መቼም ስለሬዲዮ ሲነሳ የተለያዩ ትዝታዎች ተግተልትለው የማይመጡበት ሰው አለ ቢባል ቁጥሩ በጣም ጥቂት ነው። ምነው ቢሉ ሬዲዮ ያልገባበት ቀዳዳ፣ ያልወጣው ዳገት፤ ያልወረደው ቁልቁለት፣ ያልቀዘፈው አየር፣ ያላቋረጠው ባህር፤ ያላነሳው ቁም ነገር፣ ያልተረከው ትርክት፣ ያላዜመው ዜማ የለምና ነው። ለእዚህም ነው በሬዲዮ ያልተዝናና፣ ከሬዲዮ ያልተማረ፣ በሬዲዮ ያልተከዘ፣ በሬዲዮ ያልሳቀ፣ በሬዲዮ (ያላለቀሰ?)፣ በሬዲዮ ያላፈቀረ/ያልተፈቀረ፣ በሬዲዮ . . . የለም የሚባለው፡፡
ብዙ የምርምርና የሙከራ ተግባራትን በማለፍ ከ1830 (እ.አ.አ) ጀምሮ ወደሥራ የገባው፤ በ1895 በጣሊያኑ ተወላጅ ጉግሌሞ ማርኮኒ አማካይነት «ሬዲዮ» የሚል ስያሜውን ያገኘው የመገናኛ መሳሪያ፤ ከዛ በፊት «ሽቦ አልባ ቴሌግራፍ» በሚል ይታወቅ እንደነበር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ ቀኑ የሬዲዮ ነው። በመሆኑም «ውይይት፣ መቻቻል እና ሰላም/Dialogue, Tolerance and Peace» በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ «የዓለም ሬዲዮ ቀን» እየተከበረ ይገኛል። እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታና የይዘት ምርጫ መሪ-ቃሉን መሰረት ባደረገ መልኩ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፤ ኮንፈረንሶች፣ ህዝባዊ ውይይቶች፣ አውደ-ጥናቶችና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ናቸው። ዝግጅቶቹ ከሚያተኩሩባቸው ዋና ዋና ርእሰ-ጉዳዮች መካከል፤ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችን ስለማዳበር፣ ሰብዓዊ እኩልነት፣ ልዩ ድጋፍ እና እገዛን ስለሚሹ ወገኖች (አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶች፤ ህፃናት . . .)፣ ስለግጭትና አዘጋገብ፣ የዘር/ቀለም ጉዳይ፣ ሰላምና ወንድማማችነት… ሌሎችም ይገኛሉ።
የእለቱ መከበር በርካታ ዓላማዎች ቢኖሩትም፤ ፈጣሪውንና የሬዲዮንን ውለታ በማስታወስ መዘከር፣ የሬዲዮ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍን ማጠናከር፣ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጎልበት፣ ሬዲዮ ወደሥራ ከገባበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያበረከተውን አስተዋፅኦና የተጫወተውን ሁለንተናዊ ሚና ማወደስ፣ የሰዎችን መረጃ የማግኘት መብትና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት ማፅናት፣ ስለሬዲዮ ጣቢያዎች መስፋፋትና መጠናከር መምከር፣ ተደራሽነቱን ማስፋፋት፣ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርንና አሰራርን ፈር ማስያዝ፣ ለሬዲዮ መገናኛ ዘርፍ መስፋፋት መንግሥታት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የሚገባቸው ስለመሆኑ፣ የህዝብ/አድማጭ ተደራሽነት፣ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትና ሌሎችም ይገኙበታል።
በየዓመቱ፣ በዛሬው እለት የሚከበረው «የዓለም ሬዲዮ ቀን» በመጀመሪያ ሀሳቡ በስፔን ከሚገኝ አንድ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን አካዳሚ (በ2010) ፈለቀ፤ ዩኔስኮ ተቀበለውና በ36ኛ (2011) ጉባኤው አፀደቀው። ተመድም አፍታም ሳይቆይ በ2012 ይሁንታውን አሳወቀና ድጋፉን ሰጠ። በተለይ እለቱ የተመድ ሬዲዮ የተከፈተበት (1948) እለት በመሆኑም በቀላሉ በድርጅቱ በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል። («ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ» እንዲሉ) እለቱ ከ«የዓለም ሬዲዮ ቀን» ባለፈ የተመድ ሬዲዮ ጣቢያ መቋቋምንም አጣምሮ የያዘ ‹‹ድርብ በዓል›› ነው ማለት ይቻላል።
ባለፈው ዓመት በዓሉ «Media Sport» በሚል መሪ ቃል በተከበረበት ወቅት በ2011 ለበዓሉ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የሰጠው ዩኔስኮ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳሰፈረው ህጋዊ የሆኑ በዓለማችን በአጠቃላይ 44 ሺህ ሬዲዮ ጣቢያዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። በማያያዝም ይህ ቁጥር ብዙ ቢመስልም በቂ ነው ማለት እንደማይቻልም አሳስቧል።
እንደድርጅቱ እምነት ዓለማችን በርካታ ፍላጎቶችና ልዩነቶች ያሉባት ከመሆኗ አኳያ ሲመዘን፤ ይህ የሬዲዮ ተቋማቱ ቁጥር በቂ አይደለም። በዓለማችን ከሚታዩት የብሔር፣ ነገድ፣ ቀለም፣ ሥርዓተ-ፆታ፣ ሃይማኖት፣ እድሜ ልዩነቶች፤ ከአካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ህፃናት፣ አረጋውያን… ፍላጎት አኳያ ሲታይ የተቋማቱ ቁጥር እጅግ አነስተኛና ገና ብዙ የሚቀረው ዘርፍ ነው።
ሬዲዮ ካሉት የመገናኛ ብዙኃን አይነቶች ሁሉ በተሻለ ደረጃ ለህብረተሰቡ የላቀ ተደራሽነት ያለው ከመሆኑ አንፃር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከማስፈን፣ ግጭቶችን ከማስቀረት/ማስወገድና በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ከመፍጠር፣ ከማቀራረብና አንድነትን ከማምጣት አኳያ የተጫወተውና እየተጫወተ ስላለው ሚና፤ እንዲሁም ወደፊት መደረግ ስላለበት ጉዳይ በየአገራቱ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ክበቦች… ውስጥ ውይይቶች፣ ክርክሮች፣ ሽልማት የሚያስገኙ ውድድሮች ወዘተ. እየተደረጉ ይገኛሉ።
በሬዲዮ በተላለፉ ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈጠሩ ሰብዓዊ ቀውሶችና ቁሳዊ ውድመቶች ተመዝዘው ወጥተው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን፤ ይህ አይነቱ ከሙያው ሥነ-ምግባር ፈፅሞ ያፈነገጠ አሰራር እንዳይደገም ሲመከርበት ሰንብቷል።
ሬዲዮ በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተመራጭና ተደማጭ፣ ተዘውታሪ ከመሆኑ አንፃር የሬዲዮ ጋዜጠኞች ሙያቸውን ህዝብን ከማሳወቅ፣ ከማንቃት፣ ከማግባባት . . . ባፈነገጠ መልኩ መጠቀም የሌለባቸው፤ በሐሰት ዜናዎች አማካይነት ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ከሙያው ሥነምግባር ውጪ መሆኑ እየተመከረበትና የሬዲዮ ጣቢያዎችም ሆኑ የሬዲዮ ጋዜጠኞች ለሙያቸው ታማኝ፤ ለሥነ-ምግባር ተገዥ መሆን እንዳለባቸው አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ጋዜጠኞች በገለልተኝነት አቋማቸው መፅናትና አድማጭን በቅንነትነና በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባቸውም እንደዛው፡፡
የሬዲዮ ፕሮግራሞች በይዘቶቻቸው ለሰላም፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነት… ቅድሚያ ሊሰጡ የሚገባ መሆኑ፤ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሰላምን ምንነትና አስፈላጊነት ማስረፅ እንደሚገባቸው፤ ለነፃ የመረጃ ፍሰት፣ ድምፃቸውን ለታፈኑ ወገኖች ድምፅ መሆን የሬዲዮ ጋዜጠኛነት ዋና ዓላማ መሆኑ ሁሉ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ እየተላለፉ ያሉ መልእክቶች ናቸው።
ሬዲዮንን ከሁሉም መገናኛ ብዙኃን በተለየ ተመራጭ የሚያደርጉት ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፤ ዋጋው ቀላል መሆኑ፣ ለአያያዝ ያለው ምቹነት፣ በገጠራማ አካባቢዎች ተደራሽ መሆኑ፣ አደጋ ሲደርስ ለህዝብ ለማሳወቅና ለመከላከል ተግባር ቀዳሚ መልእክት አድራሽ መሆኑ ሲሆን፤ በተለይ ህብረተሰብ አሳታፊነቱ ጥንካሬውንና አስፈላጊነቱን ያጎላዋል።
መንግሥታት ሰላምን ለማስፈን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር፣ ድህነትን ለመዋጋትና ልማትን ለማፋጠን፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር. . . በአገራት መካከል ሁለንተናዊ ግንኙነትን ለማሳለጥ ከፈለጉ የሬዲዮ መገናኛውን ዘርፍ ማጠናከር፣ ማስፋፋት፣ መደገፍ፣ ነፃ ማድረግ፣ መተባበር. . . ያለባቸው መሆኑም በዩኔስኮም ሆነ በሌሎች የውይይት መድረኮች የመወያያ ርእሰ-ጉዳይ ሆኖ እየተመከረበት ነው።
ምንም እንኳን ከሌሎቹ የመገናኛ ብዙኃን ቴክኖሎጂዎች ጋር በንፅፅር ሲታይ ሬዲዮ የበለጠ ለህዝብ ተደራሽ ቢሆንም፤ አፍሪካን በመሳሰሉና በማደግ ላይ ባሉ አህጉራት 75 በመቶ (በቤተሰብ ደረጃ) ያህሉ የሬዲዮ አድማጭና ተሳታፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለእንደነዚህ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ሬዲዮ ልዩ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ለሬዲዮ ተመራጭነት እንደማሳያነት ይቀርባሉ።
ከዩኔስኮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሬዲዮ የሚቀርቡ ትምህርታዊ የግብርና ፕሬግራሞችን የሚከታተሉ ገበሬዎች ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። የሬዲዮን አስፈላጊነት በመረዳት መንግሥታት የሬዲዮ፤ በተለይም የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችን በማስፋፋት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን . . አስፈላጊውን ሁሉ እያደረጉ ነው።
ይህንን የሬዲዮ በዓል ምክንያት በማድረግ በርካታ አገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (በተለይም በጋዜጠኝነት መስክ የሚያሠለጥኑ)፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት . . . የየራሳቸውን የሬዲዮ ቀን ሰይመው በማክበር ላይ ይገኛሉ። ምክንያታቸውንም «ለሁለንተናዊ ማህበራዊ ለውጥ ሲባል» በማለት ያስረዳሉ።
በአሁኑ ሰዓት በተለያየ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሬዲዮ ዘመናዊነቱን እያሳደገ በመሄድ ላይ ይገኛል። በመሆኑም የንግድ ሬዲዮ፣ የማህበረሰብ ሬዲዮ፣ ኤኤም፣ ኤፍኤም፣ ሳተላይት ሬዲዮ . . . እና ሌሎችም በየአገራቱ በስፋት በመሰማት ላይ ይገኛሉ፤ በተለይ በአፍሪካ – ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉት አገራት ከፍተኛ ማህበራዊ ለውጥ በማምጣት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ባጠቃላይ 70 የሬዲዮ ጣቢያዎች ያሏት ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 48ቱ የአካባቢ ሬዲዮኖች (ኤፍኤም) ናቸው።
ህንድ – ዓለምን እየመራች ስለመሆኗ ብቻ ሳይሆን ልምዷን ለሌሎች እያካፈለች እንደሆነም ይታወቃል። በላቲን አሜሪካ (ፔሩ በ1ኛነት ስትመራ ኢኳዶር፣ ቦሊቪያና ብራዚል ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ) ውስጥ በሥራ ላይ ካሉት 10,000 የአካባቢ ሬዲዮ ጣቢያዎች ሌላ ሌሎች 10,000 የሚሆኑ ተመዝግበው ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። አንድ ዩኒሴፍ የጠቀሰው ጥናት እንዳመለከተው፤ በዓለማችን ካሉ መሪዎች መካከል 83 በመቶዎቹ ሬዲዮ የሚያዳምጡና «ትክክለኛ መረጃ የሚገኘው ከሬዲዮ ነው» ብለው የሚያምኑ ናቸው። በዓለም ላይ ካሉት ጎልማሶች 70 በመቶዎቹ የሬዲዮ አድማጮች ሲሆኑ፤ ትክክለኛ መረጃ የሚገኘውም ከሬዲዮ ነው ባዮች ናቸው።
ይህን የህንድንም ሆነ የላቲን አሜሪካ አገራትን የሬዲዮ መስፋፋት ስንመለከት የሌሎቹ ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን እንገነዘባለን። በመሆኑም የዩኔስኮንና የተመድን የተደራሽነት፣ አካታችነትና ተሳታፊነት ጥያቄ መጋራታችን የግድ ይሆናል።
ወደ ማጠቃለሉ እንሂድ፤ በዛሬው ቀን ዓመታዊው «የዓለም ሬዲዮ ቀን» እየተከበረ መሆኑን አንስተናል። ዓላማውን ቃኝተን ሂደቱን ተመልክተናል። የሬዲዮ መገናኛ ብዙኃንን በተለይ ወስደን ያበረከተውን ሁለንተናዊ አስተዋፅኦና ሊያከናውናቸው የሚገቡትን መሰረታዊ ተግባራት ጠቋቁመን ይበጃል የተባለውን አስምረንበት መጥተናል። ከሁሉም በላይ ከተደራሽነት፣ አሳታፊነት፣ ተጠቃሚነት፤ ከሙያዊ ሥነ-ምግባር ጥሰት፣ አገር ግንባታ፤ የህዝብ ለህዝብ መልካም ግንኙነት እና ለመሳሰሉት አንኳር ተግባራት ልዩ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ተመልክተናል። ከዚህ አኳያም፤ ሬዲዮ የቀድሞ መልካም ተሞክሮውንና ቀዳሚ ተምሳሌትነቱን እንደያዘ፤ ድምፃቸውን ለታፈኑ ድምፅ እንደሆነ እንዲቀጥል፤ ለእዚህም መንግሥታት፣ ህብረተሰቡ፣ የሚዲያ ተቋማት፤ በተለይም በመንበሩ ላይ የተቀመጡትና ብእሩን የጨበጡት ጋዜጠኞች ተገቢውንና ለዓለም ሰላም፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደር መስፈን . . . የሚበጀውን ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ እያሳሰብን እዚሁ ላይ እንሰናበታለን። ለዓለማችን የሚበጃት «ውይይት፣ መቻቻል እና ሰላም» ነውና የሬዲዮም ሆነ የሌሎች ሚዲያዎች ጋዜጠኞቻችን ሚዛንም እዚሁ ላይ ሊንተራስ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
ግርማ መንግሥቴ