የትግራይ ሕዝብ ናፍቆት ጦርነት እና የጦርነት ወሬ አይደለም!

በብዙ የሕይወት ፈተናዎች ውስጥ ለሚገኘው የትግራይ ሕዝብ አሁን ላይ የሚያስፈልገው ጦርነት እንዳልሆነ ለማንኛውም ጤናማ አእምሮ፣ መንፈስ እና ልብ ላለው ሰው የተሰወረ አይደለም። በእርግጥ ከትናንት ዛሬ ሊያስከትል ከሚችለው መጠነ ሰፊ ጥፋት እና ውድመት አኳያ ጦርነት እና የጦርነት ወሬ የሚናፍቅ ሕዝብ አለ ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር ተጨባጭ ነገር የለም።

ዘመኑ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ፣ በንግግር እና በውይይት ይፈታሉ የሚል የአስተሳሰብ ግዝፈት የሚታይበት ነው። ዓለማችን በቀደሙት ዘመናት ብዛት ያላቸው አውዳሚ ጦርነቶችን አስተናግዳ፤ ከጦርነት ጥፋት የተማረችበት እና ለእዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ተሐድሶ ፈጥራ በፅናት የቆመችበት ነው።

አሁን ያለው ትውልድ በየትኛውም ሁኔታ ከጦርነት ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ አይደለም፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላም በሰፈነባት ዓለም ውስጥ በመተባበር እና በመተጋገዝ አሁናዊ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በጋራ የመሻገር መነቃቃት ውስጥ ያለ ነው። ተጨባጭ ዓለም አቀፍ እውነታውም ቢሆን በብዙ ስለሰላም መጮህን እና ማዜምን የሚያስገድድ ነው።

ጦርነት ናፋቂነት ዘመኑ ያለፈበት ዓለምን ብዙ ዋጋ አስከፍሎ ያለፈ፤ ከሰው ልጅ የተሳሳተ ማንነት የሚቀዳ የጥፋት እሳቤ ፍሬ ነው። ጀማሬው በየትኛውም መንገድ ያማረ ቢመስልም ፍጻሜው ግን ጥፋት እና ውድመት ነው። ከእዚህም አልፎ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ጽልመት የማልበስ የጥፋት ጉዞ አልፋ እና ኦሜጋ ነው።

በእዚህ ዘመን ስለጦርነት አደባባይ ወጥቶ መፎከር ሆነ የጦርነት ሐዋሪያ ሆኖ ስለ አትራፊነቱ ለመስበክ ድፍረት ማግኘት፣ ለሰው ልጅ ክብር የማጣት፣ የአላዋቂነት ማሳያ፣ ሞት እና ጥፋትን በአደባባይ የመስበክ ከንቱነት መገለጫ ነው። ከሰው ልጅ ብሩህ ነገዎች ላይ የማመጽ ከእርግማን ሁሉ የከፋው እርግማን ነው።

እውነታው በግጭት እና በጦርነት ዘመናቸውን ለመገበር ለተገደዱ ሀገራት እና ሕዝቦች ትርጓሜው ከእዚህምያለፈ ትናንትን ብቻ ሳይሆን ዛሬን እና ነገን ትርጉም እና ተስፋ አልባ የማድረግ፤ በማህበረሰብ ፍጥረታዊ ተስፋ ላይ የመነሳት የጥፋት ሁሉ ጥፋት ነው። ትውልዶችን ከፍጥረታዊ ተስፋቸው የመናጠቅ የጨለማ ጉዞ ነው።

የእነዚህ ሀገራት ሕዝቦች የሚፈልጉት ተመልሰው ወደ ጦርነት መግባት እና አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ሳይሆን ከጦርነት እና ከግጭት ለዘለቄተው የሚወጡበትን የአስተሳሰብ ተሐድሶ ነው። በጦርነት ምክንያት የተሰበሩ ልቦችን መጠገን፤ ያጋጠሙ የሥነ ልቦና ስብራቶችን ማከም የሚያስችል እድል ነው።

በግጭት ብዙ ዋጋ እንደከፈለ ማህበረሰብ፤ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው በቀደመው ዘመንም ሆነ አሁን ላይ በስሙ በተካሄዱ ጦርነቶች ከደረሰበት መጠነ ሰፊ ጥፋት ማገገም የሚያስችል፣ በጦርነቶቹ የደረሰበትን የልብ ስብራት የሚጠገን፣ ከሥነልቦና ጠባሳ የሚፈውስ እና ሰላም እና ሰላሙን የሚያጸና ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ ተሐድሶ ነው።

በጦርነት “ጀግና ጀግና” እያለ ውድ በሆነው ሕይወቱ የሚቆምር ተስፈኛ ሳይሆን፤ ከትናንት ስህተቶች ተምሮ እና ታርሞ ለትግራይ ሕዝብ ብሩህ ነገዎች የራሱን እና የቡድን ፍላጎቶችን መስዋዕት ማድረግ የሚችል፤ ለእዚህም በቂ ዝግጁነት የፈጠረ ጀግና ነው።

ከበሮ እየደለቀ እና እያስደለቀ፣ ሁሌም የጦርነት ዜማ እና ገድል የሚያነበንብ ፖለቲከኛ ሳይሆን፤ የሚፈልገው ለሰላም ያለውን ቀናኢነት ተቀብሎ፣ ስለሰላም የሚያዜም፣ በሰላምውስጥ ስላለ ልማት እና ብልፅግና አብዝቶ የሚሰብከው ለእዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ተሐድሶ የፈጠረ ኃይል ነው።

ለዘመናት አብሮ በወዳጅነት እና በጉርብትና ከኖረው ሕዝብ ጋር ባልተገባ የጠላትነት ትርክት ወደ ግጭት የሚከተው እና ከእዚህ አተርፋለሁ ብሎ ባልተገባ ተስፋ ዋጋ የሚያስከፍለው ሳይሆን፤ ባሕል ፣ሃይማኖቱን እና ማህበረሰባዊ ማንነቱን የሚያከብር የሕይወት መርህ ሰላሙን የሚሰጠው ነው።

ከአሁናዊ የሕይወት ፈተናዎች የሚታደገው እንጂ ሁሌም የጦርነት ገድል እያወራ ለጦርነት ተነስ፣ ታጠቅ የሚለውን አይደለም። ሕዝቡ በብዙ ተነስቶ፣ ታጥቆ እና ብዙ የሕይወት መስዋእትነት ከፍሎ ያተረፈው አንዳች ነገር የለም። ጦርነት በየዘመኑ ካስከፈለበት መጠነ ሰፊ ጥፋት እና ውድመት ብዙ የተማረ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ መቼም ቢሆን ጦርነት እና የጦርነት ወሬ የሚናፍቅ ሕዝብ አይደለም።

የናፈቀው ሰላም እና ልማት ነው፤ የናፈቀው ልጆቹን አሳድጎ ለወግ ለማዕረግ የሚያበቃበት እድል ነው፤ የናፈቀው ዘላቂ ሰላም ነው። የናፈቀው ብዙ ትውልድ መስዋዕት የከፈሉበት እውነተኛ ነጻነት እና ዴሞክራሲ ነው!

 

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You