አንተነህ ቸሬ
ምርጫ 2013 ሊካሄድ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። በየካቲት ወር መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት በተወዳዳሪዎች መካከል የምርጫ ክርክር የማከናወን ፍላጎት ላላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና መገናኛ ብዙኃን ጥሪ አቅርቦ ነበር።
በተጨማሪም ቦርዱ አገር አቀፍ ክርክሩ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ የሚካሄድ እንደሆነም ገልፆ ነበር። አሁን የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ያለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ግብዣ መሰረትም የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ለቦርዱ ፍላጎታቸውን በጹሑፍ ካቀረቡ ተቋማት መካከል አስራ አንዱ የቦርዱን ይሁንታ አግኝተዋል። ከእነዚህ መካከል ሦስቱ መገናኛ ብዙኃን ናቸው። ቦርዱም ክርክር እንዲያዘጋጁ ስለመረጣቸው ተቋማት ለፖለቲካ ፓርቲዎች አሳውቋል።
የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ጥያቄ ካቀረቡ አምስት መገናኛ ብዙኃን መካከል በቦርዱ እውቅና የተሰጣቸው አሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ሲሆኑ፤ ከተቋማት ደግሞ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ (Inter Africa Group)፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር (Ethiopian Economics Association)፣ የኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች የልማት ማኅበር (Ethiopian Center For Disability and Development Association)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች እና ሴታዊት ሙቭመንት የተሰኙ ተቋማትና እንቅስቃሴዎች ናቸው።
የምርጫ ክርክሩን እንዲያዘጋጁ በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይሁንታ የተሰጣቸው ተቋማት ይፋ በተደረጉበት ወቅት እንደተገለፀው፤ ክርክሩ የሚካሄድባቸው ቋንቋዎች ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛና አፋርኛ ይሆናሉ። ሴታዊት ሙቭመንት ክርክሮችን ለማዘጋጀት ያቀደ ሲሆን፤ ክርክሮቹ ተቀርጸው በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ይሆናል። በክርክሮቹ 10 የተመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ርዕሰ ጉዳዩም የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ እንደሚሆን ታውቋል። ለክርክር የሚሆኑ ጥያቄዎችም በማህበራዊ (Social Media) እና መደበኛ (Mainstream) ሚዲያዎች አማካኝነት እንደሚሰበሰቡ አዘጋጁ ለምርጫ ቦርድ ያስገባው የመወዳደሪያ እቅድ ዝርዝር ያሳያል።
ከ30 እስከ 50 የሚደርሱ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ክርክር ለማዘጋጀት ያቀደው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢ.ሰ.መ.ጉ) በበኩሉ፤ ተወዳዳሪዎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚከላከሉበት ስልታዊ እቅድን ጨምሮ በሴቶችና አካል ጉዳተኞች መብት ዙሪያ አከራከራለሁ ብሏል።
የኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማሕበር ደግሞ ‹‹በመሬት አስተዳደር ፖሊሲ ላይ ከ15 እስከ 20 የዘርፉ ባለሙያዎች በሚሳተፉበት ሁኔታ አንድ የክርክር መድረክ አዘጋጃለሁ፤ ክርክሩም ተቀድቶ በቴሌቪዥን ይተላለፋል›› ብሏል።
በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የክርክር መድረክ ለማዘጋጀት ያቀደው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር፤ አምስት የክርክር መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ጠቁሞ፤ ክርክሮቹ ተቀድተው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሕዝብ እንደሚቀርቡ አስታውቋል።
በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ሦስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የምርጫ ክርክሮችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በበኩሉ፤ በተመረጡ ዋና ዋና ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሦስት የክርክር መድረኮችን በደብረ ብርሀን፣ በአርባ ምንጭና በጂግጂጋ ከተሞች በአማርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች አዘጋጃለሁ ብሏል።
አሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን 12 የክርክር መድረኮችን ለማዘጋጀት ማቀዱንና ከእነዚህም መካከል አራቱ በቀጥታ፤ ስምንቱ ደግሞ ተቀድተው የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በበኩሉ፤ 13 ክርክሮችን ለማዘጋጀት ያቀደ ሲሆን፤ አራት በሃገር አቀፍ ደረጃ፣ ሦስት በኦሮሚያ፣ ሁለት በአማራ፣ ሁለት በሶማሌ፣ ሁለት በአፋር እንዲሁም ሁለት የምርጫ ክርክር መድረኮችን በሐዋሳ እንደሚያዘጋጅ አመልክቶ ከሁለቱ በስተቀር ቀሪዎቹ በቀጥታ ስርጭት የሚቀርቡ ይሆናሉ ተብሏል።
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በአንድ ጊዜ ከሦስት እስከ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉባቸውና በተቋሙ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት አርትዖት ተሰርቶባቸው በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ 25 የኦሮምኛ፣ 10 የሱማሌኛ፣ 10 የአፋርኛና 10 የአማርኛ፣ በአጠቃላይ 55፣ የምርጫ ክርክር መድረኮች እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል።
በዚሁ ሂደት መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክርም ተጀምሯል። ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) እና በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተላለፉት ክርክሮች ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውንና ተመርጠው ስልጣን ቢይዙ ሊተገብሯቸው ያቀዷቸውን ዓላማዎቻቸውን በመገናኛ ብዙኃን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
የምርጫ ክርክሮች በምርጫ የሚወዳደሩ ፖለቲከኞች ፖሊሲዎቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው፣ ከሌሎች የምርጫ ተወዳዳሪዎች የሚለዩባቸውን ጉዳዮች የሚያመላክቱባቸውና በምርጫ ቢያሸንፉ ሊያከናውኗቸው ስላቀዷቸው ተግባራት የሚገልፁባቸው መድረኮች ናቸው። እነዚህ መድረኮች መራጩ ሕዝብ የትኛውን ተወዳዳሪ መምረጥ እንዳለበት አቅጣጫ በመጠቆም ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው።
በአንዳንድ አገራት፣ የምርጫ ክርክሮች በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ውስጥ ከሚከወኑ ተግባራት መካከል ጎላ ብለው ይታያሉ። ለአብነት ያህል በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት ውስጥ የሁለቱ አንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የዴሞክራቲክ እና የሪፐብሊካን) እጩዎች የሚደርጓቸው የምርጫ ክርክሮች የበርካቶችን ቀልብ ይስባሉ። በእነዚህ መድረኮች ላይ ጥሩ ነጥቦችን የሚያስቆጥሩ እጩዎች ወደ ነጩ ቤት የመገሥገሥ እድላቸውን ያሰፋሉ።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት የምርጫ ክርክሮች ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያግዙ ወሳኝ መሳሪያዎች ናቸው። ዓለም አቀፍ የእድገት ማዕከል (International Growth Center – IGC) የተባለው ተቋም ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ መራጮች በምርጫ ክርክሮች አማካኝነት መረጃ እንዲያገኙ እድል መፍጠር ዴሞክራሲያዊ ተሳትፏቸውን በማሳደግ የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን እንዲሁም የመረጧቸውን ፖለቲከኞች የስራ አፈፃፀም የመገምገም እድላቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ ያስችላል።
ተቋሙ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ያከናወነው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ መራጮች የምርጫ ክርክሮችን ከተመለከቱ በኋላ ስለተወዳዳሪዎቹ የነበራቸው ግንዛቤ ከመጨመሩም ባሻገር ተመራጮቹም ቃላቸውን አክብረው በመንቀሳቀሳቸው የተሻለ የስራ አፈፃፀም አስመዝግበዋል።
ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚደረጉት የምርጫ ፉክክሮች ገና መጀመራቸው ቢሆንም እስካሁን የተመለከትናቸው ክርክሮች ከተለመደው አካሄድ ተሽለው መገኘት እንደሚኖርባቸው ለማሳሰብ የሚያስገድዱን ጉዳዮች እንዳሉ ታዝበናል።
ሰሞኑን ከተመለከትናቸው የምርጫ ክርክር መድረኮች እንደታዘብነው ብዙ ፓርቲዎች አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ ልማዳዊ አሰራር የሆኑትን ስድብና ዘለፋን በመድረኮቹ ላይ ሲጠቀሙ ተስተውለዋል። ከቃላት አጠቃቀማቸው ጀምሮ ሃሳቦቻቸውን የሚያቀርቡባቸው መንገዶች ከአሁኑ መስተካከል እንደሚገባቸው ታዝበናል።
ፓርቲዎች በጥቅሉ ‹‹የፖሊሲ ሰነድ አዘጋጅተናል›› ብሎ ከመናገር ባሻገር፣ ሰነዳቸውን በቅጡ አንብበውና ዝግጅት አድርገው አማራጭነታቸውን በሚያሳይ መልክ ሰነዳቸውን ለመተንተን ሲቸገሩ መታየት የለባቸውም። ይህ የሰነድ ትንተና ችግርም ከአጀንዳ ወጥቶ እዚህም እዚያም መርገጥንና መወነጃጀልን እንደሚያስከትል ታዝበናል፤ በመርህ አልባነት የታጀበ የሌሎችን አማራጭ የማጣጣልና የራስን አማራጭ ማቅረብ ያለመቻል አባዜ ውስጥ እንደሚከትም ተመልክተናል።
በሌላ በኩል የምርጫ ክርክሮችና በክርክር መድረኮቹ ላይ የሚቀርቡ ሃሳቦች ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ ሊሆኑ እንደሚገባም አስተውለናል። የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች በቅጡ ሳይነገነዘቡ የሚቀርቡ አማራጮች ‹‹ለማን ነው የሚቀርቡት?›› ያሰኛሉ።
በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ስለዴሞክራሲ፣ የመንግሥት አወቃቀር፣ ፌደራሊዝም … የሚቀያቀርቧቸው አማራጮች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እንጂ ለሌላ አገርና ዜጎች እንዳልሆነ ለፓርቲዎቹ ማስታወስ ይገባ ይሆን? ሃሳቦቻቸውንና አማራጮቻቸውን እንዴት በዝርዝር ሊያስፈፅሙ እንዳቀዱ አጠር አድርገው ማስረዳት እጅግ ወሳኝ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ ማወቅ አለባቸው።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ኃላፊነት ያለባቸው ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳዎቻቸውም ሆኑ ማኒፌስቶዎቻቸው የሐሳብ ልዩነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በፈረሙት የጋራ ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ የተፎካካሪዎቻቸውን ስም ከማጥፋትና ከውንጀላ መታቀብ ይኖርባቸዋል።
የምርጫው ውጤት አሳማኝ ሆኖ ቅቡልነት ማግኘት የሚችለው ሒደቱ የተስተካከለ ሲሆን ብቻ ነው። ቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ቀንና ድኅረ ምርጫ ሒደቶቻቸው ከተስተካከሉ ውጤቱም አሳማኝ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች መተማመን ይኖርባቸዋል።
መተማመንን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ወገኖች ኃላፊነት አለባቸው። መንግሥት የሕዝብን ደኅንነትና የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ፣ አገር በሕግና በሥርዓት እንድትመራ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። የሕግ የበላይነት እንዲከበር የማድረግ፣ የተቋማትን ነፃነትና ገለልተኛነት የማጠናከር እንዲሁም የሕግ ማዕቀፎችን ከወቅቱ ቁመና ጋር የማመጣጠን ኃላፊነቶች አሉበት።
ከዚህ ተቃራኒ የሆነው አካሄድ ግን ገዥውን ፓርቲ ‹‹ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ›› የሚልበትን እንዲሁም ሌሎች ተፎካካሪዎችን ደግሞ ለአመፅ ማነሳሳቱ አይቀርም። ይህ ዓይነቱ አጉራ ዘለል አካሄድ ደግሞ በብዙ ችግሮች የተወጠረችውን አገር ጉዞዋን ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገዋል። ስለሆነም የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ መከበር አለበት።
ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ተገዢ ያልሆነ የሴራ ፖለቲካ ትርፉ እርስ በእርስ መፋጀትና አገርን ማፍረስ ነው። በሃሳብ ግብይት በኩል ለሕዝብ ዳኝነት በመቅረብ የአሸናፊነትን መንበር መቀዳጀት የመሰለ ሥልጡን አካሄድ እያለ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ‹‹ዓይንህን ለአፈር›› የሚያባብል ኋላቀር ድርጊት ውስጥ መገኘት አሳፋሪ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት የሚቻለው የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ነው።
የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ራሳቸውን ከሴራ፣ ከቂም፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነትና ከጉልበተኝነት አባዜ ማላቀቅ ይኖርባቸዋል። ሃሳብን ማዕከል ላደረገ የውይይትና የሰለጠነ ክርክር ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። የምርጫ ተፎካካሪዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ፖሊሲያቸውን በግልጽ ማሳየት አለባቸው። አማራጭ ፖሊሲ ሳይኖራቸው ሕዝብ ፊት እየቀረቡ ማደናገር የእስካሁኑን አዙሪት ከመድገም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም!
የምርጫ ክርክሮቹ ገና የተጀመሩ ቢሆንም መሰል ተገቢ ያልሆኑ እሳቤዎችና ድርጊቶች ከአሁን መታረምና የክርክር መድረኮቹን ለታለመላቸው ሰላማዊ ዓላማ ማዋል ይገባል። በቀጣይ የሚካሄዱ የምርጫ ክርክሮች የተወዳዳሪዎች አማራጭ ሃሳቦች የሚቀርቡባቸው እንጂ ነጥብ ለማስቆጠርና በስድብ ‹‹የሕዝብን ቀልብ እገዛለሁ›› የሚል ምኞት ማስፈጸሚያዎች መሆን የለባቸውም።
በእርግጥ የምርጫ ክርክሮች በባህርያቸው ዱላ ቀረሽ ሙግቶች የሚስተናገዱባቸውን መድረኮች ናቸው። ተፎካካሪዎቹ አንዱ የሌላውን ሃሳብ ውድቅ ለማድረግ ሲሉ የሚጠቀሟቸው የማሳመኛና ተፅዕኖ የመፍጠሪያ ስልቶች እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ። በሰለጠኑት አገራት ጭምር በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው የምርጫ ክርክሮች ጭምር በኃይለ ቃላት የታጀቡና ውጥረት የነገሰባቸው እንደነበሩ አይዘነጋም።
የሆነው ሆኖ የምርጫ ክርክሮች ተወዳዳሪዎች ፖሊሲዎቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው መድረኮች ናቸው። ስለሆነም በመድረኮቹ መታየት ያለባቸው ሃሳቦች የተወዳዳሪዎቹን ፖሊሲዎች ለመራጩ ሕዝብ ማሳየት የሚችሉና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ አማራጮችን የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው።
መድረኮቹ መራጩ ሕዝብ የፓርቲዎቹን አማራጮችና አቋሞች ተመልክቶ ድምፁን ለየትኛው ፓርቲ መስጠት እንደሚኖርበት እንዲወስንና ምርጫውን እንዲያስተካክል የሚያግዙ የሃሳብ ግብይት ስፍራዎች (Market place of Ideas) እንደሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።
በቀጣይ በሚካሄዱ የምርጫ ክርክሮች ፓርቲዎች ለአገሪቱ ይበጃሉ ያሏቸውን አማራጮቻቸውን በመረጃ አስደግፈው፤ በርዕዮተ ዓለምና በፖሊሲ ንድፈ ሃሳብ አጎልብተው የሰለጠነ ክርክር በማድረግ መራጩ ሕዝብ መሪዎቹን/ተወካዮቹን እንዲመርጥና ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ማገዝ አለባቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013