ህጻናት በተለያዩ ምክንያቶች ቤተሰባቸውን ሲያጡና በቅርብ የሚንከባከባቸው ዘመድ ከሌለ የህጻናቱ እጣ ፈንታ የሚሆነው አንድም በጉደፈቻ ባህር አቋርጠው መሄድ አልያም በሀገር ውስጥ ለጎዳና ህይወት መዳረግ ነው። ከአመታት በፊት ደግሞ አለም አቀፉ የጉድፈቻ እንቀስቃሴ በድሬዳዋ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። ይህንን በመገንዘብ ነበር የከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ህጻናት ቢያንስ ህጻናት የራሳቸው በሆነው ማህበረሰብ ውስጥ እንዲያድጉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የድሬዳዋ ህጻናት ማቆያና ማገገሚያ ማዕከልን አቋቁሞ ወደ ስራ የገባው። በዚህ አይነት በ2005 አ.ም አገልግሎቱን መስጠት የጀመረው ማዕከሉ በተለያዩ ምክንያቶች ጠባቂ ቤተሰብ የሌላቸውን በማሰባሰብና ለዚሁ ሲባል በተከራየው ቤት ወስጥ በማቆየት እዚሁ ሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ ህጻናቱን ወስደው እንዲያሳድጉ እያደረገ ይገኛል።
«በድሬዳዋ ከተማ ወላጅ አልባ ህጻናት በርካታ ችግሮች ይደርሱባቸው ነበር። በአንድ ወቅት ተጥለው የነበሩ ህጻናት ፖሊስ ሳይደርስላቸው በጅብ ለመበላት የበቁም ነበሩ። ለውጪ ጉድፈቻ የሚሰጡትም ቢሆን በርካታ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል» የሚሉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ የህጻናት ዳይሬክቶሬት የህጻናት መብት ማስረጽና ተሳትፎ ባለሙያ ወይዘሮ አበራሽ ቦጋለ የማዕከሉን ምስረታና ጉዞ እንደሚከተለው አጫውተውናል። ከአስር አመት በፊት በግለሰብ ደረጃ የተቋቋሙት ግብረ ሰናይ ድርጅቶችቸ በሙሉ ዋናው ትኩረታቸው አድርገው ሲሰሩ የነበረው ህጻናትን በጉዲፈቻ ወደውጪ መላክ ላይ ነበር። ይህ ደግሞ ህጻነቱ በግዚያዊነት ጥሩ ህይወት እንዲያገኙ የሚያስችል ቢሆንም ሲያድጉ ለከፍተኛ የስነ ልቦና ችግር የሚዳርጋቸው ነው። አሁን ግን ማዕከሉ ቀስ በቀስ በሀገር ውስጥ የጉዲፈቻና የአደራ ቤተሰብ በማሰባሰብ ማገናኘት ላይ በስፋት ሲሰራ በመቆየቱ የነበሩት በሙሉ ስራቸውን እያቆሙ ለመውጣት በቅተዋል።
የህጻናት ማቆያና ማገገሚያ ማዕከሉ የሚመራው በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በወጣው መመሪያና ደንብ መሰረት ነው። ይህንንም መነሻ በማድረግ በማዕከሉ ላሉት አንድ ህጻን ሊያገኝ የሚገባው የመጠለያ ፤ የምግብ የጤና የትምህርትና የስነ ልቦና ጥበቃ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። ወደ ማዕከሉ የሚገቡት በተለያየ መንገድ ሲሆን አንድ ህጻን ተጥሎ ከተገኘ በመጀመሪያ ከፖሊስ ጋር በፍርድ ቤት እንዲሁም በጤና በኩል ያሉት ሁኔታዎች ተጣርተው እስኪጠናቀቁ ደረስ የግዴታ ሁለት ወር በማዕከሉ እንክብካቤ እየተደረገለት እንዲቆይ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ እንደ ሁኔታው ለአደራ ቤተሰብ ወይንም ከስድስት ወር በኋላ ለጉዲፈቻ ቤተሰብ ኢትዮጵያውያን ለሆኑና በጎ ፈቃደኞች እንዲተላለፍ ይደረጋል።
በሌላ በኩል ወደ ማዕከሉ ከሚገቡት መካከል በህገወጥ የሰዎች ዝወውር ለአደጋ የተጋለጡም ይካተታሉ። ከዚህ ቀደም አንዲት አስራ ሶስት አመት ያልሞላት ልጅ ከአሰበ ተፈሪ አካባቢ በህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ጅቡቲ እንወስድሻለን በማለት ወደ ድሬዳዋ ከተማ ይዘዋት ይመጣሉ። እዛም አሸዋ ቀፊራ የሚባለው አካበቢ አንዲት ሴትዮ ጋር እንድትቀመጥ ትደረጋለች። የተቀበለቻት ሴትዮ ግን ስራ አስገባሻለሁ ብላ ከወሰደቻት በኋላ ለሌሎች አራት ወንዶች አሳልፋ ትሰጣትና እንድትደፈር ታደርጋለች። ደፋሪዎቹ ኮካ ወደሚባለው አካባቢ ወስደው ከጣሏት በኋላ ፖሊስ መረጃ ይደርሰውና እሷን ወደ ድሬዳዋ ህጻናት ማቆያና ማገገሚያ ማእከል በማምጣት እነሱም ወንጀለኞቹን መከታተላቸውን ይቀጥላሉ። ማዕከሉ ልጅቷን ተቀብሎ የህክምና አገልግሎት እያገኘች ረዘም ያለ ግዜ እንድትቆይ ካደረገ በኋላ ጤናዋ ሲስተካከል ከባለሙያዎች ጋር ወደትውልድ ቦታዋ በመላክ የደረሰው ነገር ሙሉ ለሙሉ ሳይነገራቸው የጤና ችግር ብቻ ገጥሟት እንደነበር በማስመሰል ከቤተሰቧ ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል። ፖሊስም በበኩሉ ሲያደርገው የነበረው ክትትል ውጤታማ ሆኖለት ደፋሪዎቹንና አሳልፋ የሰጠቻትን ሴትዮ ለፍርድ በማቀረብ ህጋዊ ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ አድርጓል። ማዕከሉ በተመሳሳይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂ የሆኑ በርካታ ህጻናትን ሲንከባከብ ቆይቷል።
አገልግሎቱ የሚሰጠው ተጥለው የሚገኙ ህጻናትን ከሆኑ በመጀመሪያ ከፖሊስና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወደ ተቋሙ እንዲገቡ ይደረጋል። በሁለተኛ ደረጃ በአብዛኛው የሚስተዋለው በተለያዩ ወንጀሎች አናት ወይንም አባት ወይንም ሁለቱም በህግ ጥላ ሰር ውለው በማረሚያ ቤት ሲቆዩ ልጆቹ ከእነሱ ጋር መሆን ስለሌለባቸው የሚረከብ የቅርብ ቤተሰብ ከሌለ በማቆያው እንዲቀመጡ ይደረጋል። ከቤተሰባቸው አንዱ ወይንም ሁለቱም የአእምሮ የጤና እክል የገጠማቸው ሆነው ከተገኙም ህጻናቱ ላይ ሊደረስ የሚችለውን ችግር በመገመት ተቋሙን እንዲቀላቀሉ ይደረጋል። በተጨማሪ በወላጆቸ መካከል በሚፈጠር ጸብ አለመስማማት ሲፈጠርና ዘመድ አዝማድ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር በተቋሙ በመግባት ጤናቸው እንዲጠበቅ ትምህርት እንዲማሩና ሌሎች ልጆች ከቤተሰብ የሚያገኟቸው ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታዎች እንዳይጓደሉባቸው ያደረጋል። በተጨማሪ ህጻናቱ ከቤተሰብ በመለየታቸውና ደርሰውባቸው የነበሩ አንዳንድ ችግሮች ለጭንቀትና ለስነ ልቦናዊ ቀውስ ይዳርጋቸዋል። በመሆኑም በማዕከሉ ያሉት የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንዲከታተሏቸው የሚደረግ ሲሆን የሚንከባከቧቸውም ሞግዚቶች የእናት ምትክ በሆነ ፍቅርን እንክብካቤን እንዲሰጧቸው ይደረጋል።
ማዕከሉ ለችግር ተጋልጠው ያገኛቸውን ህጻናት ከአሳዳጊዎች ጋር የሚያገናኝበትም መንገድ መንግስት ያስቀመጣቸውን መመሪያዎች ተከትሎ ነው። በዚህም መሰረት ህጻናቱ በአደራም ሆነ በጉዲፈቻ ወደ አዲሱ ቤተሰብ ከመቀላቀላቸው በፊት የሚቀበላቸው ቤተሰብ ያለበት ሁኔታ ማለትም ገቢው፤ ከሱስ ነጻ መሆን፤ በወንጀል የሚጠረጠሩ መሆናቸውን አጠቃለይ የጤናቸው ሁኔታ በተለይ (ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች በቤተሰብ ውስጥ መኖር አለመኖራቸው ) እንዲሁም ለምን ህጻናቱን መውሰድ እንደፈለጉ ተጠይቀውና ምርመራ ተደርጎ ህጻናቱን እንዲረከቡ ይደረጋል። ለዚህም በእያንዳንዱ ቀበሌ ይህንን ለመስራት የተቋቋመ ኮሚቴ አለ። ይህም ወሳጅ ቤተሰብ ያለበትን አጠቃለይ ሁኔታ የሚያጠራ ይሆናል። ኮሚቴው ህጻናቱ ወደ አሳዳጊ ቤተሰቦቻቸው ከመሄዳቸው በፊት ክትትልና ምርመራ እንደሚያደርግ ሁሉ አሳዳጊዎቻቸው ከወሰዷቸው በኋላም በአዲሱ ቤተሰብ ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ የሚከታተል ይሆናል። በዚህም ተረካቢዎቹ ህጻናቱን ከመውሰዳቸው በፊት ያቀረቧቸው ነገሮች መኖር አለመኖራቸውን እንዲሁም ሌላ አዲስ የተፈጠሩ ነገሮች ካሉና ለህጻናቱ ሁለንተናዊ አድገት እንቅፋት የሚሆኑ ከሆነ የሚስተካከሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ካልሆነም ህጻናቱ ወደማሳደጊያው እንዲመለሱ የሚደረግ ይሆናል። በአብዛኛው እነዚህ አካሄዶች ከሶስት ወር እስከ አንድ አመት የሚወስዱ ሲሆን ህጻናቱ የጤና አክል ያለባቸው ከሆኑ ደግሞ ፈቃደኛ ሆኖ የሚቀበላቸው ባለመኖሩ በህጻናት ማቆያና ማገገሚያ ማዕከሉ በመሆን ህክምናቸውን እንዲከታተሉ የሚደረግ ይሆናል።
የአደራ ቤተሰብ የሚባለው ህጻናቱ ቋሚ ነገር እስኪመቻችላቸው በግዚያዊነት የሚቆዩበት ሲሆን የጉዲፈቻው ግን በዘላቂነት አንድ የአብራክ ክፋይ ለጅ የሚያገኘውን ሁሉ የሚያካትት ነው። ነገር ግን እስካሁን በአደራ የሚወሰዱትን ህጻናት በሙሉ ፍርድ ቤት እያቀረቡ ወደ ጉዲፈቻ በማድረግ ራሳቸው እንደ ልጃቸው እያሳደጓቸው ይገኛል። ጉዲፈቻ ለመውሰድ የሚመዘገቡትም የፆታና የአንዳንድ መስፈርቶች በማስቀመጥ አብዛኛው ሰው ይፈልግ የነበረው ሴቶችን ብቻ የነበረ ቢሆንም በማስተማርና ወንዶቹንም እንዲወሰዱ እየተደረገ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ሀምሳ አራት ህጻናት በህጻናት ማቆያና ማገገሚያ ማዕከሉ ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሲሆን ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ከአንድ መቶ ሀምሳ ዘጠኝ ህጻናትን ከሀገር ውስጥ አሳዳጊዎች ጋር ለማገናኘት መብቃቱን። አሁንም ድረስ በአማካይ ከሁለት እስከ አምስት ልጆች በወር ማዕከሉን እየተቀላቀሉ ይገኛል ሲሉ ባለሙያዋ ተናግረዋል።ተጥለው ከተገኙ ህጻናት ይልቅ ወላጆቻቸው በህይወት እያሉ በህግ ጠላ ስር በመዋላቸው አልያም የጤና እክል ገጥሟቸው የሚመጡ ህጻናት በማዕከሉ ረዥም ግዜ ይቆያሉ። በዚህ አይነት እስከ አራት አመት በማዕከሉ የሚቆዩ ያሉ ሲሆን ከቤተሰብ አለመስማማት ጋር በተያያዘ እድሚያቸው አስራ ስድስት አመት ሞልቷቸውም በማዕከሉ እየተማሩና እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚገኙ መኖራቸውንም ባለሙያዋ ገልጸዋል።
በተጨማሪ ማዕከሉ አንዳንድ ግዜ ከጤና ጋር በተያያዘ የሚገጠሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ። እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲገጥሙ ቢሮው ራሱ አዲስ አበባ ድረስ በመውሰድ ከፍተኛ ህክምና እንዲያገኙ የሚያደርግ ቢሆንም አንዳንዶቹ ችግሮች ከአቅም በላይ በመሆናቸው የሚደግፍ አካል በማፈላለግ ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል። እንዲህ አይነት ችግር የገጠማቸውን ልጆች በሀገር ውስጥ የአደራና ጉዲፈቻ ቤተሰብ በመቀበል ረገድ ተነሳሽነት የለም። ከዚህ ቀደም አንዲት እናት አንድ ልጅ ወስደው አዲስ አበባ ድረስ በመመላለሰ ቢያሳክሙም ለወጥ ማግኘት ባለመቻላቸውና ሀኪሞችም ለመዳን ተስፋ የሌለው መሆኑን ስለነገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ አንዲት እናት የወሰዷት ልጅ የማየት ችግር ቢገጠማትም አንድ ግዜ እግዚአብሄር የሰጠኝ ናት ብለው በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ችግሩ በመሰረቱ የሚቀረፍ ባለመሆኑ በዘላቂነት ህጻናትን ለመታደግ የእየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም ባለሙያዋ እንደሚከተለው አብራርተዋል። በርካታ ህጻናት ከአጎራባች ከተሞች የሚመጡ በመሆኑ በድሬዳዋ ከተማም ሆነ በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በስፋት እየተሰጠ ይገኛል። ከፖሊስም ጋር በመሆን በተለይ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠር የሚሰሩ ስራዎች አሉ ከሁሉም አልፎ ለችግር የተጋለጡትን ለመንከባከብ ደግሞ ሀብት ማሰባሰብ ስለሚያስፈልግ በቅርቡ ከመቶ ብር ገቢ ሀያ አምስት ሳንቲም ማሰባሰብ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁን አሁን በኮሮና ምክንያት ቢቆምም በርካታ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ሰርግ ልደትና ሌሎች ባዕላትን በግቢው በመገኘት ከህጻናቱ ጋር እያከበሩ ቤተሰብ እንዳላቸው እንዲሰማቸው እያደረጓቸው ይገኛል ።
እስካሁን ድረስ ቢሮው የህጻናት ማቆያውን እየተገለገለ ያለው ከፍተኛ ወጪ በማወጣት አንድ ሰፊ ግቢ ያለው ባለ አንድ ወለል ፎቅ ቤት በመከራየት ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ከተማ መስተዳድሩ ቦታ ተሰጥቶት በጀት ተበጅቶለት ህንጻ አስገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ በመሆኑ በቅርቡ ህጻናቱ ወደ አዲሱ ማቆያ የሚዛወሩ ይሆናል። ህንጻው የህጻናት ማቆያና ማገገሚያ ማዕከልና ከጎኑ ደግሞ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች እንክብካቤ የሚሰጥበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቢሮው በዋናነት ለችግር የተዳረጉ ህጻናትን ባሉበት ከወላጅም ሆነ ከዘመድ ጋር ሆነው ይደገፋሉ። በተጨማሪም በከተማ መስተዳደሩ ስራ ያለውና ከ2000 አ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ሌላው ቢሮው ስር ያለው የሴቶች የጥቃት ማዕከል ነው። ይህ ማዕከል ጥቃት የደረሰባቸውና ለጎጂ ልማዳዊ ድርጅቶች ተዳደርገው ለችግር የተዳረጉ ሴቶች የህግ ጉዳያቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ በሽምግልናና በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ፍትህ ሳያገኙ አንዳይቀሩ የሚጠበቁበት ነው። በዚህ ማዕከልም በከተማው ካሉ ትምህርት ቤቶችና ቀበሌዎች ጋር በጥምረት የሚሰራበት ሲሆን ልጆች ከጠዋት እስከ ማታ ትምህርት ከሌላቸው አልባሌ ቦታ በመዋል ለተለያዩ ችግሮች አንዳይጋለጡ እንዲያሳልፉ የሚደረግበት ነው። ይህ ቦታ ለልጆች መዝናኛና የጥናት ቦታ የተሟላለት ሲሆን የተሟላ ስብእና እንዲኖራቸውና በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ በፈቃዳቸውና ከትምህርት ቤት ሲላኩ በባለሙያዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጥበት ነው። በተጨማሪም የጎዳና ተዳደሪነት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ከስደት ተመላሾች ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ባለሙያዋ ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2013