
አዲስ አበባ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት / ተመድ/ የፀጥታው ምክር ቤት ሰሞኑን በትግራይ ክልል ጉዳይ ያወጣው መግለጫ ዓለም የኢትዮጵያን እውነታ እየተገነዘበ መምጣቱን እንደሚያሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ የጋዜጣ መግለጫ እንዳስታወቁት፤የሰሜኑ የኢትዮጵያን ክፍል በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሰሞኑን ከወትሮው ለየት ያለ መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው ከዚህ ቀደም ከምዕራቡ ዓለም ሲንፀባረቁ የነበሩትን አሉታዊ አስተያየቶች ትክክል እንዳልሆኑ ያሳየ ነው። ዓለም የኢትዮጵያን እውነታ እየተገነዘበ ስለመምጣቱ ማሳያ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ በመግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ አካባቢ እያቀረበ ላለው የሰብአዊ ድጋፍ እውቅና መስጠቱን ያስታወቁት አምባሳደር ዲና፣ መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ ክፍል ባለው ጉዳይ ምንም እያደረገ አይደለም የሚለውን የምዕራቡን ዓለም አስተያየት ውድቅ ያደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።
መግለጫው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ባከበረ መልኩ የጋራ መፍትሄ ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ አንፀባርቋል። የኢትዮጵያን ነፃነት ያከበረ እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያገናዘበ በመሆኑ ሚዛናዊ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ተረድቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲያስተጋባ የነበራቸው ጽምፆች አሁን በምክር ቤቱ መግለጫ ተብራርተዋል ያሉት አምባሳደር ዲና፤ በተለይ አንዳንድ አገራት እና ተቋማት በኢትዮጵያ ያሰራጯቸውን የተዛቡ መረጃዎችን የቀየረ መሆኑን አስታውቀዋል።
የምክር ቤቱ መግለጫ የረድኤት ተቋማት የሰብአዊ መብትን በጠበቀ መልኩ የሚሰጡትን ዕርዳታ እንዲጨምሩ መልዕክት የተላለፈበት በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ሃሳብ የደገፈ አካሄድ እንዳለው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከአፍሪካ እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ ጥሰቶችን ለማጣራት የሚያደርገውን ጥረት የተገነዘበ መግለጫ በመሆኑ እውነታውን ያሳየ መግለጫ ነው በሚል ቃል አቀባዩ አወድሰውታል።
በህዳሴው ግድብ፣ መንግሥት በትግራይ ክልል እያከናወነ ባለው ሥራ፤ በሱዳን ድንበር ጉዳይ እና ሌሎች አጀንዳዎች በተመለከተ ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ በጀርመን አገር የሚገኙ ምሁራንን እና ታዋቂ ሰዎችን ባማከለ ሁኔታ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል። ከጀርመን በተጨማሪ በካናዳ፣ በዩጋንዳ እንዲሁም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች ኢትዮጵያውያንን እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሰዎችም በመጋበዝ እና ከየገራቱ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር የኢትዮጵያን እውነታዎች ለማስረዳት ጥረት መደረጉን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ላይ በህዳሴውም ግድብ ሆነ የድንበር ጉዳዩን እንዲሁም ከትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያሉ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
አምባሳደር ዲና እንዳስታወቁት፤ባለፈው ሳምንት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያ አፍሪካ የትብብር ፎረም ዋና ጸሐፊ ጋር መክረዋል። በወቅቱ አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የፎረሙ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት በመግለጽ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል። ከሩሲያ ባለፈ ከቪዬትናም ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ስልሚቻልባቸው ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም