
አዲስ አበባ:- ‹‹የሰው ልጅ ክቡር ፍጡር በመሆኑ ይጠበቃል እንጂ አይገደልም፣ ድርጊቱን እናወግዛለን፣ ልብና አእምሮን የሚገዛ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲገነባ እንጸልያለን›› ሲሉ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ዶክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ አስታወቁ።
ዶክተር አባ ተሾመ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ‹‹የሰው ልጅ ክቡር ፍጡር ነው፤ ክቡር ነገር ይጠበቃል እንጂ አይገደልም።ድርጊቱን ከማውገዝም ባለፈ ወደ ተግባር የሚለውጥ፣ ልብና አእምሮን የሚገዛ፣ ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርገንና ወደለውጥ የሚያስገባን የፖለቲካ ሥርዓት ልንገነባ ይገባል››፡፡
ድርጊቱን አውግዘን አናቆምም ለተግባሩ ልባችን ተለውጦ፣ ንስሃ ገብተን፣ እውነተኛውን የፍትህና የሰላም መንገድ ልንከተል ይገባል ያሉት ዶክተር አባ ተሾመ፤ ‹‹እየሆነ ያለው ነገር የእምነት አባቶችን ያሳስባል ያስጨንቃል ፤ እንጸልያለን፣ ድርጊቱንም እናወግዛለን›› ብለዋል፡፡
የሰው ልጆች በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት ይፈናቀላሉ፣ ንጹሃን ይገደላሉ፣ በማይመለከታቸው ጉዳይ ብዙ አደጋ እየደረሰባቸው ይገኛል ይህ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
ለጥፋት ከሚያነሳሳ፣ ወደ ጦርነት ከሚያስገባና መለያየትን ከሚቀሰቅስ ነገር በመታረም የተሻለ አገር ለመመስረት ኢትዮጵያውያን ሊተባበሩ ይገባል ያሉት ዶክተር አባ ተሾመ ፣ በኢትዮጵያ ምድር የተወለደ ዜጋ የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተዋል፣ በብቸኝት ፖለቲካውን ሊመራ የሚፈልግ ሊኖር እንደማይገባ ጠቁመዋል።
እየሆነ ያለው ነገር በአገራችን ላይ ጥቁር ጠባሳ የሚጥል፣ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የሚገፍ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ቆም ብለው ማስተዋል እንዳለባቸው የጠቆሙት ዶክተር አባ ተሾመ። ለአገር፣ ለሰው ልጅ መብት የሚጠቅመውን የተሻለ ፖለቲካ ለማምጣት የሚረዳ መንገድና የውይይት አማራጭ መከተል እንዳለብን አመልክተዋል።
ሥርዓት ያለው ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ህይወት መኖር ከቻልን ሰዎች በደስታና በፍቅር መኖር ይችላሉ›› ያሉት ዶክተር አባ ተሾመ ፤ የተፈጠርነው በወንድማችነትና በቤተሰባዊነት ለመኖር እንጂ፤ በመንደር፣ በሃይማኖት፣ በባህል በጎጠኝነት ግድግዳ ልንታጠር እንደማይገባ አስታውቀዋል።
‹‹በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠራችንን ካመንን እያንዳንዳችን ወንድምና እህት ነን፣ ይህንን የምናረጋግጠው በተግባርም ወንድሜና እህቴ እንዳይፈናቀሉ፣ እንዳይሞቱ ከጠበቅኩኝ ነው›› ብለዋል።
ከፖለቲካው ጋር ተያያዥ ነገሮች አሉ፣ ምርጫም ቀርቧል፣ የኮቪድ ወረርሽኝ በዓለም ላይ እያደረሰ ያለው አደጋ ያስጨንቀናል።በእዚህ ምክንያትም ለሳምንት የሱባኤ ፆም ታውጇል፣ ከፈጣሪና እርስ በእርስ በተጣላንበት ጉዳይ ምህረት ለማግኘት ቤተ እምነቶች ጸሎት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሌሎች አገሮች የምናያቸው፣ ስንፈራው የኖርነው፤ በዘር፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት መበጣበጣችን ለአገርና ለህዝብ አንድነት አደጋ እንዳይሆን ያሰጋኛል ።የአገራችንን እድገት የማይፈልጉ ምናልባትም መበጣበጣችንን ለሚፈልጉ ጎረቤት አገሮች እጅ እንዳንሰጥ ያሳሰበኛል ብለዋል፡፡
ዓለም ወደ አንድነት እየሄደ፣ ወንድማማችነትን እያጠናከረ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ህይወቱ እየተሰባሰበ ያለበት ወቅት ነው።እኛ ያለንበት አደጋ ያሳስበናል፣ ያስጨንቀናል፣ በእግዚአብሄር ፊት ተደፍተን እንድንጸልይ ዕድል ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን እንድናይ አድርጎናል ብለዋል።
የሚመለከታቸው ሁሉ ተረጋግተው አገርን ከጥፋት የማዳን ተልዕኮ እንዳለባቸው ያመለከቱት ዶክተር አባ ተሾመ ፣ ሁሉን ያማከለና የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ መብት የሚያስከብር ፖለቲካ እንዲተገብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
መንግሥት የዜጎች መብት እንዲከበር፣ ሰዎች እንዳይገደሉና እንዳይፈናቀሉ፣ መብታቸው እንዲከበር፣ የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲተገበር፣ የዜጎች በሰላም የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ ወጥቶ የመግባት መብታቸውን ለማስከበር የተጣለበትን ሃላፊት እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም