ለምለም መንግሥቱ
ወፍ ጭጭ ሲል ከመኝታዋ ትነሳለች።መጸዳጃ ቤት ከደረሰች በኋላ በቀጥታ የምታመራው ወደ ዕለት ከዕለት ስራዋ ነው። ሳትሰለችና ሳትደክም እንደየቅደም ተከተሉ የቤት ስራዋን ትከውናለች። ቤትና ግቢውን ማጽዳት፣ ለልጆች ቁርስ አዘጋጅቶ ትምህርትቤት መሸኘት የጠዋት ቀዳሚ ተግባሯ ነው።
የቤት ጽዳቱ በመጥረጊያ በመጥረግ ብቻ አያበቃም።መቀመጫው በድንጋይና በአፈር የተሰራ መደብ የሚባለው በመሆኑ በእበት በመለቅለቅ ታሳምራለች። ቁርስ በአብዛኛው የሚዘጋጀው ከበቆሎ ቂጣ ሲሆን፣ ሀለኮ የሚባለው ቅጠልም አይቀርም። እንደማባያ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ልጆች ትምህርት ቤት ከተሸኙ በኋላ ቡና ተፈልቶ ጎረቤት ይጠራል።ቡና አፍልቶ ጎረቤት መጥራት የአንድ ሰው ተራ ብቻ አይደለም። ዛሬ አንዷ ጋር፣ነገ ደግሞ ሌላኛዋ ጋር በተራ ነው የሚፈላው።ቡናው ከነቁርሱ ተዘጋጅቶ ይቀርባል።አንድ ሰው ተራ የሚደርሰው በሳምንትና ከዚያም ባነሰ ጊዜ ሊሆን ይችላል። እንደጎረቤታሞቹ ብዛት ይወሰናል፡፡በቡና ሰዓት ያልተገኘች ጎረቤት የእርሷ ፋንታ ወይንም ድርሻዋ ቁርስ ተቀምጦላት በተመለሰች ጊዜ ቁርስሽን ብይ ተብላ ይሰጣታል።
እርሷም ስለቆያት ቁርስና ጥሩም ጎረቤት በማግኘቷ ምስጋና አቅርባ ትበላለች።በአጋጣሚ ተረኛዋ ጎረቤት ጠዋት ላይ ቡና አፍልታና ቁርስ አዘጋጅታ ጎረቤቶችዋን መጥራት ካልቻለች ቡና ማፍላት የምትችል ሴት እንድታዘጋጅ ይነገራታል። የጠዋቷ ተረኛ የማታውን አዘጋጅታ ትጠራለች። የጠዋቱን ተራ ለማታ ታደርግ እንደሆን እንጂ ማሳለፍ አይታሰብም። ‹‹የሰው ጠጥታ ዝም ትላለች እንዴ?›› የሚል ወቀሳ እንዳይደርስባት ትጠነቀቃለች።
የ ምታፈላው ቡና እንኳን ባይኖራት የቡና ቅጠል ወቅጣ ታፈላለች።ቁርስ ከበሉ በኋላ ሁሉም ወደ ሥራ ይሰማራሉ።ወደ ጥጥ፣ሙዝ ልማትና በቆሎ እርሻ በመሄድ ማሳውን መፈተሽ፣ የደረሰ ሙዝ ካለ ቆርጦ፣ ጥጥ ለቅሞ በቆሎ ሰብስቦ በጋሪ ጭኖ ወደቤት መመለስ ደግሞ ሁለተኛው የቤት እመቤት ተግባር ነው።ከዚያ ወደ ማጀት ይገባሉ።
ከቦቆሎ ድቄት በበርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብልና ሌሎችም ቅመሞች፣ ሐለኮ ከተባለው ቅጠል ጋር፣በዘይትና ጨው ጣፍጦ ‹ፖሰሴ› የሚባለውን ምግብ አብስለው በማዘጋጀት በማሳ ላይ ለሚሰሩ ሠራተኞች ያደርሳሉ፡፡
ሠራተኞቹ ብዛት ስለሚኖራቸው ምግቡ በትልቅ ድስት ነው የሚዘጋጀው፡፡ሠራተኞቹን አብልተው፡፡በቡና ቅጠል ያፈሉትን ቡናም አጠጥተው አብረው እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት ድረስ እየሰሩ ይቆያሉ።ምግብ በቀን ውስጥ ሁለቴ ነው የሚበላው። ቁርስና ምሳ፡፡እንጀራ በአካባቢው የተለመደ አይደለም።በሳምንት አንድ ጊዜ ነው የሚጋገረው።
ከበቆሎ የሚዘጋጅ ምግብ ነው የሚዘወተረው። አንዳንዴም ቆጮ በጎመን ወይም ቆጮና ‹ፖሰሴ› ታሽቶ ይበላል።ምሽት ላይ አባወራው ከማሳ፣ተማሪዎችም ከትምህርትቤት ቤት የሚሰበሰቡበት ሰዓት በመሆኑ ለቤተሰቡ ለእራት የሚሆን ምግብ ማዘጋጀትም ሆነ ስለሚዘጋጀው ምግብ ማሰብ የቤት እመቤቷ ኃላፊነት በመሆኑ ለሠራተኞች ምግብና ቡና እንዲሁም የሚጠጣ ውሃ ያደረሰችበትን ዕቃ ይዛ ቀድማ ቤት ትገባለች፡፡
በአካባቢው ባህል ቤተሰቡ እራት ከበላ በኋላ ቡና ተፈልቶ ጎረቤት ይጠራል።ልጆች ከአዋቂ ጋር አይደባለቁም።ጎረቤቱ ተሰብስቦ ቡና እየጠጣና እየተጫወተ ያመሻል። ታዲያ የጎረቤቱ እጅ ሥራ አይፈታም። በተለይ ሴቶቹ የቤት እመቤቷ ያቀረበችላቸውን ጥጥ ከፊሉ ይፈለቅቃል።ከፊሉ ደግሞ ይፈትላል።
ሰዓቱ ገደብ የለውም።ጨዋታው ሞቅ ካለና እንቅልፋቸው ካልመጣባቸው ምሽቱ ይገፋል፡፡የቤቱ እመቤት ጎረቤቶችዋን ከሸኘች በኋላ ነው ጎኗን የምታሳርፈው።አባወራው ግን በፈለገበት ሰዓት የማረፍ ወይም የመተኛት መብቱ የተጠበቀ ነው።ይሄ የቤት እመቤቷ የዕለት ተዕለት ተግባር ነው፡፡
እርሷም ይህን የዕለት ተዕለት ተግባር በፀጋ ተቀብለዋለች ማለት ይቻላል።እንዲህ እንድል ያስደፈረኝ ይህን ህይወት ከሚኖሩት ወይዘሮ ምንትዋብ ሙኩሎ ጋር በነበረኝ የአጭር የቆይታ ጊዜ ከገጽታቸውም ሆነ ከአንደበታቸው የተረዳሁት በመሆኑ ነው።በጥሩ ፈገግታ ነበር ያጫወቱኝ።ለነገሩ ምን አማራጭ አላቸው ሊባልም ይችላል።ግን ትልቁ ነገር አምኖና ፈልጎ መቀበሉ ነው፡፡
ወይዘሮ ምንትዋብ እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢያቸውን ሴቶች የዕለት ተዕለት ውሎና አዳር ሁኔታ ያጫወቱኝ በሥራ አጋጣሚ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ኡጋዮ ቀበሌ በተገኘሁበት ወቅት ነው። ወይዘሮ ምንትዋብ ተወልደው ያደጉት በዚሁ አካባቢ ሲሆን፣ኑሯቸውን ለመደጎም ንግድና አንዳንድ ተጨማሪ ሥራ ቢሰሩም ዋና መተዳደሪያቸው ግን ግብርና ነው፡፡ሙዝና ጥጥ ያለማሉ፡፡ በቆሎ ያመርታሉ፡፡
ኑሯቸው ከከተማ ወጣ ባለ አካባቢ ቢሆንም አካባቢያቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃንን የመከታተል ዕድል ሰጥቷቸዋል። በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ የተለያዩ መረጃዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው ውጭ ስላለው ነገር እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል። ለገበያና ለተለያየ ነገር ወደ ከተማ ሲወጡም እንዲሁ ተሞክሮዎችን ስለሚያገኙ የኑሮ ዘይቤያቸው የገጠሩንም የከተማውንም ያማከለ እንዲሆን አግዟቸዋል። በዚህ በተፈጠረው አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን እስከ 10ኛ ክፍል ድረስም ቢሆን በመማራቸው ጥሩ ንቃተ ህሊና እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡
ወይዘሮ ምንትዋብ በትምህርታቸው ከ10ኛ ክፍል ያልገፉት በትዳር ምክንያት ነው፡፡ በ1994 ጥር 26 ቀን ከትዳር አጋራቸው ጋር ጋብቻ ሲፈጽሙ የቤተሰብም ሆነ የሌላ አካል ተጽዕኖ አልነበረባቸውም፡፡ ፈቃደኝነታቸው ተጠይቆ ፈቅደው ነው በካቶሊክ የእምነት ሥርዓት ያገቡት። በጥንዶች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጋብቻ በገጠር የተለመደ አይደለም፡፡ግን እርሳቸው አድርገውታል። ባለቤታቸውም እንደእርሳቸው ፊደል የቆጠሩ በመሆናቸው ምክንያትም ጭምር በመሆኑ ጋብቻው ሊቀል እንደቻለ ያምናሉ።ወይዘሪት ምንትዋብና ባለቤታቸው አራት ልጆች አፍርተዋል፡፡
ወይዘሮ ምንትዋብ እንዳጫወቱኝ ጠዋትና ማታ ቡና ከጎረቤት ጋር የማይቀር በመሆኑ ማህበራዊ ትስስራቸው ጠንካራ ነው። ታዲያ የመቀራረባቸውን ያህል በመካከላቸው አለመግባባትና ፀብ ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ብገምትም። እርሳቸው ግን እንዳላጋጠማቸውና ከአምስት ጎረቤቶቻቸው ጋር በመተሳሰብ እንደሚኖሩ ነው የነገሩኝ።ጠዋት ቡና ላይ ያልተገኘ ማታው ላይ መኖር የግድ ነው። በአንደኛው ሰዓት ካልተገኘ ‹እከሌ የት ሄደ?› ተብሎ ይፈለጋል፡፡
ለመሆኑ የእረፍታቸው ጊዜ መቼ ይሆን? ወይዘሮ ምንትዋብ ‹‹ምን እረፍት አለ ብለሽ ነው፡፡ምግብ ማዘጋጀቱና የቤቱ ሥራ አያልቅም።ከግብርና ሥራው ዕሁድ ብናርፍም ጠዋት ቤተእምነት እንሄዳለን። ከዚያ መልስ የታመመ፣ የወለደ እንጠይቃለን።ብዙ ማህበራዊ ነገሮች እንፈጽማለን።
በዚህ ሁኔታ ነው የምናሳልፈው››ሲሉ ያስረዳሉ። ከቤተእምነት መልስ ቁርስ ያስፈልጋቸዋል። መቼም ቀድመው አዘጋጅተው ካልሄዱ ሲመለሱ መሥራት ግድ ነው። ይሄ ደግሞ አድካሚ ነው። ግን ወይዘሮ ምንትዋብ በዚህ በኩል የሰባት ዓመቷ ልጃቸው ቁርስ አዘጋጅታ ትጠብቃቸዋለች።ለቤተሰብ ቁርስ አዘጋጅታ የምትጠብቀውን ከተማ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች ጋር በአይነህሊናዬ ሳልኳት። በእርሷ ዕድሜ ያሉ በከተማ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ቁርስ ሊያዘጋጁ ቀርቶ እነርሱ እራሳቸው ብሉ ተብለው ሊለመኑ ይችላሉ፡፡
ወይዘሮ ምንትዋብ ኑሮን ለማሸነፍ በጣም ይጥራሉ፡፡ገቢ የሚያስገኝ ማንኛውንም ነገር ይሰራሉ። ልባሽ ጨርቅ ከኮንሶ በማምጣት፣ ለምግብ ማስቀመጫ የሚውል መሶብ ደግሞ በአካባቢው ከሚገኘውና እስረኞች ሰፍተው የሚያቀርቡትን ገዝተው በትርፍ ገበያ ወስደው ይሸጣሉ። ገበያው ከቤታቸው ብዙም አይርቅም።
በባጃጅ ለራሳቸው አስር ብር ለሚሸጡት ዕቃም እንደብዛቱ ተተምኖ በየአስራአምስት ቀኑ በመሄድ ይሸጣሉ። ለቤት የሚሆናቸውንም ገዝተው ይመለሳሉ። በአካባቢያቸው በማህበር ከተደራጁ ሴቶች ጋር በሀር ልማት ተሰማርተው በመሥራት በጋራ ከሚያገኙት ጥቅም ይጋራሉ፡፡በግላቸውም በቤት ውስጥ ሀር እያለሙ ይጠቀማሉ፡፡
የሚያገኙትን ገቢ ደግሞ በአግባቡ ነው የሚጠቀሙት። እቁብ በመጣል 30ሺ ብር ያገኙበት ጊዜ አለ።ግማሹን ለመኖሪያ ቤታቸው እድሳት፣ ግማሹን ደግሞ ባለቤታቸውን ‹‹እኔ ሰርቼ 30ሺ ብር ማግኘት ችያለሁ። አንተም ሥራ ፍጠር። ነግድ፡፡›› ብለው ለእርባታ የሚውል ከብት እንዲገዙበት እንደሰጧቸው ነገሩን። እርሳቸው እንዳሉት ቤታቸው በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ለቤተሰቡ በቂ አልነበረም።
በእርጅና ብዛትም ለመውደቅ አዘምሞ ነበር። ሆኖም ሰርተው ለፍተው ባገኙት ገንዘብ የሚመኙትን ሰፊ እና አዲስ ቤት በመሥራት ከችግራቸው መላቀቅ ችለዋል፡፡ የባለቤታቸውን እጅ ጠብቀው ለማደር ቀርቶ በሚችሉት ሁሉ እርሳቸውም ደግፈዋቸው በጋራ ሆነው ቢያድጉና ኑሯቸውን ቢለውጡ ይመርጣሉ፡፡ ሴት ልጅ አቅም ሲኖራት በባሏም ትከበራለች ብለው ያምናሉ።
በግብርና ሥራ ብቻ ከመወሰን ተጨማሪ ሥራ መስራት አስፈላጊነቱንና ጥቅሙን መረዳታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ምንትዋብ፤ ሁለቱም ፊደል መቁጠራቸው አስተሳሰባቸውን ማስፋት ካልቻለ ምንድነው ጥቅሙ ሲሉ ይጠይቃሉ። የፈጠሩት ሥራ ገንዘብ በማስገኘት ውጤት እንኳን ባይኖረው ሥራ መፍጠሩና መንቀሳቀሱ ተገቢ ነው ባይ ናቸው። ከባለቤታቸው ጋር በማንኛውም ጉዳይ በመነጋገርና በመወያየት የሚግባቡ መሆናቸው ለማደግ ላላቸው ፍላጎት ትልቅ እገዛ እያደረገላቸው ነው፡፡
ወይዘሮ ምንትዋብ እንዳሉት ባለቤታቸው በአካባቢያቸው እንደሚያዩት አንዳንድ ሰው ጠጪ አይደሉም።ፀብም በማንሳት ትዳራቸውን አያውኩም። ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡና አላስፈላጊ ጭቅጭቅ እንደሚያነሱት እንደአንዳንዶቹ ባለቤታቸው ቢረብሹ ጠንካራ ሴት ለመሆን ይቸገሩ ነበር። በትዳር አብረው በቆዩባቸው ጊዜያቶች እርስበርሳቸው ከመከባበር ውጭ የከረረ ጉዳይ በመካከላቸው ተፈጥሮ ለእርቅ ወይም ለውይይት ወደ ወላጆቻቸው የሄዱበት ጊዜ የለም።
ባለቤታቸው በንግግር ወይንም በሌላ ነገር ካስቀየሟቸው ጊዜ ወስደው የባለቤታቸው ቁጣ ሲበርድ ጉዳዩን አንስተው ይወቅሷቸዋል። በይቅርታ ከባለቤታቸው አቶ ካይሮ ጋር ሰላም ይፈጥራሉ። በዚህ አጋጣሚ እንደሚወዷቸውም ገልጸዋል።አንዳንዶች ተጣልተው ሚስት ለወራት ቤተሰቦችዋ ጋር ቆይታ የምትመለስበት ጊዜ መኖሩንና አንዳንዶቹም ፍች እንደሚፈጽሙ ይገልጻሉ።በዚህ በኩል ባለቤታቸውን ያመሰግናሉ። ይልቁንም የተጣሉትን በማስታረቅና ከእነርሱ ተሞክሮ እንዲወስዱ በማድረግ ለማስማማት ጥረት በማድረግ በአካባቢያቸው እንደሚታወቁ አጫውተውኛል፡፡
ወይዘሮ ምንትዋብ በጨዋታችን መካከል የባለቤታቸውን ሙሉ ስም እንዲነግሩኝ ስጠይቃቸው የአባታቸውን ስም እንደማይጠሩ ገለጹልኝ።ምክንያቱን ስጠይቃቸውም በባህላቸው ሚስት ‹‹የባሏን አባት ስም አትጠራም።ነውር ነው›› ከማለት ውጭ ምክንያቱን የነገራቸው ባለመኖሩ እርሳቸውም አልነገሩኝም፡፡የባለቤታቸው አባት ቤታቸው ለእንግድነት ሲሄዱ እንኳን ቀና ብለው አያዩዋቸውም።
እጃቸውን ሲያስታጥቧቸውም ሆነ ምግብ ሲያቀርቡላቸው በሙሉ አይናቸው አይተዋቸው አያውቁም፡ እጅግ ቢበዛ አክብሮት ነው የሚያስተናግዷቸው። ሊጠራቸው እንኳን ቢፈልጉ የአንደኛው ልጃቸውን ስም ጠርተው የእከሌ አባት ብለው ይጠሯቸዋል። በአካባቢያቸው ባህል ሴት ልጅ የአባቷን ድርሻ አትወርስም፡፡ አሁን ግን ነገሮች እየተለወጡ በመሆናቸው ይሄ ባህል አይቀጥልም የሚል እምነት አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013