አስመረት ብስራት
ወይዘሮ ሙሉአለም ታምሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ሰራተኛ ሆነው ሰርተዋል። አሁን ‹‹ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ ኢትዮዽያ›› የሚል ግብረ ሰናይ ደርጅት አቋቁመው ሰዎችን በመርዳት ላይ የሚገኙ እናት ናቸው። አራት ልጆችን ወልደው አሳድገው ለቁምነገር አብቅተዋል። ለዛሬ አንብቡልኝ ካሉት ሀሳባቸው አንዱን እንዲህ አዘጋጅተነዋል።
ብዙ ጊዜ ለሕፃናት የሚነገራቸው ጨዋታ እንጂ ቁምነገር አይደለም።የሰጠናቸውን የሚቀበሉ አዲስ እንግዶች ቢሆኑም የምንሰጣቸው ግን ሕይወትና እውነትን ሳይሆን ጨዋታን ብቻ ነውና ባደጉ ጊዜ የእኛ አይሆኑም።በጠዋቱ ያልማረክነው እስከ ማታ አይቆይልንም።
ጠዋት የምንለው እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ከሆነ ለሕፃናት ውድ አምስት ሰዓቶች አልፈዋል ማለት ነው።ሕፃናት ዘላለማዊውን እውነት ከአራስ ቤት ጀምሮ መስማትና መለማመድ አለባቸው።እኛ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ልንነግራቸው ብዙ እውነቶችን በልባችን ሰውረናል።አካለ መጠን ግን እስከዚያ ድረስ የሰሙትን
ነገር ተግባራዊ ለማድረግ የሚወጡበት የመስክ ሜዳ እንጂ የመማሪያ ጊዜ አይደለም።በዓለም ላይ ትልቅ የሆነውን ጉዳት ልጅ የወላጆቹን ሐሳብ ወዲያ የሚልበት ነው።ብዙ ወላጆች ተሰብረው ያነባሉ።ግን ውድ ሰዓቶችን ባለማወቅ እንዳሳለፉ አይገነዘቡም፡፡
ሕፃናት እስኪያድጉ ድረስ የማንነግራቸው ብዙ እውነቶች አሉ።በሽታቸውን፣ እውነተኛ ወላጆቻቸውን፣ የቤተሰቡን ዝብርቅርቅ፣ የቤቱን መሠረታዊ ችግር፣ በአገሪቱ ላይ ያለውን ተጨባጭ አደጋ . . . እንሸሽጋቸዋለን።
ይህ መልካም ሊሆን ይችላል።ሕፃናት ግን ከእኛ ይልቅ ለፈጣሪ የቀረቡ፣ እኛ የከበደንን እምነት በተፈጥሮ የታደሉ፣ ፈጣሪን እያዩ ማምለክ የሚችሉ ናቸው።ፈጣሪ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።በማስተዋልም ያበረታቸዋል፤ በፍቅርም ያበለጽጋቸዋል።በርኅራኄም ያሰለጥናቸዋል፡፡
ሕፃናት በብዙ ቁምነገሮች ተንቆጥቁጠዋል፤ ነገር ግን አንሰማቸውም።ቁምነገር ሲያወሩን እንቀልድባቸዋለን።እውነተኛውን እውነት ሲነግሩን ከትልቅ ሰው ይልቅ እንፈራቸዋለን።የማይሰሙ እየመሰሉን በፊታቸው ብዙ የማይገቡ ነገሮችን እንናገራለን።የማይሰማቸው እየመሰለንም ፀያፍ ንግግር
እንናገራቸዋለን።እነርሱን ዘፈን ከልክለን በፊታቸው ስንዘፍን ይገስጹናል።የሰሙትን የመኖር ጥማታቸውን አንጠቀምበትም።አጥንታቸው ለመቆም የማይችል ለጋ መሆኑን እየዘነጋን ወንበር አንለቅላቸውም፤ ልጅ ነው ይቁም እንላለን።ቶሎ ቶሎ እንደሚርባቸው ደግሞም ጉጉዎች መሆናቸውን እየረሳን ልጅ ነው ኋላ ይበላል፣ ትበላለች እንላቸዋለን።የሚማሩ፣ በንግግር የሚያምኑ ስለማይመስለን በዱላ ብቻ እናሳምናቸዋለን።
ጆን ደብልዩ ሎረንስ የተባለ ፀሐፊ በመጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡- ልጅ እየተወቀሰ ካደገ ማውገዝን ይማራል።ልጅ በጥላቻ አካባቢ ካደገ መደባደብን ይማራል።ልጅ እየተፌዘበት ካደገ ዓይነ አፋርነትን ይማራል።ልጅ በሐፍረት ካደገ ጥፋተኝነትን ይማራል።ልጅ በመቻቻል ካደገ ትዕግሥተኝነትን ይማራል።
ልጅ በመበረታታት ካደገ በራስ መተማመንን ይማራል።ልጅ በመሞገስ ካደገ ማድነቅን ይማራል።ልጅ በአግባብ ካደገ ፍትሕን ይማራል።ልጅ ዋስትና ባለው ኑሮ ካደገ ሰውን ማመን ይማራል።ልጅ በተቀባይነትና በወዳጅነት ካደገ በአጠቃላይ ዓለም ፍቅርን ማግኘት ይማራል።ስለዘህ አስተዳደጋችን ላይ ትኩረት እናድርግ ሲሉ ወይዘሮ ሙሉአለም ምክራቸውን ለግሰዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013