በጋዜጣው ሪፖርተር
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኙ የኦሮሚያ ዞኖች አንዱ ነው፡፡ የዞኑ ዋና ከተማም ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ 114 ኪሎሜትር ላይ ይገኛል፡፡ አብዛኛው የዞኑ ነዋሪ በግብርና ሥራ የሚተዳደር ሲሆን የንግድ እንቅስቃሴውም እየተጠናከረ የመጣበት ዞን ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ በዞኑ ውስጥ የሚገኘው የወንጪ ሃይቅ በገበታ ለአገር ፕሮጀክት ታቅፎ በመልማት ላይ ይገኛል፤ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፡፡ እኛም በአጠቃላይ በዞኑ እንቅስቃሴና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዞኑ አስተዳዳሪ አቶ መገርሳ ድሪብሳ ጋር ቃለምልልስ አድርገን እንደሚከተለው አሰናድተናል፤ መልካም ቆይታ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን መልክአምድራዊ አቀማመጥና ከአጎራባች ዞኖች ጋር በተያያዘ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ መገርሳ፦ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ዞኖች አንዱ ነው። የዞኑ ዋና ከተማ ወሊሶ ከአዲስ አበባ በ114 ኪሎሜትር ላይ ይገኛል። ዞኑ 11 ወረዳዎችን የያዘ እና ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የያዘ ነው። የአካባቢው አየር ንብረት በአብዛኛው ደጋና ወይና ደጋ ሲሆን የተለያዩ ሰብሎች በተለይም በጤፍ በቆሎ እና ስንዴ ይታወቃል። ከዞኑ ምርቶች ውስጥ የበቾ ማኛ ጤፍ እየተባለ የሚታወቀው ተመራጭ የምርት ዓይነት ነው።
በዞኑ ውስጥ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦችን ይዟል። ለአብነት የወንጂ ሐይቅ፤ ኦዳ ከለቻ እና አዋሽ መልካ ቁንጡሬ የተሰኙትን መስህቦች ይዟል። ዞኑ የኢትዮጵያን ማንነት አስጠብቆ ከመቆየት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንደማስረጃ ለማቅረብ በጣሊያን ወረራ ወቅት ጀግኖች የፈለቁበት ለአብነት እንደነደጃዝማች ባልቻ አባሳፎ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ እና ቀኝአዝማች በቀለ ወያ ይጠቀሳሉ፡፡ የአገሪቷን ዳር ድንበር ከጠላት ከመጠበቅ አኳያ ብቻ ሳይሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ እንደነ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የፈለቁባት ዞን ነች።
በንግዱ ዘርፍ ታታሪ ውጤታማ የሆነ እንዲሁም ጨዋ ሕዝብ ያለበት አካባቢ ነው። ሕዝቡ አቃፊነቱ እንደኦሮሞ ከሚታወቀው ባህል አኳያ በበለጠ ዞኑ ላይ የሚታይበት ሲሆን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችንም አቅፎና ጥሩ ጎረቤት አድርጎ እንደራሱ ይዞ አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው። ከስድስት ወረዳ በላይ ከጉራጌ ዞን ጋር እንዋሰናለን በሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰማው የድንበርም ሆነ የጥቅም ግጭት የሌለበት ቦታ ነው።
ሕዝቡ የተለያዩ ፍላጎቶችም ቢኖሩ ባለው ባህል አማካኝነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በመፍጠር በእራሱ የሚፈታበት መንገድ አለው። እንደመንግሥት መዋቅርም በአንድ እንደሚሰራ ሆነን እየተረዳዳንና እየተናበብን እየሰራን ነው፤ ያሉትንም ችግሮች ሌላ ችግር ሆነው መልካቸውን ሳይቀይሩ በፊት እየፈታን ነው።
ከሽማግሌዎች እና ኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማያውክ ሁኔታ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን። በአጠቃላይ በዞኑ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በአጭሩ ለማቅረብ ግን በሰላማዊነቱ እና በአብሮነቱ የሚታወቅ አካባቢ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በዞኑ ሰፊ የእርሻ መሬትና የቱሪዝም ሀብት አለ፤ ከዚህ አንጻር ኅብረተሰቡን ምን ያክል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል?
አቶ መገርሳ፦ እንደአጠቃላይ አገራችን ድሃ ነች፤ ድህነቷ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት ጠፍቶ ሳይሆን የአመራሩ ክፍተት ስላለ ነው። አመራሩ ለሕዝብ ያለውን አመለካከት ስላላስተካከለ እና መንግሥት የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ አገናዝቦ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ ካለመተግበር ችግር የሚፈቱ አልነበሩም። ጥሩ ስትራቴጂዎች ቢቀረጹም ወደተግባር በመለወጥ ረገድ እንደአገርም ችግሮች ነበሩ። እኛ ዞናችን በስፋት ደረጃ ስናየው ትንሽ ዞን ይመስላል። ነገር ግን ለአገር አንድነትና ሉአላዊነት ትልቅ ነገር ያበረከተ ነው። ለአገራቸው ብለው የተሰዉ ጀግኖች እያሉ የትናቸው ብሎ በአገር ደረጃም ቢሆን የማይታወቅበት ሁኔታ ነው ያለው። ዞኑ ለአዲስ አበባ ካለው ቅርበት አኳያ ብዙ ተጠቃሚ ነው ማለት አይቻልም። ይህ ከብዙ አኳያ ይታያል።
አንድም ከመንግሥት ትኩረት ነው፤ በሁለተኛ የመፈጸም አቅም ሁኔታችን ያለበት ችግሮች ተደምሮ ነው የሚታየው። ከዚህ አኳያ ከአዲስ አበባ ቅርበት ካላቸው ዞኖች መካከል የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖችን ብናይ የኪሎሜትር ርቀት ልዩነት አይታይባቸውም። የሚለያቸው ነገር ምሥራቅ ሸዋ ዞን ወደ ወደብ የሚያስኬድ መስመር ላይ በመሆኑ እንጂ ብዙ ልዩነት የላቸውም።
ልማት በምናይነት ጊዜ ግን ወደዞናችን መጥቶ ልማት የሚካሂድበት ሁኔታ በጣም አነስተኛ ነው። ለዚህም ማዕከላዊ ሸዋ ላይ ያለፈው የኢህአዴግ መንግሥት አመለካከት ችግር ነበረበት። ብዙ ትኩረት አግኝቶ ያልለማ ዞን ነው። አዲስ አበባ ስር ቁጭ ብሎ ውሃ የሚጠማው፣ መንገድ የሌለው ሕዝብ አለ። ስናየው ደግሞ በበቾ ሜዳ ላይ ውሃ ላይ ሆኖ ውሃ የሚጠማ አካባቢ ሆኖ ይታያል። ስለዚህ ዞኑ መልማት በሚገባው ደረጃ ያልለማ እና ትኩረት ያላገኘ ነው።
አሁን እንኳን የሥራ ዕድሎችን ፈጥረን ወደሥራ ዕድል ለማስገባት ስንፈልግ መሠረተ ልማት ከሚባሉት ውስጥ መብራት እጥረት አጋጥሞናል። ችግሩ በመኖሩ ሕዝብን ወደሥራ አስገብተን እንዲጠቀም ለማድረግ እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታ አለ። እኛ አሁን የተለየ ነገር ሊሰጠን ይገባናል፤ ሳይሆን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሚገባንን እና ሌላ አካባቢ ያለውን መሰረተ ልማት እንድናገኝ ነው።
በእርግጥ ሕዝብ ከግል ሀብቱ በመነሳት እራሱን እንዲያለማ በማድረግ ትልቅ መነሳሳት አለ። ለዚህ ማመስገን የምፈልገው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለዚህ ዞን ትልቅ አስተዋጽኦ ነው ያደረጉት። በተለይ ያለፈው ክረምት ለዞኑ ነፃ የዜግነት አገልግሎት ወጣቱ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር ዞናችን ድረስ በመምጣት ሰርተዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመምጣት ባሬላ ጭምር በመሸከም መስራት እንደምንችል እና ማድረግ እንዳለብን ያሳዩ ናቸው። በተለይም ገበታ ለአገር ፕሮጀክትን መሠረት አድርገው ልክ እንደኮይሻ እና ጎርጎራ ፤ ወንጪ ደንዲ ሐይቆች ላይ የልማት ሥራ እንዲከናወን ያመጡት ፕሮጀክት ለሕዝብም ተስፋ የሰጠ እና ወደፊት መልካም ነገር እንደሚመጣ ያሳየ ነው።
የወንጪ ልማት ሲተገበር ዞናችን እንደሚለወጥ ያየንበት ነው፡፡ ለዚህም ሕዝባችን ከወዲሁ በልማቱ ለመሳተፍም ሆነ ልማቱ የሚያመጣቸውን ጸጋዎች ለመጠቀም እራሱን እንዲያዘጋጅ እያደረግን ነው። ይህ ልማት ዞናችን ውስጥ በተገኘ የተፈጥሮ ጸጋ የተገኘ ቢሆንም የአገር ልማት ነው፤ ይህንን ሕዝቡም አረጋግጧል። ገበታ ለአገር ላይ በመሳተፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው በመሳተፍ ይህንን አሳይቷል።
የበለጠ ደግሞ ሕዝብ በቀጣይ በኢኮቱሪዝም፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታውም ብዙ ዕድሎች ይዞልን እንደሚመጣ ይታመናል። ወደኋላ ቀርተናል፣ አስታዋሽ አላገኘንም፣ መንግሥት አላስታወሰንም እንዲሁም ከሌሎች እኩል አልለማንም የሚሉ ቅሬታዎችን ሁሉ የሚቀርፍ ፕሮጀክት መሆኑን እናምናለን። ወደ ዞናችንም በጎ ገጽታ ይዞ የሚመጣ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን እያየን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በዞኑ ወጣቶች የሚያነሷቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ነበሩ፤ ይህን መሠረት አድርጎ ከለውጡ በፊት ንብረቶችን ያወደሙበት ወቅት ነበር፤ ጥያቄዎቹ በአሁኑ ጊዜ ምን ያክል ተመልሰዋል? በቀጣይስ በተጨባጭ የሚከናወኑ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
አቶ መገርሳ፦ እንደሚታወቀው እንደማንኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ከለውጡ በፊት የነበረው አስተዳደር የእራሱ ችግር ነበረው። ያንን ላለመቀበል ብዙ ችግሮች እና ያለውን ሥርዓት የመቃወም ተግባራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲደረግ ነበር። በዚህ ረገድ በአካባቢያችን ወጣቱ ብቻ ሳይሆን አዛውንቱ ጭምር ሲደረግ የነበረውን በመቃወም ሲያደርጉ የነበረው ተቃውሞ ትልቅ ነበር።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ የ2008ቱ ዓ.ም ተቃውሞ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው። በርካታ የመንግሥትና የግል ንብረቶች የወደሙበት ብቻ ሳይሆን የበርካቶች ሕይወት የጠፋበት ነበር። ልክ እንደሌላው አካባቢ ሁሉ ቀድሞ ሌሎችም ተቃውሞዎች ነበሩ ። ዋናው ነገር ግን የዞናችን ኅብረተሰብ ነባራዊ ሁኔታውን ይረዳል፤ አገሪቷ ካላት ነገር እንድትሰጠው እንጂ የሌለ ነገር እንዲቀርብለት አይጠይቅም። ካለው ነገር ማግኘት አለብኝ የሚል ጥያቄ ነው ያለው።
በሌላ በኩል በአካባቢው የነበረውን የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ለመግለጽ ጭምር ተቃውሞ አድርጓል። ከለውጡ በኋላ ደግሞ ያ የሚጠላው እና መወገድ አለበት ብሎ ያለው ሥርዓት በመወገዱ ሕዝብ እንደትልቅ መልስ አድርጎ ነው ያየው። ሥርዓቱ ከተወገደ ከለውጡ በኋላ ችግሮቼ ተራ በተራ ይፈታሉ ብሎ ተስፋ በማድረግ እየተጠባበቀ ነው።
እኛም በተለያየ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለነው የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እና የአፈፃጸም ችግሮቻችንን በመቀነስ ረገድ እራሳችንን እንድናዘጋጅ መንግሥትም ሰፊ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። ከልማትና መልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያደሩ ብዙ ሥራዎች አሉ። ለሕዝቡ የሚሰራውን ይሰራል፤ የማይሰራውን ደግሞ አይሰራም እያሉ መሄድ ሲቻል የማይፈጸሙ ቃሎችን በመግባት የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ያልተጀመሩ ሥራዎች እንዲሁም ተጀምረው ያላለቁ ፕሮጀክቶች ነበሩ።
በሁለተኛ ደረጃ ሥራቸው ተጀምሮ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ነበሩ። ለምሳሌ በአንድ ሚሊዮን ብር ተጀምሮ ሥራቸው ሳይጠናቀቅ ወጪያቸው አስር ሚሊዮን ብር ደርሶም በወቅቱ የማይጠናቀቁ ግንባታዎች የነበሩበት ዞን ነው። በመንገድ ሥራ፣ በድልድይ ግንባታ፣ በትምህርት ቤት ግንባታ ሳይጠናቀቁ ሰባትና ስምንት ዓመት ያስቆጠሩ አሉ። እነዚህን ያደሩ ሥራዎችን እያየን በዚህ ዓመት ማለቅ ያለባቸውን ለይተናል።
ለዚህም ከመንግሥት ጋር ተነጋግረን አስፈላጊውን በጀት አስመድበናል። በዘንድሮው በጀት ዓመት አብዛኛዎቹ ተጀምረው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ሰፊ ሥራ እያከናወንን እንገኛለን። በሌላ በኩል ከለውጡ በኋላ የመጡ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ግንባታቸው የተጀመሩትን ለማስቀጠል፤ መጨረስ የማንችለውን ደግሞ እንደማንጀምር ከሕዝቡ ጋር እየተማመንን ለመሄድ ወስነናል። ከዚህ አኳያ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በአንድ ዓመት የሚጠናቀቁ እና ደረጃቸውን የጠበቁ 100 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል።
ከዚህ ውስጥ ሦስቱ ትምህርት ቤቶች በእኛ ዞን ውስጥ እየተገነቡ ይገኛል። ግንባታቸውም ከግማሽ በላይ ሄዷል፤ በቀጣይም በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። በመንገድ ግንባታ፤ በውሃ መስመር ዝርጋታ፤ በጤና በትምህርት ዘርፍ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ያለምክንያት ግንባታቸው እንዲያድር አይደረግም። ይሄም የጀመርናቸው ግንባታዎች በጊዜያቸው ወቅት ለማጠናቀቅ የምናደርገውን ጥረት ያሳያል።
ሌላው የሕዝቡን ቅሬታ እያስነሳ የነበረው የአምቦ እና ወሊሶ ከተሞችን የሚያገኛቸው መንገድ ግንባታ መዘግየት ነው። ሕዝቡ ግንባታው የተጀመረበትን ዓመት በማስታወስ ቅሬታ ያቀርባል። መንገዱ 64 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በሦስት ዓመት ይጠናቃል ተብሎ ስምንት ዓመት ቆይቷል። ኮንትራክተሩን በማንሳት አምና ለመከላከያ ኮንስትራክሽን ከተሰጠ በኋላ ጥሩ አፈጻጸም ታይቷል። በሚቀጥለው ዓመት ግንባታው የተሻለ ደረጃ ሲደርስ ለአካባቢው ኢኮቱሪዝም ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታመናል።
ከሥራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርተው ገቢ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ በርካታ ክንውኖች እያደረግን ነው። በእርግጥ ወጣቱ ጋር የመንግሥት ተቀጣሪ በመሆን ብቻ ገቢ ማግኘት እንዳለበት የማሰብ ችግር አለ። በሌላ በኩል እኛም መዋቅር ጋር አስፈላጊው የሥራ ቦታ፣ ብድር እና አሰራሮችን አመቻችቶ ወጣቱን ወደሥራ የማስገባት ችግር አለ። ይህም ሆኖ ግን የማይናቅ የሥራ ዕድል ፈጠራ እየተከናነ ነው።
መንግሥት አገር በቀል ኢኮኖሚ ብሎ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ያለን የኢኮኖሚ ኃይል ለመጠቀም እየተሞከረ ይገኛል። በዚህም 47 አርሶ አደሮች ወደኢንቨስትመንት ሥራ እንዲሸጋገሩ ተደርጓል። በዚህም የኢንቨስተርነትን ስም ብቻ ሳይሆን ካፒታላቸውን በማሳደግ የሥራ ዕድልም ፈጥረዋል። በአጠቃላይ የሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች በተቻለ መጠን መልስ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ በማይናቅ ደረጃ መሻሻሎች ታይተዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ሕዝቡ እንዳይንገላታ ፈጣን አሠራር ላይ አተኩረናል። ያሉ ችግሮችንም ከአስተዳደሮች ጋር በመነጋገር እየሄድንበት ነው። በእርግጥ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል። ምክንያቱም የሲቪል ሰርቫንቱ አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ መቀየር እንዳለብን በክልል ደረጃም አቅጣጫ ተቀምጧል። ስለዚህ ሕዝቡን በአግባቡ የሚያገለግል ሲቪል ሰርቫንት ሆኖ እንዲቀጥል፤ በሌላ በኩል ችግር የታየባቸውን እያስተካከሉና እርምጃ እየወሰዱ ከመሄድ አንጻር ሰፊ ሥራ ይጠይቀናል።
ሕዝቡ ድህነቱንም ይዞ ቢሆን በሰላም መኖር ነው የሚፈልገው። ሀብትም ቢያገኝ በሰላሙ ረገድ ስጋት ውስጥ ሆኖ መኖርን አይፈልግም። ዞናችንን ለየት የሚያደርጋት ዋናው ነገር ሰላምና ጸጥታው የተጠበቀ ዞን ነው። የሰላሙ መጠበቅ ደግሞ ብዙ ፖሊስና ሚሊሻ አሊያም የጸጥታ ኃይል ስለተሰለፈ አይደለም። ሕዝቡ በእራሱ ሰላም ወዳድ በመሆኑ ለመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ትብብር በማድረግ ሕዝባዊ ሰላም ወዳድነቱን በማሳየቱ ነው።
ሰላም በመኖሩ ብዙ ጥቅም እንዲያገኝ እና ሰላሙን ቢያጣ ብዙ ችግር እንደሚደርስበት ሕዝቡን በማስገንዘብ ረገድ ዞናችን ይሰራል። ከሰላም አኳያ የተለዩ ችግሮች ሲከሰቱም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ስለማያገኙ በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ይቀራሉ። ከለውጡ በኋላ የዞኑ ሕዝብ አግኝቷል ከሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሰላሙ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በዞኑ የሚገነባው የወንጪ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥ እስከምን ድረስ ነው?
አቶ መገርሳ፦ በገበታ ለአገር የሚገነቡት ፕሮጀክቶች አገርን ማልማት ላይ ያለሙ ናቸው። በሸገር ፓርክ የተሰራው ሥራ እና እንጦጦ ላይ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ወደአገርም ለማሳደግ በማሰብ ወንጪ ላይ በገበታ ለአገር ፕሮጀክት አገራዊ ልማት ለማከናወን ታቅዷል። ወንጪ በተፈጥሮ የተገኘ፣ በተራሮች የተከበበ እና ሰፊ የቱሪስት መስህብ አቅም ያለው ሐይቅ ነው።
ወንጪ የሚለው ቃል የተገኘው ወጪቲ ከሚለው የመመገቢያ ዕቃ ሲሆን መመገቢያ ዕቃ ይመስላል የሚል ትርጓሜ የያዘ ነው። በአካባቢው ሐይቁ ተጠብቆ የኖረው ኅብረተሰቡ እና ሐይቁ ሳይገፋፉ ስነምህዳሩን በጠበቀ ሁኔታ ስለቆየ ነው። ኅብረተሰቡ ሐይቁን ልክ እንደራሱ ንብረት ነው የሚንከባከበው። ማህበረሰቡ የተለየ የአኗኗር ልምድ ያለው ከመሆኑ የተነሳ የመደማመጥ፣ የመከባበርና ለበጎ ሥራ አብሮ የመነሳት ባህል ያለው ነው። ታማኝና እንግዳ ተቀባይም ነው። ከዚህ በመነሳት ቦታው ሳይለማ በፊትም በአነስተኛ ደረጃ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ነበር።
ከአፍሪካም ሆነ ከአውሮፓ እንዲሁም ከሌላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶችን ያስተናግዳል። ለዚህም የተፈጥሮ መስህቡ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰላም ወዳድነት እና ታማኝነት ቱሪስቱ በሰላም ጎብኝቶ በሰላም እንዲመለስ በማገዙ የተነሳ ነው። በቀጣይም የወንጪ አገራዊ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ደግሞ የበለጠ ጎብኚ እና ልማት ያመጣል ተብሎ ይታመናል።
ከዚህ በፊት የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም በሚል ማህበረሰቡ ተደራጅቶ 365 ሰዎች ሥራ አግኝተውበታል። አርሶ አደሮች እና የአርሶአደር ልጆች ቱሪስቶችን በማመላለስ፤ የቱር ጋይድ በመስጠት፣ የጀልባ አገልግሎት በመስጠት የእራሳቸውን ገቢ ለማሳደግ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ብዙ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ባይሆንም ይህ ሥራቸው እንዲቋረጥ ስለማይፈልጉ በጥንካሬ ይሰራሉ። ለቦታው እንክብካቤ ስለሚያደርጉለት ልክ እንደመስኖ ቦታ ለምለም ሆኖ ይታያል።
ወጣቶቹም የአካባቢው ደን እንዳይመነጠር እና የሐይቁ እንዳይጎዳ ሲጠብቁ ኖረዋል። አሁን ደግሞ በአገራዊ ፕሮጀክት በኩል የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ወደ ወንጪ ሲመጣ ሠራተኞቹ በከፍተኛ ሁኔታ ነው የተደሰቱት። ልማቱ መጣብን ሳይሆን መጣልን በሚል መንፈስ የልጆቻችን እና የእኛም ሕይወት ይቀየራል የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል።
እውነትም ፕሮጀክቱ ወደሥራ ይቀየራል የሚል ጥያቄ ቢኖራቸውም አሁን ወደሥራ ሲገባ እና በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ሲያረጋግጡ በጣም ነው የተደሰቱት። የደስታቸውንም ሁኔታ ለመግለጽ ሕዝብ ወንጪ ሐይቅ ላይ የምስጋና ቀን አዘጋጅቶ ለዚህ ሐይቅ ልማት ከውጭም ሆነ ከመላው አገር ውስጥ የተሳተፈው ሕዝብ ምስጋና ይገባዋል ብለው ወጣቶች የአገር ሽማግሌዎች እና እኛንም ጨምሮ ሲያመሰግኑ ነበር።
የወንጪ ፕሮጀክት ዲዛይኑ አልቋል፤ ምን ምን ነገሮች ይሰራሉ የሚለው ታይቷል። ፕሮጀክቱ ለየት የሚያደርገው ኅብረተሰቡን የሚያፈናቅል አይደለም። ኅብረተሰቡን ባሳተፈ ሁኔታ ተገንብቶ ለአገልግሎት የሚበቃ በመሆኑ በደስታ ተቀብለውታል። በሁለተኛነት የመሰረተ ልማት ጥያቄያቸውንም የሚፈታ ስለሆነ ደስተኛ ናቸው። ቱሪስት ወደቦታው ሲመጣ ተሽከርካሪ አቁሞ ረጅም ርቀት በፈረስ ነበር የሚጓዘው። አሁን ግን መንግሥት እስከ ሐይቁ ድረስ መንገድ እንዲገባ ለማድረግ ግንባታውን ለኮንትራክተሮች ሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ የመብራት፣ የጤና፣ የቴሌኮም እና ሌሎች ልማቶች እንደሚሻሻሉለት ተገንዝቧል። ሐይቁን በማይረብሽ ሁኔታ ዙሪያው የሚለማበት ሁኔታ አለና ሕዝቡ በሥራ ዕድሉም ሆነ ገቢውን በማሳደግ ረገድ ሰፊ ዕድል ይዟል። ወንጪ በመሰረቱ ከማዕድን ውሃ አንስቶ ለጀልባ ጉዞ እና የደሴት ጉብኝት የተመቸ ብዙ ድብቅ ሀብቶችን የያዘ ነው።
በአካባቢው ተወዳጅ የሆነው የቆጮ ተክል እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታው አካባቢውን የተለየ ያደርገዋል። አካባቢው ደጋማ ስለሆነ በርካታ ሕዝብ አለ፤ የቦታ ጥበትም አለ። ይሄ ልማት ባይመጣ ነዋሪውን ከቦታው አንስቶ ሌላ ቦታ ማስፈር ካልተቻለ በቀር ሕይወቱን ሊቀጥል የማይቻልበት ሁኔታ ነበር። አሁን ሕዝቡ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ዘርፈ ብዙ የሥራ ዕድሎችን ስለሚያገኝ ሕይወቱንም በተሻለ መንገድ ለመምራት ያመቸዋል። ሌላው በንግድ እና በአገልግሎቱ ዘርፍ በቦታው የሚፈጠረውን ዕድል ኅብረተሰቡ ይጠቀምበታል።
ወንጪ ፕሮጀክት ከአምራች ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘም ከቀርከሃ የሚሰሩ ምርቶችን በማቅረብ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ትልቅ የምርት ማቅረቢያ ቦታ ሆኖ እንደሚያገለግል ይታመናል። የአካባቢው ሕዝብ ሥራ የማይንቅ እና ታታሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከወንጪ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ትልቁን ዕድል ለመጠቀም ይችላል።
በዞኑ የሚገኙትን ከሰበታ ጀምሮ እስከ ወንጪ ድረስ ያሉ ከተሞች ከቱሪስት ጋር በተያያዘ የእራሳቸውን ገበያ በመፍጠር ረገድ ይጠቀማሉ ተብሎ ይታሰባል። ደንዲን እና ወንጪ ሐይቆችን የሚያገናኘው የ12 ነጥብ 5 ኪሎሜትር መንገድ በዚሁ ፕሮጀክት ስር ይገነባል። ስለዚህ ቱሪስት ሁለት አማራጭ መንገዶችን ሊጠቀም ይችላል። አንድም በአምቦ በኩል ደንዲን ዞሮ ወንጪንም ሊያይ ይችላል፤ አልያም በወሊሶ በኩል አድርጎ ቀጥታ ወደ ወንጪ ሊጓዝ ይችላል፡፡
ሌላው ከአዲስ አበባ ተነስቶ በወሊሶ አድርጎ ወደወንጪና ደንዲ ይሄዳል። በአጠቃላይ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ላይ ከፍተኛ የኢኮቱሪዝም ሀብት ልውውጥ የሚካሄድበት ስፍራ ያደርገዋል። ለኅብረተሰቡም በጠቅላላ ለውጥ የሚያመጣ ፕሮጀክት ነው ብለን እናስባለን፤ ይህን ፕሮጀክት አምላክ እንዲያሳካልን እንመኛለን።
አዲስ ዘመን፦ ዞኑ ታላላቅ የኢትዮጵያ ጀግኖችን ያፈራ ቦታ ነው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ታሪክ አገር ለማሰተዋወቅ እና የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ አኳያ ምን ታስቧል?
አቶ መገርሳ፦ የአገር ባለውለታዎች ታሪክ ያልታወቀበት ምክንያት የራሳችን ችግር ነው። እንደአገር የሚያግባቡን ነገሮች ላይ ሳይሆን ሁሉም የራሱ ለማድረግ የሚቀራመትበት አሰራር ነበር የተለመደው።
እውቅና ሊሰጠው በሚገባ ደረጃ የጀግኖች ታሪከም አልተነገረም። በዚህ ማንንም አንወቅስም፤ ባለታሪኮቹ እኛ ነበርን፤ እኛ ማስተዋወቅ ነበረብን። እኛ መናገር ነበረብን እንጂ ሌላ እንዲናገርልን መፈለግ አልነበረብንም። እንግዲህ የዛሬ 125 ዓመት ጣልያን አድዋ ላይ ድል ሲደረግ እንደአገሪቷ ካሉት ጄኔራሎች ውስጥ አራትና አምስት የሚሆኑት የዚህ ዞን ተወላጆች ናቸው። ይሄ በደንብ መነገርና መጻፍ አለበት። በአግባቡ ታሪካቸው መቀመጥ ነበረበት። ለዚህ ተወቃሽ የምናደርገው እራሳችንን ነው።
አሁን የእነዚህን ሰዎች ታሪክ የማሰባሰብ እና ጀግኖቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መገልገያዎችን የማሰባሰብ ሥራ እየተከናነወነ ይገኛል። በባህልና ቱሪዝም በኩል የተለያዩ ሰነዶችን በማሰባሰብ በማዕከል ደረጃ ለቱሪስት መዳረሻነት መጠቀም እንዳለብን ወስነናል። በጀግኖቹ ቤተሰብ ደረጃ የተሰባሰቡ መረጃዎች አሉ፤ ይህ ሀብት የዞኑ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ሀብት ነውና።
የኢትዮጵያን ሀብት ከፍ በማድረግ የእነሱን ታሪክ ከፍ ስናደርግ ኢትዮጵያን በመገንባት እና የአገርን አንድነት በማስጠበቅ ረገድ ሰፊ ጥቅም ይሰጣል። ይህን ሥራ ከማከናወን ረገድ ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል። ለነዚህ ሥራዎች ደግሞ ሀብት ይፈልጋሉ። በተቻለ መጠን ሀብት በማፈላለግ እየሰራን ነው። ሥራው የግድ በመሆኑ ከእኛም አቅም በላይ የሆኑትን ጉዳዮች ሊረዱ የሚችሉትን አካላት በማደራጀት ለመስራት እቅድ አለ።
ዞኑ ትላልቅ የንግድ ዞኖች ያሉበት ነው፤ አዲስ አበባ ላይ አንጸባራቂ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ባለሀብቶች ከዞኑ የፈለቁ ናቸው፡፡ እነሱን በማስተባበር የዜግነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። ባለሀብቶቹም ደግሞ ብዙ የልማት ሥራዎችን በመስራት ላይ ያሉ በመሆናቸው ጀግኖች እንዲታወቁ ለማድረግ በሚሰሩ ሥራዎች ረገድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይታመናል። በዚህም የዞኑን ብቻ ሳይሆን የአገርን ገጽታ ከፍ ማድረግ እንችላለን የሚል ሃሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ የወንጪ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለሚፈለግለት አላማ እንዲውል ከአስተዳደሩ፣ አካባቢው ኅብረተሰብም ሆነ ከባለሀብቶች ምን የሚጠበቅ ነገር አለ?
አቶ መገርሳ፦ የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ወንጪ ፕሮጀክት የአንድ ዞን አሊያም የክልል ፕሮጀክት ሳይሆን የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክት ነው። ግንባታውም በፌዴራል መንግሥት ነው የሚከናወነው። እኛ እንደአካባቢ መስተዳድር የእራሳችን የሥራ ድርሻ አለን። የአካባቢውን ማህበረሰብ በማንቃት ለፕሮጀክቱ እንቅፋት እንዳይሆን መስራት አለብን።
አንድ መንገድ ሲሰራ የሚነካቸው መኖሪያ ቤቶች፣ አጥር እና የእርሻ ቦታዎች ስለሚኖሩ በተገቢው አሰራር ቦታው ለልማቱ እንዲውል ማገዝ አለብን። የይገባኛል ጥያቄዎች በወቅቱ መፍትሄ እንዲያገኙ እና የካሳ ክፍያዎች በወቅቱ ተከናውነው ችግሮች እንዲወገዱ በማድረግ ፕሮጀክቱ ለአንድም ሰኮንድ ሳይጓተት እንዲከናወን የሚያስችሉ ሥራዎች ይጠበቁብናል። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ሥራችንን በአግባቡ ለማከናወን ዝግጁ ነን።
ኅብረተሰቡን በተመለከተ ከፕሮጀክቱ ግንባታ ጋር በተያያዘ እራሱን እንዲያዘጋጅ አወያይተናል። ሕዝቡም ዝግጁ መሆኑን ገልጾልናል። ልማቱ የሚፈልገውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል። ሕዝብ በአብዛኛው በሙሉ እምነት ለልማቱ ተባባሪ ነው። ከልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከአሁኑ የአካባቢው ተወላጆች እና አርሶአደሮች ጭምር ሼር ካምፓኒ በማቋቋም ላይ ናቸው።
ቡርቃ ወንጪ በሚል አክሲዮን አቋቁመው አርሶአደሩም ጭምር እንዲሳተፍ እያደረጉ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ በግለሰብ ደረጃም ከልማቱ ተቋዳሽ ለመሆን ጥረቶች አሉ። ይህን ገቢ ለማግኘት እና የልማቱ ተካፋይ ለመሆን የሚደረግ ጥረት አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል። ተጂ፣ አዝጎሪ፣ ቱሉቦሎ፣ ዳሪያን፣ ሃሮ፣ እና ወሊሶ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ለቱሪስቶች ምቹ የሆነ መስተንግዶ እና አገልግሎት ለመስጠት የሚደረግ የልማት ሥራ መጠናከር አለበት።
ቱሪስቶችን ሊስቡ የሚችሉ የተለያዩ ሥራዎችን አዘጋጅተው ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፤ ይህ እንዲስፋፋ የማነቃቃት ሥራውን እናካሂዳለን። ድሮ የሚታወቀው በዞኑ ገቢ ያገኘ ሰው ወደአዲስ አበባ ሄዶ ነው የሚሰራው። አሁን አዲስ አበባ ያለው ወደዚህ እንዲመጣ ነው እያደረግን ያለነው።
ባለሀብቶች በዚህ ረገድ ፍቃደኞች ናቸው። ባለሀብቱ ልማቱን በማገዝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የቅስቀሳ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ባለሀብቶችም በዚያው ልክ እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል። በጣም የተናቁ ከተሞች ከፕሮጀክቱ በኋላ በጣም ተፈላጊ ቦታዎች ይሆናሉና የባለሀብቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች በአካባቢዎቹ የልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ መስፋት አለባቸው። ይህ ደግሞ ምኞት እና ህልም ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ዓመታት በኋላ እውን ሊሆን የሚችል ዕድል ነውና ባለሀብቶችም በስፋት ልማቱን ተንተርሰው ሊሰሩ እንደሚገባ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ከሰላም ጋር ተያይዞ ቀጣይ ምርጫ አለ፤ በዞኑ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን፣ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ምን ዓይነት ዝግጅት አድርጋችኋል?
አቶ መገርሳ፦ በሰባቱም የምርጫ ክልሎች የሚጠበቅብንን ሥራ በሁለት መልኩ እየሰራን ነው። በአንድ በኩል እንደመንግሥት የሚጠበቁብን ኃላፊነቶች አሉ። ለምርጫ ቦርድ የሚያስፈልጉ የቢሮ የቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን እንደመንግሥት ካለብን ግዴታ አኳያ እገዛ አድርገናል። በሁለተኛ መንገድ እንደፓርቲ እንወዳደራለን።
የተዘጋጁ ዕጩዎችን በማስመዝገብ እየሰራን ነው። ከዚህ አኳያ በሰባቱም የምርጫ ክልሎች በየደረጃው ዕጩዎችን አስመዝግበናል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ በግል የሚወዳደሩም በተመሳሳይ ተመዝግበው ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል። ይሄ ሁሉ የሚደረገው ለማንም ተብሎ ሳይሆን ሕዝቡ የእራሱን አማራጭ በማየት ይበጀኛል የሚለውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመርጥ ለማስቻል ነው።
እስከአሁን ሰላማዊ ሥራ ነው ያለው፤ የተለየ ችግር አላየንም። በግለሰብም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ችግርም ደርሶብኛል ብሎ ያመለከተ እንዲሁም ክስ ያቀረበብንም የለም። እኛ ለምርጫው ዝግጅት ምን ዓይነት የሥነምግባር አካሄድ መከተል እንዳለብን መንግሥት አቅጣጫ ስላስቀመጠ እንደግዳጅ ነው የምንሰራው። ችግር ቢፈጠር እኛ ስለሆንን ተጠያቂዎቹ የመጣውን አካል ሁሉ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንዲስተናገድ እያደረግን ነው።
ከዚህም በኋላ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣቸው የጊዜ ሰሌዳዎች መሠረት እንደፓርቲም ሆነ እንደመንግሥት የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን። እስከመጨረሻ የድምጽ ውጤት ይፋ እስከሚሆንበት ጊዜ ይህ ሥራችን ይቀጥላል። ምርጫው ነፃ ግልጽ እና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምን ዓይነት ሥራ ያስፈልጋል የሚለው አጫጭር ስልጠና ለሠራተኞች ተሰጥቷል፤ በቀጣይም ስልጠናዎች ይቀጥላሉ።
በመሃል የሚያጋጥሙ ችግሮችም ካሉ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል። የእኛ ዝግጅት ብቻ ብዙም ውጤት ስለማይኖረው ሕዝቡ በእራሱ ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን የበኩሉን መወጣት አለበት። እኛንም ሌሎችም ከመስመር ከወጣን መግራት መቻል አለበት። ሌሎችም ከመስመር የሚወጡ ካሉ ሕዝብ በማስተካከል በምርጫ ምክንያት ሰላሙን የሚያጣበትን ምክንያት መቀነስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ መገርሳ፦ እኔም ለሰጣችሁኝ ዕድል ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013