት ውስጥ ዋሽንት ሲጫወት ያገኙት አንድ የፖሊስ መኮንን ወደ ኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም አስገብተውት ነበር:: ዮሐንስ ግን ብዙም ሳይቆይ ከማሰልጠኛው ወጣ::
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ እንደገና ወደ ዋሽንቱ ተመለሰ:: በድጋሜ ከባለ ከበሮው ወዳጁ ጂግሶ በዳሶ ጋር በመሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከበሮና ዋሽንት ተጫወቱ:: ከቡና ቤት እስከ ሰርግ ቤት፤ ከጠጅ ቤት እስከ መኖሪያ ቤት ድረስ እየዞሩ ድግሱንና መዝናኛውን ሁሉ በከበሮና በዋሽንት አደመቁት:: በሽልማትም ብዙ ገንዘብ አገኙ::
በመቀጠልም ዮሐንስ በ1965 ዓ.ም ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ››ን ተቀላቀለ:: ትዳር የመሰረተውም በዚህ ወቅት ነበር:: ወቅቱ ደራሲ ተስፋዬ ለማ ባዘጋጀውና ‹‹እኛም አለን ሙዚቃ፣ ስሜት የሚያነቃ›› በተሰኘው ሙዚቃ አማካኝነት የባሕል የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚተዋወቁበት ወቅት ስለነበርና ሙዚቃውም ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በስፋት ማስተዋወቅ ስለቻለ የዮሐንስና የሌሎች ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ተፈላጊነት እየጨመረ መጣ::
ዝነኛው የመሰንቆ ተጫዋች ጌታመሳይ አበበ መሰንቆ አጨዋወት ያስተማረው አሜሪካዊው የሰላም ጓድ (Peace Corps) አባል ቻርልስ ሳተን አሜሪካ ከሚገኙ ወዳጆቹ ጋር በመተባበር ለ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ›› የውጭ ጉዞ ዕድል አመቻቸ:: የኦርኬስትራው አባል ዮሐንስ አፈወርቅም ወደ አሜሪካ ተጓዘ:: የኦርኬስትራው አባላት የኢትዮጵያን ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችና አጨዋታቸውን አስተዋውቀው መልካም ስም ይዘው ተመለሱ:: ከአሜሪካ መልስ በሀገር ፍቅር ትያትር ተቀጥሮ አገልግሏል:: በኋላ ግን ወደ ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ›› ተመልሶ በኦርኬስትራው መጫወት ቀጠለ::
በአብዮቱ ምክንያት፣ በ1968 ዓ.ም፣ ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ›› በመንግሥት ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ጋር እንዲቀላቀል በመደረጉ ዮሐንስም በማዘጋጃ ቤት ሥራውን ቀጠለ:: የ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› የሙዚቃ ቡድን አባል ሆኖ በተለያዩ አገራት በመዞር ዋሽንት ተጫውቷል፤ ዋሽንትን አስተዋውቋል:: በውጭ አገራትም ወደ ኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ሶቭየት ኅብረት፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ኩባ፣ ፖላንድ፣ ግሪክ፣ ሆላንድ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ኢጣሊያ፣ ጃፓንና ሌሎች በርካታ አገራት ተጉዞ ዋሽንት ተጫውቷል::
የ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ›› የሙዚቃ ቡድን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በተሳታፊ ከያኒያን፣ ቡድኑ በሸፈናቸው አካባቢዎች፣ በሙዚቃ መሣሪያዎችና አልባሳት እንዲሁም በቀረቡ የሙዚቃ ሥራዎች ብዛት ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛል:: ባለዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅም የዚህ ታሪካዊ ሁነት ተሳታፊና አድማቂ ነበር:: ዝግጅቱ የቡድኑን ሥራዎች የታደሙትን ሁሉ እጅግ ያስደመመ ነበር::
አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ የሙዚቃ ባለሙያዎችን የያዘ የሙዚቃ ቡድን ሲያቋቁም ጌታመሳይ አበበን በመሰንቆ፣ ኤልያስ አረጋን በክራር፣ ኮቱ ሁጁሉን በቤዝ ጊታር፣ ተካ ጉልማን በከበሮ እንዲሁም ዮሐንስ አፈወርቅን በከበሮ ተጫዋችነት ይዞ ነበር:: በዚህ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ዋሽንትን ተጫውቷል፤ አስተዋውቋል:: በወቅቱ ሌሎቹ ተጫዋቾች ሁለት ሁለት ሆነው በየተራ እንዲጫወቱ ሲደረግ የዋሽንቱ ንጉሥ ዮሐንስ ግን ከአንድ ሰዓት በላይ ለማይቋረጠው የሙዚቃ ዝግጅት ብቻውን ሆኖ አገልግሏል::
ባለዋሽንቱ አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ ከሚታወቁባቸው ሥራዎቻቸው መካከል አንዱ የዝነኛውና ተወዳጁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ልብ ወለድ ትረካ ማጀቢያ (የዋሽንት ድምጽ) ነው:: ይህ ማጀቢያ በደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ የተፃፈውና በአርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ የተተረከው ዘመን ተሻጋሪው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ልብ ወለድ ለበርካታ ዓመታት እንዲታወስ ካደረጉት ምስጢሮች መካከል አንዱ እንደሆነ የመጽሐፉን ትረካ ያዳመጡ ሁሉ ይመስክራሉ:: ከዋሽንቱ የሚወጣው ልብ ሰርሳሪ ድምፅ የ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››ን ክንውኖች በትውስታ የሚያወሳ፤ ትረካውም ነፍስ እንዲዘራ አድርጎታል:: የሀዲስ ብዕር/አዕምሮ፣ የወጋየሁ ድምጽ እና የዮሐንስ ትንፋሽ ተዋህደው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ዘመን ተሻጋሪ እውቅናና ተወዳጅነት እንዲያገኝ አስችለውታል:: የዮሐንስ ዋሽንት የልብ ወለዱ ትረካ በብዙኃን ልብ ውስጥ እንዲቀር አድርጓል:: ለበዛብህ እና ለሰብለስ ቢሆን ከዮሐንስ ዋሽንት የበለጠ ያዘነላቸው ማን ነው? በአጠቃላይ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ካለዮሐንስ ዋሽንት ይህን ያህል ተወዳጅ ይሆን ነበር ብሎ ማሰብ ድፍረት እንደሆነ በልበ ሙሉነት ለማናገር የሚያደናቅፍ ነገር የለም:: እንዲያውም ‹‹… ‹ፍቅር እስከ መቃብር … ደራሲ – ሀዲስ ዓለማየሁ … ተራኪ – ወጋየሁ ንጋቱ …› ከሚለው አስደማሚ ድምፅ ቀጥሎ ‹ዋሽንት – ዮሐንስ አፈወርቅ› ተብሎ ቢጨመርበት ጥሩ ነበር›› የሚሉ ቁጥራቸው ብዙ ነው::
የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቅኝቶች በረቀቀ ሁኔታ ያስደመጡት አንጋፋው ባለሙያ፤ የበርካታ አንጋፋ ድምፃውያንን ሥራዎችን በዋሽንት በማጀብ የሙዚቃዎቹ ተወዳጅነት ከፍ እንዲል አድርገዋል:: ሥራዎቻቸው በአርቲስት ዮሐንስ ዋሽንት ታጅበው ለሕዝብ ካደረሱ ድምፃውያን መካከል ጥላሁን ገሰሰ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ኂሩት በቀለ፣ ታምራት ሞላ፣ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ ተፈራ ካሳ፣ ታደሰ ዓለሙ፣ ለማ ገብረ ሕይወት፣ ሙላቱ አስታጥቄና ፀሐዬ ዮሐንስ ይጠቀሳሉ::
አርቲስት ዮሐንስ ከአንድ ሰዓት በላይ በሚቆዩ የሙዚቃ ድግሶች ላይ ሳያቋርጡ ብቻቸውን በዋሽንት የማጀብ ችሎታ ነበራቸው:: በመስኩ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች እንደሚናገሩት፣ አርቲስት ዮሐንስ ዋሽንቱን መጫወት ብቻ ሳይሆን ዓይንና ቀልብ ከሚስብ እንቅስቃሴ ጋር አዋህደው ስለሚያቀርቡት የእርሳቸውን አጨዋወት ከሌሎች ልዩ ያደርገዋል::
ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑት የዮሐንስ የዋሽንት ሥራዎች የተቀረፁት ከአብዮቱ በፊት ሲሆን፣ በሀገር ፍቅር ትያትር ሳሉ የሰሯቸው በርካታ ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የድምፅ ክምችት ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል:: የተለያዩ ድምፆችን የሚወጡና የተለያየ መጠን ያላቸው ሰባት ዋሽንቶች ነበሯቸው::
በ1995 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ትያትርና ባሕል አዳራሽ በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ ከወጣት ሙዚቀኞች ጋር በጥምረት ሰርተዋል:: ለአብነት ያህል በተወዛዋዥ መላኩ በላይ በተመሰረተውና ወጣትና አንጋፋ ሙዚቀኞችን በጋራ መድረክ ላይ በማቅረብ በሚታወቀው ‹‹ኢትዮ ከለር›› የባሕል ሙዚቃ ቡድን ውስጥ አርቲስት ዮሐንስ ከወጣት ባለሙያዎች ጋር ሆነው የተካኑበትን ዋሽንት አሽሞንሙነውታል::
አዝማሪዎችና ዋሽንት ተጫዋቾች ሙያቸው ትልቅ መሆኑን በዮሐንስ ስኬት ውስት ማየት ችለዋል:: እረኞችን ‹‹ዋሽንትም እንደዚህ ትልቅ እውቅናና አክብሮት ያስገኛል እንዴ?›› ብለው እንዲጠይቁና እንዲገነዘቡ አድርገዋል:: በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ለዋሽንት ፍቅር እንዲያድርባቸውና ዋሽንት አጨዋወትን ለመልመድ እንዲነሳሱም ያደረጉ የባሕል ሙዚቃ ታላቅ ባለውለታ ናቸው::
አንጋፋው አርቲስት የክብር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ስለዋሽንቱ ንጉሥ ሲመሰክሩ ‹‹… ዋሽንት ከኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከባዱ ነው:: ትንፋሽ ይፈልጋል። አለስልሶ ለመጫወትም ብቃት ይጠይቃል። ዮሐንስ በዚህ በኩል አንቱ የተባለ ነው፤ ምትክ የለውም… ዮሐንስን የሚያህል የሙዚቃ ጠበብት ጡረታ መውጣት የለበትም ነበር … አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሳይሆን ሳያልፉ በፊት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መመስገን አለባቸው›› ብለው ነበር።
አገር በቀል የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ የሆነውን ዋሽንትን በመጫወት የሚስተካከላቸው እንደሌለ የሚነገርላቸው አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ ለዋሉት ትልቅ ውለታ ግን እዚህ ግባ የሚባል ነገር አልተደረገላቸውም። የአሁኑ ትውልድ እርሳቸውንና ሥራዎቻቸውን እንዲያውቀው የተደረገበት መንገድም እጅግ አናሳ መሆኑን ብዙዎች በቁጭት ይናገሩታል::
ያለመሰልቸት ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ዋሽንትን በአስደማሚ ብቃት የተጫወቱት አንጋፋው አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ፤ ትዳር መስርተው አምስት ልጆችን አፍርተዋል:: የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013