አዲሱ ገረመው
ያለምክንያት ጥርሴን ብልጭ ማድረግ የዕለት ሥራዬ ነበር። ያለምክንያት ከት ብዬ እስቃለሁ ፤ የማያቋርጥ ሳቅ፤ ልክ ስቄ ስጨርስ ነፍሴ በሃሴት ስትፈነጥዝ ስጋዬ ጥያቄ ያነሳል። ለምን ትስቃለህ? ለምን ጥርስህን ትገልጣለህ? የሚሉትን የስጋዬን ጥያቄዎች ነፍሴ መሸከም ሲያቅታት ለፈራሽ ስጋ እጅ ትሰጣለች። ጥርሴን ወደውስጥ ሸሽጋ ከንፈሬን ትገጥማለች።
ፊቴ ላይ እንደ ክረምት ዝናብ ዶፍ ሆኖ የሚወርደው እንባዬ አፍንጫዬን ተሻግሮ ከንፈሬን ሲዳስስ አንዱ ከንፈሬ በሽንፈት አዘቅዝቆ ከንፈሬን ለመግጠም ይታገላል። ሳቄን እንባዬ ያሸንፈዋል። መሳቅ እፈልጋለሁ። ምንም እንኳን ከት ብዬ እንደ በፊቱ መሳቅ ብፈልግ ሳቄ ለጋ ነው፤ እድሜ የለውም። ቆይ ግን እድሜ የሌለው ሳቅ ለምን ይወለዳል። ሳቅን የማይሽር፣ እንባን የማያደርቅ ፈገግታ የስጋን አጥር ጥሶ ለምን ብርሃኑን ይረጫል። ለምን የሚለው ጥያቄ ይገርመኛል። የስጋዬ ጥያቄ ምንድነው…? ለምን እንባዬ ፈገግታዬን ያሸንፈዋል። አላውቅም! ብቻ ዝም ብዬ እንጭጭ ሳቄን በጠነከረ እንባ እተካለሁ።
ብሶት ከጭንቀት እንዲሁም ከለምን ጥያቄ ጋር ተባብረው አገጬ ላይ ያበቀሉትን ከርዳዳ ጺሜን እየፈተልኩ፤ ምርኩዝ የደገፈውን የደጃችንን በር ጠልዤ ወደ ውስጥ ገባሁ። ግቢ ማንነት ነው። ደጅ የሰውነት ሚዛን ነው፤ የእውነት ድንበር ነው። እንዴት በር ህያውነቱን በምርኩዝ ያፀናል…? እንዴት ሰው በዘመመ ማንነት ዛሬን ለመሻገር ይደክማል?
በረንዳ ላይ ቁጭ ብላ ዳንቴል የምትሰራው የልጅነት ሚስቴ፤ የቆርቆሮ በሩ በድንገት መከፈት አስደንግጧት ወስፌውን ጥላ ብድግ አለች። ምን ሆነህ ነው የኔ ፍቅር…? ሚስቴ እንባ ፊቴ ላይ የሰራውን ሸንተረር በተመለከተች ቁጥር “ምን ሆነህ ነው?” የሚለው ጥያቄዋ የማላውቀውን ቁስሌን ይቀሰቅስብኛል። ታዲያ ምን ሆነህ ነውን ሽሽት ቀና ብዬ ማየትን እፈራለሁ። ግን ደግሞ ፍቅሯ ያሸንፈኛል። ዛሬ ግን አልፌያት ወደቤት ገባሁ። ተከተለችኝ። ቆይ ምን ሆነህ ነው…? ቅድም በሰላም አልነበር እንዴ ከቤት የወጣኸው? በዚህ ፍጥነት ምን ተከስቶ ነው የተውከውንና የረሳኸውን ንዴትህ ተቀስቅሶ ስሜትህ ላይ እንዲነግስ ያደረገው? የሆንከው ነገር ካለ ንገረኝ… አለችኝ፡፡
የሆንኩትን ነገር ስለማላውቅ ዝም ከማለት ውጪ ፍቅሯ የወለደውን ጥያቄ በመልስ ማርካት ስለማልችል ጥያቄውን በዝምታ አለፍኩት። ቆይ ምንድነው የሆንኩት…? የሚያስጨንቀኝ የሚያስለቅሰኝ ነገር ምንድነው…? “አትናገርም እንዴ ቆይ እኔ ላንተ ምንህ ነኝ…?” አለችኝ። መለስኩላት አንቺማ ለኔ ውዷ ሚስቴ ነሽ አልኳት። “… አሃ ሚስትህ ነኝ ለካ… ለዛ ነው የሆንከውን የምትደብቀኝ፤ ተናገር እንጂ! የጭንቀትህ አካል ለመሆን ከሚስትነት የዘለለ ምን ልሁንልህ…? ንገረኝ እንጂ! ምን ልሁንልህ…?”
ለጥያቄዋ መልስ የለኝም። ምክንያቱም እኔ ራሴ ምን እንደሆንኩ አላውቅም። የሚስቴን ጥያቄ እኔ ራሴ ራሴን እጠይቃለሁ…። ቆይ ምን ሆኛለሁ? ምን ሆኜ ነው ልቤ በሀዘን የተመታው? የለምን ጥያቄዬን መልስ መስጠት ሲያቅተኝ ልቤን፣ ፍቅሬን፣ መልስ አልባ አርጎ እኔን የሰራኝን ፈጣሪዬን መውቀስ ጀመርኩ።
ጭላንጭል ምክንያት ብልጭ አለብኝ። ለምክንያቴ መልስ እንዳሳጥችሁኝ ፣ለምክንያታችሁ መልስ እጡ…! ለችግሮቻችሁ መፍትሄ ተቸገሩ…! እያልኩ ያቆሰሉኝን በእንባዬ የእርግማን ዶፍ አዘነብኩባቸው፡
ሳሎን ሶፋ ላይ የተቀመጠውን የሀበሻ ጀብዱ የተሰኘውን መጽሐፍ ብድግ አድርጌ ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁ። እሺ እራት እንኳን ብላ። ቢያንስ ምግቡ ድካምህን ያስታግስልሃል…! ብትለኝም ዝም ብያት ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁ።
እኔን የቸገረኝ ለሆዴ ምግብ መች ሆነና። እኔን የቸገረኝ የልብ እረፍት ነው። በሰበብ አስባቡ እንድጨነቅ፣ ሳቄ ላይ እንባ እንዲነግስ የሆነበትን ምክንያት ነው፡፡
እንዳዘነች ውስጤ ነግሮኛል። በድካሜ መድከሟ፣ በእንባዬ ማልቀሷን ልቤ ይነግረኛል። ሰሃን ላይ የዘረጋችው ቁርጥ እንጀራ ላይ ወጥ እንደጨለፈች በጣቷ እንጀራውን በወጥ ከለወሰችው በኋላ አፏ ውስጥ ከታ ጉርሻዋን ከጉንጭ ጉንጭ ስታንገላታው ምግቡ ወደ ሆድዋ አልወርድ ብሎ ከጉሮሮዋ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ሲገጥም ይታወቀኛል። አዝንላታለሁ። ምክንያቱም እወዳታለሁ። ብወዳትም ግን ለጥያቄዋ መልስ መስጠት አልችልም። ምክንያቱም እኔም ጥያቄውን እንጂ መልሱን አላውቀውም ። ለምን? አላውቅም፡፡
የሀበሻ ጀብዱን አንድ ሁለት ገጽ እንዳነበብኩ መጽሐፉን ደረቴ ላይ ለጥፌ ያነበብኩትን እያሰላሰልኩ አሸለብኩ። እውነት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ይኖራቸው ይሆን…? መልስ ቢኖራቸው እንኳን መልሶች ሁሉ ጥያቄ አይደሉምን…? እያነበብኩ ተኛሁ። ወዲያው ነቃሁ። እንደ ነቃሁ ለለምን የጥያቄ መልስ ማሰላሰል ጀመርኩ። እያሰላሰልኩ ነጋ፡፡
“ፍቅር ቁርስ ደርሷል” ሚስቴ የመኝታ ክፍሉን በር ተደግፋ የፍቅር ቃል ወደ አልጋዬ ላከች። አምሮባታል። አምሮብሻል የማለት ድፍረት ግን አላገኘሁም። ምክንያቱም ፈራሁ። ቃል ሳላወጣ ከአልጋዬ ፈንጠር ብዬ ተነስቼ እቅፍ አርጌ ልስማት አሰብኩ ግን ፍራቻዬ ሃሳቤን ገደለው። ልቤ ውስጥ በአካል ተቀምጣ ፍራቻዬን ያደመጠች ይመስል የተደገፈችውን በር ዘግታ የአልጋውን ጫፍ ተመርኩዛ አይን አይኔን እያየች ከንፈሬን ሳመቺኝ፡፡
“የኔ ፍቅር ቆንጆ ቁርስ ሰርቼልሃለሁ እሺ! ተነስ ውዴ…” ብላ የደረቀ ከንፈሬን በህይወት ከንፈሯ ካራሰች በኋላ አይኔን ስማ የዘላለሟን መውደድ፣ የእውነት ፍቅሯን ልቤ ላይ ፅፋ ከስጋዬ ላይ ተነሳች። ደረቴ ላይ ክፍቱን ያደረውን መጽሐፍ ገጥሜ አልጋው ላይ ካስቀመጥኩ በኋላ በአይኔ እየተከተልኩ ወደ ሳሎን ገባሁ፡፡
“ፍቅር እንዴት የሚጣፍጥ ቁርስ እንደሰራሁልህ አታውቅም። እኔን የሆነ ጣፋጭ ቁርስ ነው የሰራሁልህ” ብላ ሚስትን በሆነ፣ እናትን በሆነ እጇ አንድ ጉርሻ ጠቅልላ አፌ ውስጥ እንዳስቀመጠች ጉርሻዋን ሳላላምጥ ፍቅሯን በአፌ እንደ ተሸከምኩ ከተቀመጥኩበት በፍጥነት በመነሳት ወደ ውጪ አመራሁ፡፡
“የኔ ፍቅር ደስተኛ ሆነህ ዋልልኝ እሺ…። ስትመለስ ሳቅህን እንጂ እንባህን አታሳየኝ፡፡” አለችኝ። ሚስቴን እወዳታለሁ፤ ፍቅር ስለሆነች አፈቅራታለሁ። ልቧን ሃዘን እንዲዳስሰው አልፈልግም። ግና ብሄር ይሉት ጽንፈኝነት እዚህም እዚያም ሲቀነቀን ከአደባባይ ዘልሎ እጓዳዬ እንዳይጋበ ፈራሁ። ልጅስ ወልደን ለማን እናስረክበው? ፈራሁ ምክንያቴ ይህ ነበር።
ያጎረሰችኝን የፍቅር ጉርሻ ወደ ሞት ሆዴ ካወረድኩት በኋላ ለፅኑ እንባዬ ፅኑ መልስ ፍለጋ የለምን ጥያቄዬን፣ ከልቧ ፍቅር ጋር አዋህጄ እንዲህ ስል ፀልዬ በሩን ከፍቼ ወደ ውጪ ወጣሁ…። ፈጣሪ እባክህ የሚነካከሱ የኢትዮጵያ ህዝቦችን አንድ አድርግልን፤ የውጭው ንክሻ ትዳር ውስጥ እንዳይገባ ታደገን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013