የ98 ዓመቷ አዛውንት በተኩስ መሃል 10 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ከሩሲያ ጦር አመለጡ

የ98 ዓመት እድሜ ያላቸው የዩክሬን አዛውንት ሴት በተኩስ መሀል 10 ኪሎ ሜትር ርቀት በእግር ተጉዘው ከሩሲያ ጦር ማምለጣቸው አነጋጋሪ ሆኗል። አዛውንቷ አሁን በሩሲያ ቁጥጥር ስር ከወደቀችው ኦቸርታዮን ተነስተው የዩክሬን ጦር ወደ ተቆጣጠረው ቦታ መድረስ ችለዋል።

የዩክሬን ፖሊስ ሰኞ እለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለቀቀው ቪዲዮ ሊዲያ ስቴፋኒቫ የተባሉት ሴት ያለምግብ እና ውሃ እየወደቁ እና እየተነሱ መድረሳቸውን ይናገራሉ። “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተርፌያለሁ፣ ከዚህም እየተረፍኩ ነው” ሲሉ ስቴፋኒቫ ምርኩዝ ተደግፈው አልጋ ላይ ቁጭ ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል።”ምንም የቀረኝ የለም፤ ቀየየን በእግሬ ተጉዤ ለቅቄያለሁ”።

አዛውንቷ ሩሲያ በሀገራቸው ዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለው ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር እንደማይመሳሰል ተናግረዋል።”ቤቶች እየተቃጠሉ ነው፤ ዛፎች እየተነቀሉ ነው”በማለት የአሁኑን ጦርነት አስከፊነት ገልጸዋል።የዩክሬን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር በጽረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ሴትዮዋ በዩክሬን ጦር በሌሊት መገኘታቸውን እና ተፈናቃዮቹ ወደሚጠለሉበት ለወሰዳቸው ፖሊስ መስጠታቸውን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ “የህግ አስፈጻሚ አካላት የሴትዮዋን ቤተሰቦች እያፈላለጉ ነው” ብሏል። በፈረንጆች የካቲት 2022 የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አሁንም ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል ሲል አል ዐይን ዘገባ አመልክቷል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You