ታምራት ተስፋዬ
በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ጎዳና ላይ በተሽ ከርካሪ ጋሪ ላይ ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶና ሌሎችንም ፍራፍሬዎች ደርድረው ፡‹‹ኪሎ በሃያ፣ በሰላሳ ብር›› እያሉ በመሸጥ ህይወታቸውን የሚያስተዳድሩም ሆነ የፍራፍሬ ጭማቂ ቤቶችን ከፍተው ጭማቂ እና የአትክልት ምርቶችን የሚሸጡ ነጋዴዎች ለአርባ ምንጭ ከተማ እና አርሶ አደሮች የሚገባቸውን የድካምና ልፋት ዋጋ ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡ ነጋዴዎቹ ብቻ አይደሉም ማናቸውም ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ አሳ … በመጠቀም ጤናማ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች፣ለአርባ ምንጭ ምድር ያላቀረቡት ምስጋና አለ።
የጋሞ ምድር ልጆች ግን ክብርም ሆነ ገንዘብ አልተሰጠንም በሚል ሒሳብ ውስጥ መግባት አይፈልጉም፡፡ አርሶአደሮቹም ሆኑ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች በመጫን በመላው የአገሪቱ ከተማዎች የሚያደርሱ አሽከርካሪዎች ዘወትር በስራው የተጠመዱ ናቸው፡፡
ጋሞ ዞን በሀገር ደረጃ ከሚታወቅበት ከቱሪስት መስህብነቱ በማይተናነስ መልኩ በፍራፍሬ አምራችነቱ ይታወቃል፡፡በከተማዋ ዋና መንገድ ዳርቻዎች አይን የሚስቡና‹‹ሳልቀምስማ አላላፍም››የሚያሰኙ፣የማንጎ፣ የሙዝ ፣የአፕል፣ፓፓዬ እና የጬንቻ ኮክን የመሳሰሉ ከምድሪቱ የሚፈልቁ የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች ማራኪ በሆነ መልኩ ደርድረው ለገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎችም የከተማዋ ውበት ብቻ ሳይሆን ድምቀትም ጭምር ናቸው፡፡
በተለይ በከተማዋ በሰሜንና ደቡባዊ አቅጣጫ መንገዱን ተከትሎ የተንጣለለው የሙዝ ማሳ ለአርባምንጭ የኢኮኖሚ ዋልታና ማገር ነው፡፡ከዚህ ስፍራ በየቀኑ የሚጫነው የሙዝ ምርት የመላውን ኢትዮጵያ ከተሞች ያጎርሳል ።
በጋሞ ዞን በፍራፍሬ አምራችነታቸው ከሚታወቁ ወረዳዎች ዋነኞቹ ደግሞ አርባምንጭ ዙርያ ወረዳና ምዕራብ አባያ ወረዳዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚመረቱ የሙዝ፣ማንጎ፣ፓፓዬ እና አቮካዶ ምርቶች ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዓመት እስከ ዓመት የማይቋረጠው የሙዝ ምርት በቀን በአማካይ ከ70 እስከ 80 መኪኖች እየተጫነ በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም ድንበር አቋርጦ ወደ ኬንያ፣ሶማሌ እና ጅቡቲ ገበያ ይደርሳል፡፡
በዚህ የምርት ሰንሰለት ከገበሬው አንስቶ ነጋዴው ደላላው ባለመኪኖች ፣ አሽከርካሪዎች፣ ረዳቶች፣አውራጅና ጫኞችን ጨምሮ በርካቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከብዝሀ ሀብት እንዲሁም ከንግዱ ሰንሰለት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡በርካታ የፍራፍሬ ንግዱ ተዋናዮችም ከተማ ላይ ሆቴልን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ብሎም የንግድ ተቋማት በመክፈት ለብዙ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡ከፍራፍሬ ምርቱ ንግድ ገቢ የሚቋደሱት ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፡፡ መንግስትም ሆነ ከተማዋ ከቀረጥ የሚያገኙት ገቢ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ምርቱ በመላ ኢትዮጵያ ብሎም ጎረቤት አገራት ተደራሽ እንደመሆኑ ተጠቃሚዎች በአርባ ምንጭ ላይ ብቻ የሚወሰኑ አይደሉም፡፡በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ በንግድ ሰንሰለቱ ተሳታፊዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
በአካባቢው ያገኘናቸው አርሶ አደሮች በአንፃሩ የድካማቸውን ያሕል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። የሙዝ ምርት አምራቾች የሆኑት ድንበሩ ሶኔ እና እሸቱ ቻላሞ እንዳረጋገጡትም በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት አባያና ጫሞ ሃይቆች ማሳቸውን አጥለቅልቆ ፣ምርታቸውን በመውሰድ ለከባድ ኪሳራ አጋልጧቸዋል፡፡
ያለፈ ቁስላቸው በአግባቡ ሳይሽር ከአመት አመት ምርታቸውን በደላሎች ምክንያት ዋጋ ማጣቱ ደግሞ ይበልጥ አበሳጭቷቸዋል፡፡ አምራቾቹ እንደገለፁትም፣ምርቱ ከእነርሱ እጅ ወጥቶ ተጠቃሚ ዘንድ እስኪደርስ ባለው የንግድ ሰንሰለት ውስጥ በርካታ ደላሎች ይሳተፉበታል፡፡
ምርቱ ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ በትንሹ ከአምስት እጥፍ በላይ ዋጋ ተጨምሮ ይሸጣል፡፡በሂደቱም ከአምራቾቹ ይልቅ ደላሎች ይበልጥ ተጠቃሚ ናቸው። አምራቹ በአንፃሩ የድካሙን ያሕል ተገቢውን ጥቅም አያገኝም፡፡ከደላሎቹ አዙሪት ለመላቀቅ ቢፈለግ እንኳን በጥቅም የተሳሰሩ በመሆናቸው ምርቱ ገበያ እንዳያገኝ ያስደርጋሉ፡፡
ዘመናዊ መስኖን አጥብቀው የሚሹት አምራቾች፣‹‹የድካም ዋጋችን ምላሽ አግኝቶ ተጠቃሚነታችን እንዲጨምር በሌሎች ክልሎች ብሎም ዞኖች ሲመረቁ እና ሲሰሩ የሚታዩ ዘመናዊ የመስኖ መሠረተ ልማቶች እኛም ጋር እንዲሰሩ እንፈልጋለንም››ይላሉ፡፡አርሶ አደሩ ወደ ዘመናዊነት ተሸጋግሮ ይበልጥ ምርት እና ምርታማነቱ እንዲጨምር የሚመለከታቸው አካላት ፈጣን ስራ መስራት እንዳለባቸውም ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡
በእርግጥም ፍላጎታቸውን በመረዳት መጠነኛ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ ቢያደርግ ከአካባቢ የምርት አቅም አንፃር ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል መረዳት በጣም ቀላል ነው፡፡ስድስት የሚሆኑ ታላላቅ ወንዞች፣ ባሉበትና ከፍተኛ ምርት በሚታፈስበት አካባቢ ያሉት የመስኖ ግንባታዎች ረጅም አመታትን ያስቆጠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013