መላኩ ኤሮሴ
የቀቤና ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ብሄረሰብ ነው፡፡ ከእነዚህ ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ‹‹ቦበኒ ገልቲት›› ተጠቃሽ ነው፡፡ ‹‹ቦበኒ ገልቲት›› የብሄረሰቡ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ነው። ደንቡን የሚያፀድቅበት፣ የሚያሻሽልበት እና የተለያዩ ደንቦች እና መመሪያዎች የሚተላለፉበት ስብሰባ ደግሞ ‹‹ኦገት›› ተብሎ ይጠራል፡፡
በብሔረሰቡ ውስጥ ግጭት ሲፈጠር የራሱ የሆነ የአፈታት ስርአት አለው፡፡ የግጭት አፈታት ስርአቱ በስድስት ደረጃዎች እንደሚከፈል የቀቤና ብሄረሰብ የባህላዊ ዳኝነት አመራሮች አንዱ የሆኑት ኢማም ሃያቱ ካሚል ይናገራሉ፡፡ ስድስቱም ደረጃዎች፤ ጀሜ ባሊቂ፣ ቀዬ ወይም ዘኒ ባሊቂ፣ አንቲት፣ ዒሊ ዳኛ፣ ሃላ እና ኦገት በመባል ይታወቃሉ፡፡
አንድ ላይ ቡና የሚጠጡ ሽማግሌዎች (ጀሜ ባሊቂ) የሚፈቱት በአብዛኛው ቀላል ስርቆት፣ የባል ሚስት አለመግባባት እና የልጆች ጥል የመሳሰሉትን ነው። በዚህ የዳኝነት ደረጃ ውስጥ ከሚተላለፉት ቅጣቶች ጥፋተኛው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ቡና እንዳይጠጣ፣ ከብቶቹ ከአካባቢ ከብቶች ጋር አብረው እንዳይታገዱ ማድረግ ነው።
ሁለተኛው ችግሮች ከሚፈቱባቸው መንገዶች አንዱ የአንድ አካባቢ ሽማግሌዎች ‹‹ዘኒ ባሊቂ›› ተብሎ የሚጠራው የዳኝነት ደረጃ ነው፡፡ ይህ ስርአት በዋነኛነት ‘’በጀሜ በሊቃ’’ ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ላይ የተከሰቱ አዳዲስ እና የጋራ ጉዳዮችን በጥልቀት በመመልከት እርማት ይሰጣል፡፡
የቤተሰብ አባላት (አንቲት) ሶስተኛው ደረጃ ግጭት አፈታት ሲሆን፤ ቀላል ግጭት የሚታይበት የመጨረሻው ደረጃ ነው። ችግሩ በተፈጠረበት ቤተሰብ ያሉ የአባት ወገኖች ወይም የቅርብ ወራሾች ከያሉበት በመሰብሰብ ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጡበት ነው፡፡ በእነዚህ የቅርብ ዘመዶች ያልተፈቱ ችግሮች ወደ ‹‹ዒሊ ዳኛ›› (የጎሳ ሽማግሌ) እንደሚተላለፉ ያብራራሉ፡፡
ኢማም ሃያቱ እንደነገሩን ‹‹ዒሊ ዳኛ›› (የጎሳ ሽማግሌ) ማለት በብሄረሰቡ ውስጥ ከሚገኙ ጎሳዎች መካከል በአንዱ ጸብ ወይም ችግር ቢፈጠር በራሱ ጎሳ አማካኝነት ብቻ የሚፈታ የሽምግልና ሂደት ነው፡፡
ይኼ ከቤተሰብ ወጣ ያለ በአንድ አይነት ጎሳዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ወደ ኦገት (ትልቁ ሸንጎ) ሳይወሰድ በጎሳ ዳኛ (ዒሊ ዳኛ) አማካኝነት የጎሳው አባላት ቅጣት በመወሰን እንዲታረም ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ስርአት የሚታዩት ውርስ ላይ ያሉ አለመግባባቶች፣ የድንበር ግጭቶች ናቸው፡፡ በነዚህ ያልተፈታ ጉዳይ ካለ በ ‹‹ሀላ›› ሽማግሌዎች እንዲታይ ይደረጋል፡፡
በቀቤንኛ ‹‹ሀላ›› ማለት በአንድ አባት ስር የሚመደቡ ጎሳዎች ሲሆኑ፤ ችግሩ በተፈጠረው ቤተሰብ ውስጥ ቅርበት ያላቸው የቤተሰብ ስብስቦች (ጎሳዎች) የሚፈቱት የዳኝነት ስርአት ነው፡፡ ‹‹ሀላ›› ስርአት በሁሉም ጎሳዎች የማይተገበር ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያቱ የተወሰኑ ጎሳዎች ራሳቸውን የቻሉ በመሆናቸው በጎሳ ዳኞች ስለሚዳኙ ነው፡፡ ከዚህ የዳኝነት ስርአት በላይ የሆኑ ችግሮች ወደ በላያቸው ለሆነው በማስተላለፍ እንዲፈታ ይደረጋል፡፡
“ኦገት” በብሔረሰቡ ትልቅ ቦታ ያለው ነው። ከብሔረሰቡም ይሁን ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት ምክር ቤት ነው። “ኦገት” ከሚፈታቸው ችግሮች መካከል ግድያ፣ አስተዳደራዊ ድክመት እና ከሌሎች አጎራባች ብሔረሰቦች ጋር የሚፈጠር የድንበር ግጭት ተጠቃሽ ናቸው።
ቀላል ግጭቶችን አካባቢ ባሉ ሽማግሌዎች በጀሜ ባሊቂ፣ ቀዬ ወይም ዘኒ ባሊቂ እና አንቲት የዳኝነት ደረጃዎች በቅደም ተከተል እንዲመለከቱ ከተደረገ በኋላ ባለጉዳዮቹን (ሩበቱ ገይሲሱ) ተብሎ በብሔረሰቡ የሚታወቀውን ዋስ በማስጠራት ጉዳዩን በጥልቀት ይመረምራሉ፡፡ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ይወስናሉ፡፡
ኢማም ሃያቱ እንደሚያብራሩት በዚህ አሰራር ረጅም ዘመን የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች ወንጀለኛ ከማህበረሰቡ እሳት እንዳይዋዋስ ከመከልከል እስከ ከባድ ገንዘብ ቅጣት ርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ የውርስ ሀብት ክፍፍል ላይ ልጅ እናትና አባቱን በአግባቡ ያለመጦር ሲፈጠር ለቤተሰቦችና ለዘመዶቹ የሚገባውን እገዛ ሳያደርግ ሲቀር የሚፈጠሩ ግጭቶች ቅጣቱም በዳይ ወገን ለተበዳይ ማር፣ ቅቤ እና ጋቢ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ለሽማግሌዎችም በግ ወይም ፍየል አርዶ ማብላት ሽማግሌዎች ምርቃት በመስጠት እርቅ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡
ነፍስ ማጥፋት፣ ንብረት ዘረፋና ማቃጠል፣ ሚስት መንጠቅ፣ ከሌላ ብሔረሰብ ጋር ድንበር ግጭት የመሳሰሉ ከባድ ወንጀሎች ፈጻሚያቸው ከታወቀ የራሱ የሆነ የወንጀል አፈታት ተዋረዶች እንዳሉት የሚያብራሩት ኢማም ሃያቱ እነዚህም ከተራ፣ ጉዳ (ጉድዲ ባሊቂ) እና ጠዋ ሹለኑ ባሊቂ (ጉዳይ የሚጨርስ ሽማግሌ) በመባል ይታወቃሉ፡፡
‹‹ከተራ›› የሚባለው ሽማግሌዎች ከባድ ወንጀል እንደተፈጸመ ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ቦታ በመሄድ ሌላ ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈጸም፣ ግጭቱ እንዳይሰፋ እና ችግሩ እንዲፈታ ሀላፊነቱን ስጡን በማለት ሳር በመጣል ጸቡን የሚያረጋጉበት ስርአት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የተፈጠረው ወንጀል ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ሰዓት ጀምሮ በዳይ ቤት ንብረቱና ቤተሰቡን ይዞ እርቁ እስኪከናወን ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ወንዝ ተሻግሮ የሚሄድ ይሆናል፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት የበዳይ የሰባት ቤት ትውልድ ቤት ለቆ ወንዝ ተሻግሮ እንዲሄድ ይደረግ እንደነበር ያስታወሱት ኢማም ሃያቱ፤ በሂደት ይህ አካሄድ ማሻሻያ ተደርጎበት ገዳዩ ብቻ እንዲወጣ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የሚደረገው የተበዳይ ቤተሰብ የበቀል ርምጃ ሊወስድ ይችላል በሚል ስጋት ነው፡፡ ሆኖም የሟች ቤተሰብ ተለምነው እንዳይወጣ ፈቃደኛ ከሆኑ እንዳይወጡ ይደረጋል፡፡ የበዳይ ንብረቶች ከመጠበቅ ረገድ የከተራ ስርኣቱን የያዙት ሽማግሌዎች ሀላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡
ይህንን የከተራ ስርአት ‹‹ሂሩት ዒላከቲ›› (በጩኸት ጊዜ የደረሱ) ሽማግሌዎች መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፤ የተበዳይን ወገን ካረጋጉና ጉዳዩን ወደ ሽምግልና ካመጡ በኋላ የጎሳ እና ሩቅ ያሉ የኦገት ሽማግሌዎችን በመጥራት ስርአቱ ‹‹ጉዳ›› ወደሚባለው ክፍል ይሸጋገራል፡፡
ጉዳ የሚባለው ቃል መገባባት ሲሆን፤ ከከታራ ሽማግሌዎች በተጨማሪ ሌሎች ሽማግሌዎች ተጨምረው ከበዳይ አካላት ላለመነካካት፣ ባህልና ወጉን ተከትሎ ለመዳኘት እና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ለመሄድ ተበዳዮችን ቃል የሚያስገቡበት ስርአት ነው፡፡ በበዳዮች ላይም ተበዳዮች የሚገበያዩበትን ገበያ፣ የጋራ መንገድ እና ከብቶቻቸውን አብረው እንዳያሰማሩ ጊዜያዊ እገዳ ይጣልባቸዋል። በሁለቱም ወገን ዋስ ካስጠሩ በኋላ ‹‹የከተራ›› ስርዓት የተጣሰበት ብቀላ የተሞከረበት፣ መንገድ የተከለከለ፣ ንብረቱ የተወሰደበት የተበደለ ወገን ካለ ቅሬታውን አቅርቦ በጉዳይ ላይ መፍትሄ ይሰጣሉ፡፡
የተበዳይ ወገን ጉዳዩ እንዲታይለት ከተስማማ በኋላ በሽማግሌዎች ተወስኖ ከበዳይ በኩል ‹‹ኢንጂጂ ጊዛ›› (እንባ ማበሻ ገንዘብ) እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡ ይህ ገንዘብም በመጨረሻ በዳይ ላይ ከሚጣለው ቅጣት ተቀናሽ ይደረጋል። በቀጣይም የከተራው እና የጉዳው ስርዓት በደንቡ መሰረት መተግበሩን ካረጋገጡና ለተበዳይ የእንባ ማበሻውን ወስነው ካስተላለፉ በኋላ የኦገት ሽማግሌዎች የቀጣይ ስራ የሚሆነው ‹‹ጠዋ ሹለኑ ባሊቂ›› (ጉዳይ የሚጨርሱ ሽማግሌዎች) መምረጥ ይሆናል፡፡ በዚህም መረጣ ጊዜ ከሁለቱም ወገን ከኦገት ሽማግሌዎች በተጨማሪ የፈለጉትን ሽማግሌ መርጠው የመዳኘት መብት አላቸው። የሚዳኙትም በቦበኒ ገልቲት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ነው፡፡
ሶስተኛው ከባድ ወንጀል አፈታት ተዋረድ ጠዋ ሹለኑ ባሊቂ ሲሆን፤ ይህ የሽምግልና ስርዓት የወንጀል ድርጊቱን የሚያጣ፣ ግጭቱ መቼ፣ እንዴትና ማን ፈጸመው የሚለውን በጥልቀት የሚመረምር መሆኑን ኢማም ሃያቱ ያብራራሉ፡፡ ስርአቱም የሚከናወነው በተበዳይ ቀዬ ወይም ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ነው፡፡
ሽማግሌዎች ስለድርጊቱ ከተበዳይ በኩል በማድመጥ ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት የበዳይ ተወካይ ሽማግሌዎችም ስለወንጀሉ የሚያስረዱ ይሆናል፡፡ ተበዳይም በተወካዮቹ አማካኝነት ሀሳቡን የመግለጽ መብቱ ይከበርለታል፡፡ ከዚህ በኋላ የኦገት ሽማግሌዎች ከሁለቱም ወገን የወንጀል ድርጊቱን ካደመጡ በኋላ የወንጀሉን ደረጃ በመወሰን በቦኒ ደንብ የተቀመጠውን ካሳ ያስፈጽማሉ፡፡
በብሄረሰቡ ወንጀል መፈጸሙ ከተረጋገጠ የራሱ የካሳ አፈጸጸም ስርዓትም አለው፡፡ አንድ ወንጀል ሲፈጸም የካሳ አፈጻጸሙ ሊመደብ የሚችለው ከሚከተሉት ሶስት ደረጃዎች በአንዱ ነው። ጉማ (ሙሉ ካሳ)፣ መዳላ (ግማሽ ካሳ) እና መዳሊ መዳላ ነው፡፡ ሙሉ ካሳ የሚካሰው በዳዩ ድርጊቱን ሆን ብሎና አስቦበት የፈጸመው መሆኑ በተገቢው መንገድ ከተጣራ በኋላ ነው። ለተበዳይ የሚሰጠውም ገንዘብ ወይም ከብት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በበቀል ቤት ቢያቃጥል እና ነብስ ቢያጠፋ ሙሉ ካሳ ይጣልበታል።
የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ሆን ተብሎ የተፈጸመ ከሆነ ገዳዩ 150 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ አሁን ግን የሰው ህይወት እየረከሰ ይሄዳል በሚል የካሳ መጠኑ 200 ሺህ ይሁን እየተባለ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጊቱ የተፈጸመበት ሰዓት እና ሁኔታ የካሳውን ዋጋ ከፍ ዝቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ሁለተኛው ‹‹መዳላ›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ በዚህ ደረጃ የሚቀመጠው የወንጀል አይነት በሁለቱም ወገን ምንም አይነት ቂምና ጥላቻ ካልነበራቸው ነው፡፡ ወንጀለኛውም ሆን ብሎ ካልፈጸመው ከሙሉ ካሳ ያነሰ ገንዘብ ወይም ከብት እንዲቀጣ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ፡- ሳይታሰብ የተከሰተ የመኪና አደጋ ካሳው ግማሽ ይሆናል።
ሶስተኛው ‹‹መዳሊ መዳላ›› ወንጀለኛው በተበዳይ ላይ በቀልም ሆነ ምንም አይነት የጥንቃቄ ጉድለት የሌለበት ሲሆን፤ ነገር ግን ንብረት በማውደሙ ወይም ነብስ በማጥፋቱ ምክንያት የሚቀጣበት የቅጣት ደረጃ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ለአደን በወረወረው ጦር ሰው ቢገድል ቅጣቱም ከመዳላ ያነሰ ይሆናል፡፡
የኦገት ሽማግሌዎች በቦበኒ ደንብ መሰረት ያስቀመጡትን ቅጣት የበዳይ ዘመዶች (የጎሳው አባላት) በመከፋፈል የሚከፍሉት ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ ወደ እናት ዘመዶችም ጭምር በመሄድ ቅጣቱን የሚጋሩት ይሆናል፡፡
በመጨረሻ ስብሰባ ቀን በዳይ ካሳ ከተወሰነበት በኋላ ፊቱን በቅጠል ሸፍኖ ይቀርባል፡፡ ይህን ጥፋተኛ ነኝ፣ ተጸጽቻለሁ፣ እናንተን የማይበት አቅም የለኝም የሚል መልእክት አለው፡፡ ሁለቱም ወገን በባህላዊ እቃ የቀረበላቸውን ማር፣ ወተት ወይም በአካባቢው የሚገኝ ጣፋጭ ነገር በተራ ተራ ከተጎነጩ በኋላ በመተቃቀፍ እርቅ መውረዱን ያሳያሉ፡፡ ይህንኑ መጠጥ ሽማግሌዎች እና የሁለቱ ወገን ቤተሰቦች እንዲጎነጩ እንደሚደረግ ያብራራሉ፡፡
በዚህ ስርአት በዳይ ያቀረበውን በግ በማረድ በስብሰባው ላይ የታደመ ሁሉ የሚመገብ ሲሆን፤ በዳይ እና ተበዳይ በአንድ ማዕድ በመመገብ የእርቅ ስርአቱ ይጠናቀቃል፡፡ በብሔረሰቡ የእርቅ ስነስርአት መሰረት ችግሩ ከተፈታ በኋላ ወቅቱ የሰብል ጊዜ ከሆነ አብረው እንዲያርሱ፣ እንዲዘሩና እንዲወቁ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በኋላ በሁለቱም ወገኖች መካከል ምንም እንዳልተፈጠረ በሚመስል ሁኔታ ከብቶቻቸውን አብረው የሚያግዱ፣ የሚገበያዩ፣ አብረው ቡና የሚጠጡ እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚፈጽሙ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል አንድ ግጭት ወይም አደጋ ተፈጥሮ ድርጊት ፈጻሚው ካልታወቀ የብሄረሰቡን የግጭት አፈታት ስርአቶችን የማይጠቀም ሆኖ ሳለ በምትኩ ሌሎች ሂደቶችን ይከተላል፡፡ ወንጀለኛውን ለማግኘት የኦገት ሽማግሌዎች ስብሰባ በማድረግ ድርጊቱ በተፈጸመበት አካባቢ ያሉ ሽማግሌዎችን በመምረጥ እንዲያጣሩ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ እነዚህ በተመረጡ ሽማግሌዎች ወንጀለኛው ካልተገኘ በቀጣዩ ስብሰባ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ህጻናት እና ሽማግሌዎች ሁሉም በየግላቸው ተወያይተው ወንጀለኛውን እንዲያጋልጡ ይደረጋል። ይህም የሚደረግበት ምክንያት ሁሉም በየጾታው እና በእድሜ ክልሉ ሲወያይ ሀሳቡን በነጻነት የመግለጽ እድል ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡
በዚህ ውይይት ወንጀለኛው ካልተገኘ የአካባቢው ሰው በመውጣት ‹‹አያንታሙ ባሊቀት›› ታላልቅ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽግሌዎች በተቀመጡበት ከመሀከላቸው እንዲያልፉ ይደረጋል፡፡ ይህም ድርጊት ፈፃሚው ከመሀከላቸው ሲያልፍ ከሁኔታው ይረዳሉ ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡ በዚህም ሁኔታ ወንጀለኛም ሆነ ተጠርጣሪ አካል ካልተገኘ በተበዳይ ፍላጎት ሁሉም የአካባቢው ሰው ቤተሰቡን ይዞ በመውጣት ወንጀለኛውን የማያውቅ መሆኑን እና ወንጀሉን እንዳልፈጸመ የሚምል ይሆናል፡፡
በብሄረሰቡ የሚፈጠሩ ግጭቶች ተደብቀው የሚቀሩበት እድል በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም እንደዋነኛ ምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉት አንድም ዛሬ ተደብቄ ብቀርም ነገ ለልጅ ልጄ ሌላ ተመሳሳይ ወንጀል እንዲሰሩ ‹‹በርቼ›› ግፍ ይደርስብኛል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው የብሔረሰቡ ህዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኑ ወንጀል ሰርቶ መሰወር እንደሚወገዝና በመንፈሳዊ መንገድም ቅጣት እንደሚጠብቀው ስላሚያውቅ ነው፡፡
የቀቤና ብሄረሰብ አባላት ከሌሎች ብሄረሰቦች ተወላጆች ጋር በድንበርም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ግጭት የተከሰተ ከሆነ ሁለቱም ወገኖች በተስማሙት ስርአት የመዳኘት መብት ሲኖራቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ግን ለተበዳይ ፍላጎት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013