ጠንካራ መንግሥት ለማምጣት በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረግን ይጠይቃል!
ጠንካራ መንግሥት ለማምጣት በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረግን ይጠይቃል!
ሀገራችን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ተቃርባለች። በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሀገሪቱ ታሪክ ባልተለመደ መልኩ 123 የግል ተወዳዳሪዎች በርካታ የምርጫውን ሂደቶች አልፈው በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ይገኛሉ።
መራጩ ህዝብም በምርጫው ድምፁን መስጠት የሚያስችለውን ካርድ መውሰዱን ቀጥሏል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመራጮች ምዝገባው የተቀዛቀዘ ነው ሲሉ የተለያዩ ወገኖች ሲገልጹ ነበር። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንኑ ማረጋገጡ ይታወሳል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት የመራጮች ምዝገባ ሂደትን መርምሮ ችግሮች ማጋጠማቸውን አመልክቷል። በዚህም የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ መጀመሩን ጠቁሟል። ምዝገባው በወቅቱ በተጀመረባቸውም ቦታዎች በመራጮች ምዝገባ መረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች ለመመዝገብ ጊዜ መውሰዱን አይቷል፤ የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ቀናት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1500 ሰው ብቻ መመዝገብ በመቻሉ የተነሳ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በመቋረጡ እና ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት ሂደት ክፍተት መፈጠሩንም ተመልክቷል። በእነዚህ ላይ ተመስርቶም የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል።
ቀደም ሲል ታይቶ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ ከመቀዛቀዝ ለማውጣት በተከናወኑ ተግባሮች ለውጦች ታይተዋል። በአጠቃላይ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 18 ሚሊዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች መመዝገባቸውን ከቦርዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ የሚካሄድበት ቀን እንዲራዘም ውሳኔ ላይ መድረሱና ተጨማሪ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈቱ መንግሥት ህዝቡ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍና በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት እንዲጣል ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያመለክታል፤ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ዕድልም ያሰፋል። በአጠቃላይ በሚመዘገበው መራጭ አኀዝ ላይም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ያስችላል።
የመራጮች መመዝገቢያ ጊዜው ከመራዘሙ እንዲሁም ምዝገባው ባልተጀመረባቸው ክልሎችና አካባቢዎች ምዝገባው ከመጀመሩ ጎን ለጎን ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ የሚያስችሉ የቅስቀሳ ሥራዎች መጠናከር ይኖርባቸዋል፤ መራጮች የምዝገባ ጊዜ አለን በማለት እንዳይዘናጉ ማድረግ ይገባል።
መንግሥት በዚህች ሀገር ከዚህ በኋላ ስልጣን የሚያዘው በዴሞክራሲያዊ አግባብ በምርጫ ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በተደጋጋሚ እየገለጸ ነው። በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህንኑ አረጋግጠዋል። የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያስፈነጥር መሆኑን አስታውቀው፣ በጋራ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ያስፈልገናል ሲሉ ማሳሰባቸውም ይህንኑ የመንግሥት ጽኑ አቋም ያመለክታል።
ይህ የመንግሥት ቁርጠኝነት በዜጎችም መደገም ይኖርበታል። በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን ዜጎች በተለያዩ መንግሥታት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል። ይህ መስዋዕትነት ፍሬያማ እንዲሆን አሁን ያሉ ዜጎች በዘንድሮው ምርጫ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ትውልዶችን የበላው የዴሞክራሲ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንዲጀምር ማድረግ አለባችሁ።
ሀገራችን ጥሩ የምርጫ ታሪክ እንደሌላት ይታወቃል። ዜጎች ባለፉት ምርጫዎች የተካዱ እንደመሆናቸው ለምርጫ ብዙም ትኩረት ላይሰጡ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል። ምርጫን በጥርጣሬ በማየት ንቁ ተሳትፎ አለማድረግ ይኖራል። ዜጎችን ከዚህ ጥርጣሬ ለማውጣ መቀስቀስ ይገባል። በዚህ በኩል ምርጫ ቦርድ እያከናወነ ካለው ተግባር በተጓዳኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎችና የሲቪክ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው። ዜጎችም ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ይህን ዘመንና ያለፉትን ዘመናት መመርመር ይጠበቅባችኋል።
እንደሚታወቀው ሀገራችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆና ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች። ሌሎች ስኬቶችንም ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሰች ነው። በሌላ በኩል ሀገሪቱ በውስጥም በውጭም ከፍተኛ ፈተናዎች አሉባት። በምርጫ ስልጣን መያዝ የሚያስችላቸውን ዕድል ያቃጠሉ አካላት አረፈው አልተቀመጡም። ሀገራዊው ለውጥ ይበላናል ብለው የሰጉ ቡድኖች ይህን ለውጥ ለማደናቀፍ የማይሰነዝሩት ጥቃት የለም። በሀገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚታዩት ጥቃቶችና ሴራዎች ሁሉ ምርጫውን ለማሰናከል እየተፈጸሙ ያሉ ናቸው። ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖች በኢትዮጵያ የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ድጋፍም አላቸው።
እነዚህን አካላት ሁሉ ለማሳፈር በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል። ሀገሪቱ እያከናወነቻቸው የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማስቀጠልም የሚቻለው በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ጠንካራ መንግሥት ወደ ስልጣን እንዲመጣ በማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013