አንተነህ ቸሬ
ምርጫ 2013 ሊካሄድ ከ45 ቀናት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲጀመር እቅድ ወጥቶለት የነበረው የመራጮች ምዝገባ ከክልሎች የሚገኘው የቢሮዎች ትብብር በመዘግየቱ፣ የእጩዎች ምዝገባ ቀናት ከተጀመሩም በኋላ ዝግጁ ያልሆኑ የተወሰኑ ቢሮዎች የነበሩ በመሆኑ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችም ተጨማሪ ቀናት በመጠየቃቸው እና የእጩዎች ምዝገባ በመራዘሙ፣ እንዲሁም በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠሙት የቁሳቁስ ማጓጓዝ ተግዳሮቶች በመገምገምና የእጩ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ስራን በተሻለ ጥራት ለማከናወን ወደ መጋቢት 16 ቀን እንዲዛወር መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቆ ነበር። በዚህ መሰረት የተራዘመው የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሆን ተወስኖ መራጮች ሲመዘገቡ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ቦርዱ ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከፓርቲዎች ጋር በተወያየበት ወቅት እንዳስታወቀው አንዳንድ የምርጫ ሂደቶች አፈፃፀማቸው መዘግየት እየተስተዋለበትና መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በተጀመረው የመራጮች ምዝገባ የተመዘገቡት መራጮች ከሚጠበቀው በታች እንደሆነም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በወቅቱ ለጠቅላላ ምርጫው 50 ሺሕ ገደማ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የታሰበ ቢሆንም የተቋቋሙትና የመራጮች ምዝገባን እያደረጉ ያሉት የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር 25ሺ151 ብቻ እንደሆኑና ከ24 ሺህ በላይ የሚሆኑት ግን ሥራ እንዳልጀመሩ፣ የፀጥታና የትራንስፖርት ችግሮች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ችግሮች እንደሆኑ፣ በተለይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የምርጫ ጣቢያዎችን ለማቋቋም በክልሎቹ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች ፈተና ስለመሆናቸው፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ምንም የምርጫ ጣቢያዎች እንዳልተቋቋሙና የመራጮች ምዝገባም እንዳልተጀመረ እንዲሁም የመራጮች ምዝገባው እየተካሄደባቸው ባሉት የምርጫ ጣቢያዎችም ምዝገባው በተፈለገው መልኩ እየሄደ እንዳልሆነ አስረድቶ ነበር። በዚህም ምክንያት የመራጮች የምዝገባ ጊዜ እንደሚራዘም ቦርዱ ገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም መወሰኑን ይፋ አድርጓል። በዚሁ መግለጫው መሻሻሎች መኖራቸውን ይፋ አድርጓል። የምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ በቆዩባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባን ማከናወን መጀመራቸውንና እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 18 ሚልዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን 41ሺ659 የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ እንደሚገኙ አስታውቋል።
በመግለጫውም ‹‹የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ በመጀመሩ፣ ምዝገባ በጊዜው በተጀመረባቸውም ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ መረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች ለመመዝገብ ጊዜ በመውሰዱ፣ የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ቀናት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1500 ሰው ብቻ መመዝገብ በመቻሉ የተነሳ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በመቋረጡ እና ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት ሂደት ክፍተት በመፈጠሩ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ወስኗል።
በዚህም መሰረት፡-
1. የመራጮች ምዝገባ እጅግ ዘግይቶ በጀመረባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ለሶስት ሳምንታት ተራዝሟል ። ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ግንቦት 06 ቀን 2013 የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለት ነው።
2. የመራጮች ምዝገባ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በተስተጓጎለባቸው ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለሁለት ሳምንት ተራዝሟል። ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለት ነው።
3. የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ የመራጮች ምዝገባን የማስጀመር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል›› ብሏል።
የመራጮችን የምዝገባ ጊዜ ከማራዘም ባሻገርም በምርጫ አዋጁ (1162/2013) መሰረት፣ በድምጽ መስጫ ቀን የሰው መጨናነቅ እንዳይፈጠርና እና የዜጎች የመምረጥ መብትን ለማረጋገጥ፣ አንድ ምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችለውን የመራጭ ቁጥር (1500 ሰው ብቻ) መዝግበው በጨረሱ አካባቢዎች ተጨማሪ ንኡስ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ መደረጉን ቦርዱ ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንዱ ከላይ የተገለጸው የምርጫ ቦርድ መረጃ ነው። መረጃው እንደሚያሳየው ለመራጮች ምዝገባ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች (የምርጫ ጣቢያዎች መከፈት፣ የቁሳቁስ አቅርቦት …) አፈፃፀም (በተለይ እስከ ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም የነበረው) ዝቅተኛ መሆኑን ነው። ሊካሄድ ከ45 ቀናት ያነሰ ጊዜ ለቀረው አገር አቀፍ ምርጫ ይቋቋማሉ ተብለው ከታቀዱት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የተቋቋሙትና የመራጮች ምዝገባን እያደረጉ ያሉት የምርጫ ጣቢያዎች የተጠበቀውን ያህል አለመሆናቸው ያስደነግጣል። ከዚህ በተጨማሪም ተቋቁመው የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደባቸው በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች ያሉት ችግሮች ብዙ ናቸው። እነዚህ ችግሮች ከግምት ውስጥ ሲገቡ የመራጮች ምዝገባና ለምዝገባው አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑ የሚያስገርም አይሆንም።
ሌላው መራጮች ድምጽ ለመስጠት እንዲመዘገቡና የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የሚያበረታታው ነገር ሰላማዊና የሰለጠነ የምርጫ ክርክር መኖር ነው። የምርጫ ክርክሮች በምርጫ የሚወዳደሩ ፖለቲከኞች ፖሊሲዎቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው፣ ከሌሎች የምርጫ ተወዳዳሪዎች የሚለዩባቸውን ጉዳዮች የሚያመላክቱባቸውና በምርጫ ቢያሸንፉ ሊያከናውኗቸው ስላቀዷቸው ተግባራት የሚገልፁባቸው መድረኮች ናቸው። እነዚህ መድረኮች መራጩ ሕዝብ የትኛውን ተወዳዳሪ መምረጥ እንዳለበት አቅጣጫ በመጠቆም ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው። በአንዳንድ አገራት፣ የምርጫ ክርክሮች በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ውስጥ ከሚከወኑ ተግባራት መካከል ጎላ ብለው ይታያሉ።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት የምርጫ ክርክሮች ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያግዙ ወሳኝ መሳሪያዎች ናቸው። በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ የተለያዩ ተቋማት ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ መራጮች በምርጫ ክርክሮች አማካኝነት መረጃ እንዲያገኙ እድል መፍጠር ዴሞክራሲያዊ ተሳትፏቸውን በማሳደግ የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን እንዲሁም የመረጧቸውን ፖለቲከኞች የስራ አፈፃፀም የመገምገም እድላቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ ያስችላል። መራጮች የምርጫ ክርክሮችን ከተመለከቱ በኋላ ስለተወዳዳሪዎቹ የነበራቸው ግንዛቤ ከመጨመሩም ባሻገር ተመራጮቹም ቃላቸውን አክብረው በመንቀሳቀሳቸው የተሻለ የስራ አፈፃፀም አስመዝግበዋል።
ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚደረጉት የምርጫ ክርክሮችም ተጀምረዋል። ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) እና በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተላለፉት ክርክሮች ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውንና ተመርጠው ስልጣን ቢይዙ ሊተገብሯቸው ያቀዷቸውን ዓላማዎቻቸውን በመገናኛ ብዙኃን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
በባለፈው ሳምንት የትዝብት ጽሑፍ እንደጠቀስኩት፤ ሰሞኑን ከተመለከትናቸው የምርጫ ክርክር መድረኮች እንደታዘብነው ብዙ ፓርቲዎች አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ ልማዳዊ አሰራር የሆኑትን ስድብና ዘለፋን በመድረኮቹ ላይ ሲጠቀሙ ተስተውለዋል። ከቃላት አጠቃቀማቸው ጀምሮ ሃሳቦቻቸውን የሚያቀርቡባቸው መንገዶች ከአሁኑ መስተካከል እንደሚገባቸው ታዝበናል።
ፓርቲዎች በጥቅሉ ‹‹የፖሊሲ ሰነድ አዘጋጅተናል›› ብሎ ከመናገር ባሻገር፣ ሰነዳቸውን በቅጡ አንብበውና ዝግጅት አድርገው አማራጭነታቸውን በሚያሳይ መልክ ሰነዳቸውን ለመተንተን ሲቸገሩ መታየት የለባቸውም። ይህ የሰነድ ትንተና ችግርም ከአጀንዳ ወጥቶ እዚህም እዚያም መርገጥንና መወነጃጀልን እንደሚያስከትል ታዝበናል፤በመርህ አልባነት የታጀበ የሌሎችን አማራጭ የማጣጣልና የራስን አማራጭ ማቅረብ ያለመቻል አባዜ ውስጥ እንደሚከትም ተመልክተናል።
የሆነው ሆኖ የምርጫ ክርክሮች ተወዳዳሪዎች ፖሊሲዎቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው መድረኮች ናቸው። ስለሆነም በመድረኮቹ መታየት ያለባቸው ሃሳቦች የተወዳዳሪዎቹን ፖሊሲዎች ለመራጩ ሕዝብ ማሳየት የሚችሉና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ አማራጮችን የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው። መድረኮቹ መራጩ ሕዝብ የፓርቲዎቹን አማራጮችና አቋሞች ተመልክቶ ድምፁን ለየትኛው ፓርቲ መስጠት እንደሚኖርበት እንዲወስንና ምርጫውን እንዲያስተካከል የሚያግዙ የሃሳብ ግብይት ስፍራዎች እንደሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።
ባለፈው ሳምንት እንደጠቀስኩት፣ ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚደረጉት የምርጫ ፉክክሮች ገና መጀመራቸው ቢሆንም እስካሁን የተመለከትናቸው ክርክሮች ከተለመደው አካሄድ ተሽለው መገኘት እንደሚኖርባቸው ለማሳሰብ የሚያስገድዱን ጉዳዮች እንዳሉ ታዝበናል።
ከላይ ስለምርጫ ክርክሮች ሰላማዊና የሰለጠኑ መሆን አስፈላጊነት በስፋት የተጠቀሰው የምርጫ ክርክሮች ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱና እንዲመርጡ በማድረግ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስላላቸው ነው። የምርጫ ክርክሮች ከሰለጠነ የሃሳብ ግብይት መድረክነት አፈንግጠው ተለምዷዊው ያልበሰሉ ሃሳቦች የሚስተናገዱባቸው የጭቅጭቅና የስድብ ቦታዎች ከሆኑ መራጮች የምርጫ ካርድ እንዳያወጡና በምርጫው ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት የተገደበ እንዲሆን ያደርጋሉ።
ስለሆነም በቀጣይ በሚካሄዱ የምርጫ ክርክሮች ፓርቲዎች ለአገሪቱ ይበጃሉ ያሏቸውን አማራጮቻቸውን በመረጃ አስደግፈው፤ በርዕዮተ ዓለምና በፖሊሲ ንድፈ ሃሳብ አጎልብተው የሰለጠነ ክርክር በማድረግ መራጩ ሕዝብ የምርጫ ካርድ በማውጣት መሪዎቹን/ተወካዮቹን እንዲመርጥና ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ማገዝ አለባቸው።
በአገሪቱ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣበት እንዲሁም የመራጮችን ቀልብ የሚገዙ የፓለቲካ ፓርቲዎች ባልታዩበት ሁኔታ ዜጎች ለመራጭነት የመመዝገባቸውና የምርጫ ካርድ የማውጣት ፍላጎታቸው በእጅጉ የተዳከመ ሊሆን እንደሚችል ብዙም አያጠራጥርም።
ይሁን እንጂ ምርጫው መካሄዱ የሚቀር አይደለም። ምርጫ ዜጎች የሚፈልጉትን አስተሳሰብ ወደ ስልጣን ለማምጣትና የማይፈልጉትንም ለማስወገድ የሚያስችል መሳሪያ በመሆኑ ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነውም ቢሆን ‹‹ይሆነኛል›› ብለው የሚያምኑበትን የፖለቲካ ኃይል ወደ ስልጣን ለማምጣት የሚያስችላቸውን መሳሪያ (የምርጫ ካርድ) መያዝ ይጠበቅባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ዜጎች በምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ መክረዋል። ለአብነት ያህል ሰሞኑን በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ‹‹6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሊከናወን ጥቂት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል። ዜጎች የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 38 ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው ይደነግጋል። የሀገራችንን የነገ ዴሞክራሲ ለመወሰን፣ ዛሬ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ እናውጣ። ካርድ ለማውጣት ነገ አትበሉ፤ ነገ ከዛሬ ይጀምራል›› ብለዋል።
ቀደም ባለው መልዕክታቸው ደግሞ የምርጫውን ክንውኖችንና ተግዳሮቶችን ለመገምገም ከክልል ፕሬዚደንቶች እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር ባካሄዱት ውይይት የምርጫ ጣቢያዎች ዝግጁነት በአጥጋቢ ሁኔታ መከናወኑን ለማረጋገጥና መራጮች በቀሪው ጊዜ እንዲመዘገቡ ለማስቻል አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ጠቁመው ‹‹ሁሉም ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ አበረታታለሁ። የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ማረጋገጥ የሁላችንም ኃላፊነት ነው›› ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ‹‹አንድ መራጭ በመራጭነት ተሳትፎ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም እጩ ተወዳዳሪ ለመምረጥ የሚችለው በቅድሚያ በመራጭነት ሲመዘገብ ብቻ ነው። በመራጭነት ሳይመዘገብ ቀርቶ በድምፅ መስጫው እለት መራጭ ሆኖ መቅረብ አይችልም። ስለሆነም ቦርዱ ስለመራጮች ምዝገባ መጀመር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲገልጽ በመከታተልና በመመዝገብ የመራጭነትን መብትን በእጅ ማስገባት ያስፈልጋል። በማንኛውም ምርጫ ለመሳተፍ አስቀድሞ በመራጭነት መመዝገብ ቅድመ ሁኔታ ነው። አንድን ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁት መስፈርቶችና የሚያስፈልጉት ሰነዶች በምርጫ ህግና እንደ አስፈላጊነቱም በምርጫ ቦርድ በሚወጡ ዝርዝር መመሪያዎች ይቀመጣሉ። ነገር ግን እነዚህ መስፈርቶች ተገቢና አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ እንጂ አንድን ሰው ያለ አግባብ ከመራጭነት የሚያገሉ አይሆኑም።
የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው በምርጫው ዓይነት ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ አማካኝነት ሲሆን የምዝገባ ቦታውም መራጮች በሚኖሩበት ቀበሌ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው። ሆኖም በአርብቶ አደር አካባቢዎች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያ በማቋቋም የመራጮችን ምዝገባ ማከናወን ይቻላል። አንድ ሰው ለመራጭነት በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የራሱ የሆነ የመራጮች መዝገብ ይኖረዋል›› ይላል። አንድ ሰው ለመራጭነት ለመመዝገብ ወደ ምርጫ ጣቢያ በሚሄድበት ማሟላት የሚጠበቅበትን ሰነዶች ዝርዝርም ቦርዱ በተለያዩ መንገዶች እየገለፀ ይገኛል።
በሌላ በኩል ‹‹የመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ (ቁጥር 6/2013)›› ‹‹የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ›› ማለት አንድ ሰው በመራጭነት ሲመዘገብ ከተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ የሚሰጠው የመራጭነት ማረጋገጫ እንደሆነ ያስረዳል።
ስለሆነም የምርጫ ካርድ ለመራጭነት የሚሰጥ ማረጋገጫ በመሆኑና አንድ መራጭ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም እጩ ተወዳዳሪ ለመምረጥ የሚችለው በቅድሚያ በመራጭነት ሲመዘገብ (የምርጫ ካርድ ሲይዝ) ብቻ ስለሆነ ዜጎች የምርጫ ካርድ በመያዝ በምርጫው እንዲሳተፉና ‹‹ባልመረጥነው አካል እየተገዛን ነው›› ለሚለው አቤቱታቸው ራሳቸው ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። ለማንኛውም … የምርጫ ካርዷን በእጃችሁ አስገቡ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013