ዛሬ የዓለም የሬዲዮ ቀን ነው። የካቲት 06/ፌብሪዋሪ 13/ የዓለም የሬዲዮ ቀን ተብሎ እኤአ ከ2012 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ተወስኖ በእርሱም አስተባባሪነት ይከበራል። በእርግጥ የጉዳዩ አመንጪ በስፔን አገር የሚገኝ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋም ቢሆንም፤ የዘርፉን ጥቅም የተረዳው የዓለም የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ይሁንታውን የሰጠው እ.አ.አ በ2010 ነው። እነሆ ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ ይከበራል።
የዓለም የሬዲዮ ቀን ሲታሰብ ዘርፉ ለሰላም፤ ለፍቅር፤ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለአገር አንድነት ያለውን አስተዋጽዖ መርሳት አይቻልም። ጋዜጠኞችም ቆላ ወርደው፤ ደጋ ወጥተው፤ የሌት ቁርና የቀን ሀሩር ሳይበግራቸው ለሰው ልጅ ይተርፋሉ ያሏቸውን ሁሉ ለመቃረም ይለፋሉ። ለፍተውም ለአድማጭ ያደርሳሉ።
የዘንድሮው የዓለም የሬዲዮ ቀንም «መወያየት፤ መቻቻልና ሰላም» በሚል መሪ ቃል ተከብሮ እንደሚውል የተባበሩት መንግሥታት በመግለጫው አስታውቋል። አዎን! ህዝቦች በአንድነትና በፍቅር ለመኖር መወያየት፤ መቻቻል ይገባቸዋል። ሰላምም ያስፈልጋቸዋል።
እነዚህ ሦስት ጽንሰ ሀሳቦች በተለይ ለአገራችን ወቅታዊ ጥያቄዎች ናቸው። ሁላችንም በየደረጃውና በየአካባቢው ተቻችለን ልንኖር ያሻል። ተወያይተን ልንግባባ ይገባል። ልጆች ለማሳደግና አገርን ለትውልድ ለማስተላለፍም ሰላም ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ ነው። ሬዲዮ፤ ቴሌቪዥን፤ ልዩ ልዩ የህትመት ውጤቶችና ዘመነኛው ማህበራዊ ሚዲያ በጥንቃቄ ከተያዙና በኃላፊነት ከተሰራባቸው ትሩፋታቸው በርካታ ነው።
ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት በአገራችን 70 የሬዲዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል 48ቱ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚደመጡ የአካባቢ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው። የየክልል መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በዋና ከተማዋ ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ቁጥራቸው እያደገ መጥቶ 27 ደርሷል። ቀደም ሲል ገጥሟቸው በነበረው ችግር የተነሳ ቁጥራቸው አንሶ ከርሞ አሁን አሁን ያንሰራሩ የሚመስሉት የህትመት ውጤቶችም መረጃ ወደህዝብ የሚያደርሱ መሳሪያዎች ናቸው። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነው ተብሎ የሚገመተው የአገራችን ህዝብም በመደበኛ መንገድ መረጃ የሚያገኘውም ከነዚህ የመገናኛ ብዙኃን ነው።
እነዚህ ሁሉ መሳሪያዎች እንደየፈርጃቸው የየራሳቸው ተደራሲ አላቸው። በአንድነት ግን መላ ህዝቡን ያስተምራሉ፤ ያሳውቃሉ፤ ይሰብካሉ፤ አንዳንዴ ኃላፊነት የጎደለው ሲይዛቸው ደግሞ ለህዝብ መጠላላትና ግጭት ይተርፋሉ። ይኸ ሁሉ የሰው ሥራ ነው።
ይህ ውይይት፣ መቻቻልና ሰላም በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዓለም የሬዲዮ ቀን በባለሙያዎቹ ትከሻ ላይ የሚጥለው ከፍተኛ ኃላፊነት አለ፡፡ የሬዲዮ ባለሙያዎች ወይም ጋዜጠኞች ለህዝብ ከሚያቀርቡት የማስተማሪያና የማሳወቂያ መረጃ ባሻገር የውይይት መድረኮች ሆነው የህዝቡ ሐሳብ በነጻ ሊንሸራሸርባቸው ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች መቻቻልን ሊሰብኩ የሰላምን ጥቅምና ዋጋ ለህዝብ ሊገልጹ፤ ሊያሣዩ ይገባል፡፡
እንዲህ ባለ ማህበራዊ ኃላፊነት የሚመራ የጋዜጠኝነት ሙያ እንደየአግባቡ ባላቸው ተደራሽነት የህዝቡን ንቃተ ህሊና ሊያጎለብቱ ይገባቸዋል፡፡ ሥራቸውም ህዝብ ከበሽታ ራሱን የሚከላከልበትን፣ ከቀደምት አበው የተረከባትን አገር ለቀጣዮቹ የማስረከብ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣበትን፤ አንዱ ሌላውን አውቆ ወንድማማችነቱን የሚያጎለብትበትን መረጃ መሰረት ማድረግ አለበት፡፡
የአገራችን ሬዲዮ ዘርፍና ሌሎች ሚዲያዎችም ይህን ማህበራዊ ኃላፊነት መርህ አድርገው ሊይዙ ይገባል፡፡ በእኛም ሀገር ማህበረሰብ መካከል ውይይት ሊደረግባቸው የሚያስፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ እየተሸረሸረ የሚመስለው የአብሮነታችን ውጤት የሆነው መቻቻልም ይበልጡኑ ሊገነባ በዕውቀትና በሆደ ሰፊነት ሊተገበር ይገባዋል፡፡ ይሄን ሁሉ አድርገን ነገን ለማየት ደግሞ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ እናም ጋዜጠኞቻችንና ሚዲያዎች በዚህ ላይ በኃላፊነት ሊሠሩ ይገባል፡፡
አሁን በአገራችን ውስጥ የሚታየው አጠቃላይ ሁኔታ ውይይት፣ መቻቻልና ሰላምን የግድ የሚል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመገናኛ ብዙኃንና ከጋዜጠኞች በላይ ብዙ አድማጭ ተመልካች ያለው አካል የለምና ቀኑን ሲዘክሩት ባለፈው የሠሩትን ሥራ በማንሳት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚጠብቀንን አያሌ የጋራ ጉዳይና ረዥም ጉዞ በማሰብም ጭምር መሆን አለበት፡፡
በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአብዛኛው የአገራችን ክፍል ተደራሽ የሚሆነው የመገናኛ ዘዴ ሬዲዮ ነው፡፡ እናም የሬዲዮ ጋዜጠኞች እንደቀድሞው መስበክ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ራሱ ስለጋራ ጉዳዩ፤ ስለሀገሩና ስለአካባቢው ሊወያይ ይገባልና ሊያሳትፉት የግድ ነው፡፡ ሕዝቡ አብሮ መኖሩን መንገር ሳይሆን ራሱ ሲያሳይ ዋጋው ከፍ ይላል፡፡ ሰላሙን ጠብቆ ነገውን ያሣምራል፡፡
እናም ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ዘርፎችና ባለሙያዎች ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችን በማዳበር፤ በዘር በሃይማኖት በዝቶ፤ ግን ተቻችሎ የሚኖረውን የህዝባችንን እውነታ በማሳየት፤ እንዲሁም ከግጭት ይልቅ ፍቅርን፤ ከመገፋፋት ይልቅ መተቃቀፍን፤ ከመገፋፋት ይልቅ መተሳሰብን በመስበክና ፍቅር፤ ውይይትና መቻቻል ለሰላም ያለውን ዋጋ በማጉላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን። ዛሬ የሚከበረውም የዓለም የሬዲዮ ቀን መሪ ሀሳብ ከአንድ ቀን በዘለለ የሁልጊዜ መርሃችን ሊሆን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011