መርድ ክፍሉ
የህብረተሰቡን የነቃ ተሳትፎ ከሚፈልጉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ምርጫ ነው። ምርጫ ከተሳትፎ ባሻገር የአገርን እጣ ፈንታ ለመወሰንና ታሪካዊ አሻራን ለማስቀመጥ የምንጠቀምበት ነው።
በኢትዮጵያ ምርጫ የተጀመረው በንጉሣዊው ስርዓት አገዛዝ ዘመን ሲሆን ይህ ሁኔታም እስካሁን ድረስ ቀጥሏል። በተያዘው ዓመት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ይደረጋል። በዚህ ምርጫም ህብረተሰቡ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያደርገውን የመራጭነት ካርድ እንዲያወጣ ግፊት እየተደረገ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ሰሞኑን ‹‹ካርድ አወጣለሁ፣ በምክንያታዊነት እመርጣለሁ›› በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ የጋራ መግባባት ለተሻለ የሀሳብ ነፃነት ለማምጣት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ወጣቶች ያላቸውን ሀሳብ እንዲያካፍሉ አድርጓል።
ከኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የመጣው ወጣት አላዛር ሰለሞን፤ ስለምርጫ ካርድና ተረጋግቶ ስለ መምረጥ ሲነሳ ሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ህብረተሰቡ በንቃት የተሳተፈበትና ለመምረጥ ከለሊት ጀምሮ ሲጋፋ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር መስማቱን ይናገራል።
በአሁን ወቅት ያለው ወጣት ስለምርጫ እየተነገረው ያደገበት መንገድ የተዛበ በመሆኑ አብዛኛው ወጣት የመራጭነት ካርድ ለማውጣት ፍላጎቱ ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቅሳል። እራሱንም እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፤ የመራጭነት ካርድ ወጣቱ እንዲያወጣ ቅስቀሳ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም የመራጭነት ካርድ ለማውጣት ዘግይቶ እንደነበር ያስረዳል።
ምርጫው ከመድረሱ በፊት ስለምርጫና ዴሞክራሲ እንዲሁም በሰላም ስለመኖር የሚያስብ ወጣት መፈጠር የግድ ያስፈልግ እንደነበር የሚናገረው ወጣት አላዛር፤ ምርጫ የአንድ ወቅት ክስተት ቢሆንም ይዟቸው የሚመጣውን የሰላምና የዴሞክራሲ ትሩፋት ሊረዳና ሊጠቀምባቸው እንደሚገባ ይናገራል።
ቀደም ብሎ የነበረው ትውልድ ስለምርጫ ሊያውቅ ቢችልም አሁን ያለው ትውልድ ግን ሰፊ የግንዛቤ ሥራ እንደሚፈልግ ያስረዳል። ስለምርጫ ማንም ሰው ቢጠየቅ በአገሪቱ ምርጫ ለውጥ ሲያመጣ አይቶ እንደማያውቅ እንደሚናገር ይጠቁማል። በዚህ ደግሞ ወጣቱ በአሁኑ ምርጫ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብሎ እንዳያምን ማድረጉን ያብራራል።
በአገሪቱ ለውጥ ሲመጣና መንግሥት ሲቀየር የነበረው በድንጋይና በዱላ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አላዛር፤ ይህ ሁኔታ አብዛኛው ወጣት አዕምሮ ውስጥ ተከትቦ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳል። መንግሥት ስለመቀየርና አገር ስለመለወጥ ሲታሰብ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ሲታሰቡ የሰላም መንገዶች ሊታዩ ይገባ እንደነበር ያመለክታል።
በአገሪቱ ዴሞክራሲ ኖሮ እንደማያውቅ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር እንደነበር በመጥቀስ፤ ቀደም ብሎ በነበሩ ነገሥታት የዴሞክራሲ ስርዓቶች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩ ይጠቅሳል።
በአሁን ወቅት ወጣቱ የምርጫ ካርድ ለምን አልወሰደም ከመባሉ በፊት የመራጭነት ካርድ ያወጣው ሰው ብቻ በምርጫ ያምናል ወይ የሚለው መታየት አለበት። የመራጭነት ካርድ ያላወጡ ሰዎች ብዙ ሲሆኑ የሚደረገው ምርጫ ሁሉን ያካተተ አይሆንም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል። በዚህም የጥቂቶች ድምፅ ብቻ ወደሚሰማበት ሁኔታ ሊኬድ እንደሚችል ወጣት አላዛር ያብራራል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ወጣቱ የመጡበት መንገድ በተሳሳተ ግምት በመሆኑ በዴሞክራሲና በሰላማዊ ምርጫ የሚያምን ወጣት አለ ብለው እንደማያምኑ በተደረጉ ውይይቶች መታየታቸውን ወጣት አላዛር ያስረዳል። ፓርቲዎቹ የወጣት ክንፍ አደራጅተው እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ መያዛቸው አስደንጋጭ መሆኑንም ይናገራል።
ወጣት ወንደሰን ከበደ የመጣው ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወጣት ማህበር ሲሆን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በአዲስ አበባ ከተማ ያወጣው ሰው ቁጥር መምረጥ ከሚችለው ነዋሪ ብዛት ልክ አለመሆኑ እየተነገረ መሆኑን ይጠቅሳል። አገርን የሚያቆየው ወይም የሚመራን መሪ እድል የሚሰጥበትን ካርድ ብዙ ሰው አለማውጣቱ ሊያስገርም እንደማይገባ ይናገራል። በምክንያትነትም ቅድሚያ የመኖር ዋስትናን ማረጋገጥ አጠራጣሪ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነ ይጠቅሳል።
በአሁን ወቅት ሁሉም ተነስቶ የነፃነት ታጋይ ነኝ፣ የምወክልህ እኔ ነኝ፣ ችግርህን እማውቅልህ እኔ ነኝ፣ እንዲሁም ሁሉም ተነስቶ ወደ እሳት ውስጥ ግባ የሚል በመሆኑ ጉዳት እያስከተለ ነው። የወጣት አደረጃጀቶች ወጣ ብለው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የመቆንጠጥ ሁኔታዎች እንዳሉ ይጠቅሳል። በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ስልጣን ለመያዝ ህዝቡን እንደሚፈልጉት ሁሉ ለአገሪቱ ምን ሰርተው ነበር የሚለው መታየት አለበት። ወጣቱ የሚወክለውን ለመምረጥ ቅድሚያ ልቡን የሚገዛው ፓርቲ በአሁን ወቅት እንደሌለ ያመለክታል።
የመራጭነት ካርድ ሲወጣ የሚፈለገውን መምረጥ፣ ገዥ የነበረውን ከሥልጣን ማንሳት ወይም ባለመምረጥ ድምፅ መከልከል ሁሉ ያስችላል። ነገር ግን በአሁን ወቅት የመራጭነት ካርድ መውሰድ ምርጫ ካልተከናወነበት ጥቅም እንደሌለው ያመለክታል። ምክንያቱም የወጣው ካርድ ለቁጥር ብቻ ስለሚሆን ነው። ማንኛውም ሰው የመራጭነት ካርድ ለማውጣት ሲያስብ የሚወክለኝ ወይም አገሪቱን መምራት ያለበትን ፓርቲ ውስጡ ካላመነ ካርድ ስላወጣ ብቻ መምረጥ እንደሌለበት ይናገራል።
እንደ ወጣት ወንደሰን ገለፃ፤ ለምርጫው በተፎካካሪና በገዥው ፓርቲ መካከል የሚደረገው ክርክር አብዛኛው አማራጭ ላይ ሳይሆን ዘለፋ ላይ ያተኮረ ነው። መራጩ ህብረተሰብ ከክርክሩ መስማት የሚፈልገው የተሻሉ አማራጮችን እንጂ የርስበርስ ንትርክ አደለም። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አገሪቱ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ሲሆን የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባ ነበር።
በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ወደ ራሳቸው ብሄር አድልተው የሚንቀሳቀሱበት መንገድ እየበዛ ነው። ለህዝብ በሚቀርቡበት ወቅት ግን አንድነትን የሚሰብኩ ቢመስሉም ለራሳቸው ብሄር ወግነው መንቀሳቀሳቸው ችግር እየፈጠረ ነው። በዚህም ህብረተሰቡ በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች መሰላቸቱን ወጣት ወንድወሰን ይናገራል። የጋራ መግባባት ለመፍጠር ፊት ለፊት ቀርበው ሀሳባቸውን አስርፀው ገዢ የሆነ ሀሳብ ቢፈጠር መልካም ነገር ሊመጣ ይችላል።
ለቀጣይ የአገሪቱን ህልውና ለመወሰን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መሳተፍ አስፈላጊ ቢሆንም ሀሳብን በነፃነት የመግለፁ ሂደት ሲታይ ብዙ አጠያያቂ ነገሮች ይኖራሉ። አሁን ያለው ሁኔታ ወጣቱን ወዳልተገባ ነገር እየመራ በመሆኑ ማስተካከያዎች እንደሚያስፈልጉ ያመለክታል።
ከየካ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማህበር የመጣችው ወጣት ፅዮን ተሾመ እንደምትናገረው፤ በመጀመሪያ ካርድ ማውጣት ማለት በቀጣይ አምስት ዓመት ሊመራን የሚችል ፓርቲን እንደ መቅጠር ነው። ፓርቲውን አስተዳድረን ብለን የኮንትራት ውል የምንሰጠው ደግሞ ካርድ ማውጣት ሲቻል ነው። እንደ ወጣት በምርጫው ከሚሳተፉ ፓርቲዎች የሚሰሙ አማራጭ ሀሳቦችን በመያዝ ወደ ምርጫው መገባት አለበት።
የጋራ የሆነችን አገር ለመጠበቅ በቅድሚያ አገር እንዴት መቀጠል አለባት የሚለው ጉዳይ መታየት አለበት። ኢትዮጵያ በቀላሉ የተመሰረተች አገር ሳትሆን ብዙ ታሪክ ያላትና የዓለም ስልጣኔ መጀመሪያ የሆነች ነች። ኢትዮጵያ ከብሄርና ከጎሳ ብጥብጥ ወጥታ እንደ አገር መቀጠል አለባት የሚለው ጉዳይ ሁሉንም ሰው ሊያሳስበው እንደሚገባ ታመለክታለች።
ሁሉም በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች የመጀመሪያ አጀንዳቸው ሊሆን የሚገባው እንዴት አገሪቱን በአንድነት ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ጉዳይ ነው። ቀደም ብሎ በቱሪስቶች ተመራጭ የነበረችው አገር አሁን ባሉት ብጥብጦች ጎብኚዎች እየራቁ መሆናቸውን ትናገራለች።
የመራጭነት ካርድ ህብረተሰቡ አለማውጣቱ እንደሞኝነት እንደምትመለከተው የገለፀችው ወጣት ፅዮን፤ የመራጭነት ካርድ የተሻለ የሚባለውን ፓርቲ ወደ ሥልጣን ለማምጣት እንደሚረዳ ትጠቅሳለች።
የመራጭነት ካርድ ወጥቶም አሁን ያለው ደም መፋሰስ እስካልቆመ ድረስ እንዴት ምርጫ ሊኖር ይችላል የሚሉ ሰዎች መበራከታቸውን በመጠቆም፤ ይህን ሁኔታ ለማስቆም የመራጭነት ካርድ አውጥቶ በምርጫው መሳተፍ የግድ እንደሚል ታስረዳለች።
የተሻለ የሀሳብ ነፃነት እንዲኖር ምርጫ መሳተፍ አስፈላጊ ሲሆን አገሪቱን ከማስቀጠልና ከማሻገር አንፃር ወሳኝ ነገር ነው። አገሪቱን አንድ አድርጎ መግዛት የሚችልን ፓርቲ መምረጥና ማስቀመጥ የህብረተሰቡ ግዴታ መሆኑን ትጠቅሳለች።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሀፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ እንደሚናገረው፤ ስለ ምርጫ ቤት ለቤት ሄዶ መቀስቀስ ሳይሆን በተለያዩ ሀሳቦች ላይ በመሰባሰብ ውይይት ሊደረግ ይገባል። የጋራ መግባባት ምንድነው ለሚለው ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ያላቸው የጋራ መግባባት ላይ መሰረት ያደረገ ነው።
የመጀመሪያው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የጋራ መግባባት ይኖራል። በድህነት ውስጥ በመኖር መግባባት አለ። የተለያዩ ችግር ውስጥ አገሪቱ እንዳለች መግባባት ይቻላል። ሌላው ደግሞ በአገሪቱ እድገት እንዲመጣ መፈለግ ላይ መግባባት አለ። ሰላምና ነፃነት እንዲመጣ ማድረግ ላይም በተመሳሳይ መግባባት አለ።
እነዚህ ጉዳዮች እንዲቀየሩ ተስፋ ማድረግ የጋራ መግባባት የሚያመጣ ሲሆን የተሻለ የሀሳብ ነፃነት ለማምጣት ደግሞ የአገሪቱ የነፃነት ሁኔታ ከነበረበት በላቀ ደረጃና ባልተገደበ ሁኔታ ማደግ አለበት። የሚደረጉ ውይይቶችም ምክንያታዊነት ላይ ተመስርተው መካሄድ አለባቸው። እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ደግሞ ትልቁ እድል የሚመጣው በምርጫ ነው። ማንኛውንም ሀሳብ በነፃነት ለማሰብና ለመወሰን ምርጫ ከፍተኛ እድል ይሰጣል።
ሁሉም የሚፈልገውን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ አውጥቶ መቀመጥ አለበት። የህብረተሰቡን ሀሳብና ያሉትን ችግሮች ሊፈታና ነፃነትና እኩልነት ሊያረጋግጥ የሚችል ፓርቲ ለመምረጥ የግድ ካርድ ማውጣት ተገቢ መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ይናገራል።
የምርጫ ካርድ የአንድ አገር ነዋሪ በመሆን የሚገኝ እድል ሲሆን ማገናዘብና መወሰን የሚችል ሰው የአገርን እጣ ፈንታ እንዲወስን የተሰጠው እድል መሆኑን ወጣት ይሁነኝ ያስረዳል። በምርጫ ካርድ ውሳኔ የሚሰጠው ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የተሻለ ነገር አድርጎ አገሪቱን ወደፊት የሚያዘልቅ አካል በመሆኑ በመጪው ትውልድ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑ ይጠቁማል።
በዚህም የምርጫ ካርድ መያዝን እንደ ትልቅ እድል መመልከት እንደሚገባም ያስገነዝባል። መራጩ ህብረተሰቡ የመራጭነት ካርድ ማውጣት ላይ ለምን ዘገየ ሲባል የተለያዩ ምክንያቶች ሊቀመጡ ይችላሉ።
መንግሥት በሁኔታው ላይ ማስተካከል የሚገባውን መለየት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አባሎቻቸው የምርጫ ካርድ ማውጣት አለማውጣታቸውን መለየት እንዲሁም ህብረተሰቡ ግንዛቤ ይዞ እንዲመርጥ ማድረግ ያስፈልጋል ይላል።
እንደ ወጣት ይሁነኝ አባባል፤ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአባሎቻቸው ቁጥር ልክ የመራጭነት ካርድ ወጥቷል ወይ የሚለው ጉዳይ መታየት አለበት። ፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያክል አባል እንዳላቸው በመለየት ካርድ እንዲያወጡ ሊደረግ ይገባል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች መራጮች ካርድ አውጡ ብቻ ብለው ከመናገር በዘለለ ወደ ራሳቸው መመልከት ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ሲቪክ ማህበራት ህብረተሰቡ በምርጫው በንቃት ተሳታፊ እንዲሆን በአግባቡ እየቀሰቀሱ መሆናቸው ሊታይ ይገባል። ወጣቱ በተሻለ የሀሳብ ነፃነት ተወያይቶ የተጣለበትን አደራ የመወጣትና የበለፀገ አገር ለቀጣይ የማስረከብ ግዴታ አለበት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013