ማህሌት አብዱል
የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ጎጃም ክፍለ ሐገር ብቸና ከተማ ነው። ያደጉትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ደግሞ ደጀን ከተማ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴና ከዚያም ጋር ተያይዞ የጥላሁን ግዛው መገደልን ተከትሎ የትምህርት ሥርዓቱ ተቋርጦ ነበር። ይሕ በእንዲህ እንዳለ ከወቅቱ የፖለቲካ ችግር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ነፃ አውጪ ድርጅት በጎረቤት አገር ሱዳን በመቋቋም ላይ መሆኑን በሰፊው ይወራ ስለነበር ይህንኑ እንቅስቃሴ ለመቀላቀል እርሳቸውም ወደ ሱዳን ተሰደዱ።
ይሁንና የሰሙት ነገር እውን ሆኖ አላገኙትም። በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እዛው ሱዳን ለሁለት ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ አውሮፓ ጉዟቸውን ጀምረው በግሪክ ፣ በቀድሞው ዩጎዝላቪያ፣ በጣልያን አድርገው ከሁለት ዓመት መንገላታት በኋላ ጀርመን ገቡ። ጀርመን ሲደርሱ የየካቲቱ አብዮት ተቀስቅሶ የዘውዱ ሥርዓት ወደቀና ጊዜያዊ ወታራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን ያዘ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትግላቸውን በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበርን ተቀላቅለው እስከ መጨረሻው ድረስ ተሳትፈዋል። ትምህርታቸውንም ሩር በተባለ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት ፣ በታሪክና በፖለቲካል ሳይንስ አጠናቀው የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። አከታትለውም ብሬመን ከተባለ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ሳይንስ የዶክትሬት ትምህርታቸውን አጠናቀው በጥሩ ውጤት ተመርቀዋል።
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ቀደም ብለው በተማሩበት ቦኹም ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጥረው 15 ዓመታት አገልግለዋል። በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ልዩ ተቋማት እና የውጭ አገር ተማሪዎች አማካሪም በመሆን ሰርተዋል። በተጨማሪ በተለያዩ የጀርመን ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ሰርተዋል። ለአብነት ያህልም በኤምባሲ፣ በጀርመን ተራድኦ እና ልማት ድርጅት ፣ በሃይማኖትና በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሰማሩ ጀርመናውያን ወደ ኢትዮጵያ ከመሄዳቸው በፊት ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት ከ15 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
ከ33 ዓመት የጀርመን ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ከማስተማር ባሻገር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ያልነበረውን የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲመሰርቱ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የተቋሙ የመጀመሪያ ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። አሁንም በዚሁ ተቋም ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ስለ ዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት በማስተማር ላይ ይገኛሉ። እንግዳችን ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ‹‹ ማለት የምፈልገው›› እና ‹‹ መግደል መሸነፍ ነው›› የተሰኙ ሁለት መፅሃፎችን ለንባብ አብቅተዋል። ከእንግዳች ጋር በታላቁ ህዳሴ ግድብና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ውይይት እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– ‹‹ መግደል መሸነፍ ነው›› ብለው መፅሃፍ ለመፃፍ የተነሱበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– የዚህ መፅሃፍ ዋናውና ትልቁ አጀንዳ እኔ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ አውቃለሁ እስከምልበት እድሜ ድረስ ቀድመን የሰለጠንን አገር ለምን ወደኋላ እንደቀረን ለማስረዳት ነው የሞከርኩት። ምንአይነት ችግሮች ነበሩብን? በታሪካችን ፣ በሂደቱ ምንአይነት ውስብስብ ችግር ቢፈጠር ነው ወደኋላ የቀረነው? የሚለውን ለመተንተን ጥረት አድርጊያለሁ። በነገራችን ላይ ‹‹ማለት የምፈልገው›› ከሚለው የመጀመሪያው መፅሃፌ ላይ የተካተቱ ሃሳቦች ዳብረው በአዳዲስ ሃሳቦች በልፅጎ የቀረበበት ነው። በዚህ መፅሃፍ የመግደል መገደልን የጥፋት መንገድ አቁመን አገራችንን ወደሚገባት ከፍታ ለማሻገር የሚረዳንን ትክክለኛ መንገድ የሚያመላክት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል ብዬ በማሰብ ነው የፃፍኩት።
አዲስ ዘመን፡– እርሶ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ታሪካዊ ግንኙነት ላይ የተለያዩ ጥናቶችን አከናውነዋል። ለመሆኑ እነዚህ አገራት ከአባይ ወንዝ ባሻገር ምንድን ነው የሚያስተሳስራቸው?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– ከታሪክ አንፃር ብዙ ሰዎችም ተመራምረውበታል፤ ፅፈውበታልም። እኔም ከብዙ ዓመት በፊት ባከናወንኩት ጥናት ላይም አገራቱን የሚያስተሳስሯቸውን አበይት ነገሮች ለማካተት ሞክሬያለሁ። የግብፅ ፒራሚድ ሲሰራ ኢትዮጵያኖች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበራቸውና ግብፅ ድረስ ሄደው እንደገዙ ይታወቃል። ሱዳን የሚባለው አገር ሳይመሰረት ኑቢያ የሚባለው አካባቢ በሙሉ በኢትዮጵያኖች ስር እንደነበር ነው በታሪክ የሚነገረው። እናም ግንኙነቱ ከውሃው ባሻገር ታሪካዊ የሆነ የግዛት አንድነት የነበራቸው መሆኑን ያሳያናል። በተጨማሪም በንግድና በህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነት የተሳሰሩ አገራት መሆናቸውን ነው የምንገነዘበው። አሁን እንግዲህ ቀኝ ግዛት ከመጣ በኋላ ነው እንደሃገር ሆነው ድንበር ተመስርቶ አሁን የገባንበት ችግር ውስጥ የምንገኘው።
አዲስ ዘመን፡– የህዳሴው ግድብ ግንባታ መጀመር የአገራቱን ዲፕሎማሲ ግንኙነት የት አድሮሶታል ማለት እንችላለን?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እንግዲህ ከግብፆች አንፃር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲሻክር የሚፈልጉበት ሁኔታ በግልፅ ይታያል። እነሱ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን በሁሉ ነገር ለማሳነስ እና ዘላለም እንዳታድግ ለማድረግ ብዙ ሰርተዋል፤ በመስራትም ላይ ናቸው። ይሁንና ኢትዮጵያ እየጣለቻቸውና እያደገች ስለሄደች ክብሯንም ሆነ የህዝቧን ጥቅም እያስጠበቀች በምትገኝበት ጊዜ ይሄ የሴራ ፖለቲካቸው አልመቻቸው በማለቱ የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ በኩል ሰላማዊ ግንኙነቱ እንዲቀጥል መሻቱ ቢኖርም በተለይ በግብፅ በኩል እምቢተኝነቱ ቀጥሏል። ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘም ምንም እንኳን የውሃው ምንጭ እኛው ብንሆንም እንደነሱ ሌላው መጠቀም የለበትም የሚል ሃሳብ አላነሳንም። ከሱዳን ጋርም ቢሆን ከዚህ ቀደም የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበረን ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግድቡም ሆነ በመሬት ጉዳይ ግንኙነቱ እየሻከረ መጥቷል። በእርግጥ የድንበሩ ጉዳይ ይህን ያህል የሚያሳስብ አይደለም። በዚህ ምክንያት ወደ ግጭት ወይም ጦርነት እንገባለን የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም የሱዳን ህዝብ እስከማውቀው ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት የለውም። የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን እንደዚሁ ከሱዳን ጋር በማንኛውም መንገድ ወደ ግጭት ውስጥ ለመግባት አይፈልግም። ይህ መሰረታዊ እምነቴ ነው። እስከአሁን ድረስ በታሪክም እንደታየው ሁለቱ አገራት የበለጠ ተግባብተውና ተስማምተው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ይህም ወደፊትም ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ። በእርግጥ ግብፅ ይህንን ግንኙነት አትፈልገውም፤ እንዲሻክር እንደምትፈልግ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ በተለይም የሱዳን መንግስትም ቢሆን የራሱን አገር ሉዓላዊነት ማስከበር ነው ያለበት አንጂ የግብፅን ጥቅም ለማስከበር ሲል ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ሊያበላሽ አይገባም።
አዲስ ዘመን፡– የሱዳን መንግስት በተለያየ ጊዜ የአቋም መዋዠቅ ይታይበታል። ይህ ሁኔታ ለግብፅ አቋም ተንበርክካለች ለማለት ያስደፍረናል?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– አያስደፍርም። አንድ መርሳት የሌለብን ጉዳይ ሱዳንና ግብፅ ራሳቸው በመሬት ጉዳይ ጭቅጭቅ ላይ ነው ያሉት። ሁለተኛ ይሄ በሱዳን በኩል የሚታየው የአቋም መዋዠቅ የሱዳን የአገር ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታ ነው። ምክንያቱም አምባገነኑ አልበሽር ከወረዱ በኋላ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ዋና ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ነች። የሥልጣን ክፍፍሉም በወታደሩና በሲቪሉ በኩል ያለው ግንኙነትን እዚህ ደረጃ ያደረሰችው ኢትዮጵያ ነች። ስለዚህ ወታደሮቹ ብዙ የውስጥ ችግር አለባቸው። ምን ያህል እንደሚታወቅ አላውቅም እንጂ ወታደሮቹ በእነአልበሽር ጊዜ በሳውዲ አረቢያ ወታደር እያቀበሉ የመን እንዲያዋጉ ያደረጉ ጀነራሎች ናቸው። እነዚህ ጀነራሎች ጥቅማጥቅም አላቸው። በሙስናም ሆነ በሌሎችም ብልሹ አሰራሮች የተያያዘ ነገር አለ። እነሱ የሱዳን ህዝብ ጥቅም ሳይሆን የራሳቸው ጥቅም ላይ ነው ያተኮሩት። ግብፆቹ እዚህ ላይ ነው ጀነራሎቹን መከራ የሚያሳዩት ። ጀነራሎቹ በራሳቸው ጥቅም በሱዳን ጥቅም መካከል ስላሉ የመዋዠቅ ነገር ይታይባቸዋል። ነገር ግን የሲቪሉ ወገን ኢትዮጵያን የሚደግፍ አካል አለ። በመሆኑም በብዙሃኑ የሱዳን ህዝብ ድጋፍ ያለው የሲቪሉ መንግስት የተለሳለሰ አቋም ያለው በመሆኑ ለኢትዮጵያ ብዙ የሚያሰስብ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– አንደሚታወቀው ግብፅ የአባይን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም ፍላጎት ስላላት የቅኝ ግዛት ውሉ ተፈጻሚ አንዲሆን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነች። ከዚህ አንፃር በአፍሪካ ህብረት የሚደረገው ድርድር ላይ የሚያጠላው ነገር ይኖር ይሆን?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ የቅኝ ግዛት ስምምነት ከየት መጣ ብለን መጠየቅ መቻል አለብን። ይህንን ውል ግብፅ ሳትሆን የእንግሊዝ መንግስት በቅኝ ግዛት ጊዜ ያዘጋጀው መሆኑ ይታወቃል ። አሁን የሚታየው እንግሊዞች የፈጠሩት ችግር ነው። አንደኛ ይሄ ውል ሲፈረም ራሳቸው እንግሊዞችና ግብጾች ያደረጉት አንጂ ኢትዮጵያ አልካተተችበትም። ኢትዮጵያን ያላካተተ ውል ደግሞ ኢትዮጵያን አይመለከታትም። በዚህ ውል መሰረት ግብፅና ሱዳን ውሃውን እስካሁን በብቸኝነት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። አሁን ግን ያ ሁኔታ ፈፅሞ ሊቀጥል አይችልም። ኢትዮጵያ የራሷን ልማት ለማከናወን ስትነሳ ባልፈረመችው ውል ላይ ተንተርሳ ለመደራደር የምትሄድበት አግባብ የለም። ለነገሩ እነሱም ቢሆኑ ችግር ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ያ ውል ህጋዊ መሰረት እንደሌለው ያውቃሉ። ያንን የቅኝ ግዛት ውል በግድ ተቀበሉ የሚባል ነገር ጊዜው ያለፈበት ነው። የአፍሪካ
ህብረትም ቢሆን ሊቀበለው አይችልም። ግብፅ እስካሁን ታደርግ እንደነበረው ሁሉ ተፈፃሚ እንዳማይሆን ስለገባትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያደረገችው ጥረት ስላልተሳካት ነው አሁን መከራዋን እያየች ያለችው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በውሃ የመጠቀም መብቷን በሚመለከት አለምአቀፍ ትኩረትን ከማግኘት አኳያ የሰራችው ስራ ምን ያህል ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እንግዲህ ግብፆች ያለውን የፖለቲካ ድክመት ተጠቅመው የአሜሪካንን እጅ እስከ መጠምዘዝ የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ይሄ እንግዲህ ግብፆች ምን ያህል በተንኮል የተካኑ መሆናቸውን ነው የሚያመላክተው። ዋሽተውም ቢሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ወደኋላ አይሉም። ኢትዮጵያ ደግሞ እንዲህ አይነት በሃሰት ላይ የተመሰረተ ባህሪ የላትም። በጊዜ ሂደትም እነዚህ የተወናበዱትም ሆነ በተንኮልና ሴራ የወደቁትም አካላት እያዩት ሲመጡ ግብፅ የበለጠ እየተጋለጠች ነው የምትመጣው። ከዚህ አንፃር እነሱ በሄዱበት ተንኮልና ሴራ ልክ አለምን ማሳመን ችለናል ብዬ ባላምንም ኢትዮጵያም ጥቅሟን በማስጠበቅ ረገድ ደህና ደረጃ ላይ ነው ያለችው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ይህ ግን የአረብ አገራቱንም ሆነ ምዕራባውያኑን በማሳመን ረገድ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰራው ስራ አመርቂ ነው ለማለት ያስችለናል?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እዚህ ላይ እንግዲህ ትንሽ ወደኋላ መመለስ አለብን ብዬ አስባለሁ። በእኔ እምነት የኢህአዴግ 27 ዓመታት ዲፕሎማሲ የበለጠ ህወሓትን ነው እንጂ የጠቀመው ኢትዮጵያን አይደለም። ይህንን በቅርቡ ተፈጥሮ በነበረው በሰሜኑ የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ ህወሓቶች አስቀድመው በየቦታው እና ድርጅቱ የራሳቸውን ሰዎች አስገብተው ስለነበር የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ትልቅ እገዛ አድርጎላቸዋል። ይሄ ግጭቱ ይፋ ከሆነ በኋላ በአለም ፊት ታይቷል። ስለዚህ በእኔ እምነት ለ 27 ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን የጥቅማጥቅም ዲፕሎማሲ አሁን በአንድና ሁለት ዓመት ውስጥ በቀላሉ ማሸነፍ አይቻልም። ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ እውነት ለመናገር እኛ ያልተዘጋጀንበት ስለነበረና እነሱ ደግሞ የዘረጉት መረብ ጠንካራም ስለነበረ ለጊዜው የእኛን ዲፕሎማሲ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል፤ ግን ይሄ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እውነት እስከያዝን ድረስ የተሸነፍን ብንመስልም በመጨረሻ አሸናፊ እንደምንሆን አልጠራጠርም። ምክንያቱም እነሱ የሄዱበት መስመር የውሸት ነው።
ከዚህ በመነሳት የአለም ሃያላን አገራት ተገቢውን ስራ ሰርተናል ለማለት ይከብዳል። ምከንያቱም ሲሰራበት የነበረው ዲፕሎማሲ በተቃራኒው ነበር ። የኢትዮጵያ ጥቅም በሚፃረር መልኩ ነበር። እናም አሁን በግልፅ ወጥቶ የሚታየው ያው ነው። ያም ሆኖ ግን አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ብዙ ነገሮች በአፍሪካም በአለምም የተወሰዱ የተከናወኑ እርምጃዎች አሉ። እዚህ ላይ የውጪው ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ያዘነበለው መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያ የማንንም ሉዓላዊነት ተፃርራ ወይም ሌሎች አገሮችን በሚጎዳ መልኩ የተንቀሳቀሰችበት ሁኔታ የለም። ይሄ ነው ይበልጥ እየታወቀ የመጣው። ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም ለማስከበር አብራ ለማደግ የተነሳች እንጂ ልክ ግብፅ በኢትዮጵያ ድህነት ላይ እንደበለፀገችው ሁሉ ኢትዮጵያም ያንን አላደረገችም። ግብፅም ሆነ ሱዳን ይከተሉት በነበረው መንገድ ከዚህ በላይ መቀጠል አይቻልም። ኢትዮጵያ በድህነት እየማቀቀች ሌሎቹ የሚበለፅጉበት ምክንያት የለም። የግድቡ መገንባት ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ የሩሲያ መንግስት ድርድሩ በአፍሪካውያን እንዲታይ ያራመዱት አቋም ምን ያሳያል፤ በሌላ በኩል ጉዳዩ ከኢትዮጵያና ሱዳን አልፎ የሃያሉን አገራት ልዩነት ያንፀባረቀ ነው?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እውነት ነው፣ በሚገባ ተንፀባርቋል። የአሜሪካኖቹ በዶናልድ ትራምፕ ጊዜ መወናበድ የግብፆች ተንኮል እንደሆነ ቀደም ብዬ ተናግሬያለሁ። አሁን ግን ይፋ እየሆነና እየታወቀ የመጣው እውነቱ ነው። እውነቱ አንደኛ ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የራሷን ውሃ መሆኑና ማንንም ሳትጎዳ ጥቅሟን ለማስጠበቅ መነሳቷ ነው። ግድቡ ኢትዮጵያን ከችግር ሊያወጣ የሚችል ነው እንጂ በግድቡ ምክንያት ማንም ጎረቤት አገር ችግር ውስጥ እንዳይገባ ታስቦ እየተሰራ ስለመሆኑ አለም እየተረዳ መጥቷል። በዚህ ረገድ የሩሲያዎቹ፣ የቻይኖቹና የህንዶቹ ይፋዊ የሆነ ለኢትዮጵያ አቋም ማሳየት መቻል ትልቅ አንድምታ አለው። ጥሩም ተገቢም ነው። እነዚህ አገራት እዚህ አቋም ላይ የደረሱት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት እንዳላት በማመናቸው ነው። ይሄ ደግሞ ማንም አገር የራሱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ከድህነት ለመውጣት የሚያደርገው ነው።
ኢትዮጵያ ደግሞ 110 ሚሊዮን ህዝብ ይዛ ለችግር ትጋለጥ ፣ እኛ ግን ለብቻችን ብልፅግናችንን እናስቀጥል የሚለው የግብፅና የሱዳን ሃሳብ በምንም አግባብ ተቀባይነት አይኖረውም። መንግስትም ይህንን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ወደ ብልፅግና የማሸጋገር ሃላፊነት አለበት። እነዚህ አገራት ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ተመስርታ እየገነባች ስለሆነ ነው የደገፏት። በሌላ በኩል ግን ከአሜሪካ ባሻገር አውሮፓም ቢሆን ስለግድቡ ብዙ ድምፅ አይሰማም። በተለይም እንግሊዝ የችግሩ መሰረት ስለሆነች ዝም ብትልም ኢትዮጵያ ላይ ቀና የሆነ አቋም አላት ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም እንደነገርኩሽ የነገሩ ምንጭ እሷው በመሆንዋ ነው። ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣሊያን ግን በኢትዮጵያ በኩል አንዳሉ ነው እኔ የማውቀው።
እንደምታስታውሽው መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ሲመጡ የፈረንሳይና የጀርመን መንግስታት ናቸው የጋበዟቸው። ይሄ ዝም ብሎ የመጣ ነገር አይደለም። ከዚያ በኋላ ጀርመንም ቢሆን ቻንስለሯ በአባይ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም በግልፅ አሳይተዋል። ኢትዮጵያ በገዛ የተፈጥሮ ሃብትዋ የመጠቀም መብት እንዳላት ተናግረዋል። እንዳውም ግብፅ ካሳ መክፈል አለባት በማለት ነው በይፋ የተናገሩት። ምክንያቱም ውሃው ከኢትዮጵያ የሚመጣ በመሆኑ ነው። ይሄ ይሄ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ የሚያጠናክረውና በአለም በዲፕሎማሲ ፊት ብዙ ድጋፍ ሊያስገኝ የቻለው። የግብፅ ደግሞ አሻጥር እየተጋለጠ የመጣው። አሁን አሁን እንዳውም አንዳንድ ነገሮች አያለሁ፤ ናይጄሪያ በኢትዮጵያ ወገን ሆና ኢትዮጵያን ለመርዳት እንደምትፈልግ፤ ሌሎች አገራትም እንደዚሁ ተመሳሳይ ዝንባሌ እያሳዩ ነው። ይሄ ነገር እንዳውም አፍሪካና አረብ በሚል ችግር ውስጥ እንዳይከተንም እፈራለሁ። ጥቁሮቹ አፍሪካውያውያን ኢትዮጵያን ለመደገፍ ከተነሱ፣ ሌሎች አረብ አገራት ደግሞ ከግብፅ ወገን ሆነው አፍሪካን ለመፃረር ሊነሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ። እንዲህ አይነት ነገር ባይሆን ጥሩ ነው። ሁሉም ነገር በሰላም ቢያልቅ ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የድርድሩ ሂደት ከአፍሪካ ህብረት እጅ እንዲወጣ ግብፅና ሱዳን የሚያደርጉት ጥረት እንዴት ይታያል?
ፕሮፈሰር መሃመድ፡– እኔ እስከማውቀው ድረስ ግብፅ አፍሪካዊ ስሜት የነበራት በጀማል አብዱልናስር ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ ግብፅ የአፍሪካ ነፃ አውጪ ድርጅቶችን በሙሉ ይደግፍ ነበረ። ለአፍሪካ ህብረት መመስረትም ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት አገሮች አንዷ ነች። ግብፅ ናስር ከሄዱ እና ሳዳት ከሞቱ በኋላ ከአፍካዊነት ወደ አረቡ አለም ነው ያዘነበለችው። አሁን እንደሚታየው የግብፅ ከአፍሪካውያን ጋር አብራ መስራት ያለመፈለጓ ጎዳት እንጂ አልጠቀማትም። ግብፅ ለእኔ በጣም አጣብቂኝ እና አስጨናቂ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው። ያቀደችው፤ ያሰበችው ሁሉ አልተሳካም። ስለዚህ አሁን የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ይፈታ የሚለውንም ነገር ስታስብ ከሳዳት ጀምሮ እስካሁን ያለው ፀረ አፍሪካ ማለት ባይቻል እንኳን ከአፍሪካ ይልቅ የአረብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት አሁን ላይ የጎዳቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም አፍካውያን ነን ፣ ችግራችንን የአፍሪካ ህብረት ይፍታልን ካሉ ለአፍሪካ ያሳዩት መልክ በቂ አልነበረም ማለት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ውጪ ብዙ አገሮችን የሚያካትት በመሆኑ ግብፆች የአፍሪካውያኖችን ልብ ለማግኘት የተቸገሩ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ይሄ ችግር የለባትም። እውነት ለመናገር አረቦችም በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው አመለካከት እየተቀየረ መጥቷል። የነበራቸውን ጥላቻም ረገብ አድርገውታል። ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው እንደዚህ አልነበረም። አረብ ሊግ ብዙ ጊዜ የሚያስተልፈው ውሳኔ ከኢትዮጵያ በተፃራሪው የቆመና ግልፅ ወገንተኝነት የሚታይበት ነበር። ከመገንጠል ጥያቄ ጀምሮ አሁን ስለተከሰተው ችግር ድረስ ውግንናቸው ወዴት እንደሆነ ይታወቃል። እስከማስታውሰው ድረስ አብዛኞቹ የአረብ አገራት ግብፅን የሚደግፍና ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ነበር የሚያራምዱት። አሁን ላይ የአለም ፖለቲካም እየተቀየረ ነው። አሁን ላይ በሰላምና በውይይት እንጂ በጦርነት ችግር መፈታት እንደማይቻል አገራት ተገንዝበዋል። ግብፅ ይህንን ሰላማዊ መንገድ ስታምንበትና ወደ ቀልቧ ስትመለስ ምንአልባት የተረጋጋ ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ግብፅ የለመደችው እስካሁን በሌላው ድክመትና በሌላው ድህነት ላይ ለመበልፀግ ነው። ይሄ ነገር መቆም አለበት፤ ቆሟልም ደግሞ። ከዚህ ወዲያም ፈፅሞ ወደ ኋላም ሊመለስ አይችልም።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የጉብኝት ጥሪ ያልተቀበሉበት ምክንያት ምንድነው ይላሉ? ከበስተጀርባውስ ምንአንድምታ ይኖረዋል ብለው ይገምታሉ?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– ይህንን ጉዳይ በሚመለከት አንዳንድ የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ ባለሙያዎች በአልጀዚራም ሆነ በሌሎች አለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ እየቀረቡ የሚናገሩት ነገር አለ። ግድቡ ሱዳንንም አይጎዳም የሚል አቋም ነው ያላቸው። የኢትዮጵያም አቋም ይኸው ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድብ የምትሰራው ሌሎችን ለመጉዳት አስባ አይደለም። በዚያ መልክ ደግሞ የተንቀሳቀሰ የፖለቲካ አካሄድ የለም። አሁን ላይ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ግብፆች የበለጠ ውሸታቸው የሚጋለጥ ነው የሚሆንባቸው። ኢትዮጵያ ምንም የምትደብቀውም ሆነ የምታፍርበት ነገር ስለሌላት ነው በይፋ እንዲጎበኙ የጋበዘቻቸው። ይህንን ማንም መጥቶ ማየትና እውነታውን መገንዘብ የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው። በመሆኑም እዚህ መጥተው መጎብኘታቸው እነሱ ለሚያከናውኑት ተንኮልና ሴራ እንቅፋት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይሄም ራሱ የበለጠ ራሳቸውን ያሳጣል እንጂ አይጠቅማቸውም። ለዚህም ነው መምጣትና መጎብኘት ያልፈለጉት ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ምንአልባት ሁለቱም አገራት በእምቢታቸው የፀኑት ያለባቸውን የውስጥ ፖለቲካ ትኩሳት ለመሸፈን ሊሆን አይችልም?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እውነት ለመናገር ይሄ ግልፅ ሆኖ የሚታየው ሱዳን ላይ ነው። ፕሬዚዳንት አልሲሲ ሱዳን ሲመጡ ምን ያህል ረብሻ ሱዳን ውስጥ እንደነበር አይተናል። እሳቸውን ላለመቀበል በተደረገው ተቃውሞ ነው ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው የተመለሱት። ስለዚህ እውነቱን ለመናገር የሱዳን ህዝብ ግድቡንም ሆነ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሚመለከት ግልፅ አቋም ነው ያለው። ያም ለወታደሩም ግፊት በማድረግ ረገድ ጫና ማሳደሩ አይቀርም። ወታደሮቹም ከዚህ የበለጠ ቢለጥጡት ራሳቸውንና አገራቸውን ችግር ውስጥ ነው እንጂ የሚከቱት መፍትሄ አይሆንም። ግብፅ ውስጥ በትክክል ለመናገር ቢከብድም አልሲሲ የሚከተሉት ፖለቲካ ራሱ በራሳቸው ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያነሳሳ በተጨባጭ አይተናል።
ይሄ እንግዲህ እሳቸው የአገር ውስጥና የውጪውን ፖለቲካ አስታከው የግብፅን ጥቅም አስጠብቃለሁ ብለው ከተነሱ ነገር እነሱ እንደሚፈልጉት ሳይሆን ሲቀር መነሳቱ አይቀርም። እኔ እንደምገምተው ግብፅም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ወደ ጦርነት መግባት ትፈልጋለች ብዬ አላምንም። ጦርነት ማንንም አይጠቅምም። ህዝቦችም ይህንን ይፈልጋሉ ብዬ አላምንም። መንግስታት ግን በራሳቸው ላይ ሌላ ችግር እየፈጠሩ ያንን ሁኔታ ለማራዘም ይሞክራሉ እንጂ በግብፅም ሆነ በሱዳን በኩል ጦርነት መፍትሄ ነው ወደ ጦርነት እንሂድ የሚል ነገር አላየንም። ይህም መታወቅ አለበት። ምክንያቱም የአለም ሁኔታ ነው ይህንን የሚያንፀባርቀው። በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በቀላሉ ወደ ጦርነት መግባት ይቻል ነበር። አሁን ግን ሁኔታው በራሱ አስቸጋሪ በመሆኑ የሚቻል አይደለም። ወደዚያ እንድንገባ የሚፈልጉ ሃይሎች እንዳሉ ይታወቃል። ሆኖም ቀላል አይሆንም።
አዲስ ዘመን ፡– የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ይጠናቀቃል ከተባለበት ዓመት በላይ መዘግየቱ የምን ውጤት ነው ይላሉ? ባለፉት ሶስት አመታት የግንባታው ፍጥነት በሚገባው ልክ ሄዷል ማለት ይቻላል?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– ይሄውልሽ ይሄንን የህወሓትን አጠቃላይ ባህሪና አባካኝነት በአንድ ምሳሌ ልጥቀስልሽ ፤ በደርግ ጊዜ ጣና በለስ ፕሮጀክት ነበር። በጣም ስኬታማ የነበረ ፕሮጀክት ነበር። በዚያን ጊዜ ምዕራባውያን በሙሉ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ጥለው ምንም የማይሰጥበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። እንግዲህ በዚያ ጊዜ ነው የአውሮፓ ህብረት ገንዘብ ሰጥቶ ጣና በለስ ፕሮጀክት እውን መሆን የቻለው። እናም ዋናው የአውሮፓ ህብረት አላማ የዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ ስለነበር ኢትዮጵያ ደግሞ ከረሃብ መውጣት አለባት ብለው ስለሚያምኑ አማራጭ ነገሮችን ልትሰራ የምትችልበትን ፕሮጀክት ነው የነደፈው። የአውሮፓ ህብረት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሆኖ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው። ምክንያቱም በዚያ ወቅት በነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ እንግሊዝና ጀርመን የጣና በለስ ፕሮጀክት እንዲተገበር አይፈልጉም ነበር። ያሸነፉትም ፈረንሳይና ጣሊያኖች ናቸው። ሳሊኒም በዚያ ፕሮጀክት ነው በኢትዮጵያ ውስጥ እግሩን ያስገባው።
እናም ያ በጣም ስኬታማ እየሆነ መጣ። ጣና በለስ ፕሮጀክት ቢኖር ዛሬ ከፍተኛ ውጤት ይኖረው ነበር። ግን ህወሓት መጀመሪያ እንደመጣ ያፈረሰው ጣና በለስ ፕሮጀክትን ነው። ምክንያቱም ጣና በለስ ሲጀመር ሳዳት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጃለሁ ግድብ እሰራለሁ ብላ ካሰበች እኔ ጦርነት አውጃለሁ ብሎ ነበር ። ይሄም ደግሞ በአደባባይ የተናገረው ነው። ስለዚህ ያን ያህል ነበር። የህወሃት አመራሮች ግብፅን ለማስደሰት ሲሉ የጣና በለስ ፕሮጀክትን ምስቅልቅሉ እንዲወጣ አድርገውታል። ያለውንም ገንዘብ ጠቅልሎ ወደ መቀሌ ነው የወሰደው። ይሄ በታሪክ የሚያሳዝን ነው። አሁን ታዲያ ይህንን አይነት አቋም ያለው ድርጅት ግድብ ሰርቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ቆሟል ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም የሚያስብ ቢሆን ኖሮ ጣና በለስ ፕሮጀክት መጥፋት አልነበረበትም። ግንባታውን ያስጀመሩትም ቢሆን ሁኔታዎች እየተቀያየሩ በመምጣታቸው እስኪ እናስፈራራበት በሚል ተነስተው እንደሆነ አስባለሁ። በዚያ ላይ በዚህ ግድብ ስም ሙስና ተስፋፋበት እንጂ ግድቡ ይህንን ያህል ውጤት ያመጣል ተብሎ አልነበረም። ምንአልባት ህወሓት ስልጣን ላይ ቢቀጥል ኖሮ ችግሩ የተባባሰ ይሆን ነበር። የፖለቲካው መቀየር ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ መልክ መምጣት ለግድቡ ጥሩ ነገር ነው። አሁን የግድቡ ስራ እየሄደ ነው። ውስጡን ባላውቅም ግድቡ ከማለቅ ወደኋላ የማይመለስ ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ ህዝቦቿን ወደ ብልጽግና አመራለሁ ካለች ይሄ ግድብ ማለቅ አለበት። እስከተወሰነ ጊዜም ቢሆን መስዋዕትም ተከፍሎ ማለቅ አለበት። ምክንያቱም ወሳኝ ነው። በመሆኑም ይሄ ነገር በመንግስትም ታስቦበት ወደ ፍፃሜ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ። መቼ የሚለውን ነገር ባላውቅም።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንፃር በዲፕሎማሲም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ይቀራታል የሚሉት ስራ ካለ ይግለፁልን?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እንግዲህ በግድቡ ጉዳይ የነበረውን የሜቴክ ሚና የታረመ ይመስለኛል። እሱ ደግሞ ባይታረም ትልቅ ችግር ነበር። ያንን በማረም ሂደት የተወሰነ መስዋዕት ተከፍሏል ብዬም አምናሁ። የጊዜም፤ የገንዘብም። አሁን ላይ ሂደቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ደርሷል የሚል ግምት አለኝ። ምንአልባት እንደተባለው በጊዜ ላይፈፀም ይችላል እንጂ መፈፀሙ አይቀርም። ምክንያቱም አሁን የተመቻቸ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ከዲፕሎማሲው አንፃር በእርግጥ ህወሓት ባደረገው ስራ ያልተዘጋጀችባቸው ሁኔታ ስለነበረ ኢህአዴግ ራሱ ነው ተቀይሮ ስልጣን ላይ የመጣው። ስለዚህ አሁንም ቢሆን ብዙ የሚታዩ ነገሮች አሉ። ከዲፕሎማሲው አንፃር አሁንም የኢህአዴግ አምባሳደሮች እዛው ቦታ ላይ ናቸው። በእርግጥ ሁሉንም ሰው በአንድ ጊዜ መቀየር ለመንግስት ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ሰው አንደ ዳቦ ተጠፍጥፎ አይወጣም። ጊዜ ይወስዳል። ቅድሚያ የሚሰጥበትም ሁኔታ አለ። የአገሪቱ ሁኔታ ዝም ብሎ እንዳላየ ለማየት የሚቻልበት ሁኔታ የለም። ነገር ግን ራሱ ፈተናው ትምህርት ነው። እናም ይህንን ፈተና ማለፍና ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደረስበት ሁኔታ አለ። እኔ ተስፋ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– እንደአጠቃላይ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያሎዎት ምልከታ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መሀመድ፡– እንግዲህ ይሄ ምርጫ መካሄድ የነበረበት ቀደም ብሎ ነው። ግን በኮቪድ 19 ምክንያት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል። የኢትጵያም ፖለቲካ ሁኔታም በእርግጥ እንዲሁ ዝም ብሎ ያለምርጫ ሊቀጥል የሚችልበት እድል የለም። ምርጫ መካሄድ አለበት። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የሰሜኑ ችግር ተፈጠረ። ያ ሁሉ ሆኖ ግን የኢትዮጵያ መንግስትና ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ሰላማዊና ፍትሃዊ አንዲሆን የማድረግ ፍላጎት አንዳላቸው አምናለሁ። ነገር ግን ይሄ ምርጫ ተካሂዶ ህጋዊ የሆነ መንግስት ስልጣን ላይ እንዳይመጣ የማይፈልግ ሃይል አለ። ጥቅሙ የተነካበት ሃይል አለ፣ በጦር ሜዳ የተሸነፈ አለ፤ ስለዚህ ይህንን ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዳይሆን የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል፤ ይጠበቃልም። ያም ሆኖ ግን መንግስት ባለው ሃይልና ባለው መሳሪያና ዘዴ ተጠቅሞ ሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ አዲስ መንግስት አንዲመሰረት ማድረግ ከቻለ መልካም ነው። ለአገራችን ህልውናም ሆነ ለፖለቲካው ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ግን ይሄ ነገር አንዲበላሽ የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ መታወቅ አለበት። ከተሳካላቸው አገሪቱን ለማፍረስ ወደኋላ ይላሉ ብዬ አላምንም። ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ካልሆነ ወይም ደግሞ ቢራዘም የበለጠ ችግር ውስጥ እንገባለን ብዬ እገምታለሁ። ይህ ከሆነ ደግሞ ብዙ እንጎዳለን። በመሆኑም መንግስትና ምርጫ ቦርድ ይህ እንዳይሆን የበኩላቸውን መስራት ይጠበቅባቸዋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– ለአገር ሰላም መደፍረስም ሆነ ለግጭቶች መባባስ የእናንተ የአገሪቱ ሊሂቃን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይነሳል። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ፕሮፌሰር፡– ልክ ነው። የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ተወጥተን ቢሆን ኖሮ የተሻለ ደረጃ እንደርስ ነበር። እንዳልደረስንም ይታወቃል። ለችግሩ መባባስም የእኛ ድርሻ እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለውም። እኛ ምሁራን ከድሮም ጀምሮ የሚጠበቅብን ሚና ተጫውተን አገራችንን አሻግረናል የሚል አምነት የለኝም። ወደኋላ ያስቀረንም ሚናችንን በሚገባ አለመወጣታችን ነው። እንግዲህ የአገሪቱ ድህነት ፣ ወደኋላ መቅረት የሚያሳየው ትርጉም ከባድ ነው። ምሁሩም ቢሆን የራሱን ነገር የሚያየው ከራሱ ጥቅም አንፃር ነው። የእኔ ቦታ የት ነው ? ምንድን ነው? ወደሚለው የበለጠ ያደላል። ስለዚህ ሁላችንም ከተጠያቂነት አናመልጥም።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር መሀመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013