ወቅቱ ከትናንት ስህተቶቻችን ታርመን የተሻሉ ነገዎቻችንን የምንሠራበት ነው!

ከተዛቡ የሐሰት ትርክቶች፣ ከተበላሸ ማንነት እና ከዘቀጠ ስብዕና የሚመነጭ ጽንፈኛ አስተሳሰብ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ከጥፋት ውጪ ሊያተርፍ የሚችለው አንዳች ነገር የለም። አስተሳሰቡ ትናንት መላውን የሰው ልጅ በተለያዩ ወቅቶች እና ቦታዎች ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዳስከፈለ ሁሉ ዛሬም በተመሳሳይ ያለመታረም የታሪክ ምዕራፍ ላይ ያለን ማኅበረሰብ ተመሳሳይ ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው።

የሰው ልጅ ከትናንት ስህተቶቹ ተምሮ ዛሬ ላይ የተሻለ ሕይወት የመኖር ፍጥረታዊ የመታረም ዕድል ያለው ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ማኅበራዊነቱ ደግሞ ዕድሉን በተሻለ መንገድ የራሱ ለማድረግ የሚያስችለው እንደሆነም ይታመናል። ይህንን ዕድል በአግባቡ መገንዘብ ያልቻለ ማኅበረሰብ የትናንት ሆነ የዛሬ ታሪኩ በጥፋት አዙሪት የተሞላ ነው። ነገዎቹም የትናንቱ ጥላ መሆናቸው የማይቀር ነው።

ትናንት/ታሪክ በማኅበራዊ የሕይወት ትርክት ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እና በብዙ የሚዘከረው ከትናንት በአግባቡ ለመማር ነው። በትናንት ስህተቶች ዛሬን አበላሽቶ ነገን ተስፋ አልባ ላለማድረግ ነው። ዛሬን ከተመሳሳይ ስህተት በመታደግ ነገን ተስፋ አድርጎ ለመሥራት ነው። ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ነገን የመኖር መናፈቅ ትልቁ ምስጢር ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ያላለፈ ሀገር/ማኅበረሰብ የለም። የትኛውም ማኅበረሰብ የዚህ ተፈጥሯዊ ሂደት አካል ነው። ዛሬ ላይ ትላልቅ የምንላቸው ሀገራት እና ሕዝቦች ብዙ ዋጋ ባስከፈሏቸው የትናንት የስህተት ትርክቶች የተሞሉ ናቸው። ዛሬ ላይ የሆኑትን መሆን የቻሉት፤ ስህተቶቻቸውን ቆም ብለው በማየት የመታረም ዕድሎቻቸውን በአግባቡ መጠቀም ስለቻሉ ነው።

እነዚህ ሀገራት እና ሕዝቦች በተዛቡ የሐሰት ትርክቶች፣ በተበላሸ ማንነት እና ከዘቀጠ ስብዕና በመነጩ ጥፋቶች በብዙ ተፈትነዋል። ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘ ይብዛም ይነስ የየራሳቸውን የጨለማ ዘመን አሳልፈዋል። ዘመኑ በፈጠረው ድባቴም ብዙ ተስፋ የመቁረጥ ቀናትን አስተናግደዋል። በራሳቸው አንደበት በተሰበረ ልብ የሚተረክ ታሪክ አላቸው።

እነዚህ ሀገራት እና ሕዝቦች ትናንት ላይ በተሠሩ ስህተቶች ብዙ ዛሬዎቻቸውን ገብረዋል፤ በገበሯቸው ዛሬዎች መጠንም የሕይወት ትርጓሜ ግራ መጋባት ውስጥ ገብተዋል። ራሳቸውን እና ለጥፋት የዳረጓቸውን የአስተሳሰብ ዝንፈት በሰከነ አዕምሮ እና ሰብዓዊ መመዘኛ መርምረው በብዙ ውግዘት ከራሳቸው አርቀው፤ በጠራ በእውነት እና እውቀት የትውልዶች መማሪያ የፊደል ገበታ አድርገውታል።

በዚህም ከትናንት የተሻሉ ዛሬዎች መኖር ችለዋል። ነገዎቻቸውንም በብዙ ተስፋ መሥራት እና መጠበቅ የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ማንነት ገንብተዋል። ከትናንቶቻቸው ተምረው ለሌሎች የሚተርፍ የሥልጣኔ እና ራስን የማወቅ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገብተዋል። ራሳቸውን አትርፈው ብዙ ማትረፍ በሚያስችል የሕይወት እውነት ውስ ጥ መጓዝ ችለዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ዓለምአቀፋዊ እውነታ ብዙ ልንማር ይገባል። ትናንቶቻችንን በሰከነ መንፈስ እና በተረጋጋ አዕምሮ ገምግመን፤ ከትናንት ስህተቶቻችን ተምሮ መታረም የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ማንነት ልንገነባ ይገባል። ባልታረሙ ዛሬዎች ላይ ሆነን የምንከፍለውን ያልተገባ ዋጋ ማስቆም ይጠበቅብናል።

እስከ ዛሬ ብዙ ትናንቶችን ካሳጡን ከተዛቡ የሐሰት ትርክቶች፣ ከተበላሸ አካሄድና እና ከማይመጥነን ስብዕና ራሳችን መጠበቅ፤ ወደዚህ መዛነፍ የሚወስዱ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ፣ እና ማኅበረሰባዊ ዝንፈቶቻችንን በማረም፣ ዛሬዎቻችንን ከትናንት ጥላ መታደግ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይኖርብናል።

ነገ ላይ ሆነን ለመገኘት የምናልማቸው ሕልሞቻችን ካልታረሙ ዛሬዎች ሊፈጠሩ እና ሊሰፉ የሚችሉ አይደሉም። እስከ ዛሬ ባሉት የታሪክ ምዕራፎቻችን ይህ ዓይነቱ ጉዞ ምንም አላተረፈልንም። ካልተገባ ፉከራ እና ቀረርቶ፤ እርስ በርስ መገዳደል አልታደገንም። የምንፈልገውን ዘላቂ ሰላም እና ልማትም አላመጣልንም።

ዛሬዎቻችንን ከትናንት ስህተቶቻችን ሳናጣራ የምንጓዘው የዛሬ ጉዟችን የቱንም ያህል የቀለለ እና ስኬታማ የሚያደርገን ቢመስልም፤ ከመጣንበት እና ዛሬም ካለንበት የግጭት አዙሪት ለዘለቄታው ሊታደገን አይችልም። ይህንን የማድረግ አቅምም የለውም። ዛሬዎቻችንን ከማበላሸት ነገዎቻችንን ከማጨለም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

አሁን ለኛ ለኢትዮጵያውያን ቆም ብሎ የማሰብ ጊዜያችን ነው፤ ከትናንት ስህተቶች ራሳችንን አርመን አዲስ የታሪክ ጉዞ በመጀመር የመጨረሻው መጀመሪያ ላይ ነን። ይህንን ለማድረግ እስከዛሬ ባደሩ ስህተቶቻችን የከፈልነው ያልተገባ ዋጋ ከሚገባው/ከሚጠበቀው በላይ ነው!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You