እንግሊዝ የመጀመሪያዎቹን ፈቃደኛ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ላከች

እንግሊዝ የመጀመሪያዎቹን ፈቃደኛ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ላከች። እንግሊዝ በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተው መርሀ ግብሯ የመጀመሪያዎቹን ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን ያለፈው ሰኞ እለት ወደ ሩዋንዳ መላኳን ተዘግቧል።ዘገባው ወደ ሩዋንዳ በረዋል የተባሉት ስደተኞች ማንነት ግልጽ አለመሆኑንም ጠቅሷል።

ይህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተው ስደተኞችን የማስወጣት መርሀ ግብር እንግሊዝ በሚቀጥሉት ወራት በግዴታ ለማስወጣት ካቀደችው እቅድ የተለየ ነው ተብሏል። እንግሊዝ በፍቃደኝነት ወደ ሩዋንዳ ለመሄድ ፍቃደኛ የማይሆኑትን በግዴታ የምታስወጣው በእንግሊዝ ቻናል በኩል በትንንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ለማስቆም ነው።

የእንግሊዝ መንግሥት በፍቃደኝነት ወደ ሩዋንዳ ለሚመለሱ ስደተኞች ለእያንዳንዳቸው 3ሺ ዶላር እንደሚሰጥ ገልጿል። ስደተኞች እንግሊዝን ለቀው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጣቸው ቢሆንም በዚህ እቅድ ግን ገንዘቡ የሚሰጣቸው በሩዋንዳ ለመኖር ሲስማሙ ነው።

የመንግሥት ቃል አቀባይ እንደገለጹት፤ ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ባላቸው የስደተኞች እና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት መሰረት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ ችለዋል።”ይህ ስምምነት በእንግሊዝ የስደተኝነት ሰነድ የሌላቸው ሰዎች ህይወታቸውን በሰላም ወደሚመሩበት ሰላማዊ ሶስተኛ ሀገር እንዲሸጋገሩ አስችሏል” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ ከጦርነት እና ረሃብ በመሸሽ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በትናንሽ ጀልባዎች ተጉዘው እንግሊዝ ገብተዋል። መንግሥት ስደተኞችን ከእንግሊዝ 6ሺህ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሩዋንዳ ለመላክ ሲነሳ ያጋጠመውን የህግ እና የፖለቲካ ተቃውሞ ለማሸነፍ ሁለት ዓመት ፈጅቶበታል፡፡በመጨረሻም ፓርላማው ከፋፋይ የተባለውን እቅድ ባለፈው ሳምንት ማጸደቁን ጠቅሶ አል ዐይን ዘግቧል፡፡

በአነስተኛ ጀልባዎች ተጓጉዘው የእንግሊዝ ቻናልን በማቋረጥ ከዚያ የሚደርሱትን ጥገኝ ነት ጠያቂዎች ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቱ ሀገር ለማዛወር እና በቋሚነትም ኑሯቸውን ከዚያ እንዲያደርጉ በማቀድ ሁለቱ ሀገሮች የተፈራረሙት ስምምነት ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩ ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You