
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከስምንት ዓመታት በኋላ ካሜሩን በምታዘጋጀው የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን ማረጋገጡን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ሽልማቶች እየተበረከቱለት ይገኛል:: ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የመጨረሻ የማጣሪያ ውድድራቸውን ከወር በፊት የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድንን ገጥመው በተመለሱ ማግስት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ አምስት ሚሊየን ብር መሸለማቸው ይታወቃል:: ከዚያ በኋላ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያበረክተው ሽልማት ተጠባቂ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ላለፉት ሳምንታት ዝምታን መርጦ ቆይቷል::
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ ግን የዋልያዎቹን ሽልማት በተመለከተ ዝምታውን የሰበረ ውሳኔ እንዳስተላለፈ አሳውቋል:: በዚህም እኤአ ከ2013 በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊነታቸውን ያረጋገጡት የዋልያዎቹ አባላት የስድስት ሚሊየን ብር ሽልማት እንዲሰጣቸው መወሰኑ ተረጋግጧል:: ሽልማቱም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድሩን በሚያደርግበት ሐዋሳ ከተማ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ለዋልዎቹ የአምስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ሲያበረክቱ ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፋቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱት የቀድሞው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ ሳይካተቱ መቅረታቸው በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱ ይታወሳል:: ፌዴሬሽኑ አሁን ባዘጋጀው ሽልማትም አሰልጣኝ አብረሃም መካተት አለመካተታቸው የተገለፀ ነገር የለም::
ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ በምድብ አስራ አንድ ከኮትዲቯር፣ኒጄርና ማዳጋስካር ጋር ተደልድለው በሰበሰቡት ዘጠኝ ነጥብ ከምድባቸው ሁለተኛ ሆነው እንዳለፉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዘጠኙ ነጥቦች ሦስቱን ማግኘት የቻሉት በቀድሞው አሰልጣኝ አብረሃም እየተመሩ ኮትዲቯርን ባህርዳር ስቴድየም ላይ ሁለት ለአንድ በመርታት ነበር:: ይህም ከኮትዲቯር ጥንካሬ አኳያ በአሰልጣኝ አብረሃም የተገኘው ሦስት ነጥብ ዋጋው ትልቅ በመሆኑ አሰልጣኙ የዋልያዎቹ ስኬትና ሽልማት ተቋዳሽ መሆን እንደሚገባቸው ብዙዎች የተስማሙበት ሃሳብ ሆኗል::
ፌዴሬሽኑ ለዋልያዎቹ የስድስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ለመስጠት በወሰነበት ስብሰባ ሌሎች ውሳኔዎችንም እንዳሳለፈ ተጠቁሟል:: ከ17ዓመት በታች ውድድር ላይ ለሚሰሩት ለክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ስራ ድጋፍ የሚሆን የሦስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ ብር ድጋፍ ለማድረግ ተወስኗል:: በዚህም መሰረት እያንዳንዱ የክልል እና የከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እያንዳዳቸው የሦስት መቶ ሺ ብር ድጋፍ እንዲሰጣቸው እና ስራቸው በአግባቡ ስለመሰራቱ እያንዳንዱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክትትል እንዲያደርግ መወሰኑ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013