ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ዛሬ ለሀገር ስለሚጠቅሙ አስፈላጊ ወጣቶች እናወራለን። ሀገር የምትፈልጋቸው ወጣቶች ምን አይነት እንደሆኑ እናወጋለን። እስኪ ልጠይቃችሁ ሀገራችን ናት ያልተመቸችን ወይስ እኛ ናት ያልተመቸናት? ይሄን ጥያቄ በመመለስ ቀጣዩን ጽሁፍ እንድታነቡ እጋብዛችኋለው። እኔ ግን ለሀገራችን ያልተመቸናት እኛ ነን እላለው። እኛ ለሀገራችን ብንመች ሀገራችን ለእኛ የማትመችበት ምንም ምክንያት የለም።
እሷ የአባቶቻችን ሀቅ ናት። የነምኒልክ ፣የነአብዲሳጋ የነዘርዐደረስ ርስት። እኛ እንጂ እሷ ውሸት ሆና አታውቅም። ሀገር እኮ የእኔና የእናንተ አስተሳሰብ ናት። በተዛባ አስተሳሰብ የፈጠርናትን ሀገራችንን አትመችም ብሎ ማሰብ ፍርደ ገምደል ያስብላል። የትኛውም ህዝብ በአንድ ልብ በአንድ ሀሳብ ከቆመ ሀገሩን እንደሚፈልገው አድርጎ መስራት ይችላል እላለው። ብዙዎቻችን ወደ ሀገራችን ጣታችንን የምንቀስር ነን። እንደምታውቁት ሀገራችን ኢትዮጵያ ወጣት ካለባቸው የአለም ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት። ግን በሚፈለገው መልኩ ወጣቱ በሀገር ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ አይታይም። ወጣት ለአንድ ሀገር ዋልታና ማገር ነው።
አሁን ላይ በኢኮኖሚ አቅማቸው የአለምን ስልጣኔ በበላይነት የሚመሩ ሀገራት አንድ ወቅት ላይ ወጣቶቻቸውን የተጠቀሙ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ በኢኮኖሚ ኋላ የቀሩ ሀገራት የወጣት ሀይላቸውን ሳይጠቀሙ ያለፉ እንደሆነ መገመት አይከብድም። ሀገራችን ኢትዮጵያ በጉያዋ ብዙ ወጣቶችን ታቅፋ በመካንነት የምትኖር ሀገር ናት። የወጣቱን ሀይል፣ እወቀትና ጊዜ የሚፈልጉ በርካታ አገልግሎቶች ቢኖሩም በተፈለገው መልኩ ጥቅም ላይ ሲውል የሚታይ የወጣት ሀይል የለም። አብዛኛው ወጣት ስራ ፈጥሮ ከመስራት ይልቅ የመንግስትን እጅ የሚጠብቅ ነው። አብዛኛው ወጣት በሱስና በማይጠቅመው ነገር ጊዜውን የሚያጠፋ ነው። አብዛኛው ወጣት ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ በአቋራጭ መበልጸግን የሚናፍቅ ነው።
እንደዚህ አይነት ወጣቶች ለሀገርና ወገን ሸክም ከመሆን ባለፈ ለሀገር የሚፈይዱት አንዳች ነገር የለም። ከትንሽ ነገር ተነስቼ እንዴት ትልቅ ቦታ ልደርስ እችላለሁ የሚሉ ወጣት አስተሳሰቦች ሀገር አፍራሽ እንጂ ገንቢ አይደሉም። ሀገር ራዕይ ያለው ወጣት ትፈልጋለች። የሚሰሩ እጆች፣ በቅንነት የተሞሉ ልቦች ትሻለች። ሀገራችን ኢትዮጵያ ይሄን ሁሉ ወጣት ይዛ ለምን ድሃ የሆነች ይመስላችኋል? በአንድ ሀገር ላይ የህዝብ ቁጥር ወይም የወጣት መብዛት ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡
እጅ መስራት ካለመደ፣ አእምሮ ማሰብ ካልጀመረ፣ ልብ ትህትናን ካልተማረ የወጣት መኖር ብቻውን ጥቅም የለውም። ወጣት ሀይልና ብልጽግና የሚሆነው ከስንፍና ወጥቶ መስራት ሲጀምር ነው። ተምሮ ስራ ከመጠበቅ ስራ ፈጥሮ ለሌሎች እድል መፍጠር ሲቻል ነው። አሁን ላይ በህዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ ሆነው በኢኮኖሚ አቅማቸው የበለጸጉ ብዙ ሀገራት ሞልተዋል። ዋናው የህዝብ ቁጥር መብዛት ሳይሆን የህዝብ የስራ ባህል ነው።
የስራ ባህል ባልዳበረባት ሀገር ላይ የወጣት መብዛት ብቻውን ችግር እንጂ መፍትሄ አይሆንም። የሀገራችን ወቅታዊ ችግርም ከዚህ የዘለለ አይደለም። የተማሩ ብዙ ወጣቶች አሉን..ግን የመንግስትን እጅ የሚጠብቁ ናቸው። ብዙ ወጣቶች አሉን ግን ስራ ፈጥሮ ለመስራት የሰነፉ ናቸው። ብዙ ወጣቶች አሉን ግን ብዙ ጊዜአቸውን በሱስና በማይጠቅም ነገር ላይ የሚያሳልፉ ናቸው።
ሀገር የምትፈልጋቸው ወጣቶች ብርሀናማ ናቸው። በራዕይ የተሞሉ…ከትንሽ ነገር ተነስተው ልቅ ቦታ ለመድረስ የሚታትሩ እንዲህ ናቸው። ይሄን ጽሁፍ የምታነቡ ወጣቶች ሀገራችሁ የእናተን ሀይል ፣የእናተን እውቀት ትፈልጋለችና ለሀገራችሁና ለህዝባችሁ መልካም ነገር ለመስራት ትጉ። የነገዋ የኢትዮጵያ ተስፋ በእናንተ እጅ ውስጥ ነው። ብዙ ያደረገላችሁን ሀገርና ህዝብ ለማገዝ ትክክለኛ ጊዜ ላይ ናችሁና ከስንፍና ወታችሁ ወደ ልማት ግቡ። ዘረኝነት ለእናተ አይመጥንም። ሱስና አልባሌ ነገር ጊዜአችሁን ከማባከን ባለፈ የሚሰጣችሁ ትርፍ የለም። ከትንሽ ነገር ተነስታችሁ ትልቅ ነገር መስራት ይቻላችኋል። ሁሉም ትልቅ ነገር ከትንሽ የተጀመረ ነው። ሁሉም ስኬታማ ሰው ከምንምነት የተነሳ ነው እርግጥ ውስጣቸው አንድ ሀይል ነበር..እርሱም ስኬታማ የመሆን ጽኑ ፍላጎት ነው። ጽኑ ፍላጎት ካላችሁ እመኑኝ የፈለጋችሁትን መሆን ትችላላችሁ፡፡
ብዙዎቻችን ራዕይ አልባ ነን። በወጣትነታችን ውስጥ ለሀገር የሚሆን ምንም የለም..ይሄ ደግሞ ወደ ፊት እንዳንሄድ የሚከለክለን አደገኛ ነገር ነው። መጀመሪያ የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ራዕይ ልበሱ ከዛም ወደ ፈለጋችሁበት መሄድ ትችላላችሁ። ህልማችሁ ሀብታም መሆን ከሆነ፣ ህልማችሁ ገንዘብ ማግኘት ከሆነ፣ ህልማችሁ ቤትና መኪና ከሆነ በህልማችሁ በኩል የምታገኙት ነውና ይቻላችኋል። ራዕይ ገንዘብን መፍጠር ሲችል ገንዘብ ግን ሁልጊዜ ራዕይን መፍጠር ይቸግረዋል። ሁሉ ነገር እንዲኖራችሁ ከሁሉ አስቀድማችሁ መልካም ራዕይን የእናተ አድርጉ። ገንዘብ እያላቸው ራዕይ የሌላቸው ሰዎች አታውቁም? እኔ ግን አውቃለው። የምትፈልጉትን የሚሰጣችሁ ራዕያችሁ ነው።
ራዕይ ያለው ዜጋ በመሆን የሀገራችሁን ትንሳኤ እንድታበስሩ አዛችኋለው። በወጣቱ ዘንድ በብዛት የተለመደውና ጥንካሬአቸውን የሚያጡበት አንዱና ዋነኛው ነገር ምንም የለኝም የሚል አፍራሽ አመለካከት ነው። ትልቅ የሚሆኑት ትንንሽ ነገሮች እንደሆኑ ገና አልገባንም። በአንድ ጊዜ ትልቅ ነገር የምንመኝ ነን። ትላልቅ ነገሮች የተቀመጡት ደግሞ ለሚሰሩና ለሚሞክሩ ነው። አጠገባችን ያለን ትንሽ ነገር ወደ ትልቅ የሚለውጥ ህልምና ራዕይ ያስፈልጋል። ውስጣችን ለመለወጥ የሚሆን በቂ ራዕይ ስለሌለ ሁልጊዜ ሰበበኞች ነን። ልባም ሰው ሰበብ አይፈልግም። ተነስቶ ይሰራል እንጂ። የቁጥር መጀመሪያ ዜሮ አይደል? ዜሮ የሌለበት ትልቅ ቁጥር ታውቃላችሁ? አታውቁም አይደል….ትልቅ ነገር ከፈለጋችሁ ከዜሮ ጀምሩ። ከምንምነት ተነሱ። ታላቅ ነገር ያለው ምንምነት ውስጥ ነው፡፡
ለምሳሌ ብናይ ሊንደን ጆንሰን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት ያልሰሩት ስራ አልነበረም። በልጅነታቸው ጫማ ጠርገዋል፣ የጽዳት ስራ ሰርተዋል፣ ሳህን አጥበዋል፣ አትክልተኛ ሆነው ሰርተው ነበር። በእኛም ሀገር ከትንሽ ነገር ተነስተው ትልቅ ቦታ የደረሱ በርካታ ሰዎችን አውቃለው። እናተም ህልማችሁ ማደግና መለወጥ ከሆነ አሁን ካላችሁበት ቦታ ላይ ተነስታችሁ የምትፈልጉትን መሆን ትችላላችሁ። ለምንም ነገር ህልማችሁ ይቅደም። የምትፈልጉት ድንቅ ነገር ሁሉ ህልማችሁን ተከትሎ የሚመጣ ነው። መጀመሪያ ከሱስ ውጡ። መጀመሪያ ከዘረኝነት ነጻ ሁኑ። መጀመሪያ ለአባቶቻችሁ ስርዐት ተገዙ። መጀመሪያ የተማረ ሳይሆን የተባረከ ትውልድ ለመሆን ጣሩ። ውስጣችሁ ሳይጠራ አስተሳሰባችሁ ሳይስተካከል የምታሳኩት ጥሩ ነገር የለም። ለሀገር የሚሆን ጥሩ ሀሳብ ጥሩ ምኞት ይኑራችሁ። በራዕይ መኖር ስልጣኔ ነው። በዚህ ስልጡን ዘመን ላይ እየኖርን ጊዜን በማይጠቅም ነገር ላይ እንደማሳለፍ የሚቆጭ ምንም ነገር የለም። ጊዜው ለራሳችንም ለሌሎችም መልካም ስራ የምንሰራበት ወቅት ነው። ዝም ብሎ ከመኖር ውጡ። እስካሁን ለራሳችሁም ለሀገራችሁም ሳትበጁ በከንቱ የኖራችሁበት ጊዜ ነበር ከእንግዲህ ግን በዋጋ መኖር አለባችሁ። ለሀገር ስጋት ከመሆን ወጥተን ክብርና ኩራት ወደመሆን መሸጋገር አለብን። የምንደክመውም የምንበረታውም በውስጣችን ተስፋ ሲጠፋ ነው። በውስጣችን ተስፋቢስ ስንሆን በህይወታችንም ተስፋ ቢስ እንሆናለን። በውስጣችን ስንበረታ በአለምም እንበረታለን ይሄ ማለት ነጋችን የሚፈጠረን በእኛው አስተሳሰብ ልክ ነው ማለት ነው። ብሩህ ነገ እንዲኖረን ብሩህ አስተሳሰብ ሊኖረን ግድ ይላል። ከአይሳካልኝም አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ይቻላል..ወደ ይሳካልኛል ሀሳብ መምጣት አለብን። ወጣት ሀይላችሁን አትግደሉት። ሀገራችሁን ሳትጦሯት፣ ለቁም ነገር ያበቃችሁን ድሃ ወገናችሁን ሳትደግፉ ወጣትነታችሁ እንዳያልፍ ፍሩ። ለምንም ነገር የማይበገር ጠንካራ መሰረትን ገንቡ። ምንም ነገር ለማድረግ ሀይሉ አላችሁ። የወጣትነት እድላችሁን ከተጠቀማችሁ እናተ አሁን እድለኛው ሰው ናችሁ። የሚቆጫችሁ..እድለቢስ ሆናችሁ የምትኖሩት በዚህ የወጣትነት ዘመናችሁ፣ በዚህ የጉብዝና ጊዜአችሁ ላይ ለራሳችሁም ሆነ ለሀገራችሁ የሚጠቅም ጥሩ ስራ ሳትሰሩ ካለፋችሁ ነው። በአካልም በአእምሮም ተሰርቶ ያለቀ ማንነት ያስፈልጋችኋል። ስኬት ራሳቸውን ላዘጋጁ ሰዎች የተቀመጠ ነው። ለምንም ነገር የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ስኬት እየወደቁ መነሳት ነው…ወድቆ መቅረት ግን አይደለም። እየደከሙ መበርታት ነው..ደክሞ መቅረት ግን አይደለም። እየተሸነፉ ማሸነፍ ነው..ተሸንፎ መቅረት ግን አይደለም።
ስኬት መንገድ ነው..መድረሻ የሌለው ጥግ አልባ የህይወት ህልቆ መሳፍርት። ራዕይ ከሌላችሁ መነሻም መድረሻም የላችሁም። የመኖርን ትርጉም የምንረዳው በራዕይ ስንኖር ነው። ለዚች አለም ምን ያክል አስፈላጊዎች እንደሆንን የምንረዳው ዋጋ ያለን እንደሆንን ሲገባን ነው። መልካም ነገር ያለው በመራመድ ውስጥ፣ በመሞከር ውስጥ ነው። እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ለራሳችንም ሆነ ለድሃ ሀገራችን የምንጨምረው ነገር የለም። ካልሰራችሁ፣ ካልሞከራችሁ ድህነትን ምርጫ አድርጋችሁ እንደተቀመጣችሁ አስቡት። በስኬት ያልታጀበ ወጣትነት ነገ ላይ ጸጸት ይጠብቀዋል። ምንም ነገር ለማድረግ ትክክከኛው ጊዜአችሁ አሁን ያላችሁበት የወጣትነት ዘመናችሁ ነው። ሁሉን የሚሰጣችሁ መኖራችሁ ሳይሆን በመኖራችሁ ውስጥ የምትገነቡት ታላቅ ፍላጎት ነው።
በምክንያት በታጀበ እውነት ፍላጎታችሁ እንዲመራችሁ ፍቀዱ። ከድንግዝግዝ ህይወት ወጥታችሁ ለሀገራችሁ የሚሆን ብርሀንን አመንጩ። በሌሎች ብርሀን ለመኖር አትሞክሩ ሌሎች በእናተ ብርሀን እንዲመላለሱ ሆናችሁ ወጣትነታችሁን በዋጋ ኑሩት። ለስኬት ተብሎ የተፈጠረ የተለየ ቀን የለም ፡፡ራዕይ ያላቸው ሁሉ ለስኬት የተፈጠሩ ናቸው። ስኬት በራዕይ የሚፈጠር የጽኑ ፍላጎት ፍጻሜ ነው። ምንም ነገር ለማድረግ የምትጠብቁት ጊዜ አይኑር። ለመለወጥ ፍላጎት ካላችሁ አሁኑኑ መለወጥ ይቻላችኋል። እናተ ከተለወጣችሁ የማይለወጥ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር ልክ ሊሆን የእናተን መለወጥ እየጠበቀ ነው።
ለውጥ በእድሜ መጨመር ሳይሆን በአስተሳሰብ መላቅ፣ በአእምሮ መበልጸግ ነው። ለውጣችሁን የአእምሮ እንጂ የአካልና የእድሜ ለውጥ አታድርጉት። በአእምሮ ካልጎለመሳችሁ፣ በአስተሳሰብ ካልበረታችሁ የአካል ጉልምስናችሁ ምንም ነው። ለውጣችሁ ያለው በማሰባችሁ ውስጥ ነው። የነገ ብሩህ ቀናችሁ ያለው በአእምሯችሁ ውስጥ ነው። ከእስራታችሁ ወጥታችሁ ሀገራችሁ የምትፈልጋችሁ ጥሩ ዜጋ ሁኑ። በአካል ጎልምሰው በአእምሮ የደከሙ በርካታ ወጣቶች በዙሪያችን አሉ።
እነዚህ ወጣቶች በአካላቸው የሚያስቡ፣ በፈርጣማ ጡንቻቸው የሚመኩ እንሰሳዎች ናቸው። ጥሩ ከማሰብ ይልቅ ጥሩ የጸጉር ቁርጦችን በመቆረጥ ጭንቅላታቸውን የሚያሳምሩ እንዲህም ናቸው። ጭንቅላት የአሁኑን አለም ያስገኘ የለውጥ ማዕከል ሲሆን አካላዊ ጥንካሬ ብቻ ደግሞ የሚታየውን አለም የሚያጠፋ የድንቁርና ጥግ ነው። ብዙዎቻችን ከአንገት በላይ ውበት ያለ አይመስለንም። አሳራችንን የምናየው ለገጻችን ነው። ውበት ከጭንቅላት እንደሚወጣ ገና አልገባንም። ውበት ጥሩ ማሰብ ነው። ውበት በራዕይ መኖር ነው። ህልምና ራዕይ የሌለው ሰውነት ውበት የለውም። ውበታችሁን ራዕያችሁ ውስጥ ፈልጉት። ሀገራችሁ የምትፈልጋችሁ ታማኝ ዜጋ በመሆን የበኩላችሁን ተወጡ እያልኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013