አዲስ አበባ፤- የግል ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 4 ቢሊዮን 121 ሚሊዮን 378 ሺህ 161 ብር የጡረታ መዋጮ መሰብሰቡን አስታወቀ።
የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው መንግስቴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው 3ነጥብ9ቢሊዮን ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም አፈጻጸሙ የእቅዱን 106 በመቶ ነው፡፡ ይህም ኤጀንሲው በግማሽ ዓመቱ ስኬታማ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኤጀንሲው ብር መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የሰበሰበውን ገንዘብ በኢንቨስትመንት ላይ በማዋል አመርቂ ሥራ አከናውኗል። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 3 ቢሊዮን 824 ሚሊዮን 492 ሺህ ለኢንቨስትመንት ያዋለ ሲሆን፤ ኤጀንሲው በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት ላይ ያዋለው ገንዘብ መጠን 27 ቢሊዮን 198 ሚሊዮን 160 ሺህ ደርሷል። በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ 155 ሚሊዮን 541 ሺህ 176 ብር ወለድ አግኝቷል።
አቶ ግዛቸው የጡረታ መዋጮን ከመሰብሰብና ለኢንቨስትመንት ከማዋል በተጨማሪ በዕድሜ፣ የሥራ ላይ ጉዳት፤ ህመም እና ለህጋዊ ወራሾች የአበል ክፍያ ሰጥቷል። የገቢ መቋረጥን በመተካትም ባለፉት ስድስት ወራት ለ2 ሺህ 505 ባለመብቶች የአበል ጥያቄ አቅርበው መረጃዎችን በማሟላት የጡረታ መዋጮ ባለመብቶች የአበል ክፍያ እንዲያገኙ ተደርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ በለፉት ስድስት ወራት የጡረታ መዋጮ በትክክል መከፈሉን ቁጥጥር ለማድረግ በ2 ሺህ 526 ድርጅቶች የኦዲት ሥራ ተሰርቷል። የባለመብቶችን መረጃዎች በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መረጃ ቋት ለማስገባት በተሰራው ስራ በስድስት ወር ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የግል ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ተጠቃሚዎችን መረጃ በመረጃ ቋት ውስጥ ማስገባት ተችሏል።
ያልተሰበሰበ የጡረታ ተጠቃሚዎች ገንዘብ በህግ አስገዳጅነት በግማሽ ዓመቱ ከ541 ድርጅቶች 45 ሚሊዮን 148 ሺህ 47 ብር ተሰብስቧል። ሆኖም አሁን በህግ አስገዳጅነት የሚሰበሰብ 93 ሚሊዮን 463 ሺህ 558 ብር አለ። ከዚህም በተጨማሪ ለድርጅቱ ፈተና የሆነበት የሠራተኞች መልቀቅ ሲሆን፤ በመንፈቅ ዓመቱ 176 ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ለቅቀዋል። የለቀቁበትም ምክንያት የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ፤ የኤጀንሲው የመንፈቅ ዓመት አፈጻጸም 91 በመቶ ነው። ይህም ሊደረስበት ከተቀመጠው ስትራቴጂክ ዕቅድ ዒላማ አንጻር ከፍተኛ አፈጻጸም ነው፡፡ ኤጀንሲው ያጋጠሙትን ችግሮች በመቅረፍና በአፈጻጸም የታዩትን ድክመቶች በማሻሻል በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ