ራስወርቅ ሙሉጌታ
በየትኛም ዓለም ቢሆን የሰው ልጅ ብቻውን ሊያስኖረው የሚያስችለው አቅም አይኖርም። ከወላጆቹ ወይን ከአሳዳጊዎችና ከአካባቢ ነዋሪዎች ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሰው ልጅ እንደ ግለሰብም እንደ ህዝብም እርስ በእርሱ እየተደጋገፈ ይኖራል።
በኢትዮጵያም ዛሬ ዛሬ እየተቀዛቀዘ ቢመጣም ተካፍሎ መብላት የተቸገረን መርዳት መተዛዘንና መደጋገፉ በህግ ባይቀመጥም የሀበሻ አንዱ መለያ ነው። ይህ ልዩ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የአንድነት የህብረት ምሰሶ የሆነው ልግስና ወይንም መስጠት እንዲጠናከር ምን ሊሰራ ይገባል ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
እንደ ሀገር በድህነት ልንታወቅ ከቻልንባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የኖረውን የልግስናና የመረዳዳት ባህላችንን እየተውን መምጣታችን ነው፡፡ ለዚህም የምናባክነው የአሮጌ ነገሮች ክምር መኖር የእኛን እርዳታ የሚሹ በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች በአካባቢያችን እያሉና እኛም ልንንደግፋቸው እየቻልን በቸልታ አይቶ እንዳላየ ማለፋችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡
እንደ ሃይማኖተኛነታችንም “ሰደቃ” ወይም “ምጽዋት” የምንሰጥ “አስራት” በኩራት ማውጣት የሚገባን ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ይህን የምናደርግ በጣም ጥቂቶች ሆነናል። ይህም የሆነበት ምክንያት ስለልግስና ያለን ግንዛቤ እንደ ማህበረሰብ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ በሌላ በኩል የግላዊነት መንፈስ እየዳበረ በመምጣቱ ነው።
በመሆኑም ይህ ሀገራዊ ጥቅም ያለው አኩሪ ባህላችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ልግስና ባህልን መሠረት አድርጎ በዘልማድ ከመከወኑ ባለፈ ያሉትን ስነልቦነናዊ ሣይንሣዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳዎች መገንዘብ ስለሚያስፈልግ እንደሚከተለው እናያቸዋለን።
ልገስና ምን ማለት ነው?
ልገስና ስንል ማካፈል፣ ማድረግ፣ መለገስ፣
መቸር (ቸር መሆን) ወዘተ ትርጉም ያለው ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ መንፈግ፣ መከልከል፣ አለማድረግ፣ አለመስጠት፣ መስገብገብ፣ መሳሳት የሚሉትን ትርጉሞች
እናገኛለን፡፡ በመሆኑም ሰው ካለው ከተቸረው ከጊዜ፣ ከገንዘብ፣ ከእውቀት፣ ከጥበብና ከጉልበት ለሌሎች ያለ ጥቅም ሲሰጥ ወይንም ሲያደርግ ማለት ይሆናል። ሰው እነዚህን ነገሮች ከተለያየ እሳቤ በመነሳት የሚያደርጋቸው ቢሆንም በዋናነት ግን በሶስት ከፋፍለን ልናያቸው እንችላለን።
ስለ ልግስና ፍልስፍና ምን ይላል?
በመጀመሪያ ደረጃ እኛን የሰው ልጆችን በምድር ላይ ለመኖር እንዲህ ያስቻሉን ሁሉም ነገራቶች ምንጭ ከተፈጥሮ እና አብረውን ከሚኖሩት ፍጥረት የተሰጡ ናቸው፡፡የምንተነፍሰው አየር የምንጠጣው ውሃ የምንበላውን የምናመርትበት ዝናብ፤ አፈር ወይም መሬት፣ እንዲሁም በሌላ መልክ የምናገኛቸው ምግቦቻችን፣ ልብሶቻችን ሌሎችም መጠቀሚያዎቻችን ሁሉ ከተፈጥሮ የተቀበልናቸው ናቸው፡፡
ስለዚህ የእኛ የሰዎች የመኖር ህልውና በሌሎች
ፍጥረትና ተፈጥሮ የመኖር ህልውና ስር በመሆኑ እኛ ለመኖር ስለተቀበልን እነሱን የሰጡንን ለማኖር ስንል ደግሞ እኛ በተራችን መስጠት አለብን ማለት ነው፡ ፡በዚህም መኖር በፍልስፍና መነጽር ስንመለከተው “ተቀብሎ እየኖሩ እየሰጡ ማኖር ይሆናል!” ማለት ነው፡፡
1. ሳይንስ ስለ ልግስና ምን ይላል?
የሥነ-ልቦና፣ የሥነ-ስስትና የሥነ-አዕምሮ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ልግስና ዋነኛ የደስተኝነት ምንጭ እንደሆነና ጭንቀትን ለመቀነስና ለማስወገድ ተመካሪ እንደ ሆነ ነው። በተጨማሪ አንዳንድ የማህበራዊ ሳይንስ ጥናቶችም የሚሰጡ ሰዎች እረጅም እድሜ እንደሚኖሩ፣ በጣም ጤነኛ እንደሚሆኑና ከታመሙም በቀላሉ እንደሚያገግሙ ያመላክታሉ፡፡ለምሳሌ ከዓመታት በፊት ዶክተር ሶፊያ የተባለች የዘርፉ ባለሙያ ያካሄደችው
“ጌሪንግ አፕ” የሚል ጥናት እንደሚያመለክተው ለረጅም ጊዜ ሳያቋርጡ የሚለግሱ ሰዎች የሰውነት ቆዳቸው እንደማያረጅ፣ አካላዊ መስላቸው ጠንካራ እንደሚሆን እንዲሁም ፀጉራቸው እንደማይነቃቀል በማንሳት ልግስና በርካታ አካላዊ ፋይዳ እንደሚያገስገኝ አስቀምጣለች፡፡
2. ሃይማኖት ስለ ልግስና ምን ይላል?
ሁሉም የሃይማኖት መጽሐፍት በአጽንኦት የሚያስተምሩት ነገር ቢኖር መስጠት አምልኮ ወይም አምላክን የምናመልክበት አንዱና ዋነኛው መንገድ እንደሆነ ሲሆን ከመስጠት የሚገኙትን ምድራዊና ሰማያዊ በረከቶችም እንደደሚከተለው ይዘረዝሯቸዋል።
1. የሚለግስስ ሰው ሃብቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ሲሰጥ ይሰጠዋል ስጥ። አምላክ በመስጠት ውስጥ በረካ ወይም በረከትን አምላክ ያስቀምጥለታል።
2. የሰው ልጅ የሚሰጠው ቢያጣ እንኳ መልካም ቃል ማውጣት እንደ ስጦታ እንደሚመዘገብለትና በዚህም ከቅጣት እንደሚድን ያስቀምጣል።
3. የፈጣሪን ቁጣ ያርቅልናል፡፡የሰው ልጅ በየቀኑ ከሚፈፅመው ሃጢያት ወይም ጥፋት የተነሳ ከፈጣሪው ከሚመጣበት ቁጣ እንዲጠበቅና ምህረት እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡መቅሰፍፈትን እንዲቀር ያደርጋል። የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ስለዚህ ልግስና የዘወትር ተግባራችን እንዲሆን ምን እናድርግ?
በቅድሚያ ሠውን ያለምንም መለያ በሠውነቱ መቀበልና ችግሩን እንደራሳችን ማየት። ቀጥለንም ለበጎ ሥራ ከይሉኝታ የጸዳን ደፋር መሆን። ከፈራን ከተጠራጠርን መሳሳት መስገብገብና መንቆጥቆጥ ስለሚበረታብን ለመስጠት እንቸገራለን። በመሆኑም ይህ እንዳይሆን ራስን ማዘጋጀት፡፡
በመጨረሻም መቼም ይሁን የት ድጋፋችንን ለሚሹ ሁሉ ለምናደርገው ልግስና ምክንያትና ነጋሪ አለመሻት እንዲሁም ነገ ይህን አደርጋለሁ ይህን ሳገኝ ይህንን እቸገራለሁ ከሚል የሩቅ ተስፋ በመታቀብ ዛሬ ልናደርግ የምንችለውን ዛሬውኑ ብናደርግ ከላይ የተጠቀሱትን የልግስና በረከቶችን ልናገኝ እንችላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013