የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራችን- ለሀገርም፣ ለወገንም!

 ሠብዓዊነት- በጊዜ፣ በቦታ፣ በሁኔታና ሌላም ጉዳዮች አይታጠርም። በየትኛውም ቦታ፣ በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ስለ ሰውነት ሲባል የሚፈጸም ሰናይ ተግባር ነው። ይሄን መሰሉ የሰው ልጅ ሠብዓዊ ተግባር ለሰው ልጆች ሲገለጽ ደግሞ፤ አንድም ሰዎች የሰዎችን ችግር የማቅለል መሻትን የሚያሳካ፤ አለፍ ሲልም የሰው ልጅ ለሰው ልጅ ሕይወት ደራሽነትን የሚያረጋግጥ ነው።

ሁለተኛም፣ ሰዎች ስለ ሠብዓዊነት አልያም በጎነት በሚያከናውኑት ተግባር የሀገርን ሁለንተናዊ ልማት እውን የማድረግ ተግባራትን ይፈጽማሉ። በዚህም ሰዎች በበጎነት ሲሰማሩ የሰው ልጆችን መጥቀም የሚያስችሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይሰማራሉ። ሀገርን እንደ ሀገር ወደ ልማት ለማሸጋገር፤ የሰው ልጆችንም በሁሉም መልኩ የሚያግዙ የወገን ደራሽነታቸውን ያረጋግጣሉ።

እነዚህ ተግባራት ከሚከናወኑባቸው እና ሰፋ ያለ የማኅበረሰብ ክፍል ከሚሳተፍባቸው ወቅትና ሁነቶች መካከል ደግሞ የክረምት ወቅት አንዱ ነው። ምክንያቱም፣ የክረምት ወቅት ተማሪው ከትምህርት ቤት ውጪ ሆኖ በየአካባቢው የሚያሳልፍበት ወቅት ነው። መምህራንም እንዲሁ፣ ለቀጣዩ ዓመት ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት እና ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ትብብር የሚያጠናከሩበት ጊዜያቸው ነው።

በእዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ታዲያ፣ እንደ ሀገር የክረምት ወቅት አንዱ እና ዋነኛ የበጎ ተግባር መፈጸሚያ፤ የሠብዓዊነት መግለጫ ወቅት ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል። ከእዚህ አኳያ እንደ ሀገር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዘመቻ ሥራነት ወጥቶ፤ በተጠናና በተደራጀ መልኩ እንዲከወን በመደረጉ፤ ከዓመት ዓመት፤ ከጊዜም ወደ ጊዜ ከፍ ያለ ውጤት እየተገኘበት ነው።

ምክንያቱም፣ ሥራው አደረጃጀት ተፈጥሮለት እና እቅድ ተነድፎለት እየተሠራ በመሆኑ፤ ምን ያህል ሰው ለእዚህ ተግባር ተሰማራ፤ ምንስ ሥራ ተሠራ፤ በሥራው ምንስ ውጤት ተገኘ፣… የሚሉ ጉዳዮች የሚታወቁበት ሆኗል። በዚሁ አግባብ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎችም መስኮች በሚከናወኑ የበጎ አገልግሎት ተግባራት ሚሊዮኖች እየተሳተፉ በቢሊዮኖች የሚተመን ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

እነዚህ ሥራዎች ደግሞ፣ አንድ እንደ ሀገር ከፍ ያለ የልማትና እድገት አቅም እየተገኘባቸው ነው። ለምሳሌ፣ በክረምት የበጎነት ተግባር አገልግሎት ከሚከናወኑ ሥራዎች አንዱ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ነው። በዚህ መሠረት ቢሊዮን ችግኞች እየተተከሉ ለሚሊዮኖች ጉርስ መፍጠር፤ እንደ ሀገርም የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት ተችሏል።

ከእዚህ በተጓዳኝ፣ በአቅመ ደካሞች የቤት ልማት (እድሳትም፣ አዲስ በመሥራትም) በመሳተፍ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን የቤት ባለቤት ማድረግ ተችሏል። በመንገድ ልማት፤ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት ጥገናና እድሳት፣ ብሎም ግብዓት ማሟላትን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ፋይዳቸው የጎላ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ በኩልም፤ በአንድ በኩል በትራፊክ መዘጋጋት ምክንያት የሚፈጠር የጊዜም፣ የገንዘብም ብክነትን ማስቀረት ያስቻለ፤ በሌላ በኩል በትራፊክ አደጋ የሚፈጠርን የሕይወት መጥፋት፤ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም አደጋ መቀነስ ያስቻለ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

በተመሳሳይ የክረምት የትምህርት ማጠናከሪያ መርሃ ግብርን ከማከናወን ጀምሮ፤ የደም ልገሳን ጨምሮ ሌሎችም የሚገለጡ ሥራዎችም አሉ። ለምሳሌ፣ በደም ልገሳ የሚደረገው የበጎነት ተግባር፤ አንድ ሰው ደም በመስጠቱ ብቻ የአንድን ወገን ሕይወት መታደግ የተቻለበት ነው። ምክንያቱም፣ ወላድ እናትን ጨምሮ በአንድም በሌላ ምክንያት በየጤና ተቋማት ደም የሚፈልጉ ወገኖች አሉ።

እናም ዛሬ ላይ የምንለግሳት አንዲት ዩኒት ደም፣ እነዚህን በደም እጦት ምክንያት ሕይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ እናቶችና ሌሎችም ወገኖችን ሕይወት የምትታደግ መሆኗን መገንዘብ ተገቢ ነው። በመሆኑም፣ የክረምቱን ወቅት ምክንያት በማድረግ የምንፈጽመው የበጎነት እና የሠብዓዊነት ተግባር፤ አንድም ለሀገራችን ልማትና እድገት የድርሻችንን የምንወጣበት፤ ሁለተኛም የወገኖቻችንን ችግር የምናቃልልበት፣ ሕይወትም የምንታደግበት እንደመሆኑ በቀሪዎቹ ጊዜያት ይሄንን በጎነትና የሠብዓዊነት ተግባር ከፍ አድርጎ መፈጸም ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You