የህፃናት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መሐመድ በሽር፤ የህፃናት ጥርስ እስከ መች መብቀል አለበት? ካልበቀለ ህጻናት መች ወደ ባለሙያ መሄድ አለባቸው? የጥርስ መብቀል ከተቅማጥ በሽታ ጋር ይገናኝ ይሆን? ለሚሉትና ለሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ያካፈሉንን እውቀት እነሆ።
ብዙ እናቶች ልጆቻቸው ጥርስ መች ማብቀል እንደሚጀምሩ በግልፅ ስለማያውቁ ልጄ እስካሁን ጥርስ አላበቀለም/ አላበቀለችም ብለው ጤና ተቋም ሲመጡ ማየት የተለመደ ነገር ነው። አንዳንድ እናቶች ደግሞ እስከመቼ ድረስ ሊያድግ እንደሚችል አያውቁም፤ በዚህ የተነሳ እራሳቸውን ሲያስጨንቁ ይታያል።
የህፃናት የጥርስ እድገት በጨቅላዎች እና በልጆች ድድ ውስጥ የጥርስ መብቀልን ይመለከታል። ይህ የሚጀምረው ብዙውን ጊዜ ልጆች ከስድስት እስከ ስምንት ወር ዕድሜ ሲሆናቸው ነው። ህፃናት በ30 ወራት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ 20 ጥርሶች ቦታቸውን ይይዛሉ።
አንዳንድ ልጆች ግን ከስምንት ወር ዕድሜያቸው በኋላም ቢሆንም ምንም አይነት ጥርስ ላያሳዩ ይችላሉ፣ ይህ ግን ብዙውን ጊዜ የተለመደ ቢሆንም እስከ 13 ወር ምንም ጥርስ የማብቀል ምልክት ካልታየ ለባለሙያ ማሳየት ተገቢ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ሁለቱ የታችኛው የፊት ጥርሶች (የታችኛው ኢንሲዘሮች) ቀድመው ይበቅላሉ። ቀጥለው ሁለቱ የላይኛው የፊት ጥርሶች (የላይኛው ኢንሲዘሮች) ይበቅላሉ።
ከዚያም ሌሎች የወተት ጥርሶች (ኢንሲዘሮች)፣ የላይኛውና የታችኛው መንጋጋዎች፣ የውሻ ክራንቻዎች፣ በመጨረሻም የላይኛውና የታችኛው መንጋጋዎች ይበቅላሉ።
ልጆች ጥርስ ማብቀል ሲጀምሩ ምን አይነት ምልክቶች ያሳያሉ?
ልጆች ጥርስ ማብቀል ሲጀምሩ መነጫነጭ ወይም መበሳጨት፣ ጠንካራ ነገሮችን መንከስ ወይም ማኘክ፣ ልጋግ ማዝረብረብ የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ። የድድ ማበጥና መጠንከር፣ ምግብ እምቢ ማለት፣ የእንቅልፍ ለመተኛት መቸገርም ሌሎቹ መለያዎች ናቸው።
መፍትሄው ምንድን ነው? በዚህ ጊዜ ማድረግ ያለብን ልጆች የማያኝኳቸውን ቀዝቃዛ ነገሮች መስጠት። ለስለስ ያሉ ምግቦችን መስጠት፣ በቀስታ ጥርስ የሚበቅልበትን ቦታ በእጅ መንካት። በዚህ መንገድ የልጆችን የጥርስ እድገት ማገዝ እና የተሳካ ማድረግ ይቻላል።
የህፃናት ህክምና እሰፔሻሊስቱ ዶክተር ፋሲል መንበረ ጥርስ ያወጡ ህፃናት የምግብ ፍላጎታቸው በምን ምክንያት ይቀንሳል የሚለውን እንደሚከተለው ያስረዱናል።
ስለ ህፃናት ምግብ ፍላጎት መቀነስ ከማውራታችን በፊት በመጀመሪያ የህፃናት እድገትን ማወቅ ይኖርብናል:: አንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ ከአራት እስከ አምስት ወር የተወለደበትን ክብደት እጥፍ ያድጋል፣ ከዓመት በኋላ ደግሞ በሶስት እጥፍ ይጨምራል:: ለምሳሌ የወሊድ ክብደቱ ሶስት ኪሎ ግራም የነበረ ልጅ በአራት ወሩ ስድስት ኪሎ ግራም ይሆናል።
ከዓመት በኋላ ደግሞ ከዘጠኝ እስከ አስር ኪሎ ግራም ይደርሳል ማለት ነው:: ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ግን የሚጨምሩት ከሁለት እስከ ሶስት ኪሎ ግራም ብቻ ነው:: ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ምንም ኪሎ ሳይጨምሩ ወራት ሊቆጠሩ ይችላል:: ይሄ የሚያመለክተው ህፃናት በመጀመሪያው አንድ ዓመት በጣም ፈጣን እድገት ሲኖራቸው ከሁለት ዓመት በኋላ ግን እድገታቸው ቀነስ የሚል መሆኑን ነው። ስለዚህ የምግብ ፍላጎታቸው በዚያው ልክ ቀነስ ሊል ይችላል::
የህፃናት የምግብ ፍላጎት መቀነስ ምክንያቶች ምንድናቸው? እድሜ፡- ቀደም ሲል እንደተገለጸው እድሜ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ለመጥቀስ ተሞክሯል። የደም ማነስ (Anemia)፡- ህፃናት በብዙ ምክንያቶች የደም ማነስ ሊገጥማቸው ይችላል። በእኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ምክንያቱ የብረት እጥረት (Iron deficiency) ነው፤) የምግብ እጥረት (Mealnutrition) እና የንጥረ ነገሮች እጥረት ለምሳሌ:- የዚንክ የሰሌንየም እጥረት (Zinc and Selenium deficiency) ይሄ ብዙ ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ ያላገኙ ህፃናት ላይ ይታያል።
ህመም፡- ህፃናት ማንኛውም አይነት ህመም ወይም ኢንፌክሽን ከያዛቸው የምግብ ፍላጎታቸው በእጅጉ ይቀንሳል። ለምሳሌ የቶንሲል ህመም፣ የጆሮ ህመም፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እና የመሳሰሉት ሲከሰቱባቸው፤ እንዲሁም ጣፋጭ ምግብ በብዛት የሚወስዱ ከሆነ ሌላ ምግብ የመመገብ ፍላጎታቸው በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል። አልፎ ተርፎም ለአላስፈላጊ ውፍረት (obesity) ሊዳርጋቸው ይቻላል።
ፈሳሽ ነገሮችን እና ጁስ አብዝቶ መጠቀም፡- ልጆች ጨጓራቸው ትንሽ ስለሆነ በፈሳሽ ነገሮች ከተሞላ ሌላ ምግብ አልበላም ይላቸዋል። ህፃናት ጁስ በጣም ይወዳሉ፤ ሆኖም ወላጆች መጥኖ መስጠት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ እድሜያቸው ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት ያሉ ህፃናት በቀን ከ120 እስከ 180 ሲሲ ጁስ በላይ መውሰድ የለባቸውም። ከዚህ መጠን በላይ ያላቸውን ፍላጎት ከጁስ ይልቅ በወተት መተካት እንዳለባቸው ይመከራል።
የቤት ውስጥ ተፅዕኖ እና ጭንቀት፡- ቤት ውስጥ በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጭቅጭቅ ደብድብ ሲደርስባቸው ወይም ሐዘን እና መከፋት ካጋጠማቸው ህፃናት የምግብ ፍላጎታቸው ይወርዳል።
እንቅስቃሴ አለማድረግ፡- ህፃናት የአዕምሮ እና የአካል እድገታቸው እንዲፋጠንና ሰውነታቸው ጠንካራ እንዲሆን እንዲሁም የተመገቡት ምግብ በአግባቡ እንዲፈጭ በቀን ቢያንስ ከ30 እስከ 60 ደቂቃ ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህን የማያደርጉ እና በተለይ ጌም እና ቴሌቪዥን ላይ የሚውሉ ከሆነ ህፃናት የምግብ ፍላጎታቸው ዝቅ ሊል ይችላል።
ወላጆች ይሄን በመረዳት ለህፃናት እድገት ተገቢውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ዶ/ር መሐመድ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013