መላኩ ኤሮሴ
ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች አንጻር ሲታይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ) ቴክኖሎጂ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በ20ኛ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የተዋወቀ ነው፡፡ እ.ኤ.አ1956 “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካዊው የኮምፒተር ሳይንቲስት ጆን ማካርቲ በዳርትማውዝ በተደረገው ጉባኤ ነው ያስተዋወቀው፡፡ በዚያው ጉባኤ ላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አካዳሚክ መስክ ተፈጠረ፡፡
ያደጉትም ሆኑ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂውን በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡ በተለይም ካለፉት ስምንት ወራት ወዲህ ደግሞ የአርቴፊሻል አስተውሎት ቴክኖሎጂ ማዕከል በማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን እያካሄደች ነው፡፡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በመጠቀም የግብርና ዘርፍ፣ የጤና ዘርፍ እና የሚዎትሮሎጂ እና ሌሎች ዘርፎችን ችግሮች የተለያዩ ጥረቶች እያደረገች ትገኛለች፡፡
ማዕከሉ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን “አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ አውደ ርዕይ እና አውደ ጥናት በካዛንቺስ በሚገኘው በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አካሂዷል፡፡ የማዕከሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ የተካሄደው አውደ ጥናቱና የአውደ ርዕዩ ዓላማ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ በተለይም ዘርፉ በኢትዮጵያ ምን አይነት አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይችላል፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት ላይ ቴክኖሎጂው ምን አይነት እሳቤዎችን ይዞ መጣ፣ የቴክኖሎጂው ጥቅም ምንድን ነው በሚለው ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና በሀገሪቱ ያለውን ዘርፍ መደገፍ ማበረታታት፣ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚደረጉ ምርምሮችንና ጥናቶችን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ግብ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሌሎች በግላቸው የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ የምርምር ተቋማትን የሚያንቀሳቅሱ አካላት፣ የምርምር ስራዎችን የሚሰሩ እና የምርምር ውጤቶችን ወደ ምርት ለማሸጋገር እየሞከሩ የሚገኙ እንዲሁም ወደ ምርት ደረጃ የደረሱ ለጉብኝት ክፍት እንዲሆኑ ነው የተደረገው፡፡
የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ አውደ ርዕይና አውደ ጥናቱ ለአራት ቀናት የተካሄደ ሲሆን፤ በአውደ ጥናቱ ላይ በሀገሪቷ የሚገኙ ምሁራንና ተመራማሪዎች በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለውን ለማየት እድል የፈጠረ ነው፡፡ ምሁራን ተሰብስበው ለአንድ ዓላማና ግብ ትኩረት አድርገው የተከራከሩበትና የመከሩበት ነበር፡፡
በአውደ ጥናት በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡ የኤሮስፔስ ዘርፍ ችግሮች እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት የመፍትሔ አቅጣጫ ምክክር፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በፋይናንስ ዘርፍ ያለው እገዛ፣ በግብርና ዘርፍ ባሉ ተግዳሮቶች እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም ሜትዎሮሎጂ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
በተመሳሳይ አውደ ርዕዩ ላይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል፣ ሌሎች ተቋማት እና ግለሰቦች ከ40 እስከ 50 የሚሆኑ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ ስራዎቻቸውን ይዘው ለቀረቡ አካላት እውቅናም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም በግላቸው እየተንቀሳቀሱ ላሉት ትልቅ እድል ነው፡፡ አውደ ርዕዩን በርካቶች ጎብኝተዋል፡፡ ይህም በርካቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በርካታ የዘርፉ ወዳጆችም አውደ ርዕዩን ጎብኝተውታል፡፡ ጎብኚዎች በቀረቡት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች ደስተኛ ናቸው፡፡ የተሻለ ግንዛቤም ያገኙበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቦታው ስራቸውን ይዘው ከተገኙት የዘርፉ ተሳታፊዎች ባሻገር በቤታቸው ሆነው እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ላይም የተለያዩ ምርምሮች እያካሄዱ ያሉ አሉ፡፡ አውደ ርዕዩ እነዚህን አካላት በሙሉ የሚያነቃቃ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክሮች ተካሂደዋል፡፡ በመድረኩ ውይይት ምክክር ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል አርቴፊሻል አስተውሎት ለጤናው ዘርፍ ባለው ፋይዳ ዙሪያ የሚያጠነጥነው ተጠቃሽ ነው፡፡ የሀገሪቱ የጤና አገልግሎት በበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያሉበት ዘርፍ መሆኑን የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ መሰረተ ልማት፣ የህክምና ተቋማት ከተገልጋዩ ርቀው መገኘታቸው፣ የተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መብዛት እና ሌሎችም አንኳር ችግሮች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
በጤናው ዘርፍ ለሚስተዋሉ ችግሮች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፈ ብዙ ምላሽ ማዘጋጀት ይቻላል ያሉት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት ምሁር ዶክተር አዳነ ነጋ የጤናው ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶችን እንዲጠቀም መክረዋል፡፡ በሽታን መለየት፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት መዘርጋት፣ የታማሚዎችን ማህደር በአግባቡ ለመሰነድ እና ለሌሎችም አገልግሎት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እምቅ አቅም እንዳለ አመላክተዋል፡፡
በዚህም የዜጎችን የጤና ችግር ከመቅረፍ ባለፈ ዘመናዊ እና የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት በመገንባት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማስፋት ይቻላል ያሉት ዶክተር አዳነ ነጋ፤ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል በሽታን መለየት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን እውን ለማድረግ እና በሌሎችም የጤናው ዘርፍ ችግሮች ዙሪያ ትኩረት አድርጎ እየሰራባቸው ካሉ ዘርፎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በአውደ ርዕዩ ላይ ስራዎቻቸውን ካቀረቡት የዘርፉ ተዋናዮች ደቦ ኢንጂነሪንግ ተጠቃሽ ነው፡፡ ደቦ ኢንጂነርንግ በተለያዩ ዘርፎች የሰራቸውን ሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶችን አቅርቧል፡፡ የደቦ ኢንጂነርንግ መስራችና ስራ አስኪያጅ እንዲሁም የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ጃርኒያ ባይሳ እንደተናገሩት ደቦ ኢንጂነርንግ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው አውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ ችግሮችን የሚፈቱ ሰው ሰራሽ የአስተውሎት ውጤቶችን ይዞ ቀርቧል፡፡
ደቦ ኢንጂነርንግ ይዞ ከቀረበው ሰው ሰራሽ የአስተውሎት ውጤቶች መካከል ዕጽዋትን ፎቶ በማንሳት ብቻ በሽታን የሚለይ መተግበሪያ አንዱ መሆኑን ያብራሩት መምህር ጃርኒያ፤ መተግበሪያው በሽታው በእጽዋት ላይ ከመከሰቱ አስቀድሞ በቅድሚያ ምልክቶችን ብቻ በመለየት በሽታውንና በሽታውን ለመከላከል መወሰድ ያለባቸውን መፍትሄዎች ጭምር ለተገልጋዮቹ የሚጠቁም ነው። መተግበሪያው ያለ ኢንተርኔት ግንኙነት የሚሰራ ሲሆን ለጊዜው በአራት ቋንቋዎች እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
በምስል የዕፅዋትን በሽታ የሚለየው መተግበሪያ ጀርሚያ ባይሳ እና ቡዔዝ ብርሃኑ በተባሉ ሁለት ወጣቶች የተሰራ ሲሆን ፤ እ.አ.አ ለዚህ ስራቸውም ወጣቶቹ በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የግሪን ኢኖቬሽን ሽልማትን፣ በ2020 ደግሞ በአፍሪቃ ደረጃ በየዓመቱ በሚዘጋጅ ሜስት አፍሪካ በተባለ ውድድር የኢትዮጵያ አሸናፊ መሆናቸውን ጃርሚያ ተናግረዋል።
እንደ ጃርሚያ ገለጻ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ በትራንስፖርት ዘርፍ ለትራፊክ ቁጥጥር አጋዥ የሆነ ቴክኖሎጂ፣ በጤናው ዘርፍ ደግሞ በኮቪድ-19 በሽታ የተያዘን ሰው መለየት የሚያስችልና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን የሚቆጣጠር እንዲሁም የወባ በሽታ አምጭ እና ሌሎች ትንኞችን የሚለይ ቴክኖሎጂ ሰርተዋል።
በአውደ ርዕይና አውደ ጥናት ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጃርሚያ ከጓደኛው ጋር በመሆን የሰራቸውን ስራዎች መጎብኘታቸው፣ ማድነቃቸውና ማበረታታቸው ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረበት ተናግሯል፡፡ በቀጣይም በጅማና በአካባቢዋ ብቻ የታጠረውን የቴክኖሎጂ እገዛ በማስፋፋት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የማዳረስ ህልሙን እንዲያሳካ ስንቅ እንደሆነው አንስቷል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ አቶ ግርማይ ተክሌ በአውደ ርዕዩ ላይ ስራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሌላኛው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ባለቤት ናቸው፡፡ ኔክስት ወርድ ፕሪዲክሽን ቴክኖሎጂ (በትግርኛ ቋንቋ አረፍተ ነገሮች በሚዋቀሩበት ወቅት ቀጣይ ቃል የሚተነብይ መተግበሪያ ነው ይዘው የቀረቡት)፡፡ ምርምሩ ለምረቃቸው የሰሩት ነው፡፡
ትግርኛ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚናገረው ቋንቋ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ቀጣይ ቃል የሚተነብይ ቴክኖሎጂ እንዳልነበር የሚያብራሩት አቶ ግርማይ አዲስ የተሰራው መተግበሪያ በትግርኛ በሚጻፍበት ወቅት ቀጣይ ቃል የሚተነብይ ነው ብለዋል፡፡ ይህ መተግበሪያ ለቋንቋው እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡ ብዙ ስራዎችን በቀላሉ መስራት የሚያስችል ነው፡፡
መተግበሪያው በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ስራ ላይ ሳይውል መቆየቱን የሚያብሩት አቶ ግርማይ፤ አውደ ርዕዩ ስራዎቹን እንዲያስተዋውቄ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ መተግበሪያው ወደ ስራ እንዲገባ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ያብራራሉ፡፡
አውደ ርዕይ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት አቶ ግርማይ፤ በርካታ ጎብኚዎች ስለ መተግበሪያው ግንዛቤ ጨብጠው መመለሳቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ትልቅ እድል መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ ሌሎች ወጣቶችም የተሻሉ ስራዎችን እንዲሰሩ በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ግርማይ እንደሚሉት፤ አውደ ርዕዩ ከቢዝነስ ሰዎች ጋር የሚገናኙበት እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት እና ወደ ስራ ለማዋል ፍላጎቱ እና አቅሙ ካላቸው የቢዝነስ ሰዎች ጋር ተቀራርበው የሚሰሩበት እድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡ መሰል አውደ ርዕዮችና አውደ ጥናቶች በአመት አንዴ ወይም ሁለቴ ተደርገው መቆም ያለባቸው አይደሉም፡፡ በየጊዜው መደረግ እንዳላባቸው ያሳስባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013